የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • wp17 ቁጥር 6 ገጽ 12-14
  • የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች የበዙት ለምንድን ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች የበዙት ለምንድን ነው?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2017
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የመጀመሪያው መጽሐፍ ቅዱስ
  • የግሪክኛ ሰብዓ ሊቃናት ትርጉም
  • የላቲን ቩልጌት ትርጉም
  • አዳዲስ ትርጉሞች እየበዙ መጡ
  • የአምላክ ስምና “አዲስ ኪዳን”
    ለዘላለም ጸንቶ የሚኖረው መለኮታዊው ስም
  • ጥንትም ሆነ ዛሬ ጠቃሚ የሆነው “ሴፕቱጀንት”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2002
  • መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ዘመናችን የደረሰው እንዴት ነው? ክፍል አንድ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • ዕብራይስጥ እና ግሪክኛ መማር ያስፈልግሃል?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2009
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2017
wp17 ቁጥር 6 ገጽ 12-14
በጥቅልል ላይ የተጻፉ፣ የታተሙና በኤሌክትሮኒክ ፎርማት የተዘጋጁ የተለያዩ መጽሐፍ ቅዱሶች

የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች የበዙት ለምንድን ነው?

በዛሬው ጊዜ በጣም ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች የኖሩት ለምንድን ነው? አዳዲስ የመጽሐፍ ትርጉሞች መዘጋጀታቸው መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት ያግዛል ወይስ እንቅፋት ይፈጥራል? እነዚህን ትርጉሞች ያዘጋጀው ማን እንደሆነና የተዘጋጁበትን ዓላማ ማወቅህ በዚህ ረገድ ሊረዳህ ይችላል።

መጀመሪያ ግን፣ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው እንዴት ነው? የተጻፈውስ መቼ ነው? የሚሉትን ጥያቄዎች እንመርምር።

የመጀመሪያው መጽሐፍ ቅዱስ

መጽሐፍ ቅዱስ በተለምዶ በሁለት ክፍሎች የተከፈለ ነው። የመጀመሪያው ክፍል ‘የአምላክን ቅዱስ ቃል’ የያዙ 39 መጻሕፍትን ያካተተ ነው። (ሮም 3:2) የመጀመሪያው መጽሐፍ የተጻፈው በ1513 ዓ.ዓ. ሲሆን የመጨረሻው የተጻፈው ደግሞ ከ443 ዓ.ዓ. በኋላ ነው፤ አምላክ በእነዚህ 1,100 የሚያህሉ ዓመታት ውስጥ ታማኝ ሰዎችን በመንፈሱ እየመራ እነዚህ መጻሕፍት እንዲጻፉ አድርጓል። እነዚህ ሰዎች በአብዛኛው የጻፉት በዕብራይስጥ ስለሆነ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ተብሎ ይጠራል፤ በተለምዶ ብሉይ ኪዳን በመባልም ይታወቃል።

ሁለተኛው ክፍል 27 መጻሕፍትን የያዘ ሲሆን እነዚህም ቢሆኑ “የአምላክ ቃል” ናቸው። (1 ተሰሎንቄ 2:13) አምላክ የኢየሱስ ክርስቶስን ታማኝ ደቀ መዛሙርት በመንፈሱ በመምራት እነዚህን መጻሕፍት እንዲጽፉ አድርጓል፤ ይህ ክፍል የተጻፈው በአንጻራዊ ሁኔታ በጣም አጭር በሆነ ጊዜ ማለትም ከ41 ዓ.ም. እስከ 98 ዓ.ም. ድረስ ባሉት ወደ 60 የሚጠጉ ዓመታት ውስጥ ነው። እነዚህ ሰዎች በአብዛኛው የጻፉት በግሪክኛ ስለሆነ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ተብሎ ይጠራል፤ በተለምዶ አዲስ ኪዳን በመባልም ይታወቃል።

እነዚህ በመንፈስ መሪነት የተጻፉ 66 መጻሕፍት አንድ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ ተብለው ይጠራሉ፤ አምላክ ለሰው ዘር የላከው መልእክት እነዚህን መጻሕፍት በሙሉ ያካተተ ነው። ይሁን እንጂ ከዋናው ቅጂ በተጨማሪ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች የተዘጋጁት ለምንድን ነው? ከዋና ዋናዎቹ ምክንያቶች መካከል ሦስቱ የሚከተሉት ናቸው፦

  • ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ማንበብ እንዲችሉ ለማድረግ።

  • መጽሐፍ ቅዱስን በእጃቸው ይገለብጡ የነበሩ ሰዎች የሠሯቸውን ስህተቶች በማረም የመጀመሪያውን የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ መልሶ ለማስገባት።

  • መጽሐፍ ቅዱስን በዘመናዊ ቋንቋ ለማዘጋጀት።

እነዚህ ነጥቦች ሁለት ጥንታዊ ትርጉሞች እንዲዘጋጁ ምክንያት የሆኑት እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

የግሪክኛ ሰብዓ ሊቃናት ትርጉም

ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ ከ300 ዓመታት ገደማ በፊት አይሁዳውያን ምሁራን የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን ወደ ሌላ ቋንቋ ማለትም ወደ ግሪክኛ መተርጎም ጀመሩ። ይህ ትርጉም የግሪክኛ ሰብዓ ሊቃናት ትርጉም በመባል መታወቅ ጀመረ። ይህ ትርጉም የተዘጋጀው ለምን ነበር? በዚያ ጊዜ ከዕብራይስጥ ይልቅ ግሪክኛ ይናገሩ የነበሩ ብዙ አይሁዳውያን ‘ቅዱሳን መጻሕፍትን’ መረዳትና ተግባራዊ ማድረግ እንዲችሉ ለመርዳት ነበር።—2 ጢሞቴዎስ 3:15

በተጨማሪም የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም በሚሊዮን የሚቆጠሩ አይሁዳውያን ያልሆኑ ግሪክኛ ተናጋሪ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት ማወቅ እንዲችሉ ረድቷቸዋል። እንዴት? ፕሮፌሰር ዊልበርት ፍራንሲስ ሃዋርድ እንደተናገሩት “ሚስዮናውያን ከአንዱ ምኩራብ ወደ ሌላው እየሄዱ ‘ኢየሱስ መሲሕ እንደሆነ ከቅዱሳን መጻሕፍት ማስረጃ እየጠቀሱ የሚያብራሩት’ ይህንን ትርጉም ተጠቅመው ነበር፤ በመሆኑም ይህ ትርጉም የቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስ ሆነ።” (የሐዋርያት ሥራ 17:3, 4፤ 20:20) ፍሬድሪክ ፋይቪ ብሩስ የተባሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር እንደተናገሩት በርካታ አይሁዳውያን “ለሰብዓ ሊቃናት ትርጉም የነበራቸው ፍቅር እንዲጠፋ” ያደረገው አንዱ ምክንያት ይህ ነበር።

የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ቀስ በቀስ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን ሲያገኙ እነዚህን መጻሕፍት ከሰብዓ ሊቃናት የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም ጋር አንድ ላይ አደረጓቸው፤ በዛሬው ጊዜ በእጃችን ያለው ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ላይ የተሰባሰበው በዚህ መልክ ነበር።

የላቲን ቩልጌት ትርጉም

መጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎ ከተጠናቀቀ ከ300 ዓመታት ገደማ በኋላ፣ የሃይማኖት ምሁር የነበረው ጀሮም መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ላቲን ቋንቋ የተረጎመ ሲሆን ይህም ከጊዜ በኋላ ላቲን ቩልጌት ተብሎ መጠራት ጀመረ። ከላቲን ቩልጌት በፊትም ቢሆን በላቲን የተዘጋጁ የተለያዩ ትርጉሞች ነበሩ፤ ታዲያ አዲስ የላቲን ትርጉም ማዘጋጀት ያስፈለገው ለምን ነበር? ዚ ኢንተርናሽናል ስታንዳርድ ባይብል ኢንሳይክሎፒዲያ እንደገለጸው፣ ጀሮም “በተሳሳተ መንገድ የተተረጎሙ አገላለጾችን፣ በግልጽ የሚታዩ ስህተቶችንና ያለአግባብ የተጨመሩና የተቀነሱ ነገሮችን” ማረም ፈልጎ ነበር።

ጀሮም እንዲህ ያሉትን አብዛኞቹን ስህተቶች ማረም ችሏል። ሆኖም ከጊዜ በኋላ የቤተ ክርስቲያን ባለ ሥልጣናት እጅግ አስከፊ ነገር አደረጉ! ተቀባይነት ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም የላቲኑ ቩልጌት ብቻ እንደሆነ በይፋ ያወጁ ሲሆን ለቀጣዮቹ ብዙ መቶ ዘመናት ተቀባይነት ያለው ብቸኛ ትርጉም የላቲን ቩልጌት ሆነ። በመሆኑም ይህ ትርጉም ተራ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ማወቅ እንዲችሉ ከመርዳት ይልቅ አብዛኛው ሰው መጽሐፍ ቅዱስን እንዳይረዳው አድርጓል፤ ምክንያቱም ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ የላቲን ቋንቋ በብዙሃኑ ዘንድ ጨርሶ የማይታወቅ ቋንቋ ሆኖ ነበር።

አዳዲስ ትርጉሞች እየበዙ መጡ

ከዚያ በኋላ ባሉት ዘመናት የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ተዘጋጁ፤ ከእነዚህም መካከል አንዱ በአምስተኛው መቶ ዘመን ገደማ ጥቅም ላይ የዋለውና በስፋት የሚታወቀው ሲሪያክ ፐሺታ ነው። ሆኖም እስከ 14ኛው መቶ ዘመን ድረስ ተራው ሕዝብ በአፍ መፍቻ ቋንቋው መጽሐፍ ቅዱስን ማግኘት እንዲችል የተጠናከረ ጥረት ማድረግ አልተጀመረም ነበር።

በ14ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ አካባቢ እንግሊዛዊው ጆን ዊክሊፍ የአገሩ ሰዎች በሚገባ ሊረዱት በሚችሉት በእንግሊዝኛ ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስን አዘጋጀ፤ ይህም መጽሐፍ ቅዱስ በሞተ ቋንቋ ብቻ ተወስኖ እንዳይቀር የሚያስችል መንገድ ጠርጓል። ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ዮሐንስ ጉተንበርግ የማተሚያ መሣሪያ የፈለሰፈ ሲሆን ይህም የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን አዳዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን በመላው አውሮፓ በሚነገሩ የተለያዩ ቋንቋዎች ማዘጋጀትና ማሰራጨት እንዲችሉ መንገድ ከፍቶላቸዋል።

ከጊዜ በኋላ ተጨማሪ የእንግሊዝኛ ትርጉሞች ተዘጋጁ፤ በዚህም ምክንያት ተቺዎች ‘በተመሳሳይ ቋንቋ የተለያዩ ትርጉሞችን ማዘጋጀት በእርግጥ አስፈላጊ ነው?’ የሚል ጥያቄ ማንሳት ጀመሩ። በ18ኛው መቶ ዘመን የኖሩት ጆን ሉዊስ የተባሉ እንግሊዛዊ ቄስ እንደሚከተለው በማለት ጽፈዋል፦ “ቋንቋ በጊዜ ሂደት ያረጃል እንዲሁም ለመረዳት አስቸጋሪ ይሆናል፤ በመሆኑም የጥንት ትርጉሞችን ማሻሻልና አሁን ያለው ትውልድ በሚረዳው ቋንቋ እንደገና ማዘጋጀት ያስፈልጋል።”

በአሁኑ ጊዜ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን የድሮ ትርጉሞችን ለማሻሻል በሚያስችል የተሻለ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ስለተጻፈባቸው ቋንቋዎች ያላቸው እውቀት ከምንጊዜውም ይበልጥ ጨምሯል፤ እንዲሁም በቅርብ ጊዜ የተገኙ በርካታ ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች አሏቸው። ይህም የመጀመሪያውን የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ በተሻለ መንገድ ለመረዳት ያስችላቸዋል።

ስለዚህ አዳዲስ የመጽሐፍ ትርጉሞች መዘጋጀታቸው በጣም ጠቃሚ ነው። እርግጥ፣ ከአንዳንዶቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ጋር በተያያዘ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።a ይሁን እንጂ አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም የሚያዘጋጁት ሰዎች ይህን ያደረጉት ለአምላክ ባላቸው እውነተኛ ፍቅር ተነሳስተው ከሆነ የትርጉም ሥራቸው ከፍተኛ ጥቅም ሊያስገኝልን ይችላል።

መጽሐፍ ቅዱስን በራስህ ቋንቋ ኢንተርኔት ላይ ሆነህ ወይም በተንቀሳቃሽ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያህ ለማንበብ ከፈለግክ www.jw.org/amን መመልከት ትችላለህ። የሕትመት ውጤቶች > መጽሐፍ ቅዱስ በሚለው ሥር ተመልከት

a በግንቦት 1, 2008 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “ጥሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም መምረጥ የምትችለው እንዴት ነው?” የሚል ርዕስ ተመልከት።

መጽሐፍ ቅዱስና የአምላክ ቅዱስ ስም

በኢየሱስ ዘመን የነበሩ ሰዎች ይጠቀሙበት የነበረ መለኮታዊው ስም ያለበት የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም ቁራጭ

በኢየሱስ ዘመን ሰዎች ይጠቀሙበት የነበረ መለኮታዊው ስም ያለበት ጥንታዊ የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም ቁራጭ

አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትና በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ይሖዋ የሚለውን የአምላክን ቅዱስ ስም ይጠቀማል። አብዛኞቹ ዘመናዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ግን ይህን አያደርጉም። ይሖዋ በሚለው ስም ፋንታ “ጌታ” የሚለውን የማዕረግ ስም ይጠቀማሉ። አንዳንድ ተርጓሚዎች ለዚህ የሚያቀርቡት ምክንያት የአምላክን የግል ስም የሚወክሉት አራት የዕብራይስጥ ፊደላት (የሐወሐ) በግሪክኛው ሰብዓ ሊቃናት ትርጉም ውስጥ አይገኙም የሚል ነው። ይሁን እንጂ ይህ ሐሳብ እውነት ነው?

በኢየሱስ ዘመን የነበሩ ሰዎች ይጠቀሙባቸው የነበሩ ጥንታዊ የሰብዓ ሊቃናት የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ቁርጥራጮች በ20ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ላይ ተገኝተዋል። በእነዚህ ቁርጥራጮች ላይ የአምላክ ቅዱስ ስም በዕብራይስጥ ፊደላት ተጽፎ ይገኛል። ይሖዋ የሚለውን መለኮታዊ ስም አውጥተው “ጌታ” የሚል ትርጉም ባለው ኪርዮስ በሚለው የግሪክኛ ቃል የተኩት ከጊዜ በኋላ የነበሩ ገልባጮች ሳይሆኑ አይቀሩም። አዲስ ዓለም ትርጉም መለኮታዊውን ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በቀድሞ ቦታው ላይ መልሶ አስገብቷል።

የመጽሐፍ ቅዱስ ይዘት ተለውጧል?

ሙት ባሕር የተገኘው የኢሳይያስ ጥቅልል

ከ2,000 ዓመት በፊት የተዘጋጀውና በሙት ባሕር የተገኘው የኢሳይያስ ጥቅልል። ይዘቱ በዛሬው ጊዜ በእጃችን ካለው መጽሐፍ ቅዱስ ጋር በጣም ተመሳሳይ ነው

እርግጥ ነው፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ገልባጮች ስህተት የሠሩባቸው ጊዜያት አሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ ስህተቶች የመጽሐፍ ቅዱስን ይዘት አልለወጡትም። “ገልባጮች ከሠሩት ስህተት መካከል የትኛውም ቢሆን በክርስትና መሠረተ ትምህርቶች ላይ ተጽዕኖ አላሳደረም።”—አወር ባይብል ኤንድ ዚ ኤንሸንት ማኑስክሪፕትስ

አይሁዳውያን ገልባጮች ያስገቡት ስህተት በጣም ጥቂት ነው። “ክርስትና ከተመሠረተ በኋላ በነበሩት ጥቂት መቶ ዘመናት ውስጥ የነበሩ አይሁዳውያን ጸሐፍት የዕብራይስጡን መጽሐፍ ቅዱስ በሚገለብጡበት ወቅት ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርጉ ነበር።”—ሰከንድ ቶውትስ ኦን ዘ ዴድ ሲ ስክሮልስ

ለምሳሌ ያህል፣ በሙት ባሕር ከተገኙት ጥቅልሎች መካከል አንዱ የኢሳይያስ መጽሐፍ ጥቅልል ነው፤ ይህ ጥንታዊ ቅጂ ምሁራን ከዚያ በፊት በእጃቸው ከነበረው ቅጂ 1,000 ዓመት ቀደም ብሎ የተዘጋጀ ነው። ታዲያ የዚህ ጥቅልል ይዘት በዛሬው ጊዜ ካለው የኢሳይያስ መጽሐፍ ጋር ሲነጻጸር እንዴት ነው? “የተጨመረ ወይም የተቀነሰ ቃል የምናገኘው በጣም ጥቂት ቦታዎች ላይ ነው።”—ዘ ቡክ። ኤ ሂስትሪ ኦቭ ዘ ባይብል

አንዳንድ ገልባጮች በጥንቃቄ ጉድለት ፊደላትን፣ ቃላትን፣ ወይም ሐረጎችን አለዋውጦ እንደመጻፍ ያሉ ስህተቶችን የሠሩባቸው ጊዜያት ቢኖሩም በአሁኑ ጊዜ እነዚህን ስህተቶች በቀላሉ ለይቶ ማወቅና ማረም ይቻላል። “በዛሬው ጊዜ ከሚገኙ ጥንታዊ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች መካከል የአዲስ ኪዳንን ያህል ይዘቱ እንዳልተቀየረ የሚያረጋግጥ ማስረጃ ሊቀርብለት የሚችል ጽሑፍ የለም።”—ዘ ቡክስ ኤንድ ዘ ፓርችመንትስ

“አሁን በእጃችን ያለው መጽሐፍ ቅዱስ በተደጋጋሚ በእጅ የተገለበጠና በአውሮፓ በሚገኙ ማተሚያ ቤቶች በተደጋጋሚ የታተመ ቢሆንም፣ በግብፅ ከተገኘው በፓፒረስ ላይ የተጻፈ በጣም ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ ጋር አንድ ዓይነት ሊባል የሚችል መሆኑ ስጋት ያደረባቸውን አማኞች በእጅጉ የሚያረጋጋ ነው።”—ዘ ቡክ። ኤ ሂስትሪ ኦቭ ዘ ባይብል

ታዲያ የመጽሐፍ ቅዱስ ይዘት ተለውጧል? በፍጹም አልተለወጠም ብለን በእርግጠኝነት መናገር እንችላለን!

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ