የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w15 9/15 ገጽ 8-12
  • ሕሊናችሁ አስተማማኝ መሪ ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሕሊናችሁ አስተማማኝ መሪ ነው?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2015
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ምክንያታዊ ሁኑ
  • ገንቢ በሆነ መዝናኛ መደሰት
  • በቅንዓት እንድንሠራ ያነሳሳናል
  • ጥሩ ሕሊና ይዘህ መኖር የምትችለው እንዴት ነው?
    ‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’
  • ሕሊናህ በሚገባ ሠልጥኗል?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
  • በአምላክ ፊት ጥሩ ሕሊና መያዝ
    ከአምላክ ፍቅር ሳትወጡ ኑሩ
  • ሕሊናዬን ማሠልጠን የምችለው እንዴት ነው?
    የወጣቶች ጥያቄ
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2015
w15 9/15 ገጽ 8-12
በጥንት ጊዜ አንድ ባልና ሚስት ክርስቲያን ባልንጀራቸው ከአንድ ሥጋ ቤት ሥጋ ሲገዛ በመመልከታቸው ሲበሳጩ

ሕሊናችሁ አስተማማኝ መሪ ነው?

“የዚህ ትእዛዝ ዓላማ ከንጹሕ ልብ፣ ከጥሩ ሕሊና . . . የሚመነጭ ፍቅር እንዲኖረን ነው።”—1 ጢሞ. 1:5

መዝሙሮች፦ 57, 48

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

  • ሕሊናችን ከጤና ጋር በተያያዘ ትክክለኛ ውሳኔ እንድናደርግ የሚረዳን እንዴት ነው?

  • መዝናኛን በተመለከተ መመሪያ በመስጠት ረገድ ሕሊናችን ምን ጠቃሚ አስተዋጽኦ ያበረክታል?

  • ሕሊናችን የትኞቹን መልካም ሥራዎች እንድናከናውን ሊያነሳሳን ይችላል?

1, 2. ሕሊና የሰጠን ማን ነው? ይህ ችሎታ ያለን በመሆኑስ አመስጋኝ ልንሆን የሚገባን ለምንድን ነው?

ይሖዋ አምላክ ሰዎችን የፈጠረው ነፃ ምርጫ ማለትም የፈለጉትን የመምረጥ ነፃነት እንዲኖራቸው አድርጎ ነው። አምላክ ለመጀመሪያዎቹ ወንድና ሴት እንዲሁም ለዘሮቻቸው ትክክለኛ ምርጫ እንዲያደርጉ የሚረዳ መሪ ማለትም ሕሊና ሰጥቷቸዋል፤ ይህም ትክክልና ስህተት የሆኑ ነገሮችን መለየት የሚያስችል ውስጣዊ ዳኛ ነው። ሕሊናችንን በአግባቡ ከተጠቀምንበት ጥሩ ነገር እንድናደርግና ስህተት ከመሥራት እንድንርቅ ሊረዳን ይችላል። በመሆኑም ሕሊናችን አምላክ እንደሚወደንና ሰዎች ሁሉ መልካም በማድረግ አንድነት እንዲኖራቸው ፍላጎት እንዳለው የሚያሳይ ማስረጃ ነው።

2 ዛሬም ቢሆን ሰዎች ሕሊና አላቸው። (ሮም 2:14, 15⁠ን አንብብ።) ምንም እንኳ ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ከያዘው የሥነ ምግባር መሥፈርት እጅግ የራቁ ቢሆኑም ጥሩ ነገር የሚያደርጉና መጥፎ ነገር የሚጠሉ አንዳንድ ግለሰቦች ያጋጥሙናል። ብዙ ሰዎች የለየለት መጥፎ ድርጊት ከመፈጸም እንዲቆጠቡ የሚያደርገው ሕሊና ነው። ሰው ሁሉ ሕሊና ባይኖረው ኖሮ በዓለም ላይ ያለው ሁኔታ ምን ያህል የከፋ ይሆን እንደነበር መገመት ትችላለህ! ዛሬ ከምንሰማው ክፉ ድርጊት የባሰ እንሰማ ነበር። አምላክ ለሰዎች ሕሊና በመስጠቱ ምንኛ አመስጋኞች ነን!

3. ሕሊና በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል የምንለው ለምንድን ነው?

3 ከሌሎች ሰዎች በተለየ የይሖዋ አገልጋዮች ሕሊናቸውን ለማሠልጠን ጥረት ያደርጋሉ። ሕሊናቸው የሚነግራቸው ነገር የአምላክ ቃል ትክክልና ስህተት እንዲሁም ጥሩና መጥፎ የሆነውን በተመለከተ ከያዘው መሥፈርት ጋር የሚስማማ እንዲሆን ይፈልጋሉ። በአግባቡ የሠለጠነ ሕሊና በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል። ይሁንና ክርስቲያናዊ ሕሊናን ማሠልጠንና በዚያ መጠቀም አእምሮን የማሠራት ጉዳይ ብቻ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ጥሩ ሕሊናን ከእምነትና ከፍቅር ጋር ያያይዘዋል። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የዚህ ትእዛዝ ዓላማ ከንጹሕ ልብ፣ ከጥሩ ሕሊናና ግብዝነት ከሌለበት እምነት የሚመነጭ ፍቅር እንዲኖረን ነው።” (1 ጢሞ. 1:5) ሕሊናችንን ካሠለጠንነውና የሚነግረንን ነገር ከሰማን ለይሖዋ ያለን ፍቅር እያደገ ይሄዳል፤ እምነታችንም ይጠናከራል። ደግሞም ሕሊናችንን የምንጠቀምበት መንገድ የመንፈሳዊነታችንን ጥልቀት፣ የልባችንን ጥሩነትና ይሖዋን ለማስደሰት ያለንን ብርቱ ፍላጎት ያሳያል። በእርግጥም ሕሊናችን የሚያሰማው ድምፅ እውነተኛ ማንነታችንን በሚገባ ያሳያል።

4. ሕሊናችንን ማሠልጠን የምንችለው እንዴት ነው?

4 ይሁን እንጂ ሕሊናችንን ማሠልጠን የምንችለው እንዴት ነው? ዘወትር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት፣ ባነበብነው ነገር ላይ ማሰላሰልና ያገኘነውን እውቀት በሥራ ላይ ማዋል ይህን ለማድረግ የሚያስችሉን ቁልፍ ነገሮች ናቸው። ይህ ሲባል ግን መረጃዎችን መሰብሰብና ደንቦችን ማጥናት ማለት ብቻ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታችን ስለ ይሖዋ፣ ስለ ማንነቱ፣ ስለ ባሕርያቱ እንዲሁም ስለሚወዳቸውና ስለሚጠላቸው ነገሮች ያለን ግንዛቤ ከዕለት ወደ ዕለት እያደገ እንዲሄድ ሊረዳን ይገባል። እንዲህ ከሆነ ሕሊናችን ይሖዋ አምላክ ካወጣቸው መሥፈርቶች ጋር የሚስማማ ይሆናል። ይህ ደግሞ ይበልጥ እሱን እየመሰልን እንድንሄድ ያነሳሳናል።

5. በዚህ ርዕስ ውስጥ የትኞቹን ጉዳዮች እንመለከታለን?

5 ይሁንና እንዲህ ብለን እንጠይቅ ይሆናል፦ ውሳኔ ማድረግ በምንፈልግበት ጊዜ በደንብ የሠለጠነ ሕሊና ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው? የእምነት ባልንጀራችን በሕሊናው ተመርቶ ያደረገውን ውሳኔ ማክበር የምንችለው እንዴት ነው? እንዲሁም ሕሊናችን በቅንዓት እንድንሠራ ሊያነሳሳን የሚችለው እንዴት ነው? እነዚህን ጥያቄዎች በአእምሯችን በመያዝ ሕሊናችን በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችልባቸውን ሦስት አቅጣጫዎች እንመልከት፦ (1) ጤና፣ (2) መዝናኛ እና (3) አገልግሎት።

ምክንያታዊ ሁኑ

6. ከሕክምና ጋር በተያያዘ ምን ጥያቄ ይነሳል?

6 መጽሐፍ ቅዱስ ጎጂ ልማዶችን እንድናስወግድ እንዲሁም እንደ መብልና መጠጥ ባሉ ነገሮች ረገድ ልከኛ እንድንሆን ያበረታታናል። (ምሳሌ 23:20፤ 2 ቆሮ. 7:1) ዕድሜያችን ቢገፋም ወይም ሌሎች የአቅም ገደቦች ቢኖሩብንም እንኳ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ማድረጋችን በተወሰነ መጠን ለጤንነታችን አስተዋጽኦ ያበረክታል። በአንዳንድ አገሮች፣ ዘመናዊ ሕክምናም ሆነ ሌሎች አማራጭ የሕክምና ዘዴዎች ይገኛሉ። ወንድሞችና እህቶች የትኛውን የሕክምና ዓይነት ቢጠቀሙ የተሻለ እንደሚሆን ምክር ለመጠየቅ ወደ ቅርንጫፍ ቢሮዎች በየጊዜው ደብዳቤዎች ይልካሉ። ብዙዎች “አንድ የይሖዋ አገልጋይ እንዲህ ዓይነት ሕክምና ማድረግ ይችላል?” ብለው ይጠይቃሉ።

7. ከሕክምና ጋር በተያያዘ ውሳኔ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

7 አንድ የይሖዋ ምሥክር ከሕክምና ጋር በተያያዘ ምን ማድረግ እንዳለበት ጥያቄ ቢያቀርብም እንኳ ቅርንጫፍ ቢሮውም ሆነ የጉባኤው ሽማግሌዎች ለግለሰቡ የመወሰን ሥልጣን የላቸውም። (ገላ. 6:5) ይሁንና ግለሰቡ ጥበብ የታከለበት ውሳኔ ማድረግ እንዲችል ይሖዋ ስለ ጉዳዩ ያለውን አመለካከት ሊጠቁሙት ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ክርስቲያን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኘውን “ከደም . . . ራቁ” የሚለውን መመሪያ ማስታወስ ይኖርበታል። (ሥራ 15:29) ከዚህ በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው ሙሉውን ደም ወይም ከአራቱ ዋና ዋና የደም ክፍልፋዮች አንዱን መውሰድ የሚጠይቅ ሕክምና ተቀባይነት የለውም። አንድ ክርስቲያን ይህን ማወቁ ከአራቱ ዋና ዋና ክፍልፋዮች የተገኙ አነስተኛ ተዋጽኦዎችን በተመለከተ የግል ውሳኔ በሚያደርግበት ጊዜም እንኳ ሕሊናውን ማዳመጥ ይኖርበታል።a ይሁንና የሕክምና ዓይነቶችን ስናማርጥ መመሪያ ሊሆነን የሚችል ምን ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር አለ?

8. ፊልጵስዩስ 4:5 ለጤንነታችን ከምንሰጠው ትኩረት ጋር በተያያዘ ሊጠቅመን የሚችለው እንዴት ነው?

8 ምሳሌ 14:15 “ተላላ ቃልን ሁሉ ያምናል፤ ብልህ ግን አካሄዱን አንድ በአንድ ያጤናል” ይላል። አንዳንድ የበሽታ ዓይነቶች ፈውስ የሌላቸው ሊሆኑ ይችላሉ። በመሆኑም አንዳንድ የሕክምና ዓይነቶች በጣም ውጤታማ እንደሆኑ ሲወራ ብንሰማና ወሬው እንዲሁ የስሚ ስሚ ቢሆን እንዲህ ያሉትን የሕክምና ዓይነቶች በመጠቀም ረገድ ጥንቃቄ ማድረጋችን የጥበብ አካሄድ ነው። ጳውሎስ “ምክንያታዊነታችሁ በሰው ሁሉ ዘንድ የታወቀ ይሁን” ሲል በመንፈስ መሪነት ጽፏል። (ፊልጵ. 4:5) ምክንያታዊ መሆናችን መንፈሳዊ ጉዳዮችን ቸል እስክንል ድረስ ስለ ጤናችን ከሚገባው በላይ ከመጨነቅ እንድንቆጠብ ይረዳናል። የጤንነታችን ጉዳይ በሕይወታችን ውስጥ የመጀመሪያውን ቦታ ከያዘ ራስ ወዳድ የመሆን አዝማሚያ እየታየብን ሊሆን ይችላል። (ፊልጵ. 2:4) በሕይወታችን ውስጥ ትልቁን ቦታ ሊይዝ የሚገባው መንፈሳዊ ነገር ነው፤ በመሆኑም ስለ ጤንነታችን ያለን አመለካከት ምክንያታዊነት የሚንጸባረቅበት ሊሆን ይገባል።—ፊልጵስዩስ 1:10⁠ን አንብብ።

አንድ ባልና ሚስት አንድን የቪታሚን ዓይነት ሰዎች እንዲወስዱ ሲያግባቡ

ሌሎች የግል አመለካከትህን እንዲቀበሉ ጫና ታሳድራለህ? (አንቀጽ 9ን ተመልከት)

9. ሮም 14:13, 19 ከጤና ጋር በተያያዘ የምናደርገውን ውሳኔ የሚነካው እንዴት ነው? አንድነታችን አደጋ ላይ ሊወድቅ የሚችለውስ እንዴት ነው?

9 ምክንያታዊ የሆነ ክርስቲያን ሌሎች የእሱን አመለካከት እንዲቀበሉ ጫና አያሳድርም። በአንድ የአውሮፓ አገር አንድ ባልና ሚስት ጠቃሚ ናቸው ብለው ያሰቧቸውን ቪታሚኖችና የአመጋገብ ዓይነቶች በቅንዓት ያስተዋውቁ ነበር። ደግሞም የተወሰኑ ወንድሞችን ማሳመን ችለዋል፤ አንዳንዶች ግን ሐሳባቸውን አልተቀበሉም። ውሎ አድሮ ውጤቱ እንደተጠበቀው ሳይሆን ቀረ፤ በዚህ ጊዜ ብዙዎች ቅር ተሰኙ። ባልና ሚስቱ ለራሳቸው የፈለጉትን የአመጋገብ ዓይነት መከተልም ሆነ የመረጡትን ቪታሚን የመውሰድ መብት አላቸው፤ ይሁንና ከጤና ጋር በተያያዙ ጉዳዮች የተነሳ የጉባኤው አንድነት አደጋ ላይ እንዲወድቅ ማድረጋቸው ምክንያታዊ ነው? በጥንቷ ሮም የነበሩ ክርስቲያኖች አንዳንድ ምግቦችን መመገብንና የተወሰኑ ቀኖችን ማክበርን በተመለከተ ለተወሰነ ጊዜ በመካከላቸው የአመለካከት ልዩነት ተፈጥሮ ነበር። ጳውሎስ ምን ምክር ሰጣቸው? ቀናትን ማክበርን በተመለከተ እንደሚከተለው ብሏል፦ “አንድ ሰው አንዱ ቀን ከሌላው ቀን የበለጠ እንደሆነ አድርጎ ያስባል፤ ሌላው ደግሞ አንዱ ቀን ከሌሎቹ ቀናት ሁሉ የተለየ እንዳልሆነ ያስባል፤ እያንዳንዱ ሰው ሙሉ በሙሉ ያመነበትን ውሳኔ ያድርግ።” በሌሎች ፊት የሚያደናቅፍ ነገር ከማስቀመጥ መራቃቸው በጣም አስፈላጊ ነበር።—ሮም 14:5, 13, 15, 19, 20⁠ን አንብብ።

10. የሌሎችን የግል ውሳኔ ማክበር የሚኖርብን ለምንድን ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

10 አንድ የእምነት ባልንጀራችን በሕሊናው ተመርቶ ያደረገው የግል ውሳኔ ባይገባን ቸኩለን በእሱ ላይ መፍረድም ሆነ አስተሳሰቡን እንዲለውጥ መጫን አይገባንም። ምናልባት ሕሊናው አሁንም “ደካማ” ሊሆንና ተጨማሪ ሥልጠና ሊያስፈልገው ይችላል፤ አሊያም በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ በጣም ጥብቅ ሊሆን ይችላል። (1 ቆሮ. 8:11, 12) በሌላ በኩል ደግሞ እኛ ራሳችን ሕሊናችንን መመርመር ያስፈልገን ይሆናል፤ ይህም ሕሊናችን አምላክ ካወጣቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር በሚስማማ መንገድ ተጨማሪ ሥልጠና እንደሚያስፈልገው ሊያስገነዝበን ይችላል። ከጤና ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በተመለከተ እያንዳንዳችን የራሳችንን ውሳኔ ለማድረግና የሚያስከትልብንን ኃላፊነት ለመቀበል ፈቃደኛ መሆን ይኖርብናል።

ገንቢ በሆነ መዝናኛ መደሰት

11, 12. መዝናኛ ስንመርጥ የትኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ልናስታውስ ይገባል?

11 ይሖዋ ሰዎችን የፈጠረው ከመዝናኛ ደስታና ጥቅም እንዲያገኙ በሚያስችል መንገድ ነው። ሰለሞን “ለመሳቅም ጊዜ አለው፤ . . . ለጭፈራም ጊዜ አለው” ሲል ጽፏል። (መክ. 3:4) ይሁንና ማንኛውም ዓይነት ጊዜ ማሳለፊያ ጠቃሚ እንዲሁም አእምሮንና ሰውነትን የሚያድስ ነው ማለት አይደለም፤ በተጨማሪም ረዘም ያለ ሰዓት በመዝናኛ ማጥፋት አሊያም ብዙ ጊዜ ለመዝናኛ መመደብ ጥሩ አይደለም። ሕሊናችን ገንቢ በሆነ መዝናኛ እንድንደሰትና ከመዝናኛ ጥቅም እንድናገኝ ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?

12 መጽሐፍ ቅዱስ “የሥጋ ሥራዎች” ብሎ ከሚጠራቸው አንዳንድ ምግባሮች እንድንርቅ ያስጠነቅቀናል። የሥጋ ሥራዎች የሚከተሉትን ያካትታሉ፦ “የፆታ ብልግና፣ ርኩሰት፣ ዓይን ያወጣ ምግባር፣ ጣዖት አምልኮ፣ መናፍስታዊ ድርጊት፣ ጥላቻ፣ ጠብ፣ ቅናት፣ በቁጣ መገንፈል፣ ጭቅጭቅ፣ መከፋፈል፣ መናፍቅነት፣ ምቀኝነት፣ ሰካራምነት፣ መረን የለቀቀ ፈንጠዝያና እነዚህን የመሳሰሉ ናቸው።” ጳውሎስ “እንዲህ ያሉትን ነገሮች የሚፈጽሙ የአምላክን መንግሥት አይወርሱም” ሲል ጽፏል። (ገላ. 5:19-21) በመሆኑም ራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቃችን ተገቢ ነው፦ ‘ሕሊናዬ ጠበኝነት፣ ከፍተኛ ፉክክር፣ ብሔራዊ ስሜት ወይም ጭካኔ ከሚንጸባረቅበት ስፖርት እንድርቅ ይገፋፋኛል? ደግሞስ የብልግና ምስሎች የሚታዩበት አሊያም ብልሹ ምግባርን፣ ስካርን ወይም መናፍስታዊ ድርጊትን እንደ ጥሩ ነገር አድርጎ የሚያቀርብ ፊልም ለማየት ስፈተን ያስጠነቅቀኛል?’

13. በ⁠1 ጢሞቴዎስ 4:8 እና በ⁠ምሳሌ 13:20 ላይ የሚገኘውን ምክር ከመዝናኛ ምርጫ ጋር በተያያዘ ልንሠራበት የምንችለው እንዴት ነው?

13 መጽሐፍ ቅዱስ ከመዝናኛ ጋር በተያያዘ ሕሊናችንን ለመቅረጽ የሚረዱ መሠረታዊ ሥርዓቶችንም ይዟል። ከእነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች አንዱ “የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በጥቂቱ ይጠቅማል” የሚለው ነው። (1 ጢሞ. 4:8) ብዙዎች አዘውትሮ የተወሰነ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ለጥሩ ጤንነት እንደሚጠቅም እንዲሁም ሰውነትንና አእምሮን እንደሚያነቃቃ ያምናሉ። ከሌሎች ጋር አብረን ስፖርት መሥራት ብንፈልግ ከማንኛውም ሰው ጋር ብንሠራ ችግር ይኖረዋል? ምሳሌ 13:20 “ከጥበበኞች ጋር የሚሄድ ጥበበኛ ይሆናል፤ ከሞኞች ጋር የሚገጥም ግን ጉዳት ይደርስበታል” ይላል። ታዲያ ይህ ጥቅስ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ በሠለጠነ ሕሊናችን ተጠቅመን የምንዝናናበትን ነገር በጥንቃቄ መምረጥ እንዳለብን አይጠቁምም?

14. አንድ ቤተሰብ በ⁠ሮም 14:2-4 ላይ የሚገኘውን መሠረታዊ ሥርዓት ተግባራዊ ያደረገው እንዴት ነው?

14 ክርስቲያን እና ዳንዬላ በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ሁለት ልጆች አሏቸው። ክርስቲያን እንዲህ ይላል፦ “የቤተሰብ አምልኮ በምናደርግበት ምሽት ስለ መዝናኛ አንስተን ተወያየን። አንዳንድ የመዝናኛ ዓይነቶች ተቀባይነት ቢኖራቸውም አንዳንዶቹ ግን ተቀባይነት እንደሌላቸው ተስማማን። ጥሩ ጓደኛ የሚባለው ምን ዓይነት ሰው ነው? ከልጆቻችን መካከል አንዷ ትምህርት ቤት ውስጥ በእረፍት ሰዓት አንዳንድ ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች፣ በእሷ አመለካከት ተገቢ እንዳልሆነ የሚሰማትን ነገር እንደሚያደርጉ ነገረችን። እሷም እንደ እነሱ ለማድረግ እንደምትፈተን ገለጸች። ሁላችንም ሕሊና እንዳለንና የምናደርገውንም ሆነ ጓደኛ አድርገን የምንቀርባቸውን ሰዎች በሕሊናችን ተመርተን መምረጥ የእኛ ፋንታ እንደሆነ አስረዳናት።”—ሮም 14:2-4⁠ን አንብብ።

1. በአንድ ክርስቲያናዊ ስብሰባ ላይ አንድ ወጣት ሐሳብ ሲሰጥ ሌላኛው ሲያንቀላፋ፤ 2. አንድ የይሖዋ ምሥክር ወጣት ሌላኛው ወጣት የይሖዋ ምሥክር ተገቢ ያልሆነ ነገር ሲያደርግ በማየቱ ተረብሾ

በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነው ሕሊናህ ከአደጋ እንድትርቅ ሊረዳህ ይችላል (አንቀጽ 14ን ተመልከት)

15. ከመዝናኛ ጋር በተያያዘ ማቴዎስ 6:33⁠ን ግምት ውስጥ ማስገባታችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?

15 በተጨማሪም መቼ ብንዝናና ጥሩ ነው የሚለው ጉዳይ ሊታሰብበት ይገባል። እንደ ስብሰባ፣ መስክ አገልግሎትና የግል ጥናት ላሉ ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ቅድሚያ ትሰጣላችሁ? ወይስ ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎችን ለመዝናኛ በመደባችሁት ጊዜ ውስጥ እንደምንም አጣባችሁ ለማስገባት ጥረት ታደርጋላችሁ? ቅድሚያ የምትሰጡት ለየትኛው ነው? ኢየሱስ “እንግዲያው ከሁሉ አስቀድማችሁ የአምላክን መንግሥትና ጽድቅ ፈልጉ፤ እነዚህም ነገሮች ሁሉ ይሰጧችኋል” ብሏል። (ማቴ. 6:33) ሕሊናችሁ ኢየሱስ ከሰጠው ምክር ጋር በሚስማማ መንገድ መቅደም ያለበትን ነገር እንድታስቀድሙ ይገፋፋችኋል?

በቅንዓት እንድንሠራ ያነሳሳናል

16. ሕሊናችን በስብከቱ ሥራችን ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል?

16 ጥሩ ሕሊና መጥፎ ነገር እንዳንሠራ በማስጠንቀቅ ብቻ አይወሰንም። መልካም ሥራዎች እንድንሠራም ያነሳሳናል። ከቤት ወደ ቤት ሄዶ ማገልገልና መደበኛ ባልሆነ መንገድ መመሥከር ከመልካም ሥራዎች መካከል ቀዳሚውን ቦታ ይይዛሉ። ጳውሎስ ሕሊናው እንዲህ እንዲያደርግ ገፋፍቶታል። “እንዲህ የማድረግ ግዴታ ተጥሎብኛልና። እንዲያውም ምሥራቹን ባልሰብክ ወዮልኝ!” ሲል ጽፏል። (1 ቆሮ. 9:16) የእሱን አርዓያ ስንከተል ሕሊናችን ትክክለኛውን ነገር እያደረግን እንዳለን ይነግረናል። ምሥራቹን ስንሰብክ የምናነጋግራቸውን ሰዎች ሕሊና ለመማረክ ጥረት እናደርጋለን። ጳውሎስ “እውነትን በመግለጥ በአምላክ ፊት የሰውን ሁሉ ሕሊና በሚማርክ መንገድ ራሳችንን ብቁ አድርገን እናቀርባለን” ብሏል።—2 ቆሮ. 4:2

17. አንዲት ወጣት እህት ከሕሊናዋ ጋር የሚስማማ እርምጃ የወሰደችው እንዴት ነው?

17 ጃክሊን የ16 ዓመት ልጅ ሳለች በትምህርት ቤት ባዮሎጂ ተምራለች። በዚያን ጊዜ የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ በዝርዝር ተብራርቶ ነበር። ጃክሊን እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “ለሕሊናዬ ስለከበደኝ ክፍል ውስጥ በሚደረገው ውይይት እንደ ወትሮው ጥሩ ተሳትፎ ማድረግ አልቻልኩም። የዝግመተ ለውጥን ጽንሰ ሐሳብ ልደግፍ አልችልም። በመሆኑም ለአስተማሪዬ አቋሜን ገለጽኩለት። የሚገርመው ነገር፣ በጥሩ መንፈስ ያናገረኝ ከመሆኑም በላይ ለክፍሉ ተማሪዎች ስለ ፍጥረት ንግግር እንዳቀርብ ዕድል ሰጠኝ።” ጃክሊን በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነውን ሕሊናዋን በመስማቷና ከዚያ ጋር የሚስማማ እርምጃ በመውሰዷ ውስጣዊ እርካታ ተሰምቷታል። የአንተስ ሕሊና ትክክል የሆነውን ነገር እንድታደርግ ያነሳሳሃል?

18. ጥሩና አስተማማኝ ሕሊና እንዲኖረን የምንፈልገው ለምንድን ነው?

18 ሕይወታችንን ከይሖዋ መሥፈርቶችና መንገዶች ጋር ይበልጥ ለማስማማት ጥረት ማድረጋችን ምንኛ መልካም ነው! በዚህ ረገድ ሕሊናችን ወሳኝ ሚና ይጫወታል። ዘወትር የአምላክን ቃል በጥልቀት በማጥናት፣ ባወቅነው ነገር ላይ በማሰላሰልና ያገኘነውን እውቀት በሥራ ላይ ለማዋል ጥረት በማድረግ ሕሊናችንን ማሠልጠን እንችላለን። እንዲህ ካደረግን ሕሊናችን ለክርስቲያናዊ ሕይወታችን አስተማማኝ መሪ ይሆንልናል!

a በሰኔ 15, 2004 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 29-31 ላይ የወጣውን “የአንባቢያን ጥያቄዎች” ተመልከት።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ