የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w17 ሰኔ ገጽ 22-26
  • ትኩረታችሁን አንገብጋቢ በሆነው ጉዳይ ላይ አድርጉ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ትኩረታችሁን አንገብጋቢ በሆነው ጉዳይ ላይ አድርጉ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2017
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ይህ ጉዳይ አንገብጋቢ የሆነው ለምንድን ነው?
  • የይሖዋ ሉዓላዊነት ከመዳናችን ይበልጥ አስፈላጊ ነው
  • ከኢዮብ ታሪክ ምን እንማራለን?
  • ትኩረታችሁ እንዳይሰረቅ ተጠንቀቁ
  • ኢዮብ ንጹሕ አቋሙን ጠበቀ
    መጽሐፍ ቅዱስ—የያዘው መልእክት ምንድን ነው?
  • ኢዮብ የይሖዋን ስም ከፍ ከፍ አድርጓል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2009
  • የይሖዋን ሉዓላዊነት ደግፉ!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2017
  • “ይሖዋን ተስፋ አድርግ”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2022
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2017
w17 ሰኔ ገጽ 22-26
ሰይጣን በአምላክ ላይ የሰነዘረው የሐሰት ክስ ትክክል መሆኑን ለማሳየት ኢዮብን በከባድ በሽታ ያሠቃየው ከመሆኑም ሌላ የሐሰት አጽናኞቹ ተስፋ እንዲያስቆርጡት ለማድረግ ሞክሯል

ትኩረታችሁን አንገብጋቢ በሆነው ጉዳይ ላይ አድርጉ

“ስምህ ይሖዋ የሆነው አንተ፣ አዎ፣ አንተ ብቻ በመላው ምድር ላይ ልዑል እንደሆንክ ሰዎች ይወቁ።”—መዝ. 83:18

መዝሙሮች፦ 9, 22

ምን ትምህርት አግኝተሃል?

  • የይሖዋ ሉዓላዊነት ትክክለኛነት መረጋገጡ የሰው ልጆችን የሚመለከት አንገብጋቢ ጉዳይ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

  • ኢዮብ ፈተና ቢደርስበትም የይሖዋን ሉዓላዊነት እንደሚደግፍ ያሳየው እንዴት ነው? ይሁንና ኢዮብ እርማት የተሰጠው ለምንድን ነው?

  • የይሖዋን ሉዓላዊነት እንደምንደግፍ የምናሳይባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

1, 2. (ሀ) በሁሉም ሰው ፊት የተደቀነው አንገብጋቢ ጉዳይ ምንድን ነው? (ለ) ይህ ጉዳይ ምን ያህል አንገብጋቢ እንደሆነ መገንዘባችን አስፈላጊ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጡት ነገር ገንዘብ ነው። ትኩረታቸው በሙሉ ያረፈው ሀብት በማካበት ላይ ሲሆን ያላቸውን ሀብት ላለማጣት ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። ሌሎች ደግሞ ትልቅ ቦታ የሚሰጡት ለቤተሰባቸው፣ ለጤናቸው ወይም እንደ ስኬት ለሚቆጥሯቸው ነገሮች ነው።

2 ይሁን እንጂ በሁላችንም ፊት የተደቀነው አንገብጋቢ ጉዳይ የይሖዋ ሉዓላዊነት ትክክለኛነት መረጋገጡ ነው። ይህን አንገብጋቢ ጉዳይ ችላ እንዳንል መጠንቀቅ ይኖርብናል። ለዚህ ሊዳርገን የሚችለው ምንድን ነው? በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ከልክ በላይ መጠመዳችን የይሖዋ ሉዓላዊነት ትክክለኛነት መረጋገጡ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እንድንዘነጋ ሊያደርገን ይችላል። ወይም ደግሞ በሚደርሱብን ከባድ ፈተናዎች ተውጠን ለዚህ አንገብጋቢ ጉዳይ ተገቢውን ትኩረት ሳንሰጥ ልንቀር እንችላለን። በሌላ በኩል ግን፣ የይሖዋ ሉዓላዊነት ትክክለኛነት መረጋገጡ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ በተገነዘብን መጠን በዕለታዊ ሕይወታችን የሚገጥሙንን ተፈታታኝ ሁኔታዎች በተሻለ ሁኔታ ለመቋቋም የሚያስችል አቅም ይኖረናል። በተጨማሪም ይህን መገንዘባችን ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድንቀርብ ያደርገናል።

ይህ ጉዳይ አንገብጋቢ የሆነው ለምንድን ነው?

3. ሰይጣን ከአምላክ አገዛዝ ጋር በተያያዘ ምን ክሶች ሰንዝሯል?

3 ሰይጣን ዲያብሎስ በይሖዋ ሉዓላዊነት ትክክለኛነት ላይ ጥያቄ አንስቷል። ሰይጣን ‘የአምላክ አገዛዝ ትክክል አይደለም፤ ፍጥረታቱንም ጥሩ ነገር ይነፍጋቸዋል’ የሚል ክስ ሰንዝሯል። እንደ ዲያብሎስ አስተሳሰብ ከሆነ ሰዎች ራሳቸውን በራሳቸው ቢያስተዳድሩ የተሻለ ሕይወት መምራትና ይበልጥ ደስተኞች መሆን ይችላሉ። (ዘፍ. 3:1-5) በተጨማሪም ሰይጣን ‘ለአምላክ ከልቡ ታማኝ የሆነ ሰው የለም፤ የትኛውም ሰው ከባድ ችግር ቢያጋጥመው የይሖዋን አገዛዝ ለመቀበል አሻፈረኝ ይላል’ ያለ ያህል ነው። (ኢዮብ 2:4, 5) ዲያብሎስ በሰነዘረው ክስ ምክንያት፣ ይሖዋ ሰዎች ከአምላክ የጽድቅ አገዛዝ ቢያፈነግጡ ሕይወታቸው ምን ሊመስል እንደሚችል እንዲታይ ሲል የተወሰነ ጊዜ ፈቅዷል።

4. በይሖዋ ሉዓላዊነት ላይ የተነሳው ጥያቄ መልስ ማግኘት ያለበት ለምንድን ነው?

4 እርግጥ ነው፣ ይሖዋ የሰይጣን ክሶች ውሸት እንደሆኑ ያውቃል። ታዲያ አምላክ፣ ሰይጣን ለክሱ ማስረጃ ማቅረብ እንዲችል ጊዜ የሰጠውና ይህ ጉዳይ እልባት ሳያገኝ እንዲቆይ ያደረገው ለምንድን ነው? ጥያቄው የማሰብ ችሎታ ያላቸውን ፍጥረታት ሁሉ የሚመለከት ስለሆነ ነው። (መዝሙር 83:18⁠ን አንብብ።) የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት የይሖዋን አገዛዝ ለመቀበል አሻፈረን እንዳሉ አስታውስ፤ ከእነሱ በኋላ የኖሩ ብዙ ሰዎችም እንዲሁ አድርገዋል። ይህም አንዳንዶች ሰይጣን ያነሳው ክስ ትክክል ሳይሆን አይቀርም ብለው እንዲያስቡ ሊያደርግ ይችላል። ይህ ጥያቄ በሰዎችም ሆነ በመላእክት አእምሮ ውስጥ መጉላላቱን እስከቀጠለ ድረስ በተለያዩ ብሔራት፣ ጎሳዎች፣ ቤተሰቦችና ግለሰቦች መካከል ክፍፍል መኖሩ አይቀርም። የይሖዋ ሉዓላዊነት ትክክለኛነት ከተረጋገጠ በኋላ ግን ሁሉም ሰዎች ለይሖዋ የጽድቅ አገዛዝ ለዘላለም ይገዛሉ። በዚያ ጊዜ ዓለም አቀፍ ሰላም ይሰፍናል።—ኤፌ. 1:9, 10

5. ሉዓላዊነትን በተመለከተ ከተነሳው ጥያቄ ጋር በተያያዘ ከይሖዋ ጎን መቆም የምንችለው እንዴት ነው?

5 የይሖዋ ሉዓላዊነት ትክክል መሆኑ ይረጋገጣል፤ የሰይጣንና የሰው ልጆች አገዛዝ ደግሞ ከንቱ መሆኑ በገሃድ ይታያል፤ በመጨረሻም ሙሉ በሙሉ ይወገዳል። አምላክ ያቋቋመው መሲሐዊ መንግሥት ከሁሉ የተሻለ መስተዳድር መሆኑ ይረጋገጣል፤ ንጹሕ አቋማቸውን የጠበቁ ሰዎች ደግሞ የሰው ልጆች ከአምላክ አገዛዝ ጎን መቆም እንደሚችሉ ያሳያሉ። (ኢሳ. 45:23, 24) አንተስ ንጹሕ አቋማቸውን በመጠበቅ የይሖዋን ሉዓላዊነት ከሚደግፉ ሰዎች መካከል መቆጠር ትፈልጋለህ? እንደምትፈልግ የታወቀ ነው። ንጹሕ አቋማችንን ለመጠበቅ ከፈለግን ትኩረታችንን አንገብጋቢ በሆነው ጉዳይ ላይ ማድረግና ይህ ጉዳይ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ መገንዘብ አለብን።

የይሖዋ ሉዓላዊነት ከመዳናችን ይበልጥ አስፈላጊ ነው

6. የይሖዋ ሉዓላዊነት ትክክለኛነት መረጋገጡ ምን ያህል አስፈላጊ ነው?

6 ከላይ እንደተገለጸው የሰው ልጆችን የሚመለከተው አንገብጋቢ ጉዳይ የይሖዋ ሉዓላዊነት ትክክለኛነት መረጋገጡ ነው። ይህ ጉዳይ ከራሳችን ደስታ ይበልጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው። እንዲህ ሲባል ግን የእኛ መዳን ያን ያህል ትልቅ ቦታ አይሰጠውም ወይም ይሖዋ ለእኛ ግድ የለውም ማለት አይደለም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?

7, 8. የአምላክ ሉዓላዊነት ትክክለኛነት እንዲረጋገጥ ለሰው ልጆች የገባቸው ተስፋዎች መፈጸም አለባቸው የምንለው ለምንድን ነው?

7 ይሖዋ የሰው ልጆችን ከልቡ ይወዳል። እንዲያውም በእሱ ፊት በጣም ውድ ስለሆንን ዘላለማዊ መዳን እንድናገኝ ለማድረግ ሲል ልጁን ቤዛ አድርጎ ሰጥቷል። (ዮሐ. 3:16፤ 1 ዮሐ. 4:9) ይሖዋ ለሰው ልጆች የገባውን ቃል ሳይፈጽም ቢቀር ዲያብሎስ ‘አምላክ ውሸታምና ተገዢዎቹን ጥሩ ነገር የሚነፍግ ኢፍትሐዊ ገዢ ነው’ በማለት የሰነዘረው ክስ እውነት ይሆን ነበር። እንዲሁም “‘እገኛለሁ’ ያለው ታዲያ የት አለ? አባቶች በሞት ካንቀላፉበት ጊዜ ጀምሮ ሁሉም ነገር ከፍጥረት መጀመሪያ አንስቶ እንዳለ ይቀጥላል” ብለው የሚያፌዙ ሰዎች ትክክል ይሆኑ ነበር። (2 ጴጥ. 3:3, 4) በመሆኑም ይሖዋ፣ የሉዓላዊነቱ ትክክለኛነት መረጋገጥ ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆችም መዳን እንዲያስገኝ ያደርጋል። (ኢሳይያስ 55:10, 11⁠ን አንብብ።) ከዚህም በተጨማሪ የይሖዋ ሉዓላዊነት በፍቅር ላይ የተመሠረተ ነው። ስለሆነም ምንጊዜም ቢሆን ታማኝ አገልጋዮቹን እንደሚወዳቸው፣ እንደሚያደንቃቸውና ከፍ አድርጎ እንደሚመለከታቸው እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ዘፀ. 34:6

8 የይሖዋ ሉዓላዊነት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ነው ስንል መዳናችንን ወይም በይሖዋ ፊት ያለንን ዋጋ አቅልለን እንመለከታለን ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ የይሖዋን ሉዓላዊነትም ሆነ መዳናችንን በተመለከተ ተገቢ አመለካከት እንይዛለን ማለት ነው። እንዲህ ያለውን ተገቢ አመለካከት መያዛችን ትኩረታችንን በአንገብጋቢው ጉዳይ ላይ እንድናደርግና ከይሖዋ የጽድቅ አገዛዝ ጎን እንድንቆም ያስችለናል።

ከኢዮብ ታሪክ ምን እንማራለን?

9. ሰይጣን በኢዮብ ላይ ምን ክስ ሰንዝሯል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

9 መጀመሪያ ላይ ከተጻፉት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት አንዱ የሆነው የኢዮብ መጽሐፍ የይሖዋን ሉዓላዊነት በተመለከተ ተገቢውን አመለካከት መያዝ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ይገልጻል። ይህ መጽሐፍ ‘ኢዮብ ከባድ መከራ ቢደርስበት አምላክን ይክዳል’ በማለት ሰይጣን ክስ እንደሰነዘረ ይናገራል። እንዲያውም ሰይጣን፣ አምላክ ኢዮብ ላይ መከራ እንዲያደርስበት ጥያቄ አቅርቧል። ይሖዋ ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ አልሆነም። ይሁንና “ያለው ነገር ሁሉ በእጅህ ነው” በማለት ሰይጣን ኢዮብን እንዲፈትነው ፈቀደለት። (ኢዮብ 1:7-12⁠ን አንብብ።) ኢዮብ በአጭር ጊዜ ውስጥ አገልጋዮቹን፣ መተዳደሪያውንና የሚወዳቸውን አሥር ልጆቹን አጣ። ሰይጣን፣ በኢዮብ ላይ መከራ ያመጣው አምላክ ራሱ እንደሆነ ለማስመሰል ሞክሯል። (ኢዮብ 1:13-19) ከዚያም ሰይጣን፣ ኢዮብ አሰቃቂ በሆነ ሕመም እንዲሠቃይ አደረገ። (ኢዮብ 2:7) በዚህ ላይ ደግሞ ሚስቱም ሆነች አጽናኝ መስለው የቀረቡት ሦስት ጓደኞቹ የተናገሩት ተስፋ አስቆራጭ ንግግር ሥቃዩን አባባሰበት።—ኢዮብ 2:9፤ 3:11፤ 16:2

10. (ሀ) ኢዮብ በአምላክ ፊት ንጹሕ አቋም እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ኢዮብ እርማት ያስፈለገው ለምንድን ነው?

10 ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? የሰይጣን ክስ ሙሉ በሙሉ ውሸት መሆኑ ተረጋገጠ። ኢዮብ አምላክን ለመካድ ፈቃደኛ አልሆነም። (ኢዮብ 27:5) ይሁንና ኢዮብ ለጊዜውም ቢሆን አመለካከቱ ተዛብቶ ነበር። ጻድቅ መሆኑን ለማሳየት ጥረት ያደረገ ሲሆን መከራ የደረሰበት ለምን እንደሆነ ሊነገረው እንደሚገባ ተሰምቶት ነበር። (ኢዮብ 7:20፤ 13:24) ‘ኢዮብ ከደረሰበት መከራ አንጻር እንዲህ ቢሰማው አይፈረድበትም’ ብለን እናስብ ይሆናል። ሆኖም አምላክ የኢዮብ አስተሳሰብ መስተካከል እንደሚገባው ተሰምቶት ነበር። ይሖዋ ኢዮብን ምን አለው?

11, 12. ይሖዋ ኢዮብን ምን እንዲገነዘብ ረዳው? ኢዮብስ ምን ምላሽ ሰጠ?

11 አምላክ ለኢዮብ የተናገረው ሐሳብ በኢዮብ መጽሐፍ ላይ ከምዕራፍ 38 እስከ 41 ባሉት አራት ምዕራፎች ውስጥ ይገኛል። በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ ኢዮብ መከራ የደረሰበት ለምን እንደሆነ አምላክ በግልጽ የተናገረበትን ቦታ አናገኝም። አምላክ ለሚያደርገው ነገር ማብራሪያ መስጠት አይጠበቅበትም፤ ደግሞም ኢዮብን ያነጋገረው መከራ የደረሰበት ለምን እንደሆነ ለማስረዳት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ከአምላክ ታላቅነት አንጻር ሲታይ ኢዮብ እዚህ ግባ የሚባል ሰው እንዳልሆነ ሊያስገነዝበው ፈልጓል። እንዲሁም ይበልጥ አሳሳቢ የሆኑ ሌሎች ጉዳዮች እንዳሉ ኢዮብ እንዲያስተውል ረድቶታል። (ኢዮብ 38:18-21⁠ን አንብብ።) በመሆኑም ኢዮብ አመለካከቱን ማስተካከል ችሏል።

12 ይሖዋ፣ ኢዮብ ያንን ሁሉ መከራ በጽናት ከተቋቋመ በኋላ እንዲህ ያለ ቀጥተኛ ምክር መስጠቱ አሳቢነት እንደጎደለው የሚያሳይ ነው? በፍጹም፤ ኢዮብም ቢሆን እንዲህ አልተሰማውም። ኢዮብ ይሖዋ የሰጠውን ምክር ማስተዋል ችሎ ነበር። እንዲያውም “በተናገርኩት ነገር እጸጸታለሁ፤ በአፈርና በአመድ ላይ ተቀምጬም ንስሐ እገባለሁ” በማለት ተናግሯል። ይሖዋ የሰጠው ቀጥተኛ ሆኖም ፍቅር የተንጸባረቀበት ምክር እንዲህ ያለ ውጤት አስገኝቷል። (ኢዮብ 42:1-6) ወጣቱ ኤሊሁም ቀደም ሲል ለኢዮብ እርማት ሰጥቶታል። (ኢዮብ 32:5-10) ኢዮብ፣ አምላክ የሰጠውን እርማት ተቀብሎ አመለካከቱን ካስተካከለ በኋላ ይሖዋ ኢዮብ ታማኝነቱን በመጠበቁ እንደተደሰተ ገልጿል።—ኢዮብ 42:7, 8

13. ኢዮብ የደረሰበት መከራ ካበቃ በኋላም እንኳ ይሖዋ የሰጠው ምክር ጠቅሞት መሆን አለበት የምንለው ለምንድን ነው?

13 ይሖዋ ለኢዮብ የሰጠው ምክር የደረሰበት መከራ ካበቃ በኋላም እንኳ ጠቅሞት መሆን አለበት። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? “ይሖዋ ከፊተኛው የኢዮብ ሕይወት ይልቅ የኋለኛውን አብዝቶ” የባረከው ቢሆንም ጤንነቱንና ንብረቱን መልሶ እስኪያገኝ የተወሰነ ጊዜ ማለፉ አይቀርም። ከጊዜ በኋላ ኢዮብ “ሌሎች ሰባት ወንዶችና ሦስት ሴቶች ልጆች” ወልዷል። (ኢዮብ 42:12-14) ኢዮብ እነዚህን ልጆች በማግኘቱ ቢደሰትም ቀደም ሲል በሞቱት ልጆቹ ማዘኑ አይቀርም። በተጨማሪም የደረሰበት መከራ ለተወሰነ ጊዜ ወደ አእምሮው እየመጣ ረብሾት መሆን አለበት። መከራ ደርሶበት የነበረው ለምን እንደሆነ ከጊዜ በኋላ ተረድቶ የነበረ ቢሆን እንኳ ‘አምላክ ይህን ያህል እንድሠቃይ የፈቀደው ለምንድን ነው?’ የሚለው ጥያቄ አልፎ አልፎ ወደ አእምሮው ሊመጣ ይችላል። ኢዮብ እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎች ይፈጠሩበት ከነበረ አምላክ የሰጠውን ምክር ማስታወሱ እንደሚጠቅመው ጥርጥር የለውም። ይህን ማድረጉ ተገቢውን አመለካከት እንዲይዝና መጽናናት እንዲችል ይረዳዋል።—መዝ. 94:19 ግርጌ

ሆስፒታል ውስጥ የተኛች አንዲት እህት ስትመሠክር፤ አንድ ወንድም ፎቶግራፍ እቅፍ አድርጎ ይዞ፤ አንዲት እናት አደጋ በደረሰበት አካባቢ ልጇን ይዛ

በራሳችን ችግሮች ላይ ከማተኮር ይልቅ አንገብጋቢ በሆነው ጉዳይ ላይ ማተኮር እንችል ይሆን? (አንቀጽ 14⁠ን ተመልከት)

14. ከኢዮብ ታሪክ ምን ትምህርት እናገኛለን?

14 እኛም ብንሆን የኢዮብን ታሪክ መመርመራችን ተገቢውን አመለካከት እንድንይዝና መጽናኛ እንድናገኝ ያስችለናል። ይሖዋ ይህ ታሪክ እስከ ዘመናችን ተጠብቆ እንዲቆይ ያደረገው “በምናሳየው ጽናትና ከቅዱሳን መጻሕፍት በምናገኘው መጽናኛ ተስፋ ይኖረን ዘንድ ቀደም ብሎ የተጻፈው ነገር ሁሉ ለእኛ ትምህርት እንዲሆን” አስቦ ነው። (ሮም 15:4) ከዚህ ታሪክ የምናገኘው ትምህርት ምንድን ነው? ዋነኛው ትምህርት ይህ ነው፦ በራሳችን ሕይወት ከልክ በላይ ተጠምደን አንገብጋቢ የሆነውን ነገር ይኸውም የይሖዋ ሉዓላዊነት ትክክለኛነት የመረጋገጡን ጉዳይ እንዳንዘነጋ መጠንቀቅ አለብን። በተጨማሪም ኢዮብ እንዳደረገው ሁሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙን ጊዜም ታማኝነታችንን በመጠበቅ የይሖዋን ሉዓላዊነት እንደምንደግፍ ማሳየት ይኖርብናል።

15. ፈተና ሲደርስብን በታማኝነት መጽናታችን ምን ጥቅም ያስገኛል?

15 የኢዮብ ታሪክ ፈተናዎች የሚደርሱብን ይሖዋ ስላዘነብን እንዳልሆነ እንድንገነዘብ ያደርገናል፤ ይህን መገንዘባችን ሊያጽናናን ይችላል። የሚደርሱብን ፈተናዎች የአምላክን ሉዓላዊነት ለመደገፍ የሚያስችል አጋጣሚ ይሰጡናል። (ምሳሌ 27:11) መጽናታችን “በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንድናገኝ” እንዲሁም ተስፋችን ብሩህ ሆኖ እንዲታየን ያስችለናል። (ሮም 5:3-5⁠ን አንብብ።) የኢዮብ ታሪክ “ይሖዋ እጅግ አፍቃሪና መሐሪ እንደሆነ” ያሳያል። (ያዕ. 5:11) በመሆኑም ይሖዋ እኛንም ሆነ ከሉዓላዊነቱ ጎን የሚቆሙ ሰዎችን በሙሉ እንደሚባርክ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ይህን ማወቃችን “በትዕግሥትና በደስታ ሁሉንም ነገር በጽናት” እንድንቋቋም ይረዳናል።—ቆላ. 1:11

ትኩረታችሁ እንዳይሰረቅ ተጠንቀቁ

16. የይሖዋ ሉዓላዊነት ትክክለኛነት መረጋገጡ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ማስታወስ ያለብን ለምንድን ነው?

16 እርግጥ ነው፣ አንገብጋቢ በሆነው ጉዳይ ላይ ትኩረት ማድረግ ሁልጊዜ ቀላል ላይሆን ይችላል። አንዳንድ ጊዜ የሚያጋጥሙን ችግሮች አስተሳሰባችንን ይቆጣጠሩት ይሆናል። በችግሮቻችን ላይ ከልክ በላይ ትኩረት ካደረግን በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታዩ ቀለል ያሉ ችግሮች እንኳ ገዝፈው ሊታዩን ይችላሉ። በመሆኑም ምንም ዓይነት ችግሮች ቢያጋጥሙን የይሖዋን ሉዓላዊነት መደገፋችን በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ምንጊዜም ማስታወስ ይኖርብናል።

17. አዘውትረን በይሖዋ ሥራ መካፈላችን ምንጊዜም ትኩረታችንን በአንገብጋቢው ጉዳይ ላይ እንድናደርግ የሚረዳን እንዴት ነው?

17 አዘውትረን በይሖዋ ሥራ መካፈላችን ምንጊዜም ትኩረታችንን በአንገብጋቢው ጉዳይ ላይ እንድናደርግ ይረዳናል። ለምሳሌ ያህል፣ ረኔ የተባለች አንዲት የይሖዋ ምሥክር በጭንቅላቷ ውስጥ ደም ፈስሶ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ካንሰር ይዟት ነበር፤ በመሆኑም የሚሰማትን ከባድ የሕመም ስሜት መቋቋም አስፈልጓታል። ሆስፒታል ተኝታ ስትታከም ለሆስፒታሉ ሠራተኞች፣ ለታካሚዎችና የታመሙትን ለመጠየቅ ለሚመጡ ሰዎች ትመሠክር ነበር። እንዲያውም በአንድ ወቅት ሆስፒታል ተኝታ ሳለ በሁለት ሳምንት ተኩል ጊዜ ውስጥ 80 ሰዓታት በአገልግሎት አሳልፋለች። ረኔ መሞቻዋ በተቃረበበት ጊዜም እንኳ ይበልጥ አንገብጋቢ የሆነው ነገር የይሖዋ ሉዓላዊነት እንደሆነ ተገንዝባ ነበር። በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት ማድረጓ የሚሰማት ሥቃይ በመጠኑ እንዲቀልላት አድርጓል።

18. የአንዲት እህት ተሞክሮ የይሖዋን ሉዓላዊነት መደገፍ የሚያስገኘውን ጥቅም የሚያሳየው እንዴት ነው?

18 በዕለት ተዕለት ሕይወታችን አንዳንድ ጫናዎችና አስቸጋሪ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙን ጊዜም እንኳ በይሖዋ ሉዓላዊነት ላይ ትኩረት ማድረግ ይኖርብናል። ጄኒፈር የተባለች አንዲት እህት በአውሮፕላን ወደ አገሯ ለመመለስ በአየር ማረፊያ ውስጥ ለሦስት ቀናት መጠበቅ አስፈልጓት ነበር። የአውሮፕላን በረራዎች በተከታታይ ተሰረዙ። በጣም ደክሟትና ብቸኝነት ተሰምቷት ስለነበር በሐዘንና በብስጭት ስሜት ልትዋጥ ትችል ነበር። እሷ ግን ተመሳሳይ ችግር ለገጠማቸው ሌሎች ሰዎች ምሥራቹን ማካፈል እንድትችል ይሖዋ እንዲረዳት ጸለየች። ይህ ምን ውጤት አስገኘ? ለበርካታ ሰዎች የመሠከረች ሲሆን ብዙ ጽሑፎችንም አበረከተች። እንዲህ ብላለች፦ “የገጠመኝ ነገር ተፈታታኝ ቢሆንም እንኳ ይሖዋ እንደባረከኝና ስሙን ማስከበር እንድችል እንደረዳኝ ተሰምቶኛል።” በእርግጥም ጄኒፈር ትኩረቷን በይሖዋ ዓላማ ላይ አድርጋለች።

19. የይሖዋ ሕዝቦች ከእሱ ሉዓላዊነት ጋር በተያያዘ ምን አቋም አላቸው?

19 እውነተኛውን ሃይማኖት ከሐሰት ሃይማኖቶች የሚለየው አንዱ ነገር ለይሖዋ ሉዓላዊነት የሚሰጠው ትልቅ ቦታ ነው። የአምላክ ሕዝቦች ከጥንት ዘመን ጀምሮ ከይሖዋ ሉዓላዊነት ጎን ቆመዋል። እኛም እውነተኛውን አምልኮ የምንደግፍ እንደመሆናችን መጠን በግለሰብ ደረጃ ለይሖዋ ሉዓላዊነት ተመሳሳይ አመለካከት ሊኖረን ይገባል።

20. ይሖዋ ሉዓላዊነቱን ለመደገፍ የምታደርገውን ጥረት በተመለከተ ምን ይሰማዋል?

20 ይሖዋ እሱን በታማኝነት በማገልገልና ፈተናዎችን በመቋቋም ሉዓላዊነቱን ለመደገፍ የምታደርገውን ጥረት ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው አትጠራጠር። (መዝ. 18:25) የሚቀጥለው ርዕስ የይሖዋን ሉዓላዊነት በሙሉ ልባችን መደገፍ ያለብን ለምን እንደሆነና ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ ይበልጥ ያብራራል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ