“ፅንስ እያለሁ እንኳ ዓይኖችህ አዩኝ።”—መዝሙር 139:16
አምላክ ስሜትህን ይረዳልሃል?
ከሰዎች አፈጣጠር ምን እንማራለን?
በሰዎች መካከል ሊኖር ከሚችለው ዝምድና ሁሉ እጅግ የቀረበውን ማለትም በተመሳሳይ መንትያዎች (identical twins) መካከል ያለውን ዝምድና ለማሰብ ሞክር። እንዲህ ዓይነት መንትያዎች ለየት ያለ ትስስር አላቸው። እንዲያውም የመንትያዎች ጥናት ማዕከል ዳይሬክተር የሆነችውና እሷ ራሷ መንትያ ያላት ናንሲ ሴጋል እንደተናገረችው፣ አንዳንድ መንትያዎች “ምንም ማብራሪያ መስጠት ሳያስፈልጋቸው ምን ማለት እንደፈለጉ በትክክል ከሚረዳላቸው ሰው ጋር መነጋገር ምን ስሜት እንደሚፈጥር ያውቃሉ።” አንዲት ሴት በእሷና በተመሳሳይ መንትያዋ መካከል ያለውን ዝምድና ስትገልጽ “አንዳችን ስለ ሌላው ሁሉንም ነገር እናውቃለን” ብላለች።
በተመሳሳይ መንትያዎች መካከል እንዲህ ዓይነት ለየት ያለ መግባባት ሊኖር የቻለው እንዴት ነው? ጥናቶች እንደሚጠቁሙት አካባቢና አስተዳደግ ለዚህ አስተዋጽኦ ቢያደርጉም ወሳኝ ሚና የሚጫወተው ተመሳሳይ ጂን ያላቸው መሆኑ ነው።
እስቲ አስበው፦ የዚህ ሁሉ አስገራሚ ጄኔቲካዊ መዋቅር ፈጣሪ የእያንዳንዳችንን ተፈጥሮ ከማንም በላቀ ደረጃ መረዳት እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም። በእርግጥም መዝሙራዊው ዳዊት እንደሚከተለው በማለት መናገሩ ተገቢ ነው፦ “በእናቴ ማህፀን ውስጥ ጋርደህ አስቀመጥከኝ። በስውር በተሠራሁ ጊዜ . . . አጥንቶቼ ከአንተ አልተሰወሩም ነበር። ፅንስ እያለሁ እንኳ ዓይኖችህ አዩኝ፤ የአካሌ ክፍሎች በሙሉ በመጽሐፍህ ተጻፉ።” (መዝሙር 139:13, 15, 16) ጄኔቲካዊ አወቃቀራችንን ብቻ ሳይሆን አሁን ላለን ማንነት አስተዋጽኦ ያደረጉትን በሕይወታችን ውስጥ ያጋጠሙንን ክስተቶች ጠንቅቆ ማወቅና ሙሉ በሙሉ መረዳት የሚችለው አምላክ ብቻ ነው። አምላክ ስለ እኛም ሆነ ስለ ጄኔቲካዊ አወቃቀራችን ያለው ከሁሉ የላቀ እውቀት ስሜታችንን በሚገባ እንደሚረዳልን እርግጠኞች እንድንሆን ያደርገናል።
መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ በሚገባ እንደሚያውቀን የሚያሳይ ምን ማስረጃ ይዟል?
ዳዊት እንዲህ ሲል ጸልዮአል፦ “ይሖዋ ሆይ፣ በሚገባ መርምረኸኛል፤ ደግሞም ታውቀኛለህ። አንተ ስቀመጥም ሆነ ስነሳ ታውቃለህ። ሐሳቤን ከሩቅ ታስተውላለህ። ይሖዋ ሆይ፣ ገና ቃል ከአፌ ሳይወጣ፣ እነሆ፣ አንተ ሁሉን ነገር አስቀድመህ በሚገባ ታውቃለህ።” (መዝሙር 139:1, 2, 4) በተጨማሪም ይሖዋ ውስጣዊ ስሜታችንን ያውቃል፤ እንዲያውም “ሐሳብንና ውስጣዊ ዝንባሌን ሁሉ ይረዳል።” (1 ዜና መዋዕል 28:9፤ 1 ሳሙኤል 16:6, 7) እነዚህ ጥቅሶች ስለ አምላክ ምን ያስተምሩናል?
ወደ አምላክ በምንጸልይበት ወቅት፣ ሐሳባችንንና ስሜታችንን ሁሉ በቃላት አውጥተን ባንገልጽ እንኳ ፈጣሪያችን የምናደርገውን ነገር ብቻ ሳይሆን ያን ነገር እንድናደርግ ያነሳሳንን ምክንያት ጭምር ይረዳል። ከዚህም በላይ በአቅም ገደብ ምክንያት የምንመኘውን ያህል መልካም ነገር ማድረግ ባንችልም እንደዚያ ብናደርግ ደስ እንደሚለን ያውቃል። መጀመሪያውኑም በልባችን ፍቅር ያኖረው እሱ ስለሆነ በፍቅር ተነሳስተን የምናስበውንም ሆነ የምንመኘውን ነገር ለመመልከትና ለመረዳት ከልብ እንደሚፈልግ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—1 ዮሐንስ 4:7-10
ከአምላክ እይታ ውጭ የሆነ ምንም ነገር የለም። እየደረሰብን ያለውን መከራ ማንም ባያውቅልን ወይም ሙሉ በሙሉ ባይረዳልን እንኳ አምላክ እንደሚረዳልን እርግጠኞች መሆን እንችላለን
መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ማረጋገጫ
“የይሖዋ ዓይኖች ጻድቃንን ይመለከታሉና፤ ጆሮዎቹም ምልጃቸውን ይሰማሉ።”—1 ጴጥሮስ 3:12
አምላክ እንዲህ ሲል ቃል ገብቷል፦ “ጥልቅ ማስተዋል እሰጥሃለሁ፤ ልትሄድበት የሚገባውንም መንገድ አስተምርሃለሁ። ዓይኔን በአንተ ላይ አድርጌ እመክርሃለሁ።”—መዝሙር 32:8
አምላክ እጅግ ሩኅሩኅ ነው
አምላክ ያለንበትን ሁኔታና ስሜታችንን እንደሚረዳልን ማወቃችን የሚደርስብንን መከራ ለመቋቋም ሊረዳን ይችላል? በናይጄርያ የምትኖረው አና ያጋጠማትን ነገር እንመልከት። እንዲህ ብላለች፦ “በደረሰብኝ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ የተነሳ በሕይወት መኖሬ ምንም ዋጋ እንደሌለው ይሰማኝ ነበር። ባለቤቴን በሞት ያጣሁ ከመሆኑም ሌላ ሃይድሮሴፋለስ (በአንጎል ውስጥ ብዙ ፈሳሽ መከማቸት) በተባለ በሽታ ምክንያት ሆስፒታል የገባች ልጄን የማስታምመው እኔ ነበርኩ፤ ከዚያም እኔ ራሴ የጡት ካንሰር እንዳለብኝ በምርመራ ስለተገኘ ቀዶ ሕክምና፣ ኬሞቴራፒና የጨረር ሕክምና ማድረግ አስፈለገኝ። ልጄን እያስታመምኩ ባለሁበት ወቅት እኔ ራሴ ሆስፒታል መግባቴ በጣም ከብዶኝ ነበር።”
አና የደረሰባትን ችግር እንድትቋቋም የረዳት ምንድን ነው? እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “እንደ ፊልጵስዩስ 4:6, 7 ባሉ ጥቅሶች ላይ አሰላስል ነበር፤ ጥቅሱ ‘ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም . . . ልባችሁንና አእምሯችሁን ይጠብቃል’ ይላል። ይህን ጥቅስ ባሰብኩ ቁጥር፣ እኔ ራሴን ከማውቀው በላይ ይሖዋ እንደሚያውቀኝ ስለምገነዘብ ከእሱ ጋር የጠበቀ ዝምድና እንዳለኝ ይሰማኛል። በተጨማሪም በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ካሉት ውድ መንፈሳዊ ወንድሞቼና እህቶቼ ብዙ ማበረታቻ አግኝቻለሁ።
“አሁንም ከጤና ችግር ጋር እየታገልኩ ቢሆንም የእኔም ሆነ የልጄ ሁኔታ ተሻሽሏል። ይሖዋ ከጎናችን ስላለልን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙንም አሉታዊ አመለካከት ሊኖረን እንደማይገባ ተምረናል። ያዕቆብ 5:11 እንዲህ የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል፦ ‘የጸኑትን ደስተኞች እንደሆኑ አድርገን እንቆጥራቸዋለን። ስለ ኢዮብ ጽናት ሰምታችኋል፤ በውጤቱም ይሖዋ ያደረገለትን አይታችኋል፤ በዚህም ይሖዋ እጅግ አፍቃሪና [ወይም “ከአንጀት የሚራራና፣” የግርጌ ማስታወሻ] መሐሪ እንደሆነ ተመልክታችኋል።’” ይሖዋ ኢዮብ የነበረበትን ሁኔታ በሚገባ ተረድቶለት ነበር፤ እኛም ምንም ዓይነት ችግር ቢያጋጥመን ይሖዋ እንደሚረዳልን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።