የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w13 10/1 ገጽ 12-13
  • መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2013
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • 4 | በአምላክ እርዳታ ጥላቻን ድል አድርግ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2022
  • መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2011
  • መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2012
  • መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2012
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2013
w13 10/1 ገጽ 12-13
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

“ብዙ ሰዎች ይጠሉኝ ነበር”

ዎልዶ ሞያ እንደተናገረው

  • የትውልድ ዘመን፦ 1978

  • የትውልድ አገር፦ ቺሊ

  • የኋላ ታሪክ፦ በጣም ግልፍተኛ የነበረ

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የቀድሞ ሕይወቴ፦

ያደግሁት የቺሊ ዋና ከተማ በሆነችው በሳንቲያጎ ሲሆን የምንኖረው ዕፅ እንደ ልብ በሚገኝበት እንዲሁም ወንበዴዎች በተስፋፉበትና ወንጀል በሚበዛበት አካባቢ ነበር። የአምስት ዓመት ልጅ ሳለሁ አባቴ ተገደለ። ከዚያ በኋላ እናቴ ከአንድ ሰው ጋር መኖር ጀመረች፤ ሰውየው ጨካኝ ሲሆን ሁለታችንንም ዘወትር ይደበድበን ነበር። በዚያ ወቅት የደረሰብኝ በደል የተወው የስሜት ጠባሳ እስካሁን ያሠቃየኛል።

እያደግሁ ስሄድ፣ የሚደርስብኝን በደል ለመቋቋም ስል በጣም ዓመፀኛ ሆንኩ። ሄቪ ሜታል ሙዚቃ አዳምጥና ከልክ በላይ እጠጣ የነበረ ሲሆን አልፎ አልፎም ዕፅ እወስድ ነበር። ከዕፅ አዘዋዋሪዎች ጋር በጎዳና ላይ በሚደረጉ ግጭቶች ብዙ ጊዜ እካፈል የነበረ ሲሆን እነሱም በተደጋጋሚ ጊዜያት ሊገድሉኝ ሞክረዋል። በአንድ ወቅት የእኛ ተቀናቃኝ የሆነ አንድ የወንበዴዎች ቡድን እኔን ለማስገደል በጭካኔው የታወቀ ነፍሰ ገዳይ ቀጠረ፤ ሰውየው በስለት ቢወጋኝም ሳልሞት ማምለጥ ቻልኩ። በሌላ ወቅት ደግሞ የተወሰኑ የዕፅ አዘዋዋሪዎች፣ ጭንቅላቴ ላይ ሽጉጥ የደገኑብኝ ሲሆን ሊሰቅሉኝ ሞክረው ነበር።

በ1996 ካሮሊና ከምትባል አንዲት ሴት ጋር ፍቅር ያዘኝ፤ ከዚያም በ1998 ተጋባን። የመጀመሪያ ልጃችን ከተወለደ በኋላ ግን በዚህ የግልፍተኝነት ባሕርይ ከቀጠልኩ እንደ እንጀራ አባቴ ልሆንና ቤተሰቤን ልጎዳ እንደምችል ስላሰብኩ መፍራት ጀመርኩ። ስለዚህ በአካባቢያችን ከሚገኝ የተሐድሶ ማዕከል እርዳታ ለማግኘት ሞከርኩ። እዚያም የሕክምና እርዳታ የተደረገልኝ ከመሆኑም ሌላ የምክር አገልግሎት ተሰጠኝ፤ ያም ቢሆን ባሕርዬ ሊለወጥ አልቻለም። በትንሽ በትልቁ ቱግ እል ነበር፤ ቁጣዬን መቆጣጠር ጨርሶ ተስኖኝ ነበር። በቤተሰቤ ላይ ጉዳት እያደረስኩ መኖር ስላልፈለግሁ ራሴን ለመግደል ሙከራ አደረግሁ። ደግነቱ አልተሳካልኝም።

ለብዙ ዓመታት አምላክ የለሽ የነበርኩ ቢሆንም በአምላክ ማመን እፈልግ ነበር። በዚህም የተነሳ ለተወሰነ ጊዜ ወደ አንድ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መሄድ ጀመርኩ። በዚህ ጊዜ ባለቤቴ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን እያጠናች ነበር። የይሖዋ ምሥክሮችን እጠላቸው ስለነበር ብዙ ጊዜ መጥፎ ስድብ ሰድቤያቸዋለሁ። እነሱ ግን ምንጊዜም በሰላማዊ መንገድ ያናግሩኝ ነበር፤ ይህ ፈጽሞ ያልጠበቅሁት ነገር ሆነብኝ።

አንድ ቀን ካሮሊና በራሴ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ መዝሙር 83:18ን አውጥቼ እንዳነብብ ጠየቀችኝ። መጽሐፍ ቅዱሴን አውጥቼ ስመለከት ጥቅሱ የአምላክ ስም ይሖዋ መሆኑን በግልጽ እንደሚናገር አስተዋልኩ። በሃይማኖቴ ውስጥ ስለ አምላክ ብማርም ስሙ ይሖዋ መሆኑን አለመማሬ አስገረመኝ። በ2000 መጀመሪያ ላይ እኔም መጽሐፍ ቅዱስን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናት ጀመርኩ።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው?

በጥናቴ እየገፋሁ ስሄድ ይሖዋ ሩኅሩኅና ይቅር ባይ አምላክ እንደሆነ ተማርኩ፤ ይህም አጽናናኝ። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ በዘፀአት 34:6, 7 ላይ ስለ ይሖዋ ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “ሩኅሩኅ ቸር አምላክ . . . ለቍጣ የዘገየ፣ ፍቅሩና ታማኝነቱ የበዛ፣ ፍቅርን ለሺዎች የሚጠብቅ፣ ክፋትን፣ ዐመፅንና ኀጢአትን ይቅር የሚል።”

እንደዚያም ሆኖ፣ የምማረውን ነገር በሥራ ላይ ማዋል ቀላል አልነበረም። የግልፍተኝነት ጠባዬን መቆጣጠር ፈጽሞ እንደማይሳካልኝ ተሰምቶኝ ነበር። በቁጣ በገነፈልኩ ቁጥር ካሮሊና ተስፋ እንዳልቆርጥ በፍቅር ታበረታታኝ ነበር። ይሖዋ ጥረቴን እንደሚመለከት ታስታውሰኛለች። ባሕርዬን የመለወጥ ተስፋ እንደሌለኝ ብዙ ጊዜ ቢሰማኝም እሷ ያደረገችልኝ ድጋፍ ይሖዋን ለማስደሰት ጥረት ማድረጌን እንድቀጥል ብርታት ሰጥቶኛል።

መጽሐፍ ቅዱስን የሚያስጠናኝ አሌሃንድሮ፣ አንድ ቀን ገላትያ 5:22, 23ን እንዳነብብ ጠየቀኝ። ይህ ጥቅስ የአምላክ መንፈስ ፍሬ ገጽታዎች “ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ደግነት፣ ጥሩነት፣ እምነት፣ ገርነት፣ ራስን መግዛት” እንደሆኑ ይናገራል። አሌሃንድሮ እነዚህን ባሕርያት ማዳበር የምችለው በራሴ ጥንካሬ ሳይሆን በአምላክ ቅዱስ መንፈስ እርዳታ እንደሆነ ገለጸልኝ። ይህ እውነት አመለካከቴን ሙሉ በሙሉ ለወጠው!

በሌላ ጊዜ ደግሞ የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጉት አንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ ተገኘሁ። በዚያ ያሉት ሰዎች ሥርዓታማና ንጹሕ እንዲሁም እርስ በርስ የሚዋደዱ መሆናቸውን ሳይ እውነተኛውን ሃይማኖት እንዳገኘሁ እርግጠኛ ሆንኩ። (ዮሐንስ 13:34, 35) ከዚያም የካቲት 2001 ተጠመቅሁ።

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ያገኘሁት ጥቅም፦

ግልፍተኛ የነበርኩት ሰው ተለውጬ ሰላማዊ እንድሆን ይሖዋ ረድቶኛል። ከተዘፈቅሁበት ማጥ ውስጥ ጎትቶ እንዳወጣኝ ይሰማኛል። ብዙ ሰዎች ይጠሉኝ ነበር፤ ደግሞም ይህ አያስገርመኝም። አሁን ግን ከባለቤቴና ከሁለት ወንዶች ልጆቼ ጋር ይሖዋን በሰላም እያገለገልኩ ነው።

ዘመዶቼና የቀድሞ ጓደኞቼ ያደረግሁትን ለውጥ ማመን ያቅታቸዋል። በዚህም የተነሳ ከእነሱ መካከል አንዳንዶቹ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለመማር ፍላጎት አሳይተዋል። በተጨማሪም ሌሎች ይሖዋን እንዲያውቁ የመርዳት መብት አግኝቻለሁ። የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የእነሱንም ሕይወት ሲለውጥ ማየት እንዴት የሚያስደስት ነው!

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ