የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w15 3/1 ገጽ 13-15
  • ለንጉሥ የሚቀርቡ ስጦታዎች

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ለንጉሥ የሚቀርቡ ስጦታዎች
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2015
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የአረቢያን በረሃ ማቋረጥ
  • “በዘመናት ሁሉ ተደብቆ የኖረ የንግድ ሚስጥር”
  • በጥንት ዘመን የነበሩ መዋቢያዎች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2012
  • የገለዓድ በለሳን—ፈዋሽ የሆነው ቅባት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2010
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2015
w15 3/1 ገጽ 13-15
ደስ የሚል መዓዛ ያላቸው የተለያዩ ቅመሞች

ለንጉሥ የሚቀርቡ ስጦታዎች

“ኮከብ ቆጣሪዎች ከምሥራቅ አገር ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው . . . ወርቅ፣ ነጭ ዕጣንና ከርቤ በስጦታ መልክ አቀረቡለት።”—ማቴዎስ 2:1, 11

ለአንድ የተከበረ ሰው ስጦታ መስጠት ብትፈልግ ምን ትመርጥ ነበር? በጥንት ዘመን አንዳንድ ቅመሞች የወርቅን ያህል ውድ ነበሩ፤ እንዲሁም ለነገሥታት በስጦታነት ከሚቀርቡት የከበሩ ነገሮች መካከል ይገኙበት ነበር።a ኮከብ ቆጣሪዎቹ ደስ የሚል መዓዛ ያላቸው ሁለት ቅመሞችን ‘ለአይሁድ ንጉሥ’ በስጦታነት ያቀረቡት ለዚህ ነው።—ማቴዎስ 2:1, 2, 11

የበለሳን ዘይት

የበለሳን ዘይት

በተጨማሪም ንግሥት ሳባ ሰለሞንን በጎበኘችበት ወቅት ለንጉሡ ስላመጣቻቸው ነገሮች ሲገልጽ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “አንድ መቶ ሃያ መክሊት ወርቅ፣ እጅግ ብዙ ቅመማ ቅመምና የከበሩ ድንጋዮች ሰጠችው፤ የሳባ ንግሥት ለንጉሥ ሰሎሞን እንደሰጠችው ዐይነት ቅመማ ቅመም ያለ ከቶ አልነበረም።”b (2 ዜና መዋዕል 9:9) ሌሎች ነገሥታትም ለሰለሞን የበለሳን ዘይት ገጸ በረከት አድርገው ልከውለታል።—2 ዜና መዋዕል 9:23, 24

እንዲህ ዓይነቶቹ ቅመሞችና ተዛማጅነት ያላቸው ምርቶች በጥንት ዘመን በጣም ከፍ ተደርገው የሚታዩት እንዲሁም ውድ የነበሩት ለምንድን ነው? ለተለያዩ አስፈላጊ ዓላማዎች ይውሉ ስለነበር ነው፤ ለምሳሌ ውበትን ለመጠበቅና አስከሬን ለማዘጋጀት ያገለግሉ የነበረ ከመሆኑም ሌላ በሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች ላይ ጥቅም ላይ ይውሉ ነበር። (“ቅመማ ቅመሞች በጥንት ዘመን የነበራቸው ጥቅም” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) ቅመሞች በጣም ተፈላጊ የነበሩ ከመሆኑም ሌላ እነሱን ማጓጓዝና መሸጥ ከፍተኛ ወጪ ስለሚጠይቅ ዋጋቸው ውድ ነበር።

የአረቢያን በረሃ ማቋረጥ

ብርጉድ

ብርጉድ

በጥንት ዘመን ቅመም የሚገኝባቸው አንዳንድ ተክሎች በዮርዳኖስ ሸለቆ ይበቅሉ ነበር። ሌሎቹ ቅመሞች የሚመጡት ግን ከውጭ አገር ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተለያዩ የቅመማ ቅመም ምርቶች ተጠቅሰዋል። በጣም ከሚታወቁት መካከል የሳሮን አበባ፣ እሬት፣ በለሳን፣ ቀረፋ፣ ነጭ ዕጣንና ከርቤ ይገኙበታል። ከእነዚህ ሌላ ደግሞ እንደ ከሙን፣ ኮሰረትና እንስላል ያሉ የተለመዱ የምግብ ማጣፈጫዎች ተጠቅሰዋል።

እነዚህን ቅመሞች የሚያስመጡት ከየት ነበር? እሬት፣ ብርጉድና ቀረፋ የሚመጡት ከአሁኗ ሕንድ፣ ስሪ ላንካና ቻይና ነበር። እንደ ከርቤና ነጭ ዕጣን ያሉት ቅመሞች የሚገኙት ከደቡብ አረቢያ አንስቶ በአፍሪካ እስካለችው ሶማሊያ ድረስ ባለው በረሃማ አካባቢ ከሚበቅሉ ዛፎችና ቁጥቋጦዎች ነው። ናርዶስ ደግሞ በሂማላያ አካባቢ ብቻ የሚገኝ የሕንድ ምርት ነበር።

የሳሮን አበባ

የሳሮን አበባ

ብዙ የቅመማ ቅመም ምርቶች ወደ እስራኤል የሚላኩት በአረቢያ በኩል ነበር። አረቢያ በሁለተኛውና በአንደኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. “በምሥራቅና በምዕራብ መካከል ሸቀጦችን የማጓጓዙን ሥራ መቆጣጠር” የቻለችበት አንዱ ምክንያት ይህ እንደሆነ ዘ ቡክ ኦቭ ስፓይስስ (የቅመማ ቅመም መጽሐፍ) የተባለ ጽሑፍ ገልጿል። በደቡብ እስራኤል በሚገኘው በኔጌቭ ያሉት ጥንታዊ ከተሞች፣ ምሽጎችና የሲራራ ነጋዴዎች ማረፊያ የነበሩ ሰፈሮች የቅመማ ቅመም ሻጮች ለጉዞ ይጠቀሙበት የነበረውን መንገድ ለማወቅ ያስችሉናል። በተጨማሪም እነዚህ ቦታዎች “ከደቡብ አረቢያ እስከ ሜድትራንያን ይካሄድ የነበረውን እጅግ አትራፊ የሆነ . . . ንግድ” እንደሚያሳዩ የዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ማዕከል ዘግቧል።

“መጠናቸው ትንሽ፣ ዋጋቸው ከፍ ያለ እንዲሁም በሸማቾች ዘንድ ሁልጊዜ ተፈላጊ የነበሩት ቅመማ ቅመሞች በተለይ በንግድ ሸቀጥነታቸው ተመራጭ ነበሩ።” —የቅመማ ቅመም መጽሐፍ

እነዚህን ደስ የሚል መዓዛ ያላቸው ቅመማ ቅመሞች የጫኑ ሲራራ ነጋዴዎች አረቢያን በማቋረጥ እስከ 1,800 ኪሎ ሜትር የሚደርስ ርቀት አዘውትረው ይጓዙ ነበር። (ኢዮብ 6:19) መጽሐፍ ቅዱስ፣ “ሽቶ፣ በለሳን ከርቤ በግመሎቻቸው ጭነው” ከገለዓድ ወደ ግብፅ ስለወረዱ እስማኤላውያን ነጋዴዎች ይናገራል። (ዘፍጥረት 37:25) የያዕቆብ ልጆች ወንድማቸውን ዮሴፍን ለባርነት የሸጡት ለእነዚህ ነጋዴዎች ነው።

“በዘመናት ሁሉ ተደብቆ የኖረ የንግድ ሚስጥር”

እንስላል

እንስላል

አብዛኛውን የቅመም ንግድ ለብዙ መቶ ዘመናት ተቆጣጥረው የቆዩት የአረብ ነጋዴዎች ናቸው። እንደ ብርጉድና ቀረፋ ያሉት ከእስያ የሚገኙ ቅመሞች ብቸኛ አቅራቢዎች እነሱ ነበሩ። አረቦቹ፣ የምዕራቡ ዓለም በምሥራቅ ካሉት የቅመማ ቅመም አምራቾች ጋር ቀጥተኛ የንግድ ግንኙነት እንዳይመሠርት ለማድረግ ሲሉ ቅመሞቹን የሚዘጋጁበት ቦታ ድረስ ሄዶ ማምጣት ስላለው አደጋ የሚገልጹ የፈጠራ ታሪኮችን ያስወሩ ነበር። የቅመማ ቅመም መጽሐፍ የተባለው ጽሑፍ እንደሚገልጸው እነዚህ ቅመሞች ስለሚገኙበት ቦታ የነበረው መረጃ “ለረጅም ጊዜ ተደብቆ የቆየ የንግድ ሚስጥር” ነበር።

ከሙን

ከሙን

አረቦቹ ምን ዓይነት ታሪኮችን ያስወሩ ነበር? በአምስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. የኖረው ግሪካዊ የታሪክ ምሁር የሆነው ሄሮዶተስ እንደጻፈው አስፈሪ ወፎች ሊደረስባቸው በማይችሉ ገደሎች ላይ በቀረፋ ዛፎች ቅርፊት ጎጇቸውን እንደሚሠሩ የሚገልጹ ታሪኮች ይነገሩ ነበር። ሄሮዶተስ እንደጻፈው ከሆነ ታሪኮቹ፣ ይህን ውድ ቅመም ሊሰበስቡ የሚሄዱት ሰዎች ትላልቅ ሙዳ ሥጋዎችን በገደሉ ግርጌ ያስቀምጡ እንደነበር ይገልጻሉ። ከዚያም ወፎቹ ተስገብግበው ብዙ ሥጋ ወደ ጎጇቸው ሲወስዱ ጎጇቸው ጭነቱ በዝቶበት ወደ መሬት ይወድቃል። በዚህ ጊዜ ሰዎቹ በፍጥነት ቀረፋውን ሰብስበው ለነጋዴዎች ይሸጡታል። እንዲህ ዓይነቶቹ የፈጠራ ታሪኮች በሰፊው ይነገሩ ነበር። በመሆኑም “[ቀረፋ] መሰብሰብ ስላሉት አደጋዎች የሚነገረው ወሬ ቅመሙ በውድ ዋጋ እንዲሸጥ አድርጎ ነበር” በማለት የቅመማ ቅመም መጽሐፍ ገልጿል።

ኮሰረት

ኮሰረት

የኋላ ኋላ ግን የአረቦቹ ሚስጥር ስለተጋለጠ በቅመማ ቅመም ንግድ ላይ የነበራቸውን የበላይነት አጡ። በአንደኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. የግብጿ እስክንድሪያ ትልቅ ወደብ የነበራት ከመሆኑም ሌላ የቅመማ ቅመም ንግድ መናኸሪያ ሆና ነበር። መርከበኞች በሕንድ ውቅያኖስ ላይ በሚነፍሱ ነፋሶች ታግዘው የባሕር ጉዞ ማድረግ የሚችሉበትን መንገድ ስላወቁ የሮማውያን መርከቦች ከግብፅ ወደቦች ተነስተው ወደ ሕንድ መጓዝ ጀመሩ። በዚህም የተነሳ የቅንጦት ሸቀጥ የነበሩት ቅመሞች እንደ ልብ የሚገኙ ሆኑ፤ ዋጋቸውም ቢሆን ቀነሰ።

በአሁኑ ጊዜ የቅመሞች ዋጋ ከወርቅ ጋር የሚወዳደር አይደለም። ደግሞም የቅመማ ቅመም ውጤቶች ለንጉሥ ገጸ በረከት ተደርገው የሚቀርቡ ነገሮች እንደሆኑ አድርገን አናስብም። ሆኖም በዓለም ዙሪያ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አሁንም ቢሆን በተለያዩ ቅመሞች የተሠሩ ሽቶዎችንና መድኃኒቶችን ይጠቀማሉ፤ በተጨማሪም ቅመሞችን ለምግብ ማጣፈጫነት እንጠቀምባቸዋለን። በእርግጥም ከብዙ ዘመናት በፊት እንደነበረው ሁሉ በዛሬው ጊዜም ቅመሞች ያላቸው ማራኪ መዓዛ ተወዳጅ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።

የቀረፋ እንጨቶች

ቀረፋ

a መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈበት ቋንቋ “ቅመም” ወይም “ቅመማ ቅመም” ተብለው የተተረጎሙት ቃላት በዋነኝነት የሚያመለክቱት የምግብ ማጣፈጫዎችን ሳይሆን ደስ የሚል መዓዛ ያላቸው የዕፀዋት ውጤቶችን ነው።

b “ቅመማ ቅመም” የሚለው አገላለጽ በአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ላይ “የበለሳን ዘይት” ተብሎ ተተርጉሟል፤ ይህም ከዛፎችና ከቁጥቋጦዎች የሚገኙ ደስ የሚል መዓዛ ያላቸው ዘይቶችን ወይም ዕጣኖችን ያመለክታል።

ቅመማ ቅመሞች በጥንት ዘመን የነበራቸው ጥቅም

የቅብዓት ዘይትና ቅዱስ ዕጣን ለመቀመም። ይሖዋ የቅብዓት ዘይት እና ቅዱስ ዕጣን የሚቀመምበትን መንገድ ለሙሴ ነግሮት ነበር። ዘይቱም ሆነ ዕጣኑ ከአራት የተለያዩ ቅመሞች የሚሠሩ ናቸው። (ዘፀአት 30:22-25, 34-38) የቅብዓት ዘይቱን እንዲያዘጋጁና የእነዚህን ነገሮች አቅርቦት እንዲቆጣጠሩ አንዳንድ ካህናት ተመድበው ነበር።—ዘኍልቍ 4:16፤ 1 ዜና መዋዕል 9:30

ሽቶዎችና ቅባቶች ለመሥራት። የገንዘብ አቅሙ ያላቸው ሰዎች፣ ጥሩ መዓዛ ያላቸው ዱቄቶችን ለቤታቸው፣ ለልብሳቸው፣ ለአልጋቸውና ለሰውነታቸው ይጠቀሙ ነበር። (አስቴር 2:12፤ ምሳሌ 7:17፤ ማሕልየ መሓልይ 3:6, 7፤ 4:13, 14) የአልዓዛር እህት ማርያም በጣም ውድ የሆነ “ንጹሕ የናርዶስ ሽቶ” በኢየሱስ ፀጉርና እግር ላይ አፍስሳለች። “ንጹሕ የናርዶስ ሽቶ” የያዘ አንድ ትንሽ ብልቃጥ የአንድ ሰው የዓመት ደሞዝ ያህል ዋጋ ነበረው።—ማርቆስ 14:3-5፤ ዮሐንስ 12:3-5

አስከሬኖችን ለቀብር ለማዘጋጀት። ኒቆዲሞስ የኢየሱስን አስከሬን ለቀብር ለማዘጋጀት “የከርቤና የእሬት ጥቅልል” አምጥቶ ነበር። (ዮሐንስ 19:39, 40) አንዳንድ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርትም “ጥሩ መዓዛ ያላቸው ቅመሞችና ሽቶዎች” ይዘው ወደ ኢየሱስ መቃብር ሄደዋል።—ሉቃስ 23:56–24:1

ለምግብ ማጣፈጫነት። እስራኤላውያን ከዓሣና ከሥጋ የሚዘጋጁ ምግቦችን ለማጣፈጥ ቅመማ ቅመም ወይም ማጣፈጫ ይጨምሩ ነበር። በተጨማሪም የወይን ጠጅ ኃይሉ እንዲጨምር ሲባል ቅመሞች ይገቡበት ነበር።—ማሕልየ መሓልይ 8:2 NW

ለኢየሱስ የተሰጡት ሁለት ቅመሞች

ነጭ ዕጣን እና ከርቤ የሚገኙት የትናንሽ ዛፎችን ወይም የእሾሃማ ቁጥቋጦዎችን ቅርፊት በመሰንጠቅ ከሚወጣው ሙጫ ነው።

የነጭ ዕጣን ዛፍ ይበቅል የነበረው በደቡብ አረቢያ የባሕር ዳርቻዎች ላይ ሲሆን የከርቤ ቁጥቋጦ ደግሞ ከፊል በረሃማ በሆኑት የአሁኖቹ ሶማሊያና የመን ውስጥ ይገኝ ነበር። ሁለቱም ቅመሞች ደስ በሚል መዓዛቸው የተነሳ ተወዳጅ ነበሩ። ይሖዋም እነዚህ ቅመሞች ለእሱ በሚቀርብለት አምልኮ ውስጥ ጥቅም ላይ እንዲውሉ አዝዞ ነበር፤ የቅብዓት ዘይቱን ለማዘጋጀት ከሚያገለግሉት ነገሮች አንዱ ከርቤ ሲሆን ቅዱስ ዕጣን ይቀመምባቸው ከነበሩ ነገሮች አንዱ ደግሞ ነጭ ዕጣን ነው። (ዘፀአት 30:23-25, 34-37) ይሁን እንጂ እነዚህ ቅመሞች አገልግሎት ላይ የሚውሉት በተለያየ መንገድ ነበር።

ነጭ ዕጣን መዓዛው እንዲወጣ ሲባል ይጤስ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ ከከርቤ የሚወጣው ሙጫ መጤስ ስለማያስፈልገው በቀጥታ ጥቅም ላይ ይውል ነበር። ከርቤ ስለ ኢየሱስ በሚገልጹት ዘገባዎች ላይ ሦስት ጊዜ ተጠቅሷል፦ በሕፃንነቱ በስጦታነት ቀርቦለታል፤ (ማቴዎስ 2:11) በእንጨት ላይ ተሰቅሎ ሳለ ከወይን ጋር ተቀላቅሎ ለሥቃይ ማስታገሻነት ተሰጥቶታል፤ (ማርቆስ 15:23) እንዲሁም አስከሬኑ ለቀብር በሚዘጋጅበት ወቅት ጥቅም ላይ ከዋሉት ቅመሞች አንዱ ነበር። (ዮሐንስ 19:39)

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ