ከአምላክ ቃል ተማር
ሃይማኖቶች ወደፊት ምን ይጠብቃቸዋል?
ይህ ርዕስ በአእምሮህ ሊመላለሱ የሚችሉ ጥያቄዎችን በማንሳት መልሶቹን መጽሐፍ ቅዱስህ ውስጥ የት ቦታ ላይ ማግኘት እንደምትችል ይጠቁምሃል። የይሖዋ ምሥክሮች ለጥያቄዎቹ በተሰጡት መልሶች ላይ ከአንተ ጋር ለመወያየት ፈቃደኞች ናቸው።
1. ሁሉም ሃይማኖቶች ጥሩ ናቸው?
በሁሉም የሃይማኖት ቡድኖች ውስጥ አምላክን ለማስደሰት የሚጥሩ ልበ ቅን ሰዎች አሉ። አምላክ እነዚህ ሰዎች የሚያደርጉትን ጥረት የሚያስተውል ከመሆኑም ሌላ ስለ እነሱ ያስባል። የሚያሳዝነው ግን አንዳንድ ሰዎች በሃይማኖት ስም መጥፎ ድርጊቶችን ይፈጽማሉ። ባለፉት ዘመናት የሃይማኖት መሪዎች፣ ተቃዋሚዎቻቸውን እስከ ማሠቃየት እንኳ ደርሰው ነበር። (2 ቆሮንቶስ 4:3, 4፤ 11:13-15) በዛሬው ጊዜ የዜና ዘገባዎች እንደሚያሳዩት አንዳንድ የሃይማኖት መሪዎች ሽብርተኝነትን ያበረታታሉ ወይም ጦርነትን ይደግፋሉ እንዲሁም ልጆችን ያስነውራሉ።—ማቴዎስ 24:3-5, 11, 12ን አንብብ።
መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ ሃይማኖትና የሐሰት ሃይማኖት እንዳለ ይገልጻል። የሐሰት ሃይማኖት ስለ አምላክ እውነቱን አያስተምርም። ይሖዋ አምላክ ግን ሰዎች ስለ እሱ እውነቱን እንዲያውቁ ይፈልጋል።—1 ጢሞቴዎስ 2:3-5ን አንብብ።
2. ሃይማኖቶች ወደፊት ምን ይጠብቃቸዋል?
አምላክ፣ እሱን እንደሚያገለግሉ ቢናገሩም ስለ እሱ ውሸት በሚያስተምሩ ሃይማኖቶች ሰዎች እንዲታለሉ አይፈልግም። የእነዚህ ሃይማኖቶች ደጋፊዎች ሰይጣን ዲያብሎስ ከሚቆጣጠረው ከዚህ ዓለም ጋር መወዳጀት ይፈልጋሉ። (ያዕቆብ 4:4፤ 1 ዮሐንስ 5:19) መጽሐፍ ቅዱስ፣ ከአምላክ ይልቅ ሰብዓዊ መንግሥታትን የሚደግፉ ሃይማኖቶችን እንደ አመንዝራ ሴት አድርጎ ይገልጻቸዋል። የአምላክ ቃል፣ ይህችን ጋለሞታ “ታላቂቱ ባቢሎን” ብሎ ይጠራታል፤ ይህን መጠሪያ ያገኘችው በኖኅ ዘመን ከነበረው የጥፋት ውኃ በኋላ የሐሰት ሃይማኖት መፍለቂያ ከሆነችው ጥንታዊት ከተማ ነው። አምላክ በቅርቡ፣ የሰውን ዘር በሚያታልሉና በሚጨቁኑ ሃይማኖቶች ላይ ድንገተኛ ጥፋት ያመጣል።—ራእይ 17:1, 2, 5, 17ን እና ራእይ 18:8, 23, 24ን አንብብ።
3. አምላክ በመላው ምድር የሚኖሩ ሰዎች ደስተኞች እንዲሆኑ የሚያደርገው እንዴት ነው?
የሐሰት ሃይማኖቶች የሚፈረድባቸው መሆኑ የምሥራች ነው። ይህ የፍርድ እርምጃ ጭቆናን ከምድር ላይ ያስወግዳል። ከዚያ በኋላ የሐሰት ሃይማኖቶች የሰውን ዘር ማሳሳትም ሆነ መከፋፈል አይችሉም። በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች በሙሉ ብቻውን እውነተኛ የሆነውን አምላክ በማምለክ አንድ ይሆናሉ።—ኢሳይያስ 11:9ን ራእይ 18:20, 21ን እና ራእይ 21:3, 4ን አንብብ።
4. ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ምን ማድረግ አለባቸው?
ይሖዋ በዓለም ዙሪያ በሚገኙት የሐሰት ሃይማኖቶች ውስጥ ያሉትን ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች አይረሳም። እንዲህ ያሉት ሰዎች እውነትን እንዲማሩ መንገድ የከፈተላቸው ሲሆን አንድ ሆነው እንዲያመልኩት እያሰባሰባቸው ነው።—ሚክያስ 4:2, 5ን አንብብ።
ይሖዋ እሱን ለማገልገል የሚፈልጉ ሰዎችን ከቤተሰቡ ጋር እንዲቀላቀሉ ይጋብዛቸዋል። ይሖዋን ማገልገል ስንጀምር ወዳጆቻችንም ሆነ ቤተሰቦቻችን ደስ ባይላቸውም እንዲህ ማድረጋችን ብዙ ጥቅም ያስገኝልናል። ከአምላክ ጋር ወዳጅነት መመሥረት፣ አዲስና አፍቃሪ የሆነ መንፈሳዊ ቤተሰብ አባል መሆን እንዲሁም የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንችላለን።—ማርቆስ 10:29, 30ን እና 2 ቆሮንቶስ 6:17, 18ን አንብብ።
ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 15 እና 16 ተመልከት።
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
The Complete Encyclopedia of Illustration / J. G. Heck