የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • wp16 ቁጥር 6 ገጽ 4-7
  • በሰማይ ስለሚኖሩት አካላት የሚገልጹ ራእዮች

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በሰማይ ስለሚኖሩት አካላት የሚገልጹ ራእዮች
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2016
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ከሁሉ የላቀው ይሖዋ
  • ከአምላክ ጋር ያለው ኢየሱስ
  • አምላክን የሚያገለግሉ መላእክት
  • ሚሊዮኖችን የሚያስተው ሰይጣን
  • ከምድር የተዋጁ ሰዎች
  • በሰማይ የሚኖሩት አካላት ወደፊት ምን ያደርጋሉ?
  • ስለ መንፈሳዊው ዓለም የሚገልጹ ራእዮች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2010
  • መላእክት በሕይወታችን ውስጥ ምን ሚና ይጫወታሉ?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2006
  • መላእክት—“የሕዝብ አገልጋዮች የሆኑ መናፍስት”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2009
  • የአንባቢያን ጥያቄዎች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2003
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2016
wp16 ቁጥር 6 ገጽ 4-7
ኢየሱስ በመላእክት ታጅቦ ከይሖዋ ዙፋን ቀኝ ቆሞ

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ስለ መንፈሳዊው ዓለም የሚገልጹ ራእዮች

በሰማይ ስለሚኖሩት አካላት የሚገልጹ ራእዮች

መጽሐፍ ቅዱስ በዓይን የማይታየው መንፈሳዊ ዓለም ምን እንደሚመስል ፍንጭ የሚሰጡ በርካታ አስደናቂ ራእዮችን ይዟል። እነዚህን ራእዮች በትኩረት እንድትመረምር እናበረታታሃለን። ራእዮቹ በመንፈሳዊው ዓለም የሚኖሩትን አካላት በዓይነ ሕሊናችን መሳል እንድንችል ብቻ ሳይሆን እነዚህ አካላት በእኛ ላይ የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ እንድንገነዘብ ጭምር ይረዱናል፤ እርግጥ በእነዚህ ራእዮች ላይ የተገለጹት ነገሮች ሁሉ ቃል በቃል ይወሰዳሉ ማለት አይደለም።

ከሁሉ የላቀው ይሖዋ

“በሰማይ አንድ ዙፋን ተቀምጦ ነበር፤ በዙፋኑም ላይ የተቀመጠ ነበር። በዙፋኑም ላይ የተቀመጠው የኢያስጲድ ድንጋይና የሰርድዮን ድንጋይ ዓይነት መልክ ነበረው፤ በዙፋኑም ዙሪያ መረግድ የሚመስል ቀስተ ደመና ነበር።”—ራእይ 4:2, 3

“በዙሪያውም ደማቅ ብርሃን ነበር፤ ይህም ዝናባማ በሆነ ቀን በደመና ውስጥ እንደሚታይ ቀስተ ደመና ነበር። በዙሪያው ያለው ደማቅ ብርሃን ይህን ይመስላል። ደግሞም የይሖዋን ክብር ይመስል ነበር።”—ሕዝቅኤል 1:27, 28

ሐዋርያው ዮሐንስና ነቢዩ ሕዝቅኤል የተመለከቷቸው እነዚህ ራእዮች በቀላሉ በዓይነ ሕሊናችን ልንስላቸው የምንችላቸውን ነገሮች ይኸውም የሚያብረቀርቁ የከበሩ ድንጋዮችን፣ ቀስተ ደመናን እንዲሁም የዙፋንን ክብር በመጠቀም ልዑሉ አምላክ ይሖዋ ያለውን ግርማ ይገልጻሉ። እነዚህ ራእዮች፣ ይሖዋ የሚኖርበት ቦታ አስደናቂ ውበት የተላበሰና አስደሳች እንዲሁም ሰላም የሰፈነበት እንደሆነ ያሳያሉ።

አምላክ በዚህ መንገድ መገለጹ መዝሙራዊው ከጻፈው ከሚከተለው ሐሳብ ጋር የሚስማማ ነው፦ “ይሖዋ ታላቅ ነው፤ ደግሞም እጅግ ሊወደስ ይገባዋል። ከሌሎች አማልክት ሁሉ በላይ እጅግ የሚፈራ ነው። የሌሎች ሕዝቦች አማልክት ሁሉ ከንቱ ናቸው፤ ይሖዋ ግን ሰማያትን የሠራ አምላክ ነው። ሞገስና ግርማ በፊቱ ናቸው፤ ብርታትና ውበት በመቅደሱ ውስጥ አሉ።”—መዝሙር 96:4-6

ይሖዋ ከሁሉ የላቀ ቢሆንም እንኳ ወደ እሱ በጸሎት እንድንቀርብ ያበረታታናል፤ እንዲሁም ጸሎታችንን እንደሚሰማ ማረጋገጫ ሰጥቶናል። (መዝሙር 65:2) ሐዋርያው ዮሐንስ “አምላክ ፍቅር ነው” በማለት መጻፉ አምላክ እንደሚወደንና እንደሚያስብልን ያሳያል።—1 ዮሐንስ 4:8

ከአምላክ ጋር ያለው ኢየሱስ

“[የክርስቶስ ደቀ መዝሙር የሆነው እስጢፋኖስ] በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ትኩር ብሎ ወደ ሰማይ ሲመለከት የአምላክን ክብር እንዲሁም ኢየሱስ በአምላክ ቀኝ ቆሞ አየ፤ ከዚያም ‘እነሆ፣ ሰማያት ተከፍተው የሰው ልጅም በአምላክ ቀኝ ቆሞ አያለሁ’ አለ።”—የሐዋርያት ሥራ 7:55, 56

እስጢፋኖስ ይህን ራእይ ከማየቱ ከተወሰነ ጊዜ በፊት ኢየሱስ በአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ቀስቃሽነት ተገድሎ ነበር፤ እስጢፋኖስ ከላይ ያለውን የተናገረው ለእነዚሁ የሃይማኖት መሪዎች ነው። ራእዩ ኢየሱስ ከሞት ተነስቶ በሰማይ ክብር እንደተጎናጸፈ ያረጋግጣል። ይህን በተመለከተ ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት ጽፎ ነበር፦ “[ይሖዋ] ክርስቶስን ከሞት [አስነስቶ] በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ [አስቀምጦታል]፤ . . . በዚህ ሥርዓት ብቻ ሳይሆን በሚመጣውም ጭምር ከየትኛውም መስተዳድር፣ ሥልጣን፣ ኃይልና ጌትነት እንዲሁም ከተሰየመው ከየትኛውም ስም በላይ እጅግ የላቀ ቦታ ሰጥቶታል።”—ኤፌሶን 1:20, 21

ቅዱሳን መጻሕፍት ኢየሱስ ያለውን ከፍ ያለ ቦታ ከመናገር ባለፈ እሱም እንደ ይሖዋ ለሰው ልጆች ከልቡ እንደሚያስብ ይገልጻሉ። ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት፣ ሕመምተኞችንና የአካል ጉዳት ያለባቸውን ፈውሷል፤ እንዲሁም ሙታንን አስነስቷል። በተጨማሪም መሥዋዕት ሆኖ በመሞት ለአምላክና ለሰው ልጆች ጥልቅ ፍቅር እንዳለው አሳይቷል። (ኤፌሶን 2:4, 5) በአምላክ ቀኝ ያለው ኢየሱስ በቅርቡ ሥልጣኑን በመጠቀም በሁሉም ቦታ ለሚገኙ ታዛዥ የሰው ልጆች ታላቅ በረከት ያመጣል።

አምላክን የሚያገለግሉ መላእክት

“እኔም [ነቢዩ ዳንኤል] እየተመለከትኩ ሳለ ዙፋኖች ተዘጋጁ፤ ከዘመናት በፊት የነበረውም [ይሖዋ] ተቀመጠ። . . . ሺህ ጊዜ ሺዎች ያገለግሉት ነበር፤ እልፍ ጊዜ እልፍም በፊቱ ቆመው ነበር። ችሎቱ ተሰየመ፤ መጻሕፍትም ተከፈቱ።”—ዳንኤል 7:9, 10

ዳንኤል ባየው በዚህ ራእይ ላይ አንድ ብቻ ሳይሆን እጅግ ብዙ መላእክትን ተመልክቷል። ይህን ራእይ ሲመለከት በጣም ተደንቆ መሆን አለበት! መላእክት፣ ክብር የተጎናጸፉ እንዲሁም የማሰብ ችሎታ ያላቸው ኃያል መንፈሳዊ አካላት ናቸው። የተለያየ ማዕረግ ያላቸው መላእክት ያሉ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ሱራፌልና ኪሩቤል ይገኙበታል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከ250 ጊዜ በላይ ስለ መላእክት ተጠቅሷል።

መላእክት ቀደም ሲል ሰዎች የነበሩ ፍጥረታት አይደሉም። ከዚህ ይልቅ አምላክ መላእክትን የፈጠረው የሰው ልጆች ከመፈጠራቸው ከረጅም ጊዜ በፊት ነው። ምድር ስትመሠረት መላእክት በቦታው ተገኝተው የተመለከቱ ሲሆን ደስታቸውን በእልልታ ገልጸዋል።—ኢዮብ 38:4-7

ታማኝ መላእክት አምላክን ከሚያገለግሉባቸው መንገዶች አንዱ በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ ከሚከናወኑት ሥራዎች ሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ በሆነው የአምላክን መንግሥት ምሥራች በማወጁ ሥራ መካፈል ነው። (ማቴዎስ 24:14) ሐዋርያው ዮሐንስ ባየው በሚከተለው ራእይ ላይ መላእክት በዚህ ሥራ ውስጥ ያላቸው ድርሻ ተገልጿል፦ “ሌላም መልአክ በሰማይ መካከል ሲበር አየሁ፤ እሱም በምድር ላይ ለሚኖር ብሔር፣ ነገድ፣ ቋንቋና ሕዝብ ሁሉ የሚያበስረው የዘላለም ምሥራች ይዞ ነበር።” (ራእይ 14:6) መላእክት በጥንት ዘመን ያደርጉ እንደነበረው ሁሉ በዛሬው ጊዜ ከሰዎች ጋር ባይነጋገሩም እንኳ የአምላክ አገልጋዮች ምሥራቹን ሲያውጁ ቅን ልብ ካላቸው ሰዎች ጋር እንዲገናኙ ይረዳሉ።

ሚሊዮኖችን የሚያስተው ሰይጣን

“በሰማይም ጦርነት ተነሳ፦ ሚካኤልና [ኢየሱስ ክርስቶስ] መላእክቱ ከዘንዶው ጋር ተዋጉ፤ ዘንዶውና መላእክቱም ተዋጓቸው፤ ነገር ግን አልቻሏቸውም፤ ከዚያ በኋላም በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም። ስለሆነም ታላቁ ዘንዶ ይኸውም መላውን ዓለም እያሳሳተ ያለው ዲያብሎስና ሰይጣን ተብሎ የሚጠራው የጥንቱ እባብ ወደ ታች ተወረወረ፤ ወደ ምድር ተጣለ፤ መላእክቱም ከእሱ ጋር ተወረወሩ።”—ራእይ 12:7-9

በሰማይ ያለውን ሰላም የሚያደፈርስ ሁኔታ የተፈጠረበት ጊዜ ነበር። ገና በሰው ልጆች ታሪክ መጀመሪያ ላይ አንድ መልአክ ለመመለክ ባለው ከፍተኛ ምኞት የተነሳ በይሖዋ ላይ ዓመፀ፤ በዚህም ምክንያት ሰይጣን ማለትም “ተቃዋሚ” ሆነ። በኋላም ሌሎች መላእክት ከእሱ ጋር ያመፁ ሲሆን እነዚህ መላእክት አጋንንት ተብለው ይጠሩ ጀመር። ሰይጣንና አጋንንቱ እጅግ ክፉ ከመሆናቸውም በላይ ይሖዋን አጥብቀው ይቃወማሉ፤ እንዲሁም ብዙ ሰዎችን ፍቅር ከሚንጸባረቅበት የይሖዋ አመራር እንዲርቁ አድርገዋል።

ሰይጣንና አጋንንቱ ያዘቀጠ ምግባር ያላቸው ከመሆኑም በላይ ጨካኝ ናቸው። ዋነኛ የሰው ልጅ ጠላቶች ሲሆኑ በምድር ላይ ያለው መከራ እንዲባባስ ምክንያት ሆነዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ሰይጣን የታማኙን የኢዮብን ከብቶችና አገልጋዮች ገድሎበታል። በመቀጠል ደግሞ “ኃይለኛ ነፋስ” የኢዮብ ልጆች ያሉበትን ቤት እንዲመታ በማድረግ አሥሩንም ልጆቹን ገደለበት። ሰይጣን ይህም ሳይበቃው ኢዮብን “ከእግር ጥፍሩ እስከ ራስ ፀጉሩ ድረስ ክፉኛ በሚያሠቃይ እባጭ መታው።”—ኢዮብ 1:7-19፤ 2:7

ሆኖም በቅርቡ ሰይጣን ይወገዳል። ሰይጣን ወደ ምድር ከተወረወረበት ጊዜ አንስቶ “ጥቂት ጊዜ እንደቀረው” ያውቃል። (ራእይ 12:12) ሰይጣን ጥፋት ተፈርዶበታል፤ ይህ ታዲያ የምሥራች አይደለም?

ከምድር የተዋጁ ሰዎች

“በደምህም ከየነገዱ፣ ከየቋንቋው፣ ከየሕዝቡና ከየብሔሩ ሰዎችን ለአምላክ ዋጅተሃል፤ እንዲሁም ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት እንዲሆኑ አድርገሃቸዋል፤ በምድርም ላይ ነገሥታት ሆነው ይገዛሉ።”—ራእይ 5:9, 10

ኢየሱስ በምድር ላይ ትንሣኤ እንዳገኘና በሰማይ እንዲኖር ሕይወት እንደተሰጠው ሁሉ ሌሎች ሰዎችም በሰማይ ሕይወት ያገኛሉ። ኢየሱስ ለታማኝ ሐዋርያቱ እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “ለእናንተ ቦታ ለማዘጋጀት እሄዳለሁና። ደግሞም . . . እኔ ባለሁበት እናንተም እንድትሆኑ እንደገና መጥቼ እኔ ወዳለሁበት እወስዳችኋለሁ።”—ዮሐንስ 14:2, 3

እነዚህ ሰዎች ወደ ሰማይ የሚሄዱት ለአንድ ዓላማ ነው። ወደፊት በአምላክ መንግሥት አማካኝነት ከኢየሱስ ጋር በመሆን በመላው የምድር ነዋሪዎች ላይ ይገዛሉ፤ ይህ መንግሥት ለሰው ልጆች የተትረፈረፈ በረከት ያስገኛል። ኢየሱስ ባስተማረው የናሙና ጸሎት ላይ ተከታዮቹ ስለዚህ መንግሥት እንዲህ ብለው እንዲጸልዩ ነግሯቸዋል፦ “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ። መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ በሰማይ እየተፈጸመ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይፈጸም።”—ማቴዎስ 6:9, 10

ኢየሱስ ከምድር ከተዋጁት የተወሰኑ ሰዎች ጋር

በሰማይ የሚኖሩት አካላት ወደፊት ምን ያደርጋሉ?

“ከዙፋኑ አንድ ታላቅ ድምፅ እንዲህ ሲል ሰማሁ፦ ‘እነሆ፣ የአምላክ ድንኳን ከሰዎች ጋር ነው፤ . . . እሱም እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል።’”—ራእይ 21:3, 4

ይህ ትንቢታዊ ራእይ፣ ኢየሱስና ከምድር ትንሣኤ አግኝተው ወደ ሰማይ የሚሄዱ ሰዎች የሚያስተዳድሩበት የአምላክ መንግሥት የሰይጣንን ግዛት አጥፍቶ ምድርን ገነት ስለሚያደርግበት ጊዜ የሚናገር ነው። የሰው ልጆችን ለሥቃይና ለሰቆቃ የሚዳርጉ ነገሮች ከዚያ በኋላ አይኖሩም። ሞትም ጭምር ይወገዳል።

ከሞቱ በኋላ ትንሣኤ የሚያገኙት ሆኖም ወደ ሰማይ የማይሄዱት በቢሊዮን የሚቆጠሩት ሰዎችስ ምን ተስፋ አላቸው? እነዚህ ሰዎች ወደፊት ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ይኖራቸዋል።—ሉቃስ 23:43

አጋንንትን መፍራት የለብህም

በሰንሰለት እንደታሰሩ እስረኞች፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በአጉል እምነትና በክፉ መናፍስት ፍርሃት ተተብትበዋል። ከክፉ መናፍስት እንዲጠብቋቸው ሲሉ ክታቦችንና አስማታዊ የሆኑ መድኃኒቶችን ይጠቀማሉ። አንተ ግን እንዲህ ማድረግ አያስፈልግህም። መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለውን የሚያጽናና ሐሳብ ይናገራል፦ “በሙሉ ልባቸው ወደ እሱ ላዘነበሉት ሰዎች ብርታቱን ያሳይ ዘንድ የይሖዋ ዓይኖች በምድር ሁሉ ላይ ይመላለሳሉ።” (2 ዜና መዋዕል 16:9) እውነተኛው አምላክ ይሖዋ፣ ከሰይጣን እጅግ የሚበልጥ ኃይል ስላለው በእሱ ከታመንክ ይጠብቅሃል።

ይሖዋ ከክፉ መናፍስት እንዲጠብቅህ ከፈለግክ እሱን ምን እንደሚያስደስተው ማወቅና የሚያስደስተውን ነገር ማድረግ ይኖርብሃል። ለምሳሌ ያህል፣ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በኤፌሶን ከተማ ይኖሩ የነበሩት ክርስቲያኖች የአስማት መጽሐፎቻቸውን ሰብስበው አቃጥለዋል። (የሐዋርያት ሥራ 19:19, 20) አንተም በተመሳሳይ ይሖዋ እንዲጠብቅህ ከፈለግክ እንደ ጨሌ፣ ክታብ፣ የአስማት መጻሕፍት፣ የቡዳ መድኃኒትና የመሳሰሉትን እንዲሁም ጥበቃ ያስገኛሉ የሚባሉ ክሮችን ጨምሮ ከአጋንንታዊ ድርጊት ጋር ንክኪ ያለውን ማንኛውንም ዕቃ ማስወገድ ይኖርብሃል።

መጽሐፍ ቅዱስ “ራሳችሁን ለአምላክ አስገዙ፤ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙት፤ እሱም ከእናንተ ይሸሻል” ይላል። (ያዕቆብ 4:7) ይሖዋን በመታዘዝና እሱን በማገልገል ራስህን ለአምላክ ካስገዛህ ሰይጣንና አጋንንቱ ምንም ሊያደርጉህ እንደማይችሉ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ።

እነዚህ ራእዮች ይሖዋ አምላክና ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲሁም ታማኝ መላእክትና ከምድር የተዋጁ ሰዎች በጥልቅ እንደሚያስቡልንና የእኛን ደኅንነት እንደሚመኙ ያረጋግጡልናል። ወደፊት ስለሚያከናውኑት ነገር ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ከፈለግክ የይሖዋ ምሥክሮችን እንድታነጋግር ወይም www.jw.org/am ከተባለው ድረ ገጻችን ላይ ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ እንድታወርድ እናበረታታሃለን።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ