መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል
አንድ ስኮትላንዳዊ፣ ስኬታማ ከሆነው ሥራው የተሻለ ሆኖ ያገኘው ነገር ምንድን ነው? በብራዚል የሚኖር አንድ ሰው ሥነ ምግባር የጎደለው አኗኗሩንና ኮኬይን ማጨሱን እንዲተው የረዳው ምንድን ነው? በስሎቬንያ የሚኖር አንድ ሰው የአልኮል መጠጥ ከመጠን በላይ የመጠጣት ልማዱን ማስወገድ የቻለውስ እንዴት ነው? እስቲ እነዚህ ሰዎች የሚሉትን እንስማ።
“የተሳካ ሕይወት ያለኝ ይመስል ነበር።”—ጆን ሪኬትስ
የትውልድ ዘመን፦ 1958
የትውልድ አገር፦ ስኮትላንድ
የኋላ ታሪክ፦ በሥራው ስኬታማ የነበረ
የቀድሞ ሕይወቴ፦ ቤተሰቦቼ ጥሩ ኑሮ ነበራቸው። አባቴ በብሪታንያ ጦር ሠራዊት ውስጥ የጦር መኮንን ስለነበር ቤተሰባችን ወደተለያዩ ቦታዎች ተጉዟል። ከስኮትላንድ ውጪ በእንግሊዝ፣ በጀርመን፣ በኬንያ፣ በማሌዥያ፣ በአየርላንድ እና በቆጵሮስ ኖረናል። ከስምንት ዓመቴ ጀምሮ የተማርኩት ስኮትላንድ በሚገኙ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ነው። ውሎ አድሮም ከካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ተመረቅሁ።
በ20 ዓመቴ ከነዳጅ ምርት ጋር በተያያዘ ሥራ ላይ ተሰማራሁ፤ በዚህ ሥራ ላይ ለስምንት ዓመታት ቆይቻለሁ። ይህን ሥራ የጀመርኩት በደቡብ አሜሪካ ነበር፤ ከዚያም በአፍሪካ በመጨረሻም በምዕራብ አውስትራሊያ ሠርቻለሁ። በአውስትራሊያ እያለሁ አክስዮኖችን የሚያሻሽጥ ድርጅት አቋቋምኩ፤ ከተወሰነ ጊዜ በኋላም ይህን ድርጅት ሸጥኩት።
ከድርጅቱ ሽያጭ ያገኘሁት ገንዘብ ቀሪ ሕይወቴን ለመምራት በቂ ስለነበር በ40 ዓመቴ ሥራ አቁሜ የተለያዩ ቦታዎችን መጎብኘት ጀመርኩ። ከአንዴም ሁለቴ አውስትራሊያን በሞተር ብስክሌት ዞሬያለሁ፤ በተጨማሪም ዓለምን ዞሬያለሁ። በጥቅሉ ሲታይ የተሳካ ሕይወት ያለኝ ይመስል ነበር።
መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው? ሥራ ከማቆሜም በፊት አምላክ ለሰጠኝ ጥሩ ሕይወት አመስጋኝ መሆኔን የምገልጽበት መንገድ እፈልግ ነበር። በመሆኑም በልጅነቴ እሄድበት ወደነበረው የአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን መሄድ ጀመርኩ። ይሁንና ከቤተ ክርስቲያኑ ያን ያህል የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ማግኘት አልቻልኩም። ቀጥሎ ደግሞ ከሞርሞኖች ጋር ማጥናት ጀመርኩ፤ ሆኖም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እምነት ስላልነበራቸው ከእነሱም ጋር ያለኝን ግንኙነት አቋረጥኩ።
አንድ ቀን የይሖዋ ምሥክሮች ቤቴ መጡ። የሚያስተምሩት ነገር ሙሉ በሙሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ለመረዳት ጊዜ አልፈጀብኝም። ከጠቀሱልኝ ጥቅሶች አንዱ 1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4 ሲሆን ጥቅሱ የአምላክ ፈቃድ “ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲድኑ እንዲሁም የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ” እንደሆነ ይናገራል። የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲሁ ከማወቅ ባለፈ በውስጡ ያለውን ትክክለኛ እውቀት በመቅሰም ላይ ትኩረት ማድረጋቸው በጣም አስገረመኝ።
ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቴ እንዲህ ዓይነቱን ትክክለኛ እውቀት ማግኘት እንድችል ረድቶኛል። ለምሳሌ፣ አምላክና ኢየሱስ የተለያየ ማንነት ያላቸው አካላት እንጂ ሚስጥራዊ የሆነው ሥላሴ ክፍል እንዳልሆኑ ተገነዘብኩ። (ዮሐንስ 14:28፤ 1 ቆሮንቶስ 11:3) ለመረዳት የማይከብደውን ይህን እውነት ማወቄ በጣም አስደሰተኝ። በሌላ በኩል ደግሞ መጨበጫ የሌለውን የሥላሴን ትምህርት ለመረዳት ያን ያህል ጊዜ ማጥፋቴና መድከሜ አበሳጨኝ።
ብዙም ሳይቆይ በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመርኩ። በመካከላቸው የሚታየው ወዳጃዊ ስሜትና ያላቸው የላቀ የሥነ ምግባር አቋም በጣም አስገረመኝ፤ በቅዱሳን መካከል የተገኘሁ ያህል ተሰማኝ። የሚያሳዩትን ልባዊ ፍቅር ስመለከት እውነተኛውን ሃይማኖት እንዳገኘሁ እርግጠኛ ሆንኩ።—ዮሐንስ 13:35
ያገኘሁት ጥቅም፦ ከተጠመቅሁ በኋላ ዳያን ከምትባል ደስ የምትል ሴት ጋር ተገናኘሁ። ዳያን ያደገችው በይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰብ ውስጥ ነው፤ ያሏት በርካታ ግሩም ባሕርያት ስለማረኩኝ ከጊዜ በኋላ ተጋባን። ከዳያን ጋር ያለንን ወዳጅነትና የምትሰጠኝን ድጋፍ ሳስበው ከይሖዋ ያገኘኋት በረከት እንደሆነች ይሰማኛል።
እኔና ዳያን የመጽሐፍ ቅዱስ ምሥራች ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አካባቢ ሄደን የማገልገል ከፍተኛ ፍላጎት ነበረን። በመሆኑም በ2010 በመካከለኛው አሜሪካ ወደምትገኘው ወደ ቤሊዝ ሄድን። በዚህ አካባቢ አምላክን ለሚወዱ እና የመጽሐፍ ቅዱስን እውቀት ለተጠሙ ሰዎች እየሰበክን ነው።
ስለ አምላክና ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ እውቀት ማግኘቴ የአእምሮ ሰላም ሰጥቶኛል። የሙሉ ጊዜ ሰባኪ እንደመሆኔ መጠን መጽሐፍ ቅዱስን ለብዙ ሰዎች ማስተማር ያስደስተኛል። የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የተሻለ ሕይወት እንዲኖረኝ እንደረዳኝ ሁሉ የሌሎችንም ሕይወት ሲቀይር ከመመልከት የበለጠ የሚያስደስት ነገር የለም። አምላክ ለሰጠኝ ግሩም ሕይወት እሱን ማመስገን የምችልበት ከሁሉ የተሻለ መንገድ አግኝቻለሁ።
“በጣም ደግ ነበሩ።”—ማሪስዩ ኣራዉዡ
የትውልድ ዘመን፦ 1967
የትውልድ አገር፦ ብራዚል
የኋላ ታሪክ፦ ሥነ ምግባር የጎደለው ሕይወት ይመራ የነበረ
የቀድሞ ሕይወቴ፦ ያደግሁት ኣቫሬ በተባለች በሳኦ ፓውሎ የምትገኝ ትንሽ ከተማ ነው። አብዛኞቹ የከተማዋ ነዋሪዎች ላብ አደሮች ናቸው።
አባቴ የሞተው እናቴ እኔን እርጉዝ እያለች ነው። ልጅ እያለሁ እናቴ ወጣ ስትል የእሷን ልብሶች እለብስ ነበር። ሴት ለመምሰል እሞክር ስለነበር ሰዎች ግብረ ሰዶማዊ እንደሆንኩ አድርገው ይመለከቱኝ ጀመር። ከጊዜ በኋላ ከወንዶች ጋር የፆታ ግንኙነት መፈጸም ጀመርኩ።
በአሥራዎቹ ዕድሜ መጨረሻ አካባቢ ስደርስ ወንድ ሴት ሳልል አብረውኝ የፆታ ብልግና የሚፈጽሙ ሰዎችን መፈለጉን ሥራዬ ብዬ ተያያዝኩት፤ በቡና ቤቶች፣ በምሽት ክለቦች ሌላው ቀርቶ በቤተ ክርስቲያን እንኳ እንዲህ ዓይነት ሰዎች ለማግኘት እሞክር ነበር። በክብረ በዓላት ወቅት እንደ ሴት ለብሼ ሳምባ የተባለውን ጭፈራ ስለምጨፍር በጣም ታዋቂ ሆኜ ነበር።
ጓደኞቼ ግብረ ሰዶማውያን፣ ዝሙት አዳሪዎችና የዕፅ ሱሰኞች ነበሩ። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ኮኬይን ማጨስ እንድጀምር ይገፋፉኝ ነበር፤ ብዙም ሳይቆይ የኮኬይን ሱሰኛ ሆንኩ። አንዳንድ ጊዜ ሌሊቱን ሙሉ ስናጨስ እናድር ነበር። በሌሎች ጊዜያት ደግሞ ብቻዬን ሆኜ ኮኬይን ሳጨስ እውላለሁ። ሰውነቴ በጣም መንምኖ ስለነበር ኤድስ ይዞታል የሚል ወሬ ተናፈሰ።
መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው? በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለሁ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኘሁ። እነዚህ ሰዎች ለእኔ በጣም ደግ ነበሩ። ካነበቡልኝ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አንዱ ሮም 10:13 ሲሆን ጥቅሱ “የይሖዋን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል” ይላል። ይህ ጥቅስ የይሖዋን ስም መጠቀም ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እንድገነዘብ ረድቶኛል። ብዙ ጊዜ፣ ሌሊቱን ሙሉ ኮኬይን ሳጨስ ካደርኩ በኋላ መስኮቱን ከፍቼ ሰማይ ሰማዩን እያየሁ ይሖዋ እንዲረዳኝ በእንባ እለምነው ነበር።
እናቴ፣ ዕፅ እየወሰድኩ በገዛ እጄ ሕይወቴን ማበላሸቴ በጣም ያሳዝናት ነበር፤ የእሷ ሁኔታ ስላሳሰበኝ ከዚህ ልማድ ለመላቀቅ ቆርጬ ተነሳሁ። ብዙም ሳይቆይ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ እንዳጠና ያቀረቡልኝን ግብዣ ተቀበልኩ። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቴ ዕፅ ለማቆም ያደረግሁትን ውሳኔ እንደሚያጠናክርልኝ ነግረውኝ ነበር፤ ደግሞም ትክክል ነበሩ!
መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቴን ስቀጥል አኗኗሬን መለወጥ እንዳለብኝ ተገነዘብኩ። ግብረ ሰዶም ለረጅም ጊዜ አብሮኝ የቆየ ልማድ በመሆኑ ከሁሉ ይበልጥ የከበደኝ ከዚህ ልማድ መላቀቅ ነበር። ሆኖም መጥፎ ተጽዕኖ ከሚያሳድሩብኝ ነገሮች መራቄ ይህን ለማድረግ ረድቶኛል። ከቀድሞ ጓደኞቼ ጋር የነበረኝን ግንኙነት አቋረጥኩ፤ እንዲሁም ወደ መጠጥ ቤቶችና የምሽት ክለቦች መሄድ አቆምኩ።
እነዚህን ለውጦች ማድረግ ቀላል ባይሆንልኝም ይሖዋ እንደሚያስብልኝና የማደርገውን ትግል እንደሚረዳልኝ ማወቄ አጽናንቶኛል። (1 ዮሐንስ 3:19, 20) በ2002 ግብረ ሰዶምን እርግፍ አድርጌ የተውኩ ሲሆን በዚያው ዓመት ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ።
ያገኘሁት ጥቅም፦ እናቴ ባደረግሁት ለውጥ በጣም ስለተደነቀች እሷም መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች። የሚያሳዝነው ግን በአንጎሏ አካባቢ ባሉት የደም ሥሮች ላይ ጉዳት በመድረሱ ታማሚ ሆነች። ያም ሆኖ ለይሖዋና ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ያላት ፍቅር አልቀነሰም።
የሙሉ ጊዜ ሰባኪ ሆኜ ማገልገል ከጀመርኩ ስምንት ዓመት ያለፈኝ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜዬን የማሳልፈው ለሌሎች መጽሐፍ ቅዱስን በማስተማር ነው። እርግጥ ነው፣ አሁንም ቢሆን ተገቢ ያልሆኑ ምኞቶች እንዳያሸንፉኝ መታገል የሚያስፈልገኝ ጊዜ አለ። ሆኖም ለእነዚህ ምኞቶች ባለመሸነፍ ይሖዋን ማስደሰት እንደምችል ማወቄ ብርታት ይሰጠኛል።
ወደ ይሖዋ መቅረቤና እሱን የሚያስደስት አኗኗር መከተሌ ለራሴ ያለኝ ግምት የተሻለ እንዲሆን ረድቶኛል። አሁን ደስተኛ ሕይወት እየመራሁ ነው።
‘ቀዳዳ በርሜል ነበርኩ።’—ሉካ ሹትስ
የትውልድ ዘመን፦ 1975
የትውልድ አገር፦ ስሎቬንያ
የኋላ ታሪክ፦ ከመጠን በላይ ይጠጣ የነበረ
የቀድሞ ሕይወቴ፦ የተወለድኩት በስሎቬንያ ዋና ከተማ በሉብሊያና ነው። አራት ዓመት እስኪሆነኝ ድረስ ሕይወቴ አስደሳች ነበር። የአራት ዓመት ልጅ እያለሁ ግን አባቴ ራሱን አጠፋ። ይህ አሳዛኝ ሁኔታ ከተፈጸመ በኋላ እናቴ፣ እኔንና ታላቅ ወንድሜን ለማሳደግ ደፋ ቀና ማለት ጀመረች።
አሥራ አምስት ዓመት ሲሆነኝ ከአያቴ ጋር መኖር ጀመርኩ። አብዛኞቹ ጓደኞቼ ያሉት እዚያ አካባቢ በመሆኑ ከአያቴ ጋር በመኖሬ ደስተኛ ነበርኩ። ከዚህም በላይ ከእናቴ ጋር ሳለሁ ከነበረኝ የበለጠ ነፃነት አገኘሁ። በ16 ዓመቴ ቅዳሜና እሁድ ላይ የመጠጣት ልማድ ካላቸው ሰዎች ጋር ጓደኝነት መሠረትኩ። ፀጉሬን አሳደግሁ፤ አለባበሴም ዓመፀኝነት የሚንጸባረቅበት ሆነ፤ ከጊዜ በኋላ ደግሞ ማጨስ ጀመርኩ።
የተለያዩ ዕፆችን ብወስድም ይበልጥ የሚያስደስተኝ መጠጥ ነበር። መጀመሪያ ላይ እጠጣ የነበረው ትንሽ ቢሆንም ብዙም ሳይቆይ በአንድ ጊዜ ሙሉ ጠርሙስ ወይን ጠጅ እስከ መጨረስ ደረስኩ። እያደር ደግሞ፣ ምን ያህል እንደጠጣሁ እንዳይታወቅብኝ በማድረግ ረገድ የተካንኩ ሆንኩ። ብዙውን ጊዜ መጠጣቴ የሚታወቀው በትንፋሼ ብቻ ነበር። ከአራት እስከ አምስት ሊትር የሚደርስ ወይን ወይም ቢራ ከቮድካ ጋር ቀላቅዬ መጠጣት እችል ነበር፤ እንደዚያም ሆኖ ምን ያህል እንደጠጣሁ ማንም መገመት አይችልም!
ብዙ ጊዜ ጓደኞቼ ከሚጠጡት በእጥፍ የሚበልጥ መጠጥ ብጠጣም ጭፈራ ቤት አምሽተን ስንመለስ እነሱን ደግፌ ወደ ቤት የማደርሳቸው እኔ ነበርኩ። አንድ ቀን ከጓደኞቼ አንዱ ‘ቀዳዳ በርሜል’ እንደሆንኩ ሲናገር ጆሮዬ ጥልቅ አለ፤ በስሎቬንያ ሰዎች ብዙ የሚጠጣን ሰው ለመግለጽ እንዲህ ዓይነቱን የዘለፋ አነጋገር ይጠቀማሉ። የተናገረው ነገር በጣም ጎዳኝ።
ሕይወቴ ወዴት እያመራ እንዳለ ቆም ብዬ ማሰብ ጀመርኩ። በከንቱነት ስሜት የተዋጥኩ ሲሆን በሕይወቴ ምንም ቁም ነገር እንዳልሠራሁ ተሰማኝ።
መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው? በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለሁ አብረውኝ ከሚማሩት ልጆች መካከል አንዱ ባሕሪው እንደተለወጠና ረጋ ያለ ሰው እንደሆነ አስተዋልኩ። ይህን ልጅ እንዲህ የለወጠው ምን እንደሆነ ለማወቅ ስለጓጓሁ ሻይ ቤት ገብተን እንድንነጋገር ጋበዝኩት። ተገናኝተን ስናወራ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት እንደጀመረ ገለጸልኝ። ከተማራቸው ነገሮች አንዳንዶቹን ነገረኝ፤ ከልጅነቴ ጀምሮ ስለ ሃይማኖት የማውቀው ነገር ስላልነበረ ያወራልኝ ነገር ሁሉ ለእኔ አዲስ ነበር። በመሆኑም በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባዎች ላይ መገኘትና ከእነሱ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመርኩ።
መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቴ ልብ የሚነኩና ለተግባር የሚያነሳሱ እውነቶችን እንዳውቅ አድርጎኛል። ለምሳሌ ያህል፣ የምንኖረው መጽሐፍ ቅዱስ ‘የመጨረሻዎቹ ቀኖች’ ብሎ በሚጠራው ጊዜ ውስጥ እንደሆነ ተማርኩ። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) ከዚህም በተጨማሪ አምላክ በቅርቡ ክፉ ሰዎችን ከምድረ ገጽ እንደሚያጠፋና ለጥሩ ሰዎች ደግሞ በምድር ላይ በገነት ውስጥ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ እንደሚሰጣቸው አወቅሁ። (መዝሙር 37:29) እኔም ከእነዚህ ጥሩ ሰዎች መካከል ለመሆን እንድችል ሕይወቴን የማስተካከል ከፍተኛ ፍላጎት አደረብኝ።
የተማርኳቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ለጓደኞቼ ነገርኳቸው። አብዛኞቹ ያሾፉብኝ ቢሆንም እንዲህ ማድረጋቸው ባላሰብኩት መንገድ ጠቅሞኛል። የሰጡኝ ምላሽ እውነተኛ ጓደኞች እንዳልሆኑ እንድገነዘብ አስችሎኛል። ያለብኝ የመጠጥ ችግርም ከጓደኛ ምርጫዬ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ተረዳሁ። ጓደኞቼ የምላቸው ሰዎች ሳምንቱን ሙሉ በጉጉት የሚጠብቁት ቅዳሜና እሁድ ደርሶ የሚጠጡበትን ጊዜ ነበር።
ከእነዚህ ሰዎች ጋር ያለኝን ግንኙነት አቋርጬ ከይሖዋ ምሥክሮች መካከል ጥሩ ወዳጆች አፈራሁ። የይሖዋ ምሥክሮች አምላክን ከልባቸው ስለሚወዱና በእሱ መመሪያዎች መሠረት ለመኖር ከፍተኛ ጥረት ስለሚያደርጉ ከእነሱ ጋር ያለኝ ወዳጅነት ትልቅ የብርታት ምንጭ ሆኖልኛል። እያደር፣ ከመጠን በላይ የመጠጣት ልማዴን ማስወገድ ቻልኩ።
ያገኘሁት ጥቅም፦ አሁን ደስተኛ ለመሆን የግድ አልኮል አያስፈልገኝም፤ ለዚህም ይሖዋን አመሰግነዋለሁ። በቀድሞ አኗኗሬ ብቀጥል ኖሮ ምን ይገጥመኝ እንደነበር መገመት ያስቸግረኛል። ሆኖም አሁን ያለኝ ሕይወት የተሻለ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም።
ላለፉት ሰባት ዓመታት በስሎቬንያ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ የማገልገል መብት አግኝቻለሁ። ይሖዋን ማወቄና እሱን ማገልገሌ ትርጉም ያለው ሕይወት ለመምራት አስችሎኛል።