የሕይወት ታሪክ
ያገኘሁት ውድ ክርስቲያናዊ ውርስ በይሖዋ ቤት እንዳብብ አስችሎኛል
በውድቅት ሌሊት እየተጓዝን ነው፤ ከፊት ለፊታችን ወደ 1.6 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ስፋት ያለው ግዙፉና ኃይለኛው የኒጀር ወንዝ ተንጣሎ ይታያል። በናይጄርያ የእርስ በርስ ጦርነቱ የተፋፋመበት ጊዜ ስለነበር የኒጀርን ወንዝ መሻገር ለሕይወት አስጊ እንደሆነ እናውቃለን። ያም ሆኖ የመጣው ይምጣ ብለን የኒጀርን ወንዝ አቋረጥን። ከዚያ በኋላም በተደጋጋሚ ይህን ወንዝ አቋርጠናል። በወቅቱ የግድ እንዲህ ማድረግ ነበረብን። ለመሆኑ እንዲህ ያለ ሁኔታ ውስጥ ልገባ የቻልኩት እንዴት ነው? እስቲ ከመወለዴ በፊት ወደነበረው ጊዜ ልመልሳችሁ።
አባቴ ጆን ሚልስ በ1913 ኒው ዮርክ ሲቲ ውስጥ ተጠመቀ፤ በወቅቱ 25 ዓመቱ ነበር። የጥምቀት ንግግሩን የሰጠው ወንድም ራስል ነበር። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ አባባ ወደ ትሪኒዳድ የሄደ ሲሆን በዚያም ኮንስታንስ ፋርመር የተባለች ቀናተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ አገባ። አባባ፣ ዊሊያም ብራውን የተባለ ጓደኛ ነበረው፤ ወንድም ብራውን የፍጥረት ፎቶ ድራማን ለሕዝብ በሚያሳይበት ጊዜ አባባ ይረዳው ነበር። ወንድም ብራውንና ባለቤቱ በ1923 በምዕራብ አፍሪካ እንዲያገለግሉ እስከተመደቡበት ጊዜ ድረስ እንዲህ ያደርግ ነበር። ወንድም ብራውንና ባለቤቱ ወደ ምዕራብ አፍሪካ ሲሄዱ ሰማያዊ ተስፋ የነበራቸው አባቴና እናቴ ደግሞ በዚያው በትሪኒዳድ ማገልገላቸውን ቀጠሉ።
አፍቃሪ የሆኑ ወላጆች
ወላጆቼ ዘጠኝ ልጆች ነበሯቸው፤ የበኩር ልጃቸውን በወቅቱ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና የትራክት ማኅበር ፕሬዚዳንት በነበረው በራዘርፎርድ ስም ሰየሙት። እኔ ታኅሣሥ 30, 1922 ስወለድ የወርቃማው ዘመን (የአሁኑ ንቁ!) አዘጋጅ በነበረው በክሌይተን ዉድዎርዝ ስም ተሰየምኩ። ወላጆቻችን ሁላችንም መሠረታዊ ትምህርት እንድናገኝ አድርገዋል፤ በዋነኝነት ግን መንፈሳዊ ግቦችን እንድናወጣ ያበረታቱን ነበር። እማማ ቅዱሳን መጻሕፍትን ተጠቅማ አሳማኝ በሆነ መንገድ የማስረዳት አስደናቂ ችሎታ ነበራት። አባባ ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን ለእኛ መንገር ያስደስተው ነበር፤ ታሪኮቹን ሕያው ለማድረግ የተለያዩ አካላዊ መግለጫዎችን ይጠቀም ነበር።
ከቱናፑና የመጡ የድምፅ መኪና ተጠቅመው የሚሰብኩ ወንድሞች ቡድን
ወላጆቻችን ያደረጉት ጥረት ግሩም ውጤት አስገኝቷል። ከአምስት ወንዶች ልጆች መካከል እኔን ጨምሮ ሦስታችን በጊልያድ ትምህርት ቤት ተካፍለናል። ሦስት እህቶቼ ደግሞ በትሪኒዳድ እና ቶቤጎ ውስጥ ለብዙ ዓመታት በአቅኚነት አገልግለዋል። ወላጆቻችን ያስተማሩን ትምህርትና የተዉልን ጥሩ ምሳሌ “በይሖዋ ቤት” እንድንተከል አስችሎናል። የሰጡን ማበረታቻ ከዚያ እንዳንወጣና “በአምላካችን ቅጥር ግቢዎች” ውስጥ እንድናብብ ረድቶናል።—መዝ. 92:13
ቤታችን ለስብከቱ እንቅስቃሴ እንደ ማዕከል ሆኖ ያገለግል ነበር። ብዙ ጊዜ አቅኚዎች ቤታችን ተሰብስበው ወንድም ጆርጅ ያንግ ስለተባለ ትሪኒዳድን የጎበኘ ካናዳዊ ሚስዮናዊ ያወሩ ነበር። ወላጆቼ ደግሞ ቀደም ሲል የአገልግሎት ጓደኞቻቸው ስለነበሩትና በወቅቱ በምዕራብ አፍሪካ ስለሚያገለግሉት ስለ ወንድም ብራውንና ስለ ባለቤቱ በደስታ ይናገሩ ነበር። እነዚህ ሁሉ ተደማምረው፣ በአሥር ዓመቴ አገልግሎት እንድጀምር አነሳሱኝ።
ልጅ ሳለሁ የነበሩ የአገልግሎት እንቅስቃሴዎች
በእነዚያ ጊዜያት መጽሔቶቻችን የሐሰት ሃይማኖትን፣ ስግብግብነት የሚንጸባረቅበትን ንግድና ብልሹ የሆነውን የፖለቲካ ሥርዓት የሚያጋልጥ ጠንካራ መልእክት የያዙ ነበሩ። በዚህም የተነሳ በ1936 ቀሳውስቱ የመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎችን በሙሉ እንዲያግድ የትሪኒዳድን ጊዜያዊ አስተዳዳሪ ገፋፉት። በመሆኑም ጽሑፎቻችንን ለመደበቅ የተገደድን ቢሆንም ያለንን ሁሉ አሟጠን እስክንጨርስ ድረስ ማበርከታችንን አላቆምንም። ትራክቶችን ይዘን ወይም መልእክቶች የያዙ ሰሌዳዎችን አንግበን ሰልፍ እንወጣ እንዲሁም በብስክሌት እንጓዝ ነበር። ከቱናፑና ከተማ ከመጡ የድምፅ መኪና ተጠቅመው የሚሰብኩ ወንድሞች ቡድን ጋር አብረን በመሆን ትሪኒዳድ ውስጥ ወደሚገኙ እጅግ ሩቅ የሆኑ ቦታዎች በመሄድ መልእክቱን አድርሰናል። አገልግሎቱ በጣም አስደሳች ነበር! እንዲህ ባለው መንፈሳዊ ሁኔታ ውስጥ ማደጌ በ16 ዓመቴ እንድጠመቅ ምክንያት ሆኖኛል።
ከቤተሰቤ ያገኘሁት መንፈሳዊ ውርስና በልጅነቴ ያሳለፍኳቸው ተሞክሮዎች ሚስዮናዊ የመሆን ምኞት በውስጤ እንዲቀጣጠል አድርገዋል። በ1944 ወደ አሩባ ሄጄ ከወንድም ኤድመንድ ከሚንግስ ጋር አብሬ ማገልገል በጀመርኩበት ጊዜም ይህ ምኞቴ አልጠፋም ነበር። እኔና ወንድም ከሚንግስ በ1945 በተደረገው የመታሰቢያ በዓል ላይ አሥር ሰዎች በመገኘታቸው በጣም ደስ ብሎን ነበር። በቀጣዩ ዓመት በደሴቲቱ ላይ የመጀመሪያው ጉባኤ ተቋቋመ።
ኦሪስን ካገባሁ በኋላ ሕይወቴ እንደ አዲስ አብቧል
ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ኦሪስ ዊሊያምስ ለተባለች የሥራ ባልደረባዬ መደበኛ ባልሆነ መንገድ መሠከርኩላት። ኦሪስ በልጅነቷ የተማረቻቸው መሠረተ ትምህርቶች ትክክል እንደሆኑ ለማሳመን የተለያዩ የመከራከሪያ ነጥቦችን ታነሳ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን ስታጠና ግን የአምላክ ቃል በእርግጥ ምን እንደሚያስተምር ስለተገነዘበች ጥር 5, 1947 ተጠመቀች። ከጊዜ በኋላ እኔና ኦሪስ ተዋደድን፤ ከዚያም ትዳር መሠረትን። ኦሪስ ኅዳር 1950 አቅኚ ሆነች። ኦሪስን ካገባሁ በኋላ ሕይወቴ እንደ አዲስ አብቧል።
በናይጄርያ የነበረው አስደሳች አገልግሎት
በ1955 በጊልያድ ትምህርት ቤት እንድንማር ተጋበዝን። በመሆኑም እኔና ኦሪስ ሥራችንን ለቀቅን። ከዚያም ቤታችንንና ሌሎች ንብረቶቻችንን ሸጠን አሩባን ተሰናበትን። ሐምሌ 29, 1956 ከ27ኛው የጊልያድ ክፍል የተመረቅን ሲሆን በናይጄርያ እንድናገለግል ተመደብን።
በሌጎስ፣ ናይጄርያ ካለው የቤቴል ቤተሰብ ጋር፣ በ1957
ኦሪስ ወደኋላ መለስ ብላ በማሰብ የሚከተለውን ተናግራለች፦ “የይሖዋ መንፈስ አንድ ሰው ከሚስዮናዊ ሕይወት ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሙትን ውጣ ውረዶች እንዲቋቋም ይረዳዋል። ከባለቤቴ በተለየ እኔ አንድም ቀን ሚስዮናዊ የመሆን ፍላጎት አድሮብኝ አያውቅም። የምመኘው ትዳር መሥርቼና ልጆች ወልጄ መኖር ነበር። ሆኖም ምሥራቹን መስበክ ምን ያህል አጣዳፊ እንደሆነ ስገነዘብ አስተሳሰቤን ለወጥኩ። ከጊልያድ ስንመረቅ ሚስዮናዊ ሆኜ ወንጌሉን ለመስበክ ሙሉ በሙሉ ተዘጋጅቼ ነበር። ኩዊን ሜሪ በተባለችው መርከብ ላይ ስንሳፈር ወንድም ኖር ቢሮ ውስጥ የሚሠራው ዎርዝ ቶርንቶን ‘መልካም ጉዞ!’ በማለት ተሰናበተን። ከዚያም በቤቴል እንድናገለግል እንደተመደብን ነገረን። እኔም በድንጋጤ ‘ውይ!’ ብዬ በረጅሙ ተነፈስኩ። ይሁን እንጂ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከቤቴል ሕይወት ጋር የተላመድኩ ሲሆን በዚያ የማቀርበውን አገልግሎት እየወደድኩት መጣሁ። ቤቴል ውስጥ በተለያዩ የሥራ ምድቦች አገልግያለሁ። ከሁሉ በላይ የወደድኩት ግን በእንግዳ መቀበያ ክፍል ውስጥ እንድሠራ የተሰጠኝን ምድብ ነው። ሰዎችን እወዳለሁ፤ ይህ ሥራ ደግሞ ከናይጄርያ ወንድሞችና እህቶች ጋር በቀጥታ ያገናኘኛል። ብዙዎቹ ቤቴል የሚደርሱት አቧራ ለብሰው፣ ደክሟቸው፣ ተጠምተውና ተርበው ነው። እነዚህን ወንድሞችና እህቶች መንከባከብ እንዲሁም የሚያስፈልጋቸውን ነገር ማቅረብ ያስደስተኛል። እነዚህ ነገሮች ሁሉ ለይሖዋ የማቀርበው ቅዱስ አገልግሎት ክፍል እንደሆኑ ማወቄ እርካታና ደስታ አስገኝቶልኛል።” አዎ፣ እያንዳንዱ የሥራ ምድብ በይሖዋ ቤት ውስጥ የምናብብበት አጋጣሚ ሰጥቶናል።.
በ1961 ትሪኒዳድ ውስጥ በቤተሰብ አንድ ላይ ተሰባስበን ስንጫወት ወንድም ብራውን አፍሪካ ውስጥ ካገኛቸው አስደሳች ተሞክሮዎች መካከል አንዳንዶቹን ተናገረ። እኔ ደግሞ በናይጄርያ ስላለው እድገት ተናገርኩ። ከዚያም ወንድም ብራውን እጆቹን ትከሻዬ ላይ ጣል አድርጎ አባባን “ጆኒ፣ አንተ ወደ አፍሪካ ሄደህ አታውቅም፤ ዉድዎርዝ ግን መሄድ ችሏል!” አለው። አባባም “በርታ ዎርዝ! በርታ!” አለኝ። እንዲህ ካሉ በመንፈሳዊ የጎለመሱ ወንድሞች ያገኘሁት ማበረታቻ አገልግሎቴን በተሟላ ሁኔታ ለማከናወን ያለኝን ፍላጎት አጠናክሮልኛል።
ዊሊያም “ባይብል” ብራውንና ባለቤቱ አንቶኒያ በእጅጉ አበረታተውናል
በ1962 በጊልያድ ትምህርት ቤት 37ኛው ክፍል ገብቼ ለአሥር ወር ያህል ተጨማሪ ሥልጠና የማግኘት አጋጣሚ ተከፈተልኝ። በወቅቱ የናይጄርያ ቅርንጫፍ ቢሮ የበላይ ተመልካች የነበረው ወንድም ዊልፍሬድ ጉች በጊልያድ ትምህርት ቤት 38ኛው ክፍል ውስጥ ከሠለጠነ በኋላ በኢንግላንድ እንዲያገለግል ተመደበ። በመሆኑም የናይጄርያ ቅርንጫፍ ቢሮ የበላይ ተመልካች ሆኖ የመሥራት ኃላፊነት በእኔ ላይ ወደቀ። የወንድም ብራውንን ምሳሌ በመከተል በመላዋ ናይጄርያ እዘዋወር የነበረ ሲሆን ይህም በዚያ ካሉት ወንድሞች ጋር እንድተዋወቅና ለእነሱ ያለኝ ፍቅር ይበልጥ እንዲያድግ ረድቶኛል። የናይጄርያ ወንድሞች ባደጉ አገሮች ውስጥ ያሉ በርካታ ሰዎች በቀላሉ የሚያገኟቸውን ቁሳዊ ነገሮች ማግኘት ባይችሉም ደስታና እርካታ ያለው ሕይወት ይመሩ ነበር፤ ይህም ትርጉም ያለው ሕይወት በገንዘብ ወይም በቁሳዊ ንብረቶች ላይ የተመካ እንዳልሆነ በግልጽ የሚያሳይ ነበር። ካሉበት ሁኔታ አንጻር በስብሰባዎች ላይ ንጹሕና የሚያስከብር ልብስ ለብሰው ሲመጡ ማየት የሚያስደንቅ ነበር። ብዙዎቹ ወደ ትላልቅ ስብሰባዎች የሚመጡት በጭነት መኪኖችና በቦሌካጃስa (ዙሪያቸውን ክፍት የሆኑ በዚያው አካባቢ የተሠሩ አውቶቡሶች) ነበር። በእነዚህ አውቶቡሶች ላይ ብዙውን ጊዜ ትኩረት የሚስቡ አባባሎች ይለጠፉ ነበር። ከእነዚህ መካከል አንዱ “ትናንሽ የውኃ ጠብታዎች ትልቅ ውቅያኖስ ያስገኛሉ” የሚል ነበር።
ይህ አባባል ምንኛ እውነት ነው! የእያንዳንዱ ግለሰብ ጥረት ዋጋ አለው፤ እኛም የበኩላችንን አስተዋጽኦ አድርገናል። በ1974 ከዩናይትድ ስቴትስ ሌላ 100,000 የአስፋፊ ቁጥር ላይ መድረስ የቻለችው ብቸኛዋ አገር ናይጄርያ ናት። በእርግጥም ሥራው አብቦ ነበር!
እንዲህ ያለ እድገት እየታየ በነበረበት ወቅት፣ ከ1967 እስከ 1970 ድረስ ናይጄርያ በእርስ በርስ ጦርነት እየታመሰች ነበር። ከኒጀር ወንዝ ማዶ በቢያፍራ በኩል ያሉት ወንድሞች ለወራት ያህል ከቅርንጫፍ ቢሮው ጋር ያላቸው ግንኙነት ተቋርጦ ነበር። ለእነሱ የግድ መንፈሳዊ ምግብ መውሰድ ነበረብን። በመግቢያው ላይ እንደተጠቀሰው ወደ ይሖዋ በመጸለይና በእሱ በመተማመን ወንዙን በተደጋጋሚ አቋርጠናል።
የጠመንጃ ቃታ ለመሳብ ተዘጋጅተው የሚጠብቁ ወታደሮችን፣ በሽታንና ሌሎች አደገኛ ሁኔታዎችን መጋፈጥ የሚጠይቀው ይህ ጉዞ እስካሁን ድረስ በአእምሮዬ ውስጥ ቁልጭ ብሎ ይታየኛል። ተጠራጣሪ የሆኑ የፌዴራል ወታደሮችን አልፎ መሄድ በራሱ የሚያስፈራ ቢሆንም በቢያፍራ በኩል ያለውን የተከበበ ቦታ ማለፍ ደግሞ ይበልጥ ያስፈራል። በአንድ ወቅት ከአሳባ ወደ ኦኒትሻ የሚጓዘውን የመንገደኞች ታንኳ ተሳፍሬ በኃይል የሚፈሰውን የኒጀር ወንዝ በማቋረጥ በኤኑጉ ያሉትን የበላይ ተመልካቾች አበረታትቼያለሁ። ሌላ ጊዜ ደግሞ ምሽት ላይ መብራት እንዲጠፋ ወደሚደረግባት አባ የተባለች ከተማ ሄጄ በዚያ የሚኖሩ ሽማግሌዎችን ለማጠናከር ጥረት አድርጌያለሁ። በተጨማሪም በፖርት ሀርኮርት ስብሰባ እያደረግን ሳለን የፌዴራል ሠራዊት ከከተማው ውጭ ያሉትን የቢያፍራ ተዋጊዎች ጥሶ በመግባቱ ስብሰባችንን ቶሎ ብለን በጸሎት ለመዝጋት ተገደናል።
እነዚህ ስብሰባዎች እጅግ ወሳኝ ነበሩ፤ ምክንያቱም ውድ ወንድሞቻችን የይሖዋ ፍቅራዊ እንክብካቤ እንደማይለያቸው እንዲያረጋግጡ ለመርዳት እንዲሁም ገለልተኝነትንና አንድነትን በተመለከተ በወቅቱ በጣም የሚያስፈልጋቸውን ምክር ለመስጠት ያስችሉ ነበር። የናይጄርያ ወንድሞች ያን አስከፊ ጦርነት በተሳካ ሁኔታ ማለፍ ችለዋል። የጎሳ ጥላቻ የማይበግረው ፍቅርና ክርስቲያናዊ አንድነት እንዳላቸው አሳይተዋል። በዚያ የፈተና ሰዓት ከጎናቸው መሆን መቻሌን እንደ ትልቅ መብት እቆጥረዋለሁ!
በ1969 በኒው ዮርክ ያንኪ ስታዲየም በተደረገው “ሰላም በምድር ላይ” የተሰኘ ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ ሊቀ መንበር የነበረው ወንድም ሚልተን ሄንሸል ሲሆን የእሱ ረዳት በመሆን ብዙ ነገር ተምሬያለሁ። የወንድም ሄንሸል ረዳት ሆኜ ያገኘሁት ሥልጠና በ1970 በሌጎስ፣ ናይጄርያ “አምላክ ሞገስ የሚያሳያቸው ሰዎች” በሚል ርዕስ ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ስናደርግ በጣም ጠቅሞኛል። ይህ ስብሰባ የተደረገው የእርስ በርስ ጦርነቱ ካበቃ ብዙም ሳይቆይ ነበር፤ ስብሰባው በተሳካ ሁኔታ ሊካሄድ የቻለው ይሖዋ ስለረዳን ነው። በዚህ ስብሰባ ላይ 121,128 ተሰብሳቢዎች የተገኙ ሲሆን ስብሰባው በ17 ቋንቋዎች ተደርጓል። አንድ ስብሰባ ይህን በሚያህሉ ቋንቋዎች ሲደረግ ይህ የመጀመሪያው ነበር። ወንድም ኖርና ሄንሸል እንዲሁም በኪራይ አውሮፕላኖች ከዩናይትድ ስቴትስና ከኢንግላንድ የመጡ ጎብኚዎች ከጴንጤቆስጤ ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ ከፍተኛ የተጠማቂዎች ቁጥር መመልከት ችለዋል፤ በዚያን ዕለት 3,775 የሚያህሉ አዳዲስ ደቀ መዛሙርት ተጠምቀው ነበር! በሕይወቴ ውስጥ፣ ይህን ስብሰባ ያደራጀንበትን ጊዜ ያህል በሥራ ተወጥሬ የማውቅ አይመስለኝም። በአስፋፊዎች ቁጥር ላይ የታየው እድገት ከሚታሰበው በላይ እጅግ ከፍተኛ ነበር!
“አምላክ ሞገስ የሚያሳያቸው ሰዎች” በተባለው ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ ኢቦ የተባለውን ቋንቋ ጨምሮ 17 የተለያዩ ቋንቋዎችን የሚናገሩ 121,128 ሰዎች ተገኝተዋል
ናይጄርያ ውስጥ ባሳለፍናቸው ከ30 የሚበልጡ ዓመታት በምዕራብ አፍሪካ ውስጥ አልፎ አልፎ በተጓዥ የበላይ ተመልካችነትና በዞን የበላይ ተመልካችነት የማገልገል መብት በማግኘቴ ደስተኛ ነኝ። ሚስዮናውያኑ በግለሰብ ደረጃ ትኩረትና ማበረታቻ ስለተሰጣቸው በጣም አመስጋኞች ነበሩ! እነዚህ ወንድሞችና እህቶች ችላ እንዳልተባሉ እንዲሰማቸው ማድረግ ምንኛ አስደሳች ነው! ይህ ሥራ፣ ወንድሞች በይሖዋ ቤት ውስጥ እንዲያብቡ ለመርዳት እንዲሁም የይሖዋ ድርጅት ጠንካራና አንድነት ያለው ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግ በግለሰብ ደረጃ አሳቢነት ማሳየት ወሳኝ እንደሆነ አስተምሮኛል።
ያጋጠመንን የጤና እክልና የእርስ በርስ ጦርነቱን መቋቋም የቻልነው በይሖዋ እርዳታ ነው። የይሖዋ በረከት እንዳልተለየን በግልጽ ይታይ ነበር። ኦሪስ እንዲህ ብላለች፦
“ሁለታችንንም በተደጋጋሚ ወባ ይዞን ነበር። በአንድ ወቅት ዎርዝ ራሱን ስለሳተ ሌጎስ ውስጥ ወደሚገኝ አንድ ሆስፒታል ተወሰደ። ሕይወቱ ላይተርፍ እንደሚችል ተነግሮኝ ነበር፤ ደስ የሚለው ነገር ግን መትረፍ ቻለ! ራሱን ሲያውቅ፣ ይንከባከበው ለነበረ ንዋምቢዌ የተባለ ነርስ ስለ አምላክ መንግሥት ነገረው። ከጊዜ በኋላ፣ ይህን ነርስ ለመጠየቅና መጽሐፍ ቅዱስን እንዲማር ለማበረታታት ከዎርዝ ጋር አብረን ሄድን። ይህ ነርስ እውነትን የተቀበለ ሲሆን ከተወሰነ ጊዜ በኋላ አባ ውስጥ በጉባኤ ሽማግሌነት ማገልገል ጀመረ። እኔም ብሆን በርካታ ሰዎች ሌላው ቀርቶ አጥባቂ ሙስሊሞች ጭምር ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች እንዲሆኑ መርዳት ችያለሁ። የናይጄርያን ሕዝብ፣ ባሕል፣ ልማድና ቋንቋ ማወቅ እንዲሁም መውደድ መቻላችን ከፍተኛ ደስታ አስገኝቶልናል።”
ያገኘነው ሌላ ትምህርት ደግሞ የሚከተለው ነው፦ በውጭ አገር ምድባችን ውስጥ ማበብ ከፈለግን በዚያ ያሉት ሰዎች ባሕል ከእኛ ባሕል የቱንም ያህል የተለየ ቢሆን፣ ወንድሞቻንንና እህቶቻችንን ለመውደድ ጥረት ማድረግ አለብን።
አዳዲስ ምድቦች
በናይጄርያ ቤቴል ውስጥ ስናገለግል ከቆየን በኋላ በ1987 በካሪቢያን በምትገኝ ሴንት ሉሺያ የተባለች ውብ ደሴት ላይ በመስክ ሚሲዮናዊነት እንድናገለግል ተመደብን። ይህ ምድብ አስደሳች ቢሆንም ለየት ያሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎች አጋጥመውናል። አፍሪካ ውስጥ አንድ ሰው ብዙ ሚስቶችን ማግባቱ የተለመደ ነገር ነው፤ እዚህ ደግሞ አንድ ወንድና ሴት ሕጋዊ ጋብቻ ሳይፈጽሙ አብረው መኖራቸው ምንም ችግር እንደሌለው ይቆጠራል። የአምላክ ቃል ያለው ኃይል መጽሐፍ ቅዱስን የምናስጠናቸው በርካታ ሰዎች አስፈላጊውን ለውጥ እንዲያደርጉ ረድቷቸዋል።
በትዳር አብረን ባሳለፍናቸው 68 ዓመታት ሁሉ ኦሪስን ከልቤ እወዳት ነበር
በዕድሜ መግፋት ምክንያት ጉልበታችን እየደከመ ሲመጣ የበላይ አካሉ በብሩክሊን ኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ወደሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት ከ2005 አንስቶ እንድንዛወር በማድረግ ፍቅራዊ ደግነት አሳይቶናል። ይሖዋ ኦሪስን ስለሰጠኝ እስካሁን ድረስ በየዕለቱ አመሰግነዋለሁ። በ2015 ኦሪስ፣ ጠላታችን በሆነው በሞት ተሸነፈች። እሷን ማጣቴ ያስከተለብኝን ሐዘን በቃላት ልገልጸው አልችልም። ኦሪስ ጥሩ የሕይወት አጋር እንዲሁም አፍቃሪና ተወዳጅ ሚስት ነበረች። አብረን ባሳለፍናቸው 68 ዓመታት ሁሉ ከልቤ እወዳት ነበር። በትዳር ሕይወትም ሆነ በጉባኤ ውስጥ ደስተኛ ለመሆን ቁልፉ የራስነት ሥርዓትን ማክበር፣ በነፃ ይቅር ማለት፣ ትሑት መሆንና የመንፈስ ፍሬን ማፍራት እንደሆነ ተገንዝበናል።
የሚያስከፋ ወይም ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር ሲያጋጥመን፣ ለይሖዋ ስንል የከፈልናቸው መሥዋዕቶች ከንቱ እንዳይሆኑ እንጸልይ ነበር። እየተስተካከልን ስንሄድ ሁሌም ሁኔታዎች ይበልጥ እየተሻሻሉ እንደሚሄዱ አስተውለናል፤ ወደፊት ደግሞ እስካሁን ካየነው ሁሉ የተሻለ ነገር ይጠብቀናል!—ኢሳ. 60:17፤ 2 ቆሮ. 13:11
ይሖዋ ወላጆቼና ሌሎች አስፋፊዎች ያደረጉትን ጥረት የባረከው ሲሆን በቅርብ ጊዜ በሰማነው ሪፖርት መሠረት በትሪኒዳድ እና ቶቤጎ ውስጥ ከእውነተኛው አምልኮ ጎን የቆሙ 9,892 ሰዎች አሉ። በአሩባም በርካታ ወንድሞች ጉባኤውን ለማጠናከር ጥረት አድርገዋል። እኔ በነበርኩበት ጊዜ አንድ ጉባኤ ብቻ የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ በዚያ ደሴት ላይ 14 ጠንካራ ጉባኤዎች አሉ። በናይጄርያ ደግሞ የአስፋፊዎች ቁጥር ከፍተኛ ጭማሪ በማሳየት 381,398 ደርሷል። እንዲሁም በሴንት ሉሺያ የይሖዋን መንግሥት የሚደግፉ 783 አስፋፊዎች አሉ።
አሁን ዕድሜዬ ከ90 ዓመት በላይ ነው። መዝሙር 92:14 በይሖዋ ቤት ውስጥ የተተከሉ ሰዎችን አስመልክቶ ሲናገር “ባረጁ ጊዜም እንኳ ማበባቸውን ይቀጥላሉ፤ እንደበረቱና እንደጠነከሩ ይኖራሉ” ይላል። በይሖዋ አገልግሎት ላሳለፍኩት ሕይወት በጣም አመስጋኝ ነኝ። ያገኘሁት ውድ ክርስቲያናዊ ውርስ ይሖዋን በሙሉ ልቤ እንዳገለግለው አበረታቶኛል። ይሖዋ በታማኝ ፍቅሩ ተነሳስቶ ‘በእሱ ቅጥር ግቢዎች ውስጥ እንዳብብ’ አስችሎኛል።—መዝ. 92:13
a የመጋቢት 8, 1972 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ከገጽ 24-26ን ተመልከት።