የሕይወት ታሪክ
በይሖዋ ዘንድ ሁሉ ነገር ይቻላል
“ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሙታንም እንኳ ትንሣኤ ያገኛሉ።” ባለቤቴ ማይራምቡቡ በአውቶቡስ እየተጓዘች ሳለ፣ አንዲት ሴት ይህን ሐሳብ ስትናገር ጆሮዋ ውስጥ ጥልቅ አለ። ባለቤቴ ስለ ጉዳዩ ይበልጥ ለማወቅ ጓጓች። በመሆኑም አውቶቡሱ ቆሞ ተሳፋሪዎቹ ሲወርዱ ይህን ሐሳብ የተናገረችውን ሴት ተከተለቻት። ሴትየዋ አፑን ማምቤትሳድይኮቫ የምትባል ሲሆን የይሖዋ ምሥክር ነበረች። በዚያ ዘመን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መነጋገር ለአደጋ የሚያጋልጥ ነገር ነበር፤ ሆኖም ከጊዜ በኋላ ከአፑን ያገኘነው ትምህርት ሕይወታችንን ለውጦታል።
ከጠዋት እስከ ማታ መልፋት
የተወለድኩት ኪርጊስታን ውስጥ ቶክሞክ በምትባል ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ ካልክሆስ (የኅብረት እርሻ) ላይ ሲሆን ወቅቱ 1937 ነበር። ቤተሰቦቼ ኪርጊዞች ናቸው፤ የምንናገረውም የኪርጊዝ ቋንቋ ነው። አርሶ አደሮች የሆኑት ወላጆቼ በኅብረት እርሻው ላይ ከጠዋት እስከ ማታ ሲለፉ ይውሉ ነበር። ገበሬዎቹ በቋሚነት ቀለብ ይሰጣቸው የነበረ ቢሆንም ደሞዛቸው በጥሬ ገንዘብ የሚከፈላቸው በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ነበር። እናቴ፣ እኔንና ታናሽ እህቴን ለማሳደግ ብዙ ፈተና አይታለች። ትምህርት ቤት ገብቼ አምስት ዓመት ብቻ ከተማርኩ በኋላ እኔም በኅብረት እርሻው ላይ ቀኑን ሙሉ መሥራት ጀመርኩ።
ቴስኬይ አላ ቱ የተራራ ሰንሰለት
በምንኖርበት አካባቢ ድህነት ተንሰራፍቶ ስለነበር መሠረታዊ ፍላጎቶቻችንን እንኳ ለማሟላት ላባችን ጠብ እስኪል መሥራት ነበረብን። ወጣት እያለሁ ስለ ሕይወት ዓላማም ሆነ ስለ ወደፊቱ ጊዜ እምብዛም አላስብም ነበር። ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ዓላማው የሚገልጸው አስደናቂ እውነት ሕይወቴን ይለውጠዋል የሚል ሐሳብም ጨርሶ በአእምሮዬ አልነበረም። እውነት ኪርጊስታን የደረሰበትና የተሰራጨበት መንገድ አስገራሚ ነው። ታሪኩ የሚጀምረው የትውልድ አካባቢዬ በሆነው በሰሜናዊ ኪርጊስታን ነው።
የቀድሞ ግዞተኞች እውነትን ወደ ኪርጊስታን ይዘው መጡ
ስለ ይሖዋ አምላክ የሚገልጸው እውነት ኪርጊስታን ውስጥ ሥር የሰደደው በ1950ዎቹ ዓመታት ነው። በእርግጥ እውነት ወደ ሰዎች ልብ እንዲገባ የኮሚኒዝምን ርዕዮተ ዓለም ማሸነፍ ነበረበት። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም የአሁኗ ኪርጊስታን በዚያን ጊዜ በሶቪየት ኅብረት ሶሺያሊስት ሪፑብሊክ (USSR) ሥር ነበረች። በመላው ሶቪየት ኅብረት የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ደግሞ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ረገድ ገለልተኞች ነበሩ። (ዮሐ. 18:36) በመሆኑም ኮሚኒስት የሆነው መንግሥት እንደ ጠላቶቹ ቆጥሮ ያሳድዳቸው ነበር። ይሁን እንጂ የአምላክ ቃል ቅን ልብ ወዳላቸው ሰዎች እንዳይደርስ ማገድ የሚችል ርዕዮተ ዓለም የለም። በእርግጥም ረጅም በሆነው የሕይወት ዘመኔ ከተማርኳቸው ጠቃሚ ነገሮች አንዱ በይሖዋ ዘንድ ‘ሁሉ ነገር የሚቻል’ መሆኑን ነው።—ማር. 10:27
ኤሚል ያንጼን
የይሖዋ ምሥክሮች መሰደዳቸው ኪርጊስታን ውስጥ ምሥራቹ እንዲስፋፋ ምክንያት ሆኗል። እንዴት? የሶቪየት ኅብረት ግዛት የሳይቤሪያን ክልልም የሚጨምር ሲሆን የመንግሥት ጠላቶች በግዞት ወደዚያ ይወሰዱ ነበር። እነዚያ ግዞተኞች ሲለቀቁ ብዙዎቹ ወደ ኪርጊስታን መጡ፤ ከመካከላቸው አንዳንዶቹ እውነትን አውቀው ነበር። እንደዚህ ካሉት የቀድሞ ግዞተኞች አንዱ በ1919 ኪርጊስታን ውስጥ የተወለደው ኤሚል ያንጼን ነው። ኤሚል የጉልበት ሥራ ወደሚሠራበት ካምፕ ተልኮ ሳለ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኝቶ እውነትን ተማረ። ከዚያም በ1956 ወደ አገሩ ሲመለስ፣ እኔ በተወለድኩበት ክልል ውስጥ ባለው በዞኩሉክ አቅራቢያ መኖር ጀመረ። በ1958 ኪርጊስታን ውስጥ የመጀመሪያው ጉባኤ የተቋቋመው በዞኩሉክ ነው።
ቪክቶር ቪንተር
ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ ቪክቶር ቪንተር ወደ ዞኩሉክ መጣ። ይህ ታማኝ ወንድም በተደጋጋሚ ጊዜያት መከራ ደርሶበታል። ገለልተኝነቱን በመጠበቁ የተነሳ ሁለት ጊዜ የሦስት ዓመት እስራት ተፈርዶበት ነበር፤ ፍርዱን ጨርሶ ሲወጣ ደግሞ እንደገና እስራት ስለተበየነበት ወኅኒ ቤት ውስጥ አሥር ዓመት ከዚያም በግዞት አምስት ዓመት አሳልፏል። ሆኖም ስደት እውነተኛው አምልኮ እንዳይስፋፋ ማገድ አልቻለም።
እውነት ወደተወለድኩበት አካባቢ ደረሰ
ኤዱዋርት ቮርተር
በ1963 ኪርጊስታን ውስጥ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች 160 ያህል ሲሆኑ አብዛኞቹ ከጀርመን፣ ከዩክሬንና ከሩሲያ የመጡ ናቸው። ከእነሱም መካከል ጀርመን ውስጥ በ1924 የተጠመቀው ኤዱዋርት ቮርተር የሚባል ግዞተኛ የነበረ ወንድም ይገኝበታል። በ1940ዎቹ ናዚዎች ኤዱዋርትን ወደ ማጎሪያ ካምፕ ልከውት ነበር፤ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ደግሞ የሶቪየት ኅብረት ኮሚኒስቶች በግዞት ወስደውታል። በ1961 ይህ ታማኝ ወንድም ካንት ወደተባለችው ከተማ ሄደ፤ ይህች ከተማ እኔ ለተወለድኩበት አካባቢ ቅርብ ናት።
ኤሊዛቤት ፎት፤ ኦክሳማ ሱልቶኖሊዬዎ
ኤሊዛቤት ፎት የምትባል ታማኝ የይሖዋ አገልጋይም ካንት ውስጥ ትኖር ነበር። ኤሊዛቤት የምትተዳደረው ልብስ በመስፋት ነው። በሙያዋ ጎበዝ ስለሆነች ሐኪሞችና አስተማሪዎች ልብስ ለማሰፋት ወደ እሷ ይመጡ ነበር። ከደንበኞቿ አንዷ ኦክሳማ ሱልቶኖሊዬዎ የምትባል ሴት ናት፤ ይህች ሴት የአቃቤ ሕግ ቢሮ ባለሥልጣን የሆነ ሰው ሚስት ነበረች። ኦክሳማ ወደ ኤሊዛቤት የምትመጣው ልብስ ለማሰፋት ቢሆንም ስለ ሕይወት ዓላማና ሙታን ስለሚገኙበት ሁኔታ ብዙ ጥያቄዎች ትጠይቅ ነበር። ኤሊዛቤትም ጥያቄዎቿን በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅማ ትመልስላት ነበር። ውሎ አድሮ ኦክሳማ ቀናተኛ የምሥራቹ ሰባኪ ሆናለች።
ኒኮላይ ጺምፖይሽ
በዚያው ጊዜ አካባቢ ከሞልዶቫ የመጣው ኒኮላይ ጺምፖይሽ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኖ የተሾመ ሲሆን በዚሁ የአገልግሎት መብት ለ30 ዓመታት ገደማ አገልግሏል። ኒኮላይ ጉባኤዎችን ከመጎብኘቱም ሌላ ጽሑፎቻችንን የማባዛትና የማሰራጨቱን ሥራ ያደራጅ ነበር። በዚህም የተነሳ ኒኮላይ በባለሥልጣናቱ ዓይን ውስጥ ገብቶ ነበር። በመሆኑም ኤዱዋርት ቮርተር ለኒኮላይ የሚከተለውን ምክር ሰጠው፦ “ባለሥልጣናቱ ሲጠይቁህ ጽሑፎቻችንን የምናገኘው በብሩክሊን ከሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት እንደሆነ በግልጽ ንገራቸው። የሚጠይቅህን የኬጂቢ ባለሥልጣን ምንም ሳትፈራ ፊት ለፊት እያየህ አነጋግረው።”—ማቴ. 10:19
ይህን ከተነጋገሩ ብዙም ሳይቆይ ኒኮላይ፣ ካንት ውስጥ ወደሚገኘው የኬጂቢ ጠቅላይ መምሪያ ተጠራ። በዚያም ምን እንዳጋጠመው ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ባለሥልጣኑ ጽሑፎቻችንን የምናገኘው ከየት እንደሆነ ጠየቀኝ። እኔም ከብሩክሊን እንደሆነ ነገርኩት። በዚህ ጊዜ ምን እንደሚለኝ ግራ ገባው። በነፃ የለቀቀኝ ሲሆን ከዚያ በኋላም ዳግመኛ አልጠራኝም።” እንደዚህ ያሉት ደፋር የይሖዋ ምሥክሮች በሰሜናዊ ኪርጊስታን ምሥራቹን በጥንቃቄ ማሰራጨታቸውን ቀጠሉ። ከዚያም በ1980ዎቹ ዓመታት፣ ስለ ይሖዋ የሚገልጸው ውድ እውነት ወደ እኛ ቤተሰብ ደረሰ፤ እውነትን መጀመሪያ የሰማችው ባለቤቴ ማይራምቡቡ ናት።
ባለቤቴ እውነትን ወዲያውኑ ተቀበለች
ማይራምቡቡ ያደገችው ናርን በሚባለው የኪርጊስታን ክልል ውስጥ ነው። ከእሷ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኘነው ነሐሴ 1974 እህቴን ለመጠየቅ በመጣችበት ወቅት ነው። ማይራምቡቡን ገና ሳያት ወደድኳት። በዚያው ቀን ተጋባን።
አፑን ማምቤትሳድይኮቫ
ጥር 1981 ማይራምቡቡ በአውቶቡስ ተሳፍራ ወደ ገበያ እየሄደች ሳለ በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ የተጠቀሰውን ጭውውት ሰማች። ባለቤቴ ስለ ጉዳዩ ይበልጥ ማወቅ ስለፈለገች ሴትየዋን ስሟንና አድራሻዋን ጠየቀቻት። ሴትየዋም ስሟ አፑን እንደሆነ ነገረቻት፤ ሆኖም በይሖዋ ምሥክሮች ሥራ ላይ የተጣለው እገዳ በ1980ዎቹም ስላልተነሳ አፑን አድራሻዋን አልሰጠቻትም። ከዚህ ይልቅ የእኛን አድራሻ ወሰደች። ባለቤቴ ወደ ቤት ስትመጣ በደስታ እየፈነደቀች ነበር።
ማይራምቡቡ “ዛሬ የሚያስደንቅ ነገር ሰማሁ” አለችኝ። ከዚያም እንዲህ አለች፦ “አንዲት ሴት፣ ሰዎች የማይሞቱበት ጊዜ በቅርቡ እንደሚመጣ ነገረችኝ። የዱር አራዊትም እንኳ ለማዳ ይሆናሉ።” የተናገረችው ነገር ተረት እንደሆነ ተሰምቶኝ ነበር። “ለማንኛውም ወደ ቤታችን መጥታ ጉዳዩን እስክታብራራልን እንጠብቅ” ብዬ መለስኩላት።
አፑን ከሦስት ወራት በኋላ ቤታችን መጣች። ከዚያ በኋላም ሌሎች እህቶች ተመላልሰው የጠየቁን ሲሆን የኪርጊዝ ተወላጅ ከሆኑት የመጀመሪያዎቹ የይሖዋ ምሥክሮች መካከል ከአንዳንዶቹ ጋር የተዋወቅነው በዚህ መንገድ ነው። እነዚህ እህቶች ስለ ይሖዋ አምላክና ለሰው ዘር ስላለው ዓላማ የሚገልጹ አስደናቂ እውነቶችን አስተማሩን። ከጠፋችው ገነት ወደምትመለሰው ገነትa (እንግሊዝኛ) የሚለውን መጽሐፍ ተጠቅመው መጽሐፍ ቅዱስን አስጠኑን። ቶክሞክ ውስጥ የነበረው የዚህ መጽሐፍ ቅጂ አንድ ብቻ በመሆኑ መጽሐፉን በእጃችን ገልብጠን የራሳችን ቅጂ አዘጋጀን።
መጀመሪያ ከተማርናቸው ነገሮች አንዱ በዘፍጥረት 3:15 ላይ የሚገኘው ትንቢት ነው። ይህ ትንቢት የሚፈጸመው የአምላክ መሲሐዊ ንጉሥ በሆነው በኢየሱስ አማካኝነት እንደሆነ ተማርን። ይህ ሁሉም ሰው ሊሰማው የሚገባ አስፈላጊ መልእክት ነው! በመሆኑም የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በማወጁ ሥራ ለመካፈል ይበልጥ ተነሳሳን። (ማቴ. 24:14) ብዙም ሳይቆይ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ሕይወታችንን መለወጥ ጀመረ።
በእገዳው ዘመን መሰብሰብና መጠመቅ
በቶክሞክ የሚኖር አንድ ወንድም ሠርግ ጠራን። እኔና ባለቤቴ የይሖዋ ምሥክሮች ከሌሎች የተለየ ምግባር እንዳላቸው ለማስተዋል ጊዜ አልወሰደብንም። በሠርጉ ላይ የአልኮል መጠጥ አልነበረም፤ ጭፈራውም ቢሆን ሥርዓታማ ነበር። ይህ ከዚያ በፊት ከሄድንባቸው ሠርጎች በጣም የተለየ ነበር፤ በብዙዎቹ ሠርጎች ላይ ታዳሚዎቹ ሰክረው ሥርዓት የጎደለው ነገር የሚያደርጉ ከመሆኑም ሌላ አስጸያፊ ቃላት ሲናገሩ ይሰማሉ።
በተጨማሪም ቶክሞክ የሚገኘው ጉባኤ በሚያደርጋቸው አንዳንድ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ተገኘን። የአየሩ ሁኔታ በሚፈቅድበት ጊዜ ስብሰባዎቹ የሚካሄዱት ጫካ ውስጥ ነበር። ወንድሞችና እህቶች ፖሊሶች እየተከታተሉን እንደሆነ ስለሚያውቁ በአካባቢው ያለውን ሁኔታ የሚቃኝና የሚነግራቸው ሰው ይመድቡ ነበር። በቅዝቃዜው ወቅት ደግሞ ስብሰባዎቻችንን ቤት ውስጥ እናደርጋለን። ፖሊሶች ወደተሰበሰብንበት ቤት መጥተው ምን እያደረግን እንደሆነ የጠየቁባቸው ጊዜያት አሉ። እኔና ማይራምቡቡ ሐምሌ 1982 ጹይ ወንዝ ውስጥ በተጠመቅንበት ጊዜ ጠንቃቆች መሆን አስፈልጎን ነበር። (ማቴ. 10:16) ወንድሞች ጥቂት ጥቂት እየሆኑ ወደ ጫካው መጡ። ከዚያም አንድ ላይ ሆነን የመንግሥቱን መዝሙር ከዘመርን በኋላ የጥምቀት ንግግሩን አዳመጥን።
አገልግሎታችንን ለማስፋት የሚያስችለንን አጋጣሚ መጠቀም
በ1987 አንድ ወንድም ቦሊክጺ ከተማ ውስጥ የሚኖርን ፍላጎት ያለው ሰው ሄጄ እንዳነጋግር ጠየቀኝ። ከቤታችን ተነስተን ቦሊክጺ ለመድረስ በባቡር አራት ሰዓት መጓዝ ይጠይቃል። ምሥራቹን ለመስበክ ወደ ቦሊክጺ በተደጋጋሚ ጊዜ ከሄድን በኋላ ፍላጎት ያላቸው ብዙ ሰዎች እንዳሉ ተረዳን። አገልግሎታችንን ለማስፋት የሚያስችል አጋጣሚ እንደተከፈተልን ተሰማን።
እኔና ማይራምቡቡ ወደ ቦሊክጺ ብዙ ጊዜ ተጉዘናል። አብዛኛውን ጊዜ ቅዳሜና እሁድ እዚያው እያደርን እናገለግል እንዲሁም ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችን እናደርግ ነበር። ጽሑፎቻችንን የሚፈልጉ ሰዎች ብዛት በአስደናቂ ሁኔታ ጨመረ። ጽሑፎቻችንን ከቶክሞክ ይዘን የምንሄደው ሚሾክ በሚባል ድንች ለመያዝ የሚያገለግል ጆንያ ነበር። ጽሑፍ የሚፈልገው ሰው ብዙ ከመሆኑ የተነሳ በየወሩ ሁለት ጆንያ ሙሉ ጽሑፍ ብንወስድም አይበቃም። ወደ ቦሊክጺ ስንሄድና ስንመለስ ባቡሩ ላይ ለምናገኛቸው ተሳፋሪዎችም ጭምር እንመሠክር ነበር።
በ1995 ይኸውም ወደ ቦሊክጺ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሄድን ከስምንት ዓመት በኋላ በዚያ ከተማ ጉባኤ ተቋቋመ። በእነዚያ ዓመታት ከቶክሞክ ወደ ቦሊክጺ መመላለስ ብዙ ወጪ ጠይቆብናል። የገንዘብ አቅማችን ውስን ከመሆኑ አንጻር የመጓጓዣ ወጪውን መሸፈን የቻልነው እንዴት ነበር? ወጪያችንን ለመሸፈን እንድንችል አንድ ወንድም አዘውትሮ ገንዘብ ይሰጠን ነበር። ይሖዋ አገልግሎታችንን የማስፋት ፍላጎታችንን ስለተመለከተ ‘የሰማያትን መስኮቶች ከፍቶልናል።’ (ሚል. 3:10) በእርግጥም በይሖዋ ዘንድ ሁሉ ነገር ይቻላል!
ቤተሰባችንን በመንከባከብና በአገልግሎት ሥራ በዛልን
በ1992 የኪርጊዝ ተወላጅ የሆነ የመጀመሪያው የጉባኤ ሽማግሌ ሆኜ እንዳገለግል ተሾምኩ። በቶክሞክ በነበረው ጉባኤያችን አዳዲስ የአገልግሎት በሮች ተከፍተው ነበር። በተለያዩ የትምህርት ተቋማት የሚማሩ የኪርጊዝ ተወላጅ የሆኑ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ነበሩን። መጽሐፍ ቅዱስን ካስጠናናቸው ከእነዚህ ወጣቶች መካከል አንዱ አሁን በቅርንጫፍ ኮሚቴ ውስጥ የሚያገለግል ሲሆን ሁለቱ ደግሞ ልዩ አቅኚዎች ናቸው። በተጨማሪም በስብሰባዎቻችን ላይ ሌሎችን ለመርዳት ጥረት አድርገናል። በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ ጽሑፎቻችን የሚዘጋጁትም ሆነ ስብሰባዎቻችንን የምናደርገው በሩሲያኛ ነበር። ይሁን እንጂ አብዛኞቹ የጉባኤው አባላት የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ኪርጊዝ ነው። በመሆኑም እውነትን በቀላሉ መረዳት እንዲችሉ አስተረጉምላቸው ነበር።
ከባለቤቴና ከስምንቱ ልጆቻችን ጋር በ1989
እኔና ማይራምቡቡ ቁጥሩ እየጨመረ የመጣውን ቤተሰባችንን በመንከባከቡ ሥራም ተጠምደን ነበር። በአገልግሎት ስንካፈል እንዲሁም ወደ ጉባኤ ስብሰባዎች ስንሄድ ልጆቻችንን ይዘናቸው እንሄድ ነበር። ሴት ልጃችን ጉልሳይሮ ገና በ12 ዓመቷ መንገድ ላይ ለምታገኛቸው ሰዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መናገር ያስደስታት ነበር። በተጨማሪም ልጆቻችን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በቃላቸው ማጥናት ይወዱ ነበር። ልጆቻችን በጉባኤ እንቅስቃሴዎች ሥራ የበዛላቸው ነበሩ፤ ከጊዜ በኋላ ደግሞ የልጅ ልጆቻችን የእነሱን ፈለግ ተከትለዋል። አሁን በሕይወት ካሉት 9 ልጆቻችንና 11 የልጅ ልጆቻችን መካከል 16ቱ ይሖዋን ያገለግላሉ አሊያም ከወላጆቻቸው ጋር በስብሰባዎች ላይ ይገኛሉ።
አስደናቂ ለውጦች
በ1950ዎቹ ዓመታት በአካባቢያችን የይሖዋን ሥራ የጀመሩት ውድ ወንድሞችና እህቶች እኛ ያየናቸውን ለውጦች ቢያዩ እጅግ መገረማቸው አይቀርም። ከተመለከትናቸው ለውጦች አንዱ፣ ከ1990ዎቹ ጀምሮ ምሥራቹን ለመስበክና ብዙ ሆነን አንድ ላይ ለመሰብሰብ ተጨማሪ ነፃነት ማግኘታችን ነው።
ከባለቤቴ ጋር ስናገለግል
በ1991 እኔና ባለቤቴ ካዛክስታን ውስጥ በምትገኘው በአልማቲ (የቀድሞዋ አልማ አታ) በተደረገ ትልቅ ስብሰባ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ተካፈልን። በ1993 ደግሞ በኪርጊስታን ያሉ ወንድሞች ቢሽኬክ ውስጥ በስፓርታክ ስታዲየም የመጀመሪያውን ትልቅ ስብሰባ አደረጉ። አስፋፊዎች ከስብሰባው በፊት ስታዲየሙን ለማጽዳት አንድ ሳምንት ፈጅቶባቸዋል። የስታዲየሙ ዳይሬክተር በጣም ከመደነቁ የተነሳ በነፃ እንድንሰበሰብበት ፈቀደልን።
በ1994 ጽሑፎቻችን ለመጀመሪያ ጊዜ በኪርጊዝ ቋንቋ መታተማቸው አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ሌላ ክንውን ነው። አሁን በቢሽኬክ ቅርንጫፍ ቢሮ የሚገኘው የትርጉም ቡድን ጽሑፎቻችንን ወደ ኪርጊዝ ቋንቋ በቋሚነት ይተረጉማል። በ1998 ደግሞ የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ ኪርጊስታን ውስጥ ሕጋዊ እውቅና አገኘ። ድርጅቱ እያደገ ሲሆን ቁጥራችንም ከ5,000 በላይ ሆኗል። በዛሬው ጊዜ በሩሲያኛ፣ በሩሲያኛ የምልክት ቋንቋ፣ በቻይንኛ፣ በቱርክኛ፣ በኡዝቤክኛ፣ በእንግሊዝኛ፣ በኪርጊዝ እና በዊጉር ቋንቋዎች የሚካሄዱ 83 ጉባኤዎችና 25 ቡድኖች አሉን። የተለያየ ባሕልና አስተዳደግ ያላቸው እነዚህ ሁሉ ውድ ወንድሞችና እህቶች ይሖዋን በአንድነት ያገለግላሉ። እነዚህን ሁሉ አስደናቂ ለውጦች ያከናወነው ይሖዋ ነው።
ይሖዋ የእኔንም ሕይወት ለውጦታል። ቤተሰቦቼ ዝቅተኛ ኑሮ ያላቸው ገበሬዎች ሲሆኑ ትምህርት ቤት ገብቼ የተማርኩትም ለአምስት ዓመት ብቻ ነበር። ሆኖም ይሖዋ የጉባኤ ሽማግሌ ሆኜ እንዳገለግል ብሎም ውድ የሆኑትን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ከእኔ የሚበልጥ የትምህርት ደረጃ ላላቸው ሰዎች እንዳስተምር ተጠቅሞብኛል። በእርግጥም ይሖዋ በጣም አስገራሚ የሆኑ ነገሮች እንዲፈጸሙ ያደርጋል። ከራሴ ተሞክሮ እንዳየሁት “በአምላክ ዘንድ . . . ሁሉ ነገር ይቻላል”፤ ይህን ማወቄ ስለ ይሖዋ በታማኝነት መመሥከሬን እንድቀጥል ይገፋፋኛል።—ማቴ. 19:26
a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ፤ አሁን መታተም አቁሟል።