የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w15 3/15 ገጽ 19-24
  • ከታላንቱ ምሳሌ ትምህርት ማግኘት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ከታላንቱ ምሳሌ ትምህርት ማግኘት
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2015
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ጌታው ለባሪያዎቹ ንብረት ሰጣቸው
  • በፍጻሜው ዘመን በታላንቱ መነገድ
  • ጌታው ሒሳቡን ለመተሳሰብ የሚመጣው መቼ ነው?
  • ክፉና ሰነፍ ባሪያ
  • በክርስቶስ ገንዘብ አጠቃቀም ላይ የተደረገ መተሳሰብ
    “የሰላሙ መስፍን“ ሲገዛ በምድር ዙሪያ የሚገኝ ዋስትና ያለው ሕይወት
  • ትጉ ስለ መሆን የተሰጠ ትምህርት—ታላንቱ
    ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
  • ማስጠንቀቂያዎቹን ልብ እያልክ ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2024
  • ‘ታማኙ ባሪያ’ ፈተናውን አለፈ!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2004
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2015
w15 3/15 ገጽ 19-24
አንደኛው ባሪያ በአምስት ታላንት፣ ሌላኛው ደግሞ በሁለት ታላንት ሲነግዱ፣ አንድ ታላንት የተቀበለው ባሪያ ግን ታላንቱን ቀብሮት ተኛ

ከታላንቱ ምሳሌ ትምህርት ማግኘት

“ለአንዱ አምስት ታላንት፣ ለሌላው ሁለት፣ ለሌላው ደግሞ አንድ [ሰጠ]።”—ማቴ. 25:15

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

  • ኢየሱስ የታላንቱን ምሳሌ የተናገረው ለምንድን ነው?

  • ጌታው ሒሳቡን ለመተሳሰብ የሚመጣው መቼ ነው?

  • ከዚህ ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?

1, 2. ኢየሱስ የታላንቱን ምሳሌ የተናገረው ለምንድን ነው?

ኢየሱስ፣ ቅቡዓን ተከታዮቹ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በታላንቱ ምሳሌ ላይ በግልጽ አስረድቷል። ይህ ምሳሌ፣ ሽልማታቸው በሰማይም ይሁን በምድር እውነተኛ ክርስቲያኖችን በሙሉ የሚመለከት በመሆኑ የምሳሌውን ትርጉም መረዳታችን አስፈላጊ ነው።

2 ኢየሱስ የታላንቱን ምሳሌ የተናገረው ደቀ መዛሙርቱ ‘ስለ መገኘቱና ስለዚህ ሥርዓት መደምደሚያ ምልክት’ ላቀረቡለት ጥያቄ መልስ ሲሰጥ ነው። (ማቴ. 24:3) በመሆኑም ምሳሌው ፍጻሜውን የሚያገኘው በዘመናችን ሲሆን ይህ ምሳሌ፣ ኢየሱስ መገኘቱንና ንጉሥ ሆኖ እየገዛ መሆኑን የሚጠቁመው ምልክት ክፍል ነው።

3. በማቴዎስ ምዕራፍ 24 እና 25 ላይ ከሚገኙት ምሳሌዎች ምን ትምህርት እናገኛለን?

3 የታላንቱ ምሳሌ ከማቴዎስ 24:45 እስከ 25:46 ላይ ተመዝግበው ከሚገኙት ተዛማጅነት ያላቸው አራት ምሳሌዎች አንዱ ነው። ስለ ታማኝና ልባም ባሪያ፣ ስለ አሥሩ ደናግል እንዲሁም ስለ በጎችና ፍየሎች የሚያወሱት ሌሎቹ ሦስት ምሳሌዎችም ኢየሱስ የመገኘቱን ምልክት በተመለከተ ለተነሳው ጥያቄ የሰጠው መልስ ክፍል ናቸው። በአራቱም ምሳሌዎች ላይ ኢየሱስ በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት የሚኖሩ እውነተኛ ተከታዮቹ ተለይተው የሚታወቁባቸውን ነገሮች ጎላ አድርጎ ገልጿል። ኢየሱስ ስለ ታማኙ ባሪያ፣ ስለ አሥሩ ደናግልና ስለ ታላንቱ የተናገራቸው ምሳሌዎች ያተኮሩት በቅቡዓን ተከታዮቹ ላይ ነው። ስለ ታማኙ ባሪያ በሚገልጸው ምሳሌ ላይ፣ በመጨረሻዎቹ ቀናት ቤተሰቦቹን የመመገብ ኃላፊነት በአደራ የተሰጣቸው ጥቂት ቅቡዓን፣ ታማኝ እና ልባም መሆን እንዳለባቸው ኢየሱስ አበክሮ ተናግሯል። ስለ ደናግሉ በሚናገረው ምሳሌ ላይ ኢየሱስ፣ ሁሉም ቅቡዓን ተከታዮቹ ዝግጁ እና ንቁ መሆን እንዳለባቸው አሳስቧል፤ ምክንያቱም እሱ እንደሚመጣ እርግጠኛ ቢሆኑም ቀኑንም ሆነ ሰዓቱን አያውቁም። በታላንቱ ምሳሌ ላይ ደግሞ ኢየሱስ፣ ቅቡዓኑ ክርስቲያናዊ ኃላፊነታቸውን በትጋት መወጣት እንዳለባቸው ጠቁሟል። ኢየሱስ የተናገረው ስለ በጎቹና ፍየሎቹ የሚገልጸው የመጨረሻው ምሳሌ ያተኮረው ምድራዊ ተስፋ ባላቸው ተከታዮቹ ላይ ነው። እነዚህ ሰዎች ታማኝ መሆንና በምድር ላሉት የኢየሱስ ቅቡዓን ወንድሞች የተሟላ ድጋፍ መስጠት እንዳለባቸው ጎላ አድርጎ ገልጿል።a እስቲ ትኩረታችንን በታላንቱ ምሳሌ ላይ እናድርግ።

ጌታው ለባሪያዎቹ ንብረት ሰጣቸው

4, 5. ሰውየው ወይም ጌታው ማንን ያመለክታል? አንድ ታላንት ምን ያህል ዋጋ ነበረው?

4 ማቴዎስ 25:14-30⁠ን አንብብ። ቀደም ካሉት ዓመታት ጀምሮ ጽሑፎቻችን በምሳሌው ላይ የተገለጸው ሰው ወይም ጌታው ኢየሱስ እንደሆነና ወደ ሌላ አገር የተጓዘው ደግሞ በ33 ዓ.ም. ወደ ሰማይ ሲያርግ እንደሆነ ገልጸዋል። ኢየሱስ፣ ከዚያ ቀደም በተናገረው ምሳሌ ላይ ወደ ሌላ አገር የሚሄድበት ዓላማ “ንጉሣዊ ሥልጣኑን [ለመረከብ]” እንደሆነ ጠቁሟል። (ሉቃስ 19:12) ኢየሱስ በመንግሥቱ ላይ ሙሉ ሥልጣን ያገኘው ልክ ወደ ሰማይ እንደተመለሰ አልነበረም።b ከዚህ ይልቅ ‘በአምላክ ቀኝ ተቀምጦ ጠላቶቹ ለእግሩ እንደ መርገጫ እስኪደረጉ ድረስ ይጠባበቅ ነበር።’—ዕብ. 10:12, 13

5 በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው ሰው ስምንት ታላንት ነበረው፤ በወቅቱ ይህ ትልቅ ሀብት ነበር።c ሰውየው ወደ ሌላ አገር ከመሄዱ በፊት ታላንቱን ለባሪያዎቹ አከፋፈለ፤ ይህን ያደረገው እሱ በሄደበት ወቅት እንዲነግዱበት አስቦ ነው። እንደዚህ ሰው ሁሉ ኢየሱስም ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት ከፍተኛ ዋጋ ያለው ንብረት ነበረው። ይህ ንብረት ምንድን ነው? የዚህ ጥያቄ መልስ ኢየሱስ በሕይወቱ ውስጥ ትልቅ ቦታ ከሰጠው ሥራ ጋር የተያያዘ ነው።

6, 7. ታላንቱ ምን ያመለክታል?

6 ኢየሱስ ለስብከቱና ለማስተማሩ ሥራ ትልቅ ቦታ ይሰጥ ነበር። (ሉቃስ 4:43⁠ን አንብብ።) ይህን ሥራ በማከናወኑ፣ ብዙ ምርት የሚያስገኝ ማሳ ማዘጋጀት ችሏል። ከተወሰነ ጊዜ በፊት ደቀ መዛሙርቱን “ዓይናችሁን ወደ ማሳው አቅንታችሁ አዝመራው እንደነጣ ተመልከቱ” ብሏቸው ነበር። (ዮሐ. 4:35-38) ይህን የተናገረው፣ ደቀ መዛሙርቱ የሚሆኑ ሌሎች በርካታ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎችን የመሰብሰቡን ሥራ በአእምሮው ይዞ ነው። እንደ አንድ ጎበዝ ገበሬ ሁሉ ኢየሱስም ለመሰብሰብ የደረሰውን አዝመራ የሚከታተል ሰው ሳያዘጋጅ ትቶት አይሄድም። በመሆኑም ከሞት ከተነሳ ብዙም ሳይቆይ ማለትም ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት ለተከታዮቹ ‘ሂዱና ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ’ የሚል ከባድ ኃላፊነት ሰጣቸው። (ማቴ. 28:18-20) በዚህ መንገድ ኢየሱስ ውድ ሀብት ይኸውም ክርስቲያናዊውን አገልግሎት በአደራ ሰጥቷቸዋል።—2 ቆሮ. 4:7

7 ታዲያ ከዚህ አንጻር ምን ብለን መደምደም እንችላለን? ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ተልእኮ ለተከታዮቹ ሲሰጣቸው “ንብረቱን” ወይም ታላንቱን በአደራ መስጠቱ ነበር። (ማቴ. 25:14) በአጭር አገላለጽ፣ ታላንቱ የመስበክና ደቀ መዛሙርት የማድረግ ኃላፊነትን ያመለክታል።

8. እያንዳንዱ ባሪያ የተሰጠው ታላንት መጠን ቢለያይም ጌታው ከእነሱ ምን ይጠብቅ ነበር?

8 በታላንቱ ምሳሌ ላይ ጌታው ለአንዱ ባሪያ አምስት ታላንት፣ ለሌላው ሁለት፣ ለሌላው ደግሞ አንድ ብቻ እንደሰጠ ተገልጿል። (ማቴ. 25:15) እያንዳንዱ ባሪያ የተሰጠው ታላንት መጠን ቢለያይም ሁሉም ባሪያዎች የተሰጣቸውን ታላንት በመጠቀም ረገድ ትጋት እንዲያሳዩ ይኸውም በአገልግሎቱ አቅማቸው የሚፈቅደውን ያህል እንዲካፈሉ ጌታው ይጠብቅባቸዋል። (ማቴ. 22:37፤ ቆላ. 3:23) በመጀመሪያው መቶ ዘመን፣ በ33 ዓ.ም. ከዋለው የጴንጤቆስጤ በዓል አንስቶ የክርስቶስ ተከታዮች በታላንቱ መነገድ ጀመሩ። በስብከቱና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ያሳዩት ትጋት በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ በሚገባ ተመዝግቦ ይገኛል።d—ሥራ 6:7፤ 12:24፤ 19:20

በፍጻሜው ዘመን በታላንቱ መነገድ

9. (ሀ) ሁለቱ ታማኝ ባሪያዎች በታላንታቸው ምን አደረጉ? ይህስ ምን ያሳያል? (ለ) “ሌሎች በጎች” ምን ሚና ይጫወታሉ?

9 በፍጻሜው ዘመን በተለይም ከ1919 ወዲህ ባለው ጊዜ፣ በምድር ላይ ያሉት የክርስቶስ ታማኝ ቅቡዓን ባሪያዎች በጌታው ታላንት ሲነግዱ ቆይተዋል። እንደ ሁለቱ ባሪያዎች ሁሉ ቅቡዓን ወንድሞችና እህቶችም በተሰጣቸው ንብረት አቅማቸው የሚፈቅደውን ያህል ሠርተዋል። ማን አምስት ታላንት፣ ማን ሁለት ታላንት እንደተሰጠው መገመት አያስፈልግም። በምሳሌው ላይ ሁለቱም ባሪያዎች ጌታው የሰጣቸውን ንብረት እጥፍ እንዳደረጉ ተገልጿል፤ ስለዚህ ሁለቱም በእኩል ደረጃ ትጋት አሳይተዋል። ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖች በዚህ ሥራ ላይ ምን ሚና ይጫወታሉ? ትልቅ ሚና አላቸው። ኢየሱስ ስለ በጎቹና ፍየሎቹ የተናገረው ምሳሌ እንደሚያሳየው ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖች በስብከቱና በማስተማሩ ሥራ የኢየሱስን ቅቡዓን ወንድሞች በታማኝነት የመደገፍ መብት አላቸው። በእነዚህ የመጨረሻዎቹ ቀናት ሁለቱ ቡድኖች፣ ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ እንደ “አንድ መንጋ” ሆነው በቅንዓት እየሠሩ ነው።—ዮሐ. 10:16

10. ኢየሱስ መገኘቱን የሚያሳየው ምልክት አንዱ ጉልህ ገጽታ ምንድን ነው?

10 ጌታው ውጤት መጠበቁ የተገባ ነው። ቀደም ሲል እንደተገለጸው በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ታማኝ ደቀ መዛሙርቱ ንብረቱ እንዲበዛ አድርገዋል። የታላንቱ ምሳሌ በሚፈጸምበት በዚህ የመጨረሻ ዘመን ስላለው ሁኔታስ ምን ማለት ይቻላል? ታማኝና ታታሪ የሆኑት የኢየሱስ አገልጋዮች በታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የስብከቱንና ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ አከናውነዋል። የኢየሱስ ተከታዮች በኅብረት የሚያካሂዱት ሥራ በየዓመቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ የመንግሥቱ አስፋፊዎች እንዲጨመሩ አድርጓል፤ በዚህም ምክንያት የስብከቱና የማስተማሩ ሥራ፣ ኢየሱስ በመንግሥቱ ሥልጣን መገኘቱን የሚያሳየው ምልክት አንዱ ጉልህ ገጽታ መሆን ችሏል። በእርግጥም ጌታቸው እንደሚደሰት ጥርጥር የለውም!

የይሖዋ አገልጋዮች ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ የተለያዩ ዘርፎች ሲካፈሉ

ክርስቶስ ውድ የሆነውን የስብከት ሥራ ለአገልጋዮቹ በአደራ ሰጥቷል (አንቀጽ 10⁠ን ተመልከት)

ጌታው ሒሳቡን ለመተሳሰብ የሚመጣው መቼ ነው?

11. ኢየሱስ ሒሳቡን የሚተሳሰበው በታላቁ መከራ ወቅት ነው ብለን የምንደመድመው ለምንድን ነው?

11 ኢየሱስ ከባሪያዎቹ ጋር ሒሳቡን ለመተሳሰብ የሚመጣው ታላቁ መከራ ከመደምደሙ ትንሽ ቀደም ብሎ ነው። እዚህ መደምደሚያ ላይ እንድንደርስ ያደረገን ምንድን ነው? በማቴዎስ ምዕራፍ 24 እና 25 ላይ ተመዝግቦ በሚገኘው ትንቢት ላይ ኢየሱስ ስለ መምጣቱ በተደጋጋሚ ገልጿል። በታላቁ መከራ ወቅት ስለሚኖረው የፍርድ ጊዜ ሲናገር “የሰው ልጅ . . . በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል” ብሏል። በመጨረሻው ዘመን የሚኖሩ ተከታዮቹ ንቁ መሆን እንዳለባቸው ሲያሳስብም “ጌታችሁ በየትኛው ቀን እንደሚመጣ [አታውቁም]” እንዲሁም “የሰው ልጅ ባላሰባችሁት ሰዓት [ይመጣል]” በማለት ተናግሯል። (ማቴ. 24:30, 42, 44) በመሆኑም ኢየሱስ፣ “የእነዚያ ባሪያዎች ጌታ መጥቶ ሒሳቡን ከባሪያዎቹ ጋር ተሳሰበ” ሲል በዚህ ሥርዓት መጨረሻ ላይ ለፍርድ የሚመጣበትን ጊዜ ማመልከቱ እንደሆነ ከሁኔታዎቹ መረዳት ይቻላል።e—ማቴ. 25:19

12, 13. (ሀ) ጌታው ሁለቱን ባሪያዎች ምን አላቸው? ለምንስ? (ለ) ቅቡዓን የመጨረሻው ማኅተም የሚደረግባቸው መቼ ነው? (“በሞት ሲያንቀላፉ ሒሳብ መተሳሰብ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) (ሐ) በጎች ተብለው የተፈረደላቸው ሰዎች ምን ሽልማት ያገኛሉ?

12 በምሳሌው ላይ እንደተገለጸው አምስት ታላንት እና ሁለት ታላንት የተቀበሉት ሁለቱ ባሪያዎች የተሰጣቸውን ታላንት እጥፍ በማድረግ ጌታው ሲመጣ ታማኝ መሆናቸውን አሳይተዋል። ጌታውም ለሁለቱም ባሪያዎች የተናገረው ነገር ተመሳሳይ ነው፤ እያንዳንዳቸውን “ጎበዝ፣ አንተ ጥሩና ታማኝ ባሪያ! በጥቂት ነገሮች ታማኝ ሆነህ ተገኝተሃል። ስለዚህ በብዙ ነገሮች ላይ እሾምሃለሁ” ብሏቸዋል። (ማቴ. 25:21, 23) ታዲያ ጌታው ማለትም ክብር የተጎናጸፈው ኢየሱስ ወደፊት ለፍርድ ሲመጣስ ምን መጠበቅ እንችላለን?

13 በሁለቱ ባሪያዎች የተመሰሉትና ትጉህ ሠራተኛ የሆኑት ቅቡዓን ደቀ መዛሙርቱ፣ ታላቁ መከራ ከመጀመሩ በፊት የመጨረሻው ማኅተም ይደረግባቸዋል። (ራእይ 7:1-3) ኢየሱስ፣ ቃል የተገባላቸውን ሰማያዊ ሽልማት ከአርማጌዶን በፊት ይሰጣቸዋል። በስብከቱ ሥራ የክርስቶስን ወንድሞች የደገፉት ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖች ደግሞ ፍርድ በሚሰጥበት ወቅት ከበጎቹ መካከል ይቆጠራሉ፤ እንዲሁም በመንግሥቱ አገዛዝ ሥር በምድር ላይ የመኖር መብት ያገኛሉ።—ማቴ. 25:34

ክፉና ሰነፍ ባሪያ

14, 15. ኢየሱስ ከቅቡዓን ወንድሞቹ መካከል ብዙዎች ክፉና ሰነፍ እንደሚሆኑ መግለጹ ነበር? አብራራ።

14 በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው የመጨረሻው ባሪያ በታላንቱ ከመነገድ፣ ሌላው ቀርቶ ታላንቱን ገንዘብ ለዋጮች ጋር ከማስቀመጥ ይልቅ መሬት ውስጥ ቀብሮታል። ይህ ባሪያ የጌታውን ጥቅም የሚነካ ነገር ሆን ብሎ በማድረጉ መጥፎ ዝንባሌ እንዳለው አሳይቷል። ጌታው “ክፉና ሰነፍ” ብሎ የጠራው መሆኑ የሚያስገርም አይደለም። ጌታው፣ የእሱን ታላንት ወስዶ አሥር ታላንት ላለው ባሪያ ሰጠው። ከዚያም ጌታው ክፉውን ባሪያ አስመልክቶ እንዲህ አለ፦ “ውጭ ወዳለው ጨለማ ጣሉት። በዚያም ያለቅሳል፣ በሐዘንም ጥርሱን ያፋጫል።”—ማቴ. 25:24-30፤ ሉቃስ 19:22, 23

15 ኢየሱስ ከጌታው ሦስት ባሪያዎች አንዱ ታላንቱን እንደቀበረው ሲገልጽ ከቅቡዓን ተከታዮቹ መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ክፉና ሰነፍ እንደሚሆኑ መጠቆሙ ነበር? በፍጹም። የምሳሌውን አውድ እንመልከት። ኢየሱስ ስለ ታማኝና ልባም ባሪያ በተናገረው ምሳሌ ላይ ባልንጀራዎቹ የሆኑትን ባሪያዎች ስለሚደበድብ ክፉ ባሪያ ጠቅሶ ነበር። ኢየሱስ ይህን ሲል ክፉ ባሪያ የሆነ ቡድን እንደሚኖር መናገሩ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ታማኙ ባሪያ፣ የክፉ ባሪያ ዓይነት ባሕርያት እንዳያንጸባርቅ ማሳሰቡ ነበር። በተመሳሳይም ኢየሱስ ስለ አሥሩ ደናግል በተናገረው ምሳሌ ላይ ከቅቡዓን ተከታዮቹ መካከል ግማሽ የሚሆኑት እንደ አምስቱ ሞኝ ደናግል እንደሚሆኑ መግለጹ አልነበረም። ከዚህ በተቃራኒ መንፈሳዊ ወንድሞቹ ንቁና ዝግጁ ካልሆኑ ምን ሊከሰት እንደሚችል ማስጠንቀቁ ነበር።f ከዚህ አንጻር፣ ኢየሱስ ስለ ታላንቱ የሚገልጸውን ምሳሌ ሲናገር በመጨረሻዎቹ ቀናት ከሚኖሩት ቅቡዓን ወንድሞቹ መካከል ብዙዎች ክፉና ሰነፍ እንደሚሆኑ እየገለጸ አልነበረም ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ ይመስላል። ከዚህ ይልቅ ቅቡዓን ተከታዮቹ ምንጊዜም በትጋት እንዲሠሩ ማለትም በታላንታቸው ‘እንዲነግዱ’ እንዲሁም ክፉው ባሪያ ካሳየው ዝንባሌና ካደረገው ነገር እንዲርቁ እያስጠነቀቃቸው ነው።—ማቴ. 25:16

16. (ሀ) ስለ ታላንቱ ከሚገልጸው ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን? (ለ) ይህ ርዕስ ስለ ታላንቱ ከሚገልጸው ምሳሌ ጋር በተያያዘ የነበረንን ግንዛቤ ያስተካከለው እንዴት ነው? (“የታላንቱን ምሳሌ ትርጉም መረዳት” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

16 ስለ ታላንቱ ከሚገልጸው ምሳሌ የምናገኛቸው ሁለት ትምህርቶች የትኞቹ ናቸው? አንደኛ፣ ጌታው ማለትም ክርስቶስ እንደ ውድ የሚመለከተውን ነገር ይኸውም የመስበኩንና ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ተልእኮ ለቅቡዓን ባሪያዎቹ ሰጥቷቸዋል። ሁለተኛ፣ ክርስቶስ ሁላችንም በስብከቱ ሥራ ትጉህ እንድንሆን ይጠብቅብናል። እንዲህ ካደረግን ጌታው ላሳየነው እምነት፣ ትጋትና ታማኝነት ወሮታ እንደሚከፍለን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ማቴ. 25:21, 23, 34

a የታማኝና ልባም ባሪያ ማንነት በሐምሌ 15, 2013 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 21-22 ከአንቀጽ 8-10 ላይ ተብራርቷል። የደናግሉ ማንነት በዚህ መጽሔት ቀደም ባለው ርዕስ ላይ ተገልጿል። ስለ በጎቹና ፍየሎቹ ምሳሌ የሚገልጽ ማብራሪያ ደግሞ በጥቅምት 15, 1995 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 23-28 እንዲሁም በዚህ መጽሔት በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ይገኛል።

b “በታላንቱ እና በምናኑ ምሳሌ መካከል ያለው ተመሳሳይነት” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

c በኢየሱስ ዘመን አንድ ታላንት ከ6,000 ዲናር ጋር የሚመጣጠን ዋጋ ነበረው። በቀን አንድ ዲናር የሚከፈለው የቀን ሠራተኛ አንድ ታላንት እንኳ ለማግኘት 20 ዓመት ገደማ መሥራት ነበረበት።

d ሐዋርያት ከሞቱ በኋላ ሰይጣን ያስነሳው ክህደት ለበርካታ ዘመናት ተስፋፍቶ ቆይቷል። በዚያ ወቅት፣ እውነተኛ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርትን እንዲያፈሩ ለክርስቲያኖች የተሰጠውን ተልእኮ በቀጣይነት የሚያከናውን አልነበረም። ይሁንና ‘በመከሩ ወቅት’ ይኸውም በመጨረሻዎቹ ቀናት ይህ ሁኔታ ተለወጠ። (ማቴ. 13:24-30, 36-43) የሐምሌ 15, 2013 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 9-12 ተመልከት።

e የሐምሌ 15, 2013 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 7-8 ከአንቀጽ 14-18⁠ን ተመልከት።

f በዚህ እትም ላይ በሚገኘው ‘ነቅታችሁ ትጠብቃላችሁ?’ በሚለው ርዕስ ላይ አንቀጽ 13⁠ን ተመልከት።

በታላንቱ እና በምናኑ ምሳሌ መካከል ያለው ተመሳሳይነት

ጌታው ከባሪያዎቹ ጋር ሒሳብ ሲተሳሰብ

የታላንቱና የምናኑ ምሳሌዎች የሚያመሳስሏቸው ነገሮች አሉ። በሁለቱም ምሳሌ ላይ፣ ሥልጣን ያለው አንድ ሰው ጉዞ ከመጀመሩ በፊት ባሪያዎቹን ጠርቶ ገንዘቡን በመስጠት የንብረቱን መጠን እንዲጨምሩ አዟቸዋል። ከዚያም ሰውየው ከጉዞው ሲመለስ ባሪያዎቹ ገንዘቡን እንዴት ጥቅም ላይ እንዳዋሉት ጠየቃቸው። (ማቴ. 25:14-30፤ ሉቃስ 19:12-27) በሁለቱም ምሳሌዎች ላይ ጌታው (1) ኢየሱስን የሚወክል ሲሆን ባሪያዎቹ (2) ደግሞ ቅቡዓን ደቀ መዛሙርቱን ያመለክታሉ። በሁለቱም ታሪኮች ላይ ጌታው ለባሪያዎቹ ገንዘብ (3) ሰጥቷቸዋል፤ ገንዘቡ ውድ የሆነውን ደቀ መዛሙርት የማድረግ መብት ያመለክታል። በተጨማሪም ሁለቱም ዘገባዎች፣ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የክፉ ባሪያ ዓይነት ዝንባሌ ካዳበሩ ምን እንደሚገጥማቸው የሚገልጽ ማስጠንቀቂያ ይዘዋል።

በሞት ሲያንቀላፉ ሒሳብ መተሳሰብ

ከመጀመሪያው መቶ ዘመን አንስቶ ታላንቱ ለቅቡዓን ደቀ መዛሙርት ተሰጥቷቸዋል፤ በመሆኑም የተሰጣቸውን የስብከት ተልእኮ እንዴት እንደተወጡ ሒሳቡን መተሳሰብ አለባቸው። ታላቁ መከራ ከመጀመሩ በፊት ታማኝነታቸውን እንደጠበቁ የሚሞቱ ቅቡዓን የመጨረሻውን ማኅተም የሚቀበሉት ሲሞቱ ነው። ይሁንና በታላንቱ ምሳሌ ላይ ኢየሱስ የተናገረው በታላቁ መከራ ወቅት በምድር ላይ በሕይወት ካሉት ቅቡዓን ጋር ሒሳቡን ለመተሳሰብ ስለ መምጣቱ ነው።

የታላንቱን ምሳሌ ትርጉም መረዳት

ጌታው ለባሪያዎቹ ሽልማት የሰጣቸው መቼ ነው?

ጌታው ሁለቱን ታማኝ ባሪያዎች ሲያወድስ

የቀድሞው ማብራሪያ፦ ኢየሱስ በ1919 በምድር ላይ ለነበሩት ቅቡዓን ባሪያዎቹ ተጨማሪ ኃላፊነት በመስጠት ሸልሟቸዋል።

የተስተካከለው ማብራሪያ፦ ክርስቶስ ወደፊት ሲመጣ ታማኝ ቅቡዓን ባሪያዎቹን ወደ ሰማይ በመውሰድ ይሸልማቸዋል።

ክፉውና ሰነፉ ባሪያ ማን ነው?

ጌታው ክፉው ባሪያ ወደ ውጭ እንዲጣል ሲያዝዝ

የቀድሞው ማብራሪያ፦ ክፉውና ሰነፉ ባሪያ የሚያመለክተው በ1914 አካባቢ የነበሩ በስብከቱ ሥራ ለመካፈል ፈቃደኛ ያልሆኑ ቅቡዓንን ነው።

የተስተካከለው ማብራሪያ፦ ኢየሱስ ከቅቡዓን ተከታዮቹ መካከል የተወሰኑት ክፉ ባሪያ እንደሚሆኑ አስቀድሞ መናገሩ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ክርስቶስ፣ ተከታዮቹን ክፉና ሰነፍ እንደሆኑ አድርጎ እንዲመለከታቸው የሚያደርግ አስተሳሰብ ወይም ድርጊት ቢኖራቸው ምን እንደሚያጋጥማቸው ማስጠንቀቁ ነበር።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ