የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w15 1/1 ገጽ 14-15
  • መጸለይ ያለብን ወደ ኢየሱስ ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • መጸለይ ያለብን ወደ ኢየሱስ ነው?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2015
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ኢየሱስ ያስተማረን ወደ ማን እንድንጸልይ ነው?
  • የጥንቶቹ ክርስቲያኖች የሚጸልዩት ወደ ማን ነበር?
  • አምላክ ስለሚሰማቸው ጸሎቶች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2009
  • ወደ ኢየሱስ መጸለይ ይገባሃልን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • ኢየሱስ እንድንጸልይ አስተምሮናል
    ከታላቁ አስተማሪ ተማር
  • ወደ አምላክ የመጸለይ ውድ መብት
    መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምረናል?
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2015
w15 1/1 ገጽ 14-15

መጸለይ ያለብን ወደ ኢየሱስ ነው?

በቅርቡ አንድ ተመራማሪ፣ ከብዙ ሃይማኖቶች ለተውጣጡ ከ800 ለሚበልጡ ወጣቶች መጠይቅ በማዘጋጀት ጥናት አካሂዶ ነበር፤ በመጠይቁ ላይ ‘ኢየሱስ ለሚቀርቡለት ጸሎቶች መልስ ይሰጣል ብላችሁ ታምናላችሁ?’ የሚል ጥያቄ ተካትቶ ነበር። ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑት ወጣቶች ‘ኢየሱስ ለሚቀርቡለት ጸሎቶች መልስ ይሰጣል’ የሚል ጠንካራ እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል። ይሁን እንጂ አንዲት ወጣት በጥያቄው ላይ ኢየሱስ የሚለውን ስም ሰርዛ በምትኩ “አምላክ” ብላ ጻፈች።

አንተስ ምን ይመስልሃል? መጸለይ ያለብን ወደ ኢየሱስ ነው? ወይስ ወደ አምላክ?a የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት በመጀመሪያ ኢየሱስ ጸሎትን አስመልክቶ ለደቀ መዛሙርቱ ምን እንዳስተማራቸው እንመልከት።

ኢየሱስ ያስተማረን ወደ ማን እንድንጸልይ ነው?

ኢየሱስ በትምህርቱም ሆነ በድርጊቱ ወደ ማን መጸለይ እንዳለብን አሳይቷል።

ኢየሱስ ወደ አባቱ ሲጸልይ[በገጽ 14, 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ በሰማይ ወዳለው አባቱ በመጸለይ ልንከተለው የሚገባ ምሳሌ ትቶልናል

በትምህርቱ ያሳየው እንዴት ነው? ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ ኢየሱስን “እንዴት እንደምንጸልይ አስተምረን” ብሎ በጠየቀው ጊዜ ኢየሱስ ‘በምትጸልዩበት ጊዜ ሁሉ “አባት ሆይ” በሉ’ በማለት መልስ ሰጥቷል። (ሉቃስ 11:1, 2) በተጨማሪም ኢየሱስ በሰፊው በሚታወቀው የተራራ ስብከቱ ላይ አድማጮቹን እንዲጸልዩ ሲያሳስብ “በስውር ወዳለው አባትህ ጸልይ” ብሏል። እንዲሁም “አባታችሁ . . . ገና ሳትለምኑት ምን እንደሚያስፈልጋችሁ ያውቃል” በማለት አጽናንቷቸዋል። (ማቴዎስ 6:6, 8) ኢየሱስ ሰው ሆኖ ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት ላይ “አብን ማንኛውንም ነገር ብትጠይቁት በስሜ ይሰጣችኋል” በማለት ለደቀ መዛሙርቱ ነግሯቸዋል። (ዮሐንስ 16:23) በመሆኑም ኢየሱስ ያስተማረው የእሱም ሆነ የእኛ አባት ወደሆነው ወደ ይሖዋ አምላክ እንድንጸልይ ነው።—ዮሐንስ 20:17

በድርጊቱ ያሳየው እንዴት ነው? ኢየሱስ ሌሎችን እንዲጸልዩ ካስተማረበት መንገድ ጋር በሚስማማ መልኩ እሱ ራሱ “የሰማይና የምድር ጌታ አባት ሆይ፣ . . . በሕዝብ ፊት አወድስሃለሁ” በማለት ጸልዮአል። (ሉቃስ 10:21) በሌላ ወቅት ደግሞ ኢየሱስ “ወደ ሰማይ ከተመለከተ በኋላ እንዲህ አለ፦ “አባት ሆይ፣ ስለሰማኸኝ አመሰግንሃለሁ።” (ዮሐንስ 11:41) በሞት አፋፍ ላይ በነበረበት ጊዜም “አባት ሆይ፣ መንፈሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ” በማለት ጸልዮአል። (ሉቃስ 23:46) ኢየሱስ “የሰማይና የምድር ጌታ” ወደሆነው በሰማይ ወዳለው አባቱ በመጸለይ ሁላችንም በጸሎት ረገድ ልናደርገው የሚገባንን ነገር በግልጽ አሳይቶናል። (ማቴዎስ 11:25፤ 26:41, 42፤ 1 ዮሐንስ 2:6) የጥንቶቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርትስ እሱ ያስተማራቸውን ነገር የተረዱት እንዴት ነበር?

የጥንቶቹ ክርስቲያኖች የሚጸልዩት ወደ ማን ነበር?

ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከተመለሰ ከተወሰኑ ሳምንታት በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ከተቃዋሚዎቻቸው ማስፈራሪያና ዛቻ ይደርስባቸው ጀመር። (የሐዋርያት ሥራ 4:18) እርግጥ ነው፣ እርዳታ ለመጠየቅ ጸሎት አቅርበዋል፤ ይሁን እንጂ የጸለዩት ወደ ማን ነበር? “በአንድ ልብ ሆነው ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ” እነሱን መርዳቱን ይቀጥል ዘንድ ‘በቅዱስ አገልጋዩ በኢየሱስ ስም’ “ወደ አምላክ” እንደጸለዩ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (የሐዋርያት ሥራ 4:24, 30) በመሆኑም ደቀ መዛሙርቱ፣ ኢየሱስ ስለ ጸሎት የሰጣቸውን መመሪያዎች ተከትለው ነበር። የጸለዩት ወደ ኢየሱስ ሳይሆን ወደ አምላክ ነበር።

ከዓመታት በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ እሱና ጓደኞቹ የሚጸልዩት እንዴት እንደሆነ ገልጾ ነበር። የእምነት አጋሮቹ ለሆኑት ክርስቲያኖች ሲጽፍ እንዲህ ብሏል፦ “ስለ እናንተ ስንጸልይ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አባት የሆነውን አምላክ ሁልጊዜ እናመሰግናለን።” (ቆላስይስ 1:3) በተጨማሪም ጳውሎስ ለእምነት አጋሮቹ “በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ስለ ሁሉም ነገር አምላካችንንና አባታችንን ሁልጊዜ አመስግኑ” በማለት ጽፏል። (ኤፌሶን 5:20) ከዚህ ማየት እንደሚቻለው ጳውሎስ “ስለ ሁሉም ነገር” ወደ አምላካቸውና ወደ አባታቸው እንዲጸልዩ የእምነት አጋሮቹን አበረታትቷቸዋል፤ ይሁን እንጂ ጸሎት ማቅረብ ያለባቸው በኢየሱስ ስም እንደሆነ የታወቀ ነው።—ቆላስይስ 3:17

እንደ ጥንቶቹ ክርስቲያኖች ሁሉ እኛም ኢየሱስ ጸሎትን አስመልክቶ የሰጠንን ምክር በመከተል እሱን እንደምንወደው ማሳየት እንችላለን። (ዮሐንስ 14:15) የምንጸልየው በሰማይ ወዳለው አባታችን ብቻ ከሆነ በመዝሙር 116:1, 2 ላይ ያለው ሐሳብ ይበልጥ ትርጉም ያለው ይሆንልናል፤ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “የልመናዬን ድምፅ ሰምቶአልና፣ እግዚአብሔርን ወደድሁት። . . . በሕይወት ዘመኔ ሁሉ ወደ እርሱ እጣራለሁ።”b

a መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ከሆነ አምላክና ኢየሱስ እኩል አይደሉም። ስለዚህ ጉዳይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 4 ተመልከት።

b አምላክ ጸሎታችንን እንዲሰማልን ከፈለግን እሱ ያወጣቸውን የሥነ ምግባር መመሪያዎች ለመከተል ከልባችን ጥረት ማድረግ አለብን። ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 17 ተመልከት።

ወደ ኢየሱስ ጸልየዋል?

ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከሄደ በኋላ አንዳንድ ታማኝ ሰዎች እንዳናገሩት መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል፤ በተጨማሪም መላእክትን ያናገሩ ሰዎች እንዳሉ የሚገልጹ ዘገባዎች አሉ። (የሐዋርያት ሥራ 9:4, 5, 10-16፤ 10:3, 4፤ ራእይ 10:8, 9፤ 22:20) ይሁን እንጂ እነዚህ ታማኝ ሰዎች በሰማይ ላይ ወደሚገኙት ወደ እነዚህ መንፈሳዊ ፍጥረታት ጸልየዋል? በፍጹም። በሁሉም ዘገባዎች ላይ መመልከት እንደምንችለው ሰዎቹን ቀድመው ያነጋገሯቸው በሰማይ የሚገኙት መንፈሳዊ አካላት ናቸው። ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች የሚጸልዩት ወደ አምላክ ብቻ ነበር።—ፊልጵስዩስ 4:6

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ