የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • wp19 ቁጥር 3 ገጽ 14-15
  • በአሁኑ ጊዜም አስደሳች ሕይወት መምራት ይቻላል

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በአሁኑ ጊዜም አስደሳች ሕይወት መምራት ይቻላል
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2019
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ባለን ነገር መርካት
  • የጤና ችግሮችን መቋቋም
  • ትዳርን ማጠናከር
  • ትዳርን ዘላቂ ለማድረግ የሚረዱ ሁለት ቁልፍ ነገሮች
    ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?
  • ፈገግታ—ብዙ ጥቅም ያስገኝልሃል!
    ንቁ!—2000
  • የላቀ የጥበብ ምንጭ
    መጽሐፍ ቅዱስ—የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው?
  • ገንዘብ የክፋት ሁሉ ሥር ነው?
    የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2019
wp19 ቁጥር 3 ገጽ 14-15
ቀደም ሲል ከታዩት ሳይንቲስቶች አንዱ ከባለቤቱ ጋር ምግብ ሲያበስል

በአሁኑ ጊዜም አስደሳች ሕይወት መምራት ይቻላል

ወደፊት ከሕመም፣ ከእርጅናና ከሞት ነፃ የሆነ አስደሳች ሕይወት ማግኘት ትችላለህ! በአሁኑ ጊዜ ግን ሕይወት በችግርና በመከራ የተሞላ ነው። ታዲያ በዛሬው ጊዜም አስደሳች ሕይወት መምራት የምትችለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ በደስታና በእርካታ የተሞላ ሕይወት ለመምራት የሚያስችል ምክር ይሰጣል። በሕይወታችን ውስጥ ሊያጋጥሙን የሚችሉ አንዳንድ ተፈታታኝ ሁኔታዎችንና ከእነዚህ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ምክር እስቲ እንመልከት።

ባለን ነገር መርካት

መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ምክር፦ “አኗኗራችሁ ከገንዘብ ፍቅር ነፃ ይሁን፤ ባሏችሁ ነገሮች ረክታችሁ ኑሩ።”—ዕብራውያን 13:5

በርካታ ሰዎች፣ ደስተኛ ለመሆን ብዙ ቁሳዊ ነገሮች ሊኖሩን እንደሚገባ ይናገራሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ‘ባሉን ነገሮች ረክተን መኖር’ እንደምንችል ይናገራል። ታዲያ ባለን ነገር መርካት የምንችለው እንዴት ነው?

‘ከገንዘብ ፍቅር’ ራቅ። ብዙ ሰዎች ‘በገንዘብ ፍቅር’ ምክንያት ጤንነታቸውን፣ ቤተሰባቸውን፣ ወዳጆቻቸውን፣ ሥነ ምግባራቸውን አልፎ ተርፎም ክብራቸውን መሥዋዕት ያደርጋሉ። (1 ጢሞቴዎስ 6:10) እንዴት ያለ ኪሳራ ነው! ገንዘብን የሚወድ መቼም ቢሆን “አይረካም።”—መክብብ 5:10

ለቁሳዊ ነገሮች ሳይሆን ለሰዎች ቦታ ስጥ። ቁሳዊ ነገሮች ጠቃሚ እንደሆኑ አይካድም። ሆኖም ሊወዱንም ሆነ ሊያመሰግኑን አይችሉም፤ እንዲህ ማድረግ የሚችሉት ሰዎች ብቻ ናቸው። ሕይወታችን እርካታ ያለው እንዲሆን ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ “እውነተኛ ወዳጅ” ነው።—ምሳሌ 17:17

የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር በመከተል በአሁኑ ጊዜም አስደሳች ሕይወት መምራት እንችላለን

የጤና ችግሮችን መቋቋም

መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ምክር፦ “ደስተኛ ልብ ጥሩ መድኃኒት ነው።”—ምሳሌ 17:22

ደስታ እንደ “ጥሩ መድኃኒት” የጤና ችግራችንን ለመቋቋም ይረዳናል። ይሁንና የጤና ችግር እያለብን ደስተኛ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

አድናቂ ሁን። በችግሮቹ ላይ ብቻ የሚያተኩር ሰው “ዘመኑ ሁሉ አስከፊ” ይሆንበታል። (ምሳሌ 15:15) በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ “አመስጋኝ መሆናችሁን አሳዩ” የሚል ምክር ይሰጠናል። (ቆላስይስ 3:15) በጣም ጥቃቅን ቢሆኑም እንኳ በሕይወትህ ውስጥ ለሚያጋጥሙህ መልካም ነገሮች አመስጋኝ ሁን። ፀሐይ ስትጠልቅ ያላት ውበት፣ ነፋሻማ አየር የሚፈጥረው ስሜት እንዲሁም የምንወደው ሰው የሚያሳየን ፈገግታ ልባችን በደስታ እንዲሞላ ያደርጋል።

ሌሎችን እርዳ። የጤና ችግር ቢኖርብህም እንኳ “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ [ያስገኝልሃል]።” (የሐዋርያት ሥራ 20:35) ሰዎች እነሱን ለመርዳት የምናደርገውን ጥረት ሲያደንቁ እርካታ እናገኛለን፤ ይህም ችግራችንን እንድንረሳ ይረዳናል። ሌሎች ሕይወታቸው እንዲሻሻል ስንረዳ የራሳችንም ሕይወት ይሻሻላል።

ትዳርን ማጠናከር

መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ምክር፦ “ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ [እወቁ]።”—ፊልጵስዩስ 1:10

አብረው ጊዜ የማያሳልፉ ባለትዳሮች እርስ በርስ እየተራራቁ ሊሄዱ ይችላሉ። በመሆኑም ባለትዳሮች በሕይወት ውስጥ ይበልጥ አስፈላጊ ከሆኑት ነገሮች አንዱ ለሆነው ለትዳራቸው ቅድሚያ መስጠታቸው የጥበብ እርምጃ ነው።

የተለያዩ ነገሮችን አብራችሁ አከናውኑ። የምትወዱትን ነገር ብቻችሁን ከማድረግ ይልቅ አንዳንድ ነገሮችን አብራችሁ ለማከናወን ለምን ዕቅድ አታወጡም? መጽሐፍ ቅዱስ “አንድ ከመሆን ሁለት መሆን ይሻላል” ይላል። (መክብብ 4:9) ለምሳሌ አብራችሁ ምግብ ማብሰል፣ ስፖርት መሥራት፣ ሻይ መጠጣት ወይም በእግር መንሸራሸር ትችላላችሁ።

ፍቅራችሁን ግለጹ። መጽሐፍ ቅዱስ ባልና ሚስት መዋደድና መከባበር እንዳለባቸው ይገልጻል። (ኤፌሶን 5:28, 33) ሞቅ ያለ ፈገግታ ማሳየት፣ እቅፍ ማድረግ ወይም ቀለል ያለ ስጦታ መስጠት ትዳርን ለማጠናከር በእጅጉ ይረዳል። በተጨማሪም ባለትዳሮች የፆታ ስሜት የሚንጸባረቅባቸውን የፍቅር መግለጫዎች ማሳየት ያለባቸው ለትዳር ጓደኛቸው ብቻ ነው።—ዕብራውያን 13:4

“ሕይወቴ ትርጉም ያለው ሆነ!”

—ጃፓን የምትኖረው ሪዮኮ ሚያሞቶ እንደተናገረችው

ሕይወት ከባድ ነበር። ባለቤቴ የመጠጥ ሱሰኛ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ቋሚ የሆነ ሥራ አልነበረውም። አራት ልጆች ነበሩን፤ ሆኖም ባለቤቴ የአባትነት ግዴታውን አይወጣም ነበር። ሕይወቴን ለማሻሻል ብፍጨረጨርም መውጫ የሌለው ዋሻ ውስጥ እንደገባሁ ይሰማኝ ነበር። በመሆኑም ‘ይህ ዕድሌ ነው ማለት ነው? ወይስ አምላክ በቀድሞ ሕይወቴ ለሠራሁት ኃጢአት አሁን እየቀጣኝ ነው?’ ብዬ አስብ ነበር።

አንድ ቀን አንዲት የይሖዋ ምሥክር ቤቴ መጣች። ከዚያም ስለ አምላክ መንግሥትና ስለ ዘላለም ሕይወት በቅንዓትና በፈገግታ ነገረችኝ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዳጠናም ግብዣ አቀረበችልኝ። ብዙም ሳይቆይ፣ አምላክ መኖሩን እንዲሁም ጥበበኛ፣ ፍትሐዊና አፍቃሪ መሆኑን ተረዳሁ። ከዚህም በተጨማሪ ሙታን ስላሉበት ሁኔታ እንዲሁም ይህ ሁሉ መከራ የሚደርስብኝ በዕድሌ ምክንያት እንዳልሆነ ተማርኩ።

ከሁሉ በላይ ደግሞ አስደሳችና አርኪ ሕይወት መምራት የምችለው ወደ አምላክ ከቀረብኩ ብቻ እንደሆነ ተገነዘብኩ። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ማወቄ በጣም ያበረታታኝ ከመሆኑም ሌላ ነፃነትና እርካታ ያለው ሕይወት እንድመራ አስችሎኛል። በስተ መጨረሻ ሕይወቴ ትርጉም ያለው ሆነ!

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ