የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w16 ታኅሣሥ ገጽ 13-17
  • ‘በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ማተኮር ሕይወትና ሰላም ያስገኛል’

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ‘በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ማተኮር ሕይወትና ሰላም ያስገኛል’
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2016
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • “በሥጋዊ ነገሮች ላይ ማተኮር”
  • “በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ማተኮር”
  • ሕይወትንና ሰላምን እንድታገኙ እንደ መንፈስ ፈቃድ ተመላለሱ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2011
  • ስለ መንፈስ ማሰብ ሕይወት ያስገኛል!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2001
  • ሁሉም ሰው የሚያስፈልገው ምሥራች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2011
  • ውዳቂው ስጋችንን አንቆ የያዘውን ኃጢአት መዋጋት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2016
w16 ታኅሣሥ ገጽ 13-17

‘በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ማተኮር ሕይወትና ሰላም ያስገኛል’

“እንደ መንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ . . . አእምሯቸው በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ያተኮረ ነው።”—ሮም 8:5

መዝሙሮች፦ 45, 36

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

  • ተስፋችን ምንም ይሁን ምን፣ ሮም ምዕራፍ 8⁠ን መመርመራችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?

  • የአንድ ክርስቲያን ‘አእምሮ በሥጋዊ ነገሮች ላይ ሊያተኩር’ የሚችለው እንዴት ነው?

  • አእምሯችን በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ እንዲያተኩር ማድረግ ሲባል ምን ማለት ነው?

1, 2. ሮም ምዕራፍ 8 በተለይ የቅቡዓን ክርስቲያኖችን ትኩረት የሚስበው ለምንድን ነው?

በየዓመቱ ከሚከበረው የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ ጋር በተያያዘ ሮም 8:15-17⁠ን አንብበህ ታውቅ ይሆናል። ይህ ጥቅስ ክርስቲያኖች በመንፈስ መቀባታቸውን የሚያውቁት፣ መንፈስ ቅዱስ ከመንፈሳቸው ጋር ሆኖ ሲመሠክር እንደሆነ ይገልጻል። የዚህ ምዕራፍ የመጀመሪያ ቁጥር ደግሞ “ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድነት [ስላላቸው]” ሰዎች ይናገራል። ታዲያ ሮም ምዕራፍ 8 የሚሠራው ለቅቡዓን ክርስቲያኖች ብቻ ነው? ወይስ በምድር ላይ ለመኖር ተስፋ ያላቸውን ክርስቲያኖችም የሚጠቅም ሐሳብ ይዟል?

2 ይህ ምዕራፍ በዋነኝነት የተጻፈው ለቅቡዓን ክርስቲያኖች ነው። እነዚህ ክርስቲያኖች ‘መንፈስን ያገኙ’ ሲሆን ‘ከሥጋዊ አካላቸው ነፃ በመውጣት አምላክ ልጆቹ አድርጎ እንዲወስዳቸው እየተጠባበቁ’ ነው። (ሮም 8:23) የወደፊት ተስፋቸው በሰማይ የአምላክ ልጆች መሆን ነው። ይህ ሊሆን የቻለው ከተጠመቁ በኋላ አምላክ ከቤዛው ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ ኃጢአታቸውን ይቅር ስላላቸው እንዲሁም እነሱን በማጽደቅ መንፈሳዊ ልጆቹ ስላደረጋቸው ነው።—ሮም 3:23-26፤ 4:25፤ 8:30

3. ሮም ምዕራፍ 8 ምድራዊ ተስፋ ላላቸው ክርስቲያኖች ጠቃሚ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

3 ይሁን እንጂ ሮም ምዕራፍ 8 ምድራዊ ተስፋ ያላቸውን ክርስቲያኖችም ትኩረት ይስባል፤ ምክንያቱም አምላክ እነሱንም እንደ ጻድቃን ይመለከታቸዋል። ጳውሎስ ለሮም ክርስቲያኖች በጻፈው ደብደቤ ላይ ቀደም ሲል የጠቀሰው ሐሳብ ይህን ይጠቁማል። በምዕራፍ 4 ላይ ስለ አብርሃም ተናግሯል። ይህ የእምነት ሰው የኖረው ይሖዋ ለእስራኤላውያን ሕጉን ከመስጠቱ እንዲሁም ኢየሱስ ስለ ኃጢአታችን ከመሞቱ ከረጅም ጊዜ በፊት ነው። ያም ቢሆን ይሖዋ፣ አብርሃም አስደናቂ እምነት እንዳለው ስለተመለከተ እንደ ጻድቅ ቆጥሮታል። (ሮም 4:20-22⁠ን አንብብ።) ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ያሉ በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖችንም እንደ ጻድቅ ሊቆጥራቸው ይችላል። በመሆኑም በሮም ምዕራፍ 8 ላይ የሚገኘው ለጻድቃን የተሰጠ ምክር ለእነሱም ጠቃሚ ነው።

4. ሮም 8:21 በየትኛው ጥያቄ ላይ እንድናስብ ሊያነሳሳን ይገባል?

4 በሮም 8:21 ላይ ያለው ሐሳብ አዲሱ ዓለም እንደሚመጣ ማረጋገጫ ይሰጠናል። ይህ ጥቅስ “ፍጥረት ራሱ ደግሞ ከመበስበስ ባርነት ነፃ ወጥቶ የአምላክ ልጆች የሚያገኙት ዓይነት ክብራማ ነፃነት [እንደሚያገኝ]” ተስፋ ይሰጣል። በመሆኑም ሊያሳስበን የሚገባው በዚያ ተገኝተን ሽልማቱን ማግኘት የመቻላችን ጉዳይ ነው። አንተስ ሽልማቱን እንደምታገኝ ትተማመናለህ? ሮም ምዕራፍ 8 በዚህ ረገድ የሚረዳህ ምክር ይዟል።

“በሥጋዊ ነገሮች ላይ ማተኮር”

5. ጳውሎስ በሮም 8:4-13 ላይ የትኛውን አስፈላጊ ጉዳይ አንስቷል?

5 ሮም 8:4-13⁠ን አንብብ። ሮም ምዕራፍ 8 “እንደ ሥጋ ፈቃድ” የሚመላለሱ ሰዎችን “እንደ መንፈስ ፈቃድ” ከሚመላለሱት ጋር ያነጻጽራል። አንዳንዶች፣ ጥቅሱ የሚያነጻጽረው እውነት ውስጥ ያሉና የሌሉ በሌላ አባባል ክርስቲያን የሆኑና ያልሆኑ ሰዎችን እንደሆነ ያስቡ ይሆናል። ይሁንና ጳውሎስ ደብዳቤውን የጻፈው ‘ቅዱሳን እንዲሆኑ ለተጠሩና በአምላክ ለተወደዱ በሮም የሚኖሩ’ ሰዎች ነው። (ሮም 1:7) በመሆኑም ጳውሎስ ያነጻጸረው፣ እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚመላለሱ ክርስቲያኖችን እንደ መንፈስ ፈቃድ ከሚመላለሱ ክርስቲያኖች ጋር ነው። በእነዚህ ክርስቲያኖች መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው?

6, 7. (ሀ) “ሥጋ” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የትኞቹን ነገሮች ለማመልከት ተሠርቶበታል? (ለ) ጳውሎስ በሮም 8:4-13 ላይ “ሥጋ” የሚለውን ቃል የተጠቀመበት ምንን ለማመልከት ነው?

6 እስቲ በመጀመሪያ “ሥጋ” የሚለው ቃል ምን እንደሚያመለክት እንወያይ። ጳውሎስ ምን ማለቱ ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ “ሥጋ” የሚለውን ቃል በተለያየ መንገድ ይጠቀምበታል። አንዳንድ ጊዜ አካላችንን ሊያመለክት ይችላል። (ሮም 2:28፤ 1 ቆሮ. 15:39, 50) ቃሉ፣ ዝምድናንም የሚያመለክትበት ጊዜ አለ። ኢየሱስ “በሥጋ ከዳዊት ዘር” እንደነበር ተገልጿል፤ ጳውሎስም አይሁዳውያንን “የሥጋ ዘመዶቼ” ብሏቸዋል።—ሮም 1:3፤ 9:3

7 ጳውሎስ በምዕራፍ 7 ላይ የጠቀሰው ሐሳብ፣ በሮም 8:4-13 ላይ የተጠቀሰው “ሥጋ” ምን እንደሚያመለክት ለማወቅ ፍንጭ ይሰጠናል። “እንደ ሥጋ ፍላጎት [መኖርን]” በክርስቲያኖች ‘ሰውነት ውስጥ ይሠሩ ከነበሩት የኃጢአት ምኞቶች’ ጋር አያይዞ ጠቅሶታል። (ሮም 7:5) ይህም ጳውሎስ “እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ አእምሯቸው በሥጋዊ ነገሮች ላይ ያተኮረ ነው” ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ ለመረዳት ያስችለናል። ጳውሎስ የኃጢአት ምኞቶችና ዝንባሌዎች እንዲመሯቸውና እንዲቆጣጠሯቸው ስለሚፈቅዱ ወይም በሥጋዊ ፍላጎታቸው ላይ ስለሚያተኩሩ ሰዎች መናገሩ ነበር። በጥቅሉ ሲታይ እነዚህ ሰዎች ከፆታ ጋር በተያያዘም ይሁን በሌሎች ጉዳዮች ረገድ ምኞታቸውን፣ ፍላጎታቸውንና ስሜታቸውን የሚከተሉ ናቸው።

8. ቅቡዓን ክርስቲያኖችንም እንኳ “እንደ ሥጋ ፈቃድ [መኖር]” ስለሚያስከትለው አደጋ ማስጠንቀቅ ያስፈለገው ለምን ነበር?

8 ይሁንና ጳውሎስ “እንደ ሥጋ ፈቃድ [መኖር]” የሚያስከትለውን አደጋ ለቅቡዓን ክርስቲያኖች መጥቀስ ያስፈለገው ለምንድን ነው? አምላክ እንደ ወዳጆቹ አድርጎ የተቀበላቸውና እንደ ጻድቃን የሚቆጥራቸው በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ ክርስቲያኖችስ ተመሳሳይ አደጋ ሊያጋጥማቸው ይችላል? የሚያሳዝን ቢሆንም የትኛውም ክርስቲያን በኃጢአተኛ ሥጋው ምኞት መመራት ሊጀምር ይችላል። ለምሳሌ፣ ጳውሎስ በሮም ከነበሩት ወንድሞች መካከል አንዳንዶቹ “ለራሳቸው ፍላጎት ባሪያዎች” እንደነበሩ ጽፏል፤ ይህም የፆታ ፍላጎትን አሊያም የምግብ፣ የመጠጥ ወይም ሌላ ዓይነት ፍላጎትን ሊጨምር ይችላል። አንዳንዶቹ “የየዋሆችን ልብ [እያታለሉ]” ነበር። (ሮም 16:17, 18፤ ፊልጵ. 3:18, 19፤ ይሁዳ 4, 8, 12) በቆሮንቶስ ጉባኤ፣ ለተወሰነ ጊዜ ያህል “ከአባቱ ሚስት ጋር የሚኖር” ወንድም እንደነበረም እናስታውስ። (1 ቆሮ. 5:1) እንግዲያው አምላክ፣ ክርስቲያኖች “በሥጋዊ ነገሮች ላይ ማተኮር” እንደሌለባቸው በጳውሎስ በኩል ማሳሰቢያ መስጠቱ የሚያስገርም አይደለም።—ሮም 8:5, 6

9. ጳውሎስ በሮም 8:6 ላይ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ እንዴት ልንረዳው አይገባም?

9 ይህ ማስጠንቀቂያ ዛሬም ቢሆን ይሠራል። አምላክን ለበርካታ ዓመታት ያገለገለ ክርስቲያንም እንኳ በሥጋዊ ነገሮች ላይ ማተኮር ሊጀምር ይችላል። ጳውሎስ ይህን ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ ስለ ምግብ፣ ስለ ሥራ፣ ስለ መዝናኛ እንዲሁም ስለ ፍቅር ግንኙነት ጨርሶ ማሰብ እንደሌለብን መግለጹ አልነበረም። ማንኛውም የአምላክ አገልጋይ በሕይወቱ ውስጥ ስለ እነዚህ ነገሮች ማሰቡ አይቀርም። ኢየሱስ በምግብ ይደሰት የነበረ ሲሆን ሌሎችንም መግቧል። መዝናኛም ቢሆን አስፈላጊ መሆኑን ያውቅ ነበር። ጳውሎስም በትዳር ውስጥ ፍቅርን መግለጽ ተገቢ መሆኑን በደብዳቤው ላይ ገልጿል።

[በገጽ 14, 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አእምሮህ ያተኮረው በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ነው ወይስ በሥጋዊ ነገሮች? ከሌሎች ጋር የምታደርገው ውይይት ምን ያሳያል? (አንቀጽ 10, 11ን ተመልከት)

10. በሮም 8:5, 6 ላይ የሚገኘው “ማተኮር” የሚለው ቃል ምን ያመለክታል?

10 ታዲያ ጳውሎስ “በሥጋዊ ነገሮች ላይ ማተኮር” እንደሌለብን ሲናገር ምን ማለቱ ነበር? ጳውሎስ የተጠቀመበት የግሪክኛ ቃል “አእምሮን ወይም ልብን በአንድ ነገር ላይ ማሳረፍ፣ የታሰበበት ግብ ለማውጣት የማመዛዘን ችሎታን መጠቀም” የሚል ትርጉም አለው። እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ ሰዎች የኃጢአት ዝንባሌዎቻቸው ሕይወታቸውን እንዲመሩት ይፈቅዳሉ። አንድ ምሁር በሮም 8:5 ላይ ስለተጠቀሱት ሰዎች ሲናገሩ “ትኩረታቸውን የሚስበው ማለትም ከምንም በላይ የሚማርካቸው፣ አዘውትረው የሚያወሩትና የሚሠሩት እንዲሁም የሚያስደስታቸው ሥጋዊ ነገር ነው” ብለዋል።

11. በሕይወታችን ውስጥ የትኞቹ ነገሮች ትልቅ ቦታ እንዲይዙ እናደርግ ይሆናል?

11 በሮም የነበሩት ክርስቲያኖች ሕይወታቸው ያተኮረው በምን ላይ እንደሆነ መመርመራቸው አስፈላጊ ነበር። ሕይወታቸውን የሚቆጣጠሩት ወይም በሕይወታቸው ውስጥ ዋነኛውን ቦታ የያዙት “ሥጋዊ ነገሮች” ነበሩ? እኛም በዚህ ጥያቄ ላይ ማሰላሰላችን ተገቢ ነው። ትልቅ ቦታ የምንሰጠውና አዘውትረን የምናወራው ነገር ምንድን ነው? ነጋ ጠባ የሚያሳስበን ጉዳይስ ምንድን ነው? የአንዳንዶች ሕይወት ያተኮረው የወይን ጠጅ ዓይነቶችን በመቅመስ፣ ቤታቸውን በማሳመር፣ አዳዲስ ፋሽኖችን በመከታተል፣ ገንዘባቸውን የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ በማዋል፣ ወደተለያዩ ቦታዎች ሄደው በመዝናናት እና በመሳሰሉት ነገሮች ላይ ነው። እንደነዚህ ያሉት ነገሮች በራሳቸው ስህተት ናቸው ማለት አይደለም፤ ማንኛችንም በሕይወታችን ውስጥ እነዚህን ነገሮች እናደርግ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ በአንድ የሠርግ ድግስ ላይ ተጋባዦቹ የወይን ጠጅ እንዲያገኙ አድርጓል፤ ጳውሎስም “ጥቂት የወይን ጠጅ” እንዲጠጣ ጢሞቴዎስን መክሮታል። (1 ጢሞ. 5:23፤ ዮሐ. 2:3-11) ይሁን እንጂ ኢየሱስም ሆነ ጳውሎስ “አዘውትረው የሚያወሩትና የሚሠሩት እንዲሁም የሚያስደስታቸው” ከወይን ጠጅ ጋር የተያያዘ ነገር ነበር? ወሬያቸው ሁሉ ስለ ወይን ጠጅ ነበር? በፍጹም። እኛስ በሕይወታችን ውስጥ ትልቅ ቦታ የምንሰጠው ነገር ምንድን ነው?

12, 13. ትኩረት የምናደርግበት ነገር ሊያሳስበን የሚገባው ለምንድን ነው?

12 ራሳችንን መመርመራችን አስፈላጊ ነው። ለምን? ጳውሎስ “በሥጋዊ ነገሮች ላይ ማተኮር ሞት ያስከትላል” ሲል ጽፏል። (ሮም 8:6) ይህ ትኩረት ልንሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፤ በሥጋዊ ነገሮች ላይ ማተኮር በአሁኑ ጊዜ መንፈሳዊ ሞት የሚያስከትል ሲሆን ወደፊት ደግሞ ቃል በቃል ሕይወታችንን ያሳጣናል። ሆኖም ጳውሎስ፣ አንድ ሰው “በሥጋዊ ነገሮች ላይ ማተኮር” ስለጀመረ ብቻ መጨረሻው ሞት እንደሚሆን መናገሩ አልነበረም። ለውጥ ማድረግ ይቻላል። በቆሮንቶስ ይኖር የነበረውን የሥነ ምግባር ብልግና የፈጸመ ሰው እንደ ምሳሌ እንውሰድ፦ ይህ ሰው “በሥጋዊ ነገሮች” ላይ በማተኮሩ ከጉባኤ ተወግዷል። ያም ቢሆን ለውጥ ማድረግ ይችል ነበር፤ ደግሞም ለውጥ አድርጓል። ግለሰቡ ሥጋዊ ነገሮችን መከተሉን ትቶ ወደ ትክክለኛው ጎዳና ተመልሷል።—2 ቆሮ. 2:6-8

13 ይህ ሰው ለውጥ ማድረግ ከቻለ በዛሬው ጊዜ የሚገኝ ክርስቲያንም ለውጥ ማድረግ ይችላል፤ በተለይ ደግሞ በቆሮንቶስ የነበረውን ሰው ያህል ሥጋዊ ነገሮችን በመከተል ረገድ የከፋ ጎዳና ያልተከተለ ሰው መቀየር ላይከብደው ይችላል። በእርግጥም ጳውሎስ “በሥጋዊ ነገሮች ላይ ማተኮር” የሚያስከትለውን መዘዝ በተመለከተ የሰጠው ማስጠንቀቂያ፣ ክርስቲያኖች አስፈላጊ የሆነውን ማንኛውንም ለውጥ እንዲያደርጉ ሊያነሳሳቸው ይገባል!

“በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ማተኮር”

14, 15. (ሀ) ‘በሥጋዊ ነገሮች ላይ የማተኮር’ ተቃራኒ ምንድን ነው? (ለ) “በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ማተኮር” ሲባል ምን ማለት አይደለም?

14 ሐዋርያው ጳውሎስ “በሥጋዊ ነገሮች ላይ ማተኮር” እንደሌለብን ማሳሰቢያ ከሰጠን በኋላ “በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ማተኮር . . . ሕይወትና ሰላም ያስገኛል” የሚል ማበረታቻ አስፍሯል። ሕይወትና ሰላም ማግኘት እንዴት ያለ አስደሳች ሽልማት ነው! ታዲያ ይህን ሽልማት ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

15 አንድ ሰው “በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ [ያተኩራል]” ሲባል አስተሳሰቡ ከገሃዱ ዓለም የራቀ ይሆናል ማለት አይደለም። የሚያስበውም ሆነ የሚናገረው ነገር ሁሉ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ለአምላክ ስላለው ፍቅር አሊያም ስለ ወደፊት ተስፋው ብቻ ይሆናል ማለትም አይደለም። ጳውሎስና በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖሩ አምላክን ያስደሰቱ ሌሎች ክርስቲያኖች ሕይወታቸው በብዙ መንገዶች እንደሌላው ሰው እንደነበረ እናስታውስ። እንደ ማንኛውም ሰው ይበሉና ይጠጡ ነበር። ብዙዎቹ ትዳር መሥርተው ልጆች ወልደዋል፤ እንዲሁም የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ለማሟላት ይሠሩ ነበር።—ማር. 6:3፤ 1 ተሰ. 2:9

16. ጳውሎስ በተለመዱ የሕይወት እንቅስቃሴዎች ይካፈል የነበረ ቢሆንም በዋነኝነት ያተኮረው በምን ላይ ነበር?

16 ይሁንና በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት የአምላክ አገልጋዮች፣ እንደነዚህ ያሉት የተለመዱ እንቅስቃሴዎች በሕይወታቸው ውስጥ ዋነኛውን ቦታ እንዲይዙ አልፈቀዱም። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ጳውሎስ ድንኳን በመሥራት ይተዳደር እንደነበር ይገልጻል፤ ሆኖም ሕይወቱ በዋነኝነት ያተኮረው በክርስቲያናዊው የስብከትና የማስተማር ሥራ ላይ እንደነበር ዘገባው ይጠቁማል። (የሐዋርያት ሥራ 18:2-4ን እና 20:20, 21, 34, 35⁠ን አንብብ።) በሮም የነበሩ ወንድሞቹንና እህቶቹንም በዚህ ሥራ እንዲካፈሉ አበረታቷቸዋል። በእርግጥም በጳውሎስ ሕይወት ውስጥ ትልቁን ቦታ የያዙት መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ነበሩ። የሮም ክርስቲያኖች የእሱን ምሳሌ ሊከተሉ ይገባ ነበር፤ እኛም ብንሆን ይህን ማድረግ አለብን።—ሮም 15:15, 16

17. “በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ማተኮር” ምን ውጤት ያስገኛል?

17 በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ማተኮር ምን ውጤት ያስገኛል? ሮም 8:6 “በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ማተኮር . . . ሕይወትና ሰላም ያስገኛል” የሚል ግልጽ መልስ ይሰጠናል። ይህም መንፈስ ቅዱስ አእምሯችንን እንዲመራውና እንዲቆጣጠረው መፍቀድን እንዲሁም ከአምላክ አስተሳሰብ ጋር በሚስማማ መንገድ መኖርን ያመለክታል። ሕይወታችን “በመንፈሳዊ ነገሮች” ላይ እንዲያተኩር ካደረግን በአሁኑ ጊዜ የሚያረካና ትርጉም ያለው ሕይወት እንደሚኖረን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ውሎ አድሮ ደግሞ በሰማይ አሊያም በምድር የዘላለም ሕይወት እናገኛለን።

18. “በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ማተኮር” ሰላም የሚያስገኘው እንዴት ነው?

18 “በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ማተኮር . . . ሰላም ያስገኛል” የሚለውን የጥቅሱን ክፍል ደግሞ እንመልከት። ብዙዎች የአእምሮ ሰላም ማግኘት ከባድ ሆኖባቸዋል። ውስጣዊ ሰላም ለማግኘት ይጓጓሉ፤ እኛ ግን እንዲህ ያለውን ሰላም ማጣጣም ችለናል። በተጨማሪም ከቤተሰባችንም ሆነ ከጉባኤያችን አባላት ጋር ሰላማዊ ግንኙነት አለን። ይሁንና እኛም ሆንን ወንድሞቻችን ፍጽምና ይጎድለናል። በዚህም ምክንያት አንዳንድ ጊዜ ችግሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ፤ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥመን “ከወንድምህ ጋር ታረቅ” የሚለውን የኢየሱስ ምክር ተግባራዊ ማድረግ እንዳለብን ተምረናል። (ማቴ. 5:24) ወንድሞቻችንም “ሰላም የሚሰጠው አምላክ” አገልጋዮች መሆናቸውን ማስታወሳችን ይህን ማድረግ ቀላል እንዲሆንልን አስተዋጽኦ ያበረክታል።—ሮም 15:33፤ 16:20

19. በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ማተኮር የትኛውን በዋጋ ሊተመን የማይችል ሰላም ያስገኝልናል?

19 በዋጋ ሊተመን የማይችል ሌላም ዓይነት ሰላም አለ። “በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ማተኮር” ከፈጣሪያችን ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረን ያስችለናል። ኢሳይያስ ስለ ይሖዋ ሲናገር “ሙሉ በሙሉ በአንተ የሚመኩትን ትጠብቃለህ፤ በአንተ ስለሚታመኑ ዘላቂ ሰላም ትሰጣቸዋለህ” ብሎ ነበር፤ ይህ ትንቢት በኢሳይያስ ዘመን ፍጻሜውን ያገኘ ሲሆን በዘመናችንም በላቀ ሁኔታ እየተፈጸመ ነው።—ኢሳ. 26:3፤ ሮም 5:1⁠ን አንብብ።

20. በሮም ምዕራፍ 8 ላይ ለሚገኘው ምክር አመስጋኝ የሆንከው ለምንድን ነው?

20 ቅቡዓንም ሆንን ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያለን ክርስቲያኖች፣ በሮም ምዕራፍ 8 ላይ ከሚገኘው በመንፈስ መሪነት የተጻፈ ምክር ጥቅም ማግኘት እንችላለን። ሕይወታችን “በሥጋዊ ነገሮች” ላይ ያተኮረ እንዳይሆን ለተሰጠን ማሳሰቢያ ምንኛ አመስጋኞች ነን! “በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ማተኮር . . . ሕይወትና ሰላም ያስገኛል” የሚለውን በመንፈስ መሪነት የተሰጠ ማረጋገጫ እንደምንቀበል በሚያሳይ መንገድ መኖር የጥበብ አካሄድ እንደሆነ እንገነዘባለን። ይህን ማድረግ ዘላለማዊ ሽልማት ያስገኛል፤ ምክንያቱም ጳውሎስ “የኃጢአት ደሞዝ ሞት ነውና፤ አምላክ የሚሰጠው ስጦታ ግን በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ነው” ሲል ጽፏል።—ሮም 6:23

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ