የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w18 የካቲት ገጽ 28-30
  • ደስታ—ከአምላክ የምናገኘው ግሩም ባሕርይ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ደስታ—ከአምላክ የምናገኘው ግሩም ባሕርይ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2018
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ደስታ ምንድን ነው?
  • ጥሩ ምሳሌዎችን መከተል
  • ለደስታችን ምክንያት የሆኑ ነገሮች
  • ይበልጥ ደስተኛ ለመሆን ምን ማድረግ ትችላለህ?
  • ደስታ የሚያስገኘው መልካም ውጤት
  • ይሖዋን ከልብ በመነጨ ደስታ አገልግሉት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ይሖዋን በደስታ ማገልገል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • የይሖዋ ደስታ ምሽጋችን ነው
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ይሖዋ ‘እጅግ ሐሴት የምናደርግበት አምላክ’ ነው
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2018
w18 የካቲት ገጽ 28-30

ደስታ—ከአምላክ የምናገኘው ግሩም ባሕርይ

  • ፍቅር

  • ደስታ

  • ሰላም

  • ትዕግሥት

  • ደግነት

  • ጥሩነት

  • እምነት

  • ገርነት

  • ራስን መግዛት

ሁሉም ሰው ደስተኛ የሆነ ሕይወት መምራት ይፈልጋል። ይሁን እንጂ በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ማንኛውም ሰው “ለመቋቋም የሚያስቸግር” ተፈታታኝ ሁኔታ ያጋጥመዋል። (2 ጢሞ. 3:1) አንዳንዶች በፍትሕ መዛባት፣ በጤና መታወክ፣ ሥራ በማጣት፣ በሐዘን ወይም በሌሎች የሚያስጨንቁ ነገሮች የተነሳ እያደር ደስታቸውን ሊያጡ ይችላሉ። የአምላክ አገልጋዮችም እንኳ ተስፋ ሊቆርጡና ደስታ ሊርቃቸው ይችላል። አንተም እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሞህ ከሆነ እንደገና ደስተኛ መሆን የምትችለው እንዴት ነው?

ይህን ጥያቄ ለመመለስ በመጀመሪያ፣ እውነተኛ ደስታ ምን እንደሆነ እንዲሁም አንዳንዶች ችግር ቢደርስባቸውም ደስታቸውን ሳያጡ መኖር የቻሉት እንዴት እንደሆነ ማወቅ ያስፈልገናል። ከዚያም ደስታችንን ጠብቀን ለመኖር ብሎም ይበልጥ ደስተኛ ለመሆን ምን ማድረግ እንደምንችል እንመለከታለን።

ደስታ ምንድን ነው?

ደስተኛ መሆን፣ ተጫዋች ወይም ፍልቅልቅ መሆንን ብቻ እንደሚያመለክት አድርገን ልናስብ አይገባም። ሁኔታውን በምሳሌ ለማስረዳት፦ ሰካራም የሆነ ሰው ብዙ ሲጠጣ ሳቅ ሳቅ ሊለው ይችላል። ስካሩ ሲበርድለት ግን መሳቁን አይቀጥልም፤ ምክንያቱም በሐዘንና በችግር ከተሞላው ሕይወቱ ማምለጥ አይችልም። ይህ ሰው ለጊዜው ቢፈነድቅም እውነተኛ ደስታ ነበረው ማለት አይቻልም።—ምሳሌ 14:13

ከዚህ በተቃራኒ ደስታ ከልብ የመነጨ ጥልቅ ስሜት ነው። ደስታ “ጥሩ ነገር ከማግኘት ወይም አገኛለሁ ብሎ ከማሰብ የሚመጣ ስሜት” የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። ደስተኛ መሆን ሲባል በሕይወታችን ውስጥ ጥሩም ሆኑ መጥፎ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙን ደስታችንን ሳናጣ መቀጠል ማለት ነው። (1 ተሰ. 1:6) አንድ ሰው፣ የሚረብሽ ነገር ቢያጋጥመውም እንኳ ልቡ በደስታ ሊሞላ ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ሐዋርያቱ ስለ ክርስቶስ በመናገራቸው ምክንያት ተገርፈው ነበር። ሆኖም ከሳንሄድሪን ሸንጎ ሲወጡ “ስለ ስሙ ውርደት ለመቀበል ብቁ ሆነው በመቆጠራቸው ደስ እያላቸው” ነበር። (ሥራ 5:41) ሐዋርያቱ ደስ ያላቸው ስለተገረፉ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ይሁንና የአምላክ አገልጋዮች እንደመሆናቸው መጠን ለእሱ ያላቸውን ታማኝነት በመጠበቃቸው እውነተኛ ደስታ አግኝተዋል።

እንዲህ ያለው ደስታ ስንወለድ ጀምሮ የሚኖረን አሊያም ያለምንም ጥረት የምናገኘው ነገር አይደለም። ለምን? ምክንያቱም እውነተኛ ደስታ ከመንፈስ ፍሬ ገጽታዎች አንዱ ነው። በአምላክ ቅዱስ መንፈስ እርዳታ “አዲሱን ስብዕና” በተሟላ ሁኔታ መልበስ የምንችል ሲሆን ይህም ደስታን ያካትታል። (ኤፌ. 4:24፤ ገላ. 5:22) ደስታ ሲኖረን ደግሞ የሕይወትን ውጣ ውረዶች በተሻለ ሁኔታ መቋቋም እንችላለን።

ጥሩ ምሳሌዎችን መከተል

የይሖዋ ዓላማ በምድር ላይ መልካም ነገሮች እንዲኖሩ እንጂ በዛሬው ጊዜ እንደሚታየው ክፋት እንዲበዛ አይደለም። ሆኖም ሌሎች፣ የክፋት ድርጊቶችን መፈጸማቸው ይሖዋ ደስታውን እንዲያጣ አላደረገውም። የአምላክ ቃል “ብርታትና ደስታ እሱ በሚኖርበት ስፍራ ይገኛሉ” በማለት ይናገራል። (1 ዜና 16:27) ከዚህም በላይ ይሖዋ አገልጋዮቹ በሚፈጽሟቸው መልካም ነገሮች ‘ልቡ ደስ ይሰኛል።’—ምሳሌ 27:11

እኛም ነገሮች እንደጠበቅነው በማይሆኑበት ጊዜ ከልክ በላይ ባለመጨነቅ ይሖዋን መምሰል እንችላለን። ደስታችንን ከማጣት ይልቅ አሁን ባሉን ጥሩ ነገሮች ላይ ማተኮርና ወደፊት የምናገኛቸውን የተሻሉ ነገሮች በትዕግሥት መጠበቅ እንችላለን።a

ፈታኝ ሁኔታዎች ቢያጋጥሟቸውም ደስታቸውን ሳያጡ መኖር የቻሉ በርካታ ምሳሌዎችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እናገኛለን። አብርሃም የደረሱበትን ለሕይወት አስጊ የሆኑ ሁኔታዎችና ችግሮች በጽናት ተቋቁሟል። (ዘፍ. 12:10-20፤ 14:8-16፤ 16:4, 5፤ 20:1-18፤ 21:8, 9) አብርሃም፣ ሌሎች ሰዎች እንደዚህ ያሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢፈጥሩበትም ደስታውን ጠብቆ መኖር ችሏል። ይህን ማድረግ የቻለው እንዴት ነው? በመሲሑ አገዛዝ ሥር በአዲሱ ዓለም ውስጥ የመኖር ተስፋው በአእምሮው ውስጥ ብሩህ ሆኖ ይታየው ስለነበረ ነው። (ዘፍ. 22:15-18፤ ዕብ. 11:10) ኢየሱስ “አባታችሁ አብርሃም ቀኔን እንደሚያይ ተስፋ በማድረግ እጅግ ተደሰተ” በማለት ተናግሮ ነበር። (ዮሐ. 8:56) እኛም ወደፊት በምናገኘው ደስታ ላይ በማሰላሰል አብርሃምን ልንመስለው እንችላለን።—ሮም 8:21

እንደ አብርሃም ሁሉ ሐዋርያው ጳውሎስና ጓደኛው ሲላስም አምላክ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ ያሰላስሉ ነበር። ጠንካራ እምነት የነበራቸው ሲሆን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢያጋጥሟቸውም እንኳ ደስታቸውን ሳያጡ መኖር ችለዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በአሰቃቂ ሁኔታ ተደብድበው ወደ ወህኒ ከተጣሉ በኋላ “እኩለ ሌሊት ገደማ . . . እየጸለዩና አምላክን በመዝሙር እያወደሱ” እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ሥራ 16:23-25) ጳውሎስና ሲላስ ብርታት እንዲያገኙ የረዳቸው አንዱ ነገር ተስፋቸው ነው፤ ከዚህም በተጨማሪ መከራ የደረሰባቸው በክርስቶስ ስም የተነሳ መሆኑ ደስተኞች እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። እኛም አምላክን በታማኝነት ማገልገል የሚያስገኘውን መልካም ውጤት ማስታወሳችን የጳውሎስንና የሲላስን ምሳሌ ለመከተል ያስችለናል።—ፊልጵ. 1:12-14

በዛሬው ጊዜም መከራ ቢደርስባቸውም ደስታቸውን ጠብቀው ማገልገላቸው የቀጠሉ ምሳሌ የሚሆኑ በርካታ ክርስቲያኖች አሉ። ለአብነት ያህል፣ ኅዳር 2013 ሃያን የተባለው ዝናብ የቀላቀለ ከባድ አውሎ ነፋስ በማዕከላዊ ፊሊፒንስ ላይ ባደረሰው ጉዳት የተነሳ ከ1,000 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች ቤታቸውን አጥተዋል። በታክሎበን የነበረው ቤቱ የወደመበት ጆርጅ እንዲህ ብሏል፦ “ወንድሞች እንዲህ ያለ ችግር ቢያጋጥማቸውም ደስተኞች ናቸው። የሚሰማንን ደስታ በቃላት መግለጽ ያዳግተኛል።” እኛም ከባድ ችግሮች በሚደርሱብን ጊዜ፣ ይሖዋ ባደረገልን ነገሮች ላይ በአድናቆት የምናሰላስል ከሆነ ደስታችንን አናጣም። ይሖዋ ለደስታ ምክንያት የሚሆን ሌላስ ምን አድርጎልናል?

ለደስታችን ምክንያት የሆኑ ነገሮች

ከይሖዋ ጋር ካለን ዝምድና የበለጠ ለደስታችን ምክንያት የሚሆን ምን ሊኖር ይችላል? እስቲ አስበው፦ የአጽናፈ ዓለሙን ሉዓላዊ ጌታ እናውቃለን። እሱ አባታችን፣ አምላካችንና ወዳጃችን ነው!—መዝ. 71:17, 18

ሕይወታችን ከይሖዋ ያገኘነው ስጦታ ነው፤ በተጨማሪም ይሖዋ በሕይወታችን መደሰት እንድንችል አድርጎ ፈጥሮናል። (መክ. 3:12, 13) ይሖዋ ወደ ራሱ ስለሳበን አምላክ ለእኛ ያለውን ፈቃድ አውቀናል፤ እንዲሁም ሕይወታችንን እንዴት መምራት እንዳለብን ተገንዝበናል። (ቆላ. 1:9, 10) በመሆኑም ሕይወታችን እውነተኛ ትርጉም ያለው መሆን ችሏል። በሌላ በኩል ግን አብዛኛው የሰው ዘር ስለ ሕይወት ዓላማ ግልጽ የሆነ ግንዛቤ የለውም። ጳውሎስ ይህን ልዩነት ጎላ አድርጎ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “‘አምላክ ለሚወዱት ያዘጋጃቸውን ነገሮች ዓይን አላየም፣ ጆሮም አልሰማም፣ የሰውም ልብ አላሰበም።’ . . . አምላክ እነዚህን ነገሮች በመንፈሱ አማካኝነት የገለጠው ለእኛ ነውና።” (1 ቆሮ. 2:9, 10) በእርግጥም የይሖዋን ፈቃድና ዓላማ ማወቃችን የሚያስደስት አይደለም?

ይሖዋ ለሕዝቡ ያደረገውን ሌላም ነገር እንመልከት። ኃጢአታችን ይቅር ሊባልልን በመቻሉ ደስተኞች አይደለንም? (1 ዮሐ. 2:12) አምላክ መሐሪ በመሆኑ በቅርቡ አዲስ ዓለም እንደሚመጣ እርግጠኛ የሆነ ተስፋ ሊኖረን ችሏል። (ሮም 12:12) በአሁኑ ጊዜም እንኳ ይሖዋ፣ ጥሩ የእምነት አጋሮች ሰጥቶናል። (መዝ. 133:1) ከዚህም ሌላ ይሖዋ ሕዝቡን ከሰይጣንና ከአጋንንቱ እንደሚጠብቅ የአምላክ ቃል ዋስትና ይሰጠናል። (መዝ. 91:11) ከአምላክ ባገኘናቸው በእነዚህ ሁሉ በረከቶች ላይ የምናሰላስል ከሆነ ደስታችን እየጨመረ ይሄዳል።—ፊልጵ. 4:4

ይበልጥ ደስተኛ ለመሆን ምን ማድረግ ትችላለህ?

በሕይወቱ ደስተኛ የሆነ ክርስቲያን የበለጠ ደስታ ማግኘት ይችላል? ኢየሱስ “እነዚህን ነገሮች የነገርኳችሁ እኔ ያገኘሁትን ደስታ እንድታገኙና የእናንተም ደስታ የተሟላ እንዲሆን ነው” ብሏል። (ዮሐ. 15:11) ይህ አባባል ደስታችን እንዲጨምር ማድረግ እንደምንችል የሚጠቁም አይደለም? ደስታችን እንዲጨምር ማድረግ፣ እሳትን ይበልጥ ለማቀጣጠል ማገዶ ከመጨመር ጋር ሊመሳሰል ይችላል። እሳቱ ይበልጥ እንዲቀጣጠል እንጨት መማገድ አለብህ። በተመሳሳይም ደስታህ እንዲጨምር መንፈሳዊነትህን ማሳደግ አለብህ። መንፈስ ቅዱስ፣ ደስታ ለማግኘት እንደሚረዳ አስታውስ። በመሆኑም የይሖዋን መንፈስ እርዳታ ለማግኘት አዘውትረህ በመጸለይና በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው ቃሉ ላይ በማሰላሰል ደስታህ እንዲጨምር ማድረግ ትችላለህ።—መዝ. 1:1, 2፤ ሉቃስ 11:13

ከዚህም ሌላ ይሖዋን በሚያስደስቱ ሥራዎች በትጋት በመካፈል ደስታህ እንዲጨምር ማድረግ ትችላለህ። (መዝ. 35:27፤ 112:1) እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም የተፈጠርነው ‘እውነተኛውን አምላክ እንድንፈራና ትእዛዛቱን እንድንጠብቅ’ ነው፤ “ይህ የሰው አጠቃላይ ግዴታ ነው።” (መክ. 12:13) በሌላ አባባል የተፈጠርነው የአምላክን ፈቃድ እንድናደርግ ነው። ስለዚህ ይሖዋን ስናገለግል በሕይወታችን ከሁሉ የላቀ ደስታ እንደምናገኝ የተረጋገጠ ነው።b

ደስታ የሚያስገኘው መልካም ውጤት

አምላካዊ ባሕርይ የሆነው ደስታ፣ በውስጣችን ከሚሰማን ስሜት ባለፈ ብዙ ጥቅሞችን ያስገኛል። ለምሳሌ ያህል፣ ምንም ዓይነት ችግሮች ቢያጋጥሙን ሰማያዊ አባታችንን በደስታ ማገልገላችን እሱን ይበልጥ ያስደስተዋል። (ዘዳ. 16:15፤ 1 ተሰ. 5:16-18) ከዚህም ባሻገር እውነተኛ ደስታ ሲኖረን፣ ቁሳዊ ሀብት በማሳደድ ላይ ያተኮረ ሕይወት ከመምራት ይልቅ የአምላክን መንግሥት ለማስቀደም ስንል ብዙ መሥዋዕት እንከፍላለን። (ማቴ. 13:44) ይህን ማድረጋችን የሚያስገኘውን ጥሩ ውጤት ስንመለከት ደግሞ ደስታችን የሚጨምር ከመሆኑም ሌላ ለራሳችን ጥሩ አመለካከት ይኖረናል፤ ሌሎች ይበልጥ እንዲደሰቱም እናደርጋለን።—ሥራ 20:35፤ ፊልጵ. 1:3-5

“አሁን በሕይወትህ ደስታና እርካታ ካለህ ወደፊት ጤነኛ የመሆን አጋጣሚህ ሰፊ ነው።” ይህን ሐሳብ የጻፈው ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በነብራስካ ዩኒቨርሲቲ የሚገኝ አንድ ተመራማሪ ሲሆን እዚህ መደምደሚያ ላይ የደረሰው ጤናን በተመለከተ በርካታ የጥናት ውጤቶችን ከመረመረ በኋላ ነው። ይህም “ደስተኛ ልብ ጥሩ መድኃኒት ነው” ከሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ጋር ይስማማል። (ምሳሌ 17:22) በእርግጥም ይበልጥ ደስተኛ ስትሆን የተሻለ አካላዊ ጤንነት ይኖርሃል።

የምንኖረው አስጨናቂ በሆነ ዘመን ውስጥ ቢሆንም በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ እውነተኛና ዘላቂ ደስታ ማግኘት እንችላለን፤ መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት ደግሞ መጸለያችን፣ ማጥናታችንና በይሖዋ ቃል ላይ ማሰላሰላችን አስፈላጊ ነው። በተጨማሪም አሁን ባገኘናቸው በረከቶች ላይ ማተኮራችን፣ ሌሎችን በእምነታቸው መምሰላችን እንዲሁም የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም ጥረት ማድረጋችን ይበልጥ ደስተኞች ለመሆን ይረዳናል። ይህም በመዝሙር 64:10 ላይ የሚገኘውን “ጻድቅ ሰው በይሖዋ ሐሴት ያደርጋል፤ እሱንም መጠጊያው ያደርጋል” የሚለውን ሐሳብ እውነተኝነት በሕይወታችን ለማየት ያስችለናል።

a ስለ “መንፈስ ፍሬ” ገጽታዎች ከሚያብራሩት ተከታታይ ርዕሶች አንዱ ስለ ትዕግሥት የሚያወሳ ይሆናል።

b “ይበልጥ ደስተኛ ለመሆን የሚረዱ ሌሎች ነገሮች” በሚለው ሣጥን ውስጥ ተጨማሪ ነጥቦች ቀርበዋል።

ይበልጥ ደስተኛ ለመሆን የሚረዱ ሌሎች ነገሮች

  • ኑሮህ ቀላል እንዲሆን አድርግ።—ሉቃስ 12:15

  • ከራስህ ብዙ አትጠብቅ።—ሚክ. 6:8

  • የሥራ፣ የትምህርት ቤት፣ የመዝናኛና የመሳሰሉት ነገሮች ፕሮግራምህ መንፈሳዊ ነገሮችን ለማከናወን የሚያስችልህ እንዲሆን አድርግ።—ኤፌ. 5:15, 16

  • ከራስህም ሆነ ከሌሎች በምትጠብቀው ነገር ምክንያታዊ ሁን።—ፊልጵ. 4:5

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ