የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w19 ነሐሴ ገጽ 26-28
  • እምነት—በመንፈሳዊ የሚያጠነክር ባሕርይ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • እምነት—በመንፈሳዊ የሚያጠነክር ባሕርይ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2019
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • እምነት ምንድን ነው?
  • ጥሩ የልብ ዝንባሌ ያስፈልጋል
  • ዳዊት ጠንካራ እምነት ያዳበረው እንዴት ነው?
  • እምነትህን ማጠናከር የምትችለው እንዴት ነው?
  • በኢየሱስ ላይ እምነት ይኑርህ
  • “እጅግ ቅዱስ በሆነው እምነታችሁ ላይ ራሳችሁን ገንቡ”
  • ይሖዋ በገባው ቃል ላይ እምነት እንዳላችሁ በተግባር አሳዩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2016
  • “እምነት ጨምርልን”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2015
  • በእውነት ላይ የተመሠረተ እምነት አሳዩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • በእርግጥ በምሥራቹ ታምናለህ?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2003
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2019
w19 ነሐሴ ገጽ 26-28

እምነት—በመንፈሳዊ የሚያጠነክር ባሕርይ

  • ፍቅር

  • ደስታ

  • ሰላም

  • ትዕግሥት

  • ደግነት

  • ጥሩነት

  • እምነት

  • ገርነት

  • ራስን መግዛት

እምነት ታላቅ ኃይል አለው። ለምሳሌ ያህል፣ ሰይጣን መንፈሳዊነታችንን እንድናጣ ለማድረግ ቢጥርም እምነት “የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ” ለማምከን ያስችለናል። (ኤፌ. 6:16) እምነት እንደ ተራራ ያሉ ከባድ ችግሮችን በጽናት ለመወጣት ይረዳናል። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “የሰናፍጭ ቅንጣት የምታክል እምነት ካላችሁ ይህን ተራራ ‘ከዚህ ተነስተህ ወደዚያ ሂድ’ ብትሉት ይሄዳል” ብሏቸዋል። (ማቴ. 17:20) እምነት በመንፈሳዊ ጠንካራ እንድንሆን የሚረዳ ባሕርይ ከመሆኑ አንጻር የሚከተሉትን ጥያቄዎች መመርመራችን ተገቢ ነው፦ እምነት ምንድን ነው? የልባችን ዝንባሌ ከእምነታችን ጋር ምን ግንኙነት አለው? እምነታችንን ማጠናከር የምንችለው እንዴት ነው? እምነት መጣል ያለብን በማን ላይ ነው?—ሮም 4:3

እምነት ምንድን ነው?

እምነት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እውነት መሆኑን አምኖ ከመቀበል የበለጠ ነገርን ያመለክታል፤ ምክንያቱም “አጋንንትም [እንኳ አምላክ እንዳለ] ያምናሉ፤ በፍርሃትም ይንቀጠቀጣሉ።” (ያዕ. 2:19) ታዲያ እምነት ምንድን ነው?

ከጠፈር የተነሳ የምድር ፎቶግራፍ

‘ቀንና ሌሊት መፈራረቃቸውን ያቆሙ ይሆን?’ ብለን እንደማንጠራጠር ሁሉ ምንጊዜም ቢሆን የአምላክ ቃል መፈጸሙ እንደማይቀር እርግጠኞች ነን

መጽሐፍ ቅዱስ ለእምነት የሚሰጠው ፍቺ ሁለት ነገሮችን ያካተተ ነው። አንደኛ፣ “እምነት ተስፋ የተደረጉትን ነገሮች በእርግጠኝነት መጠበቅ ማለት ነው።” (ዕብ. 11:1ሀ) እምነት ካለህ ይሖዋ የተናገራቸው ነገሮች በሙሉ እውነት እንደሆኑና ፍጻሜያቸውን እንደሚያገኙ ሙሉ በሙሉ ትተማመናለህ። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ እስራኤላውያንን እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “ቀንና ሌሊት በተወሰነላቸው ጊዜ እንዳይፈራረቁ፣ የቀን ቃል ኪዳኔንና የሌሊት ቃል ኪዳኔን ማፍረስ የምትችሉ ከሆነ፣ ያን ጊዜ ከአገልጋዬ ከዳዊት ጋር የገባሁት ቃል ኪዳኔ ሊፈርስ ይችላል።” (ኤር. 33:20, 21) ፀሐይዋ ጊዜዋን ጠብቃ መውጣቷንና መጥለቋን ታቆም ይሆን የሚል ስጋት አድሮብህ ያውቃል? በዚህ የተነሳ ቀንና ሌሊት መፈራረቃቸውን ያቆሙ ይሆን ብለህስ ትሰጋለህ? ምድር በራሷ ዛቢያ ላይ እንድትሽከረከርና ፀሐይን እንድትዞር የሚያደርጉት የተፈጥሮ ሕጎች እንደማይፋለሱ እርግጠኛ ከሆንክ እነዚህን ሕጎች ያስቀመጠው ፈጣሪ ቃሉን እንደሚፈጽም ልትጠራጠር ይገባል? በፍጹም!—ኢሳ. 55:10, 11፤ ማቴ. 5:18

ሁለተኛ፣ እምነት “የምናምንበት ነገር በዓይን የሚታይ ባይሆንም እውን መሆኑን የሚያሳይ ተጨባጭ ማስረጃ ነው።” እምነት፣ አንዳንድ ነገሮች በዓይን ባይታዩም እውን መሆናቸውን የሚያሳይ “ተጨባጭ ማስረጃ” እንደሆነ ተገልጿል። (ዕብ. 11:1ለ) ይህ ሲባል ምን ማለት ነው? አንድ ትንሽ ልጅ ‘አየር እንዳለ እንዴት ታውቃለህ?’ ብሎ ጠየቀህ እንበል። አየር በዓይን የሚታይ ነገር ባይሆንም ልጁ አየር መኖሩን የሚያረጋግጠውን ማስረጃ እንዲያስተውል ትረዳዋለህ፤ ለምሳሌ ነፋስ ሲነፍስ የሚፈጠረውን ሁኔታ ልትጠቅስለት ትችላለህ። ይህ ማስረጃ፣ ልጁ በዓይኑ ሊያየው ባይችልም እንኳ አየር እንዳለ አምኖ እንዲቀበል ያደርጋል። በተመሳሳይም እምነት ጠንካራ በሆነ ማስረጃ ላይ የተመሠረተ ነገር ነው።—ሮም 1:20

ጥሩ የልብ ዝንባሌ ያስፈልጋል

እምነት በማስረጃ ላይ የተመሠረተ መሆን ስላለበት አንድ ሰው እምነት እንዲኖረው ከፈለገ መጀመሪያ “የእውነትን ትክክለኛ እውቀት” ማግኘት አለበት። (1 ጢሞ. 2:4) ይህ ብቻ ግን በቂ አይደለም። ሐዋርያው ጳውሎስ “ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃል” በማለት ጽፏል። (ሮም 10:10) አንድ ሰው እውነትን ከማመን ባለፈ ከፍ አድርጎ ሊመለከተው ይገባል። እምነቱን በተግባር ለማሳየት ማለትም ከተማረው እውነት ጋር በሚስማማ መንገድ ለመኖር የሚነሳሳው እንዲህ ካደረገ ብቻ ነው። (ያዕ. 2:20) ለእውነት ልባዊ አድናቆት የሌለው ሰው አሳማኝ የሆነ ማስረጃን እንኳ ለመቀበል ፈቃደኛ ላይሆን ይችላል፤ ምክንያቱም ቀድሞ የነበረውን አመለካከት መቀየር ወይም ለኃጢአተኛ ሥጋው የሚመቸውን ነገር ማድረጉን መተው አይፈልግም። (2 ጴጥ. 3:3, 4፤ ይሁዳ 18) በጥንት ዘመን የኖሩ ተአምራት ሲፈጸሙ ያዩ ብዙ ሰዎች እምነት ማዳበር ያልቻሉት ለዚህ ነው። (ዘኁ. 14:11፤ ዮሐ. 12:37) የአምላክ ቅዱስ መንፈስ፣ እምነት እንዲያዳብሩ የሚረዳው ለእውነት ልባዊ ፍቅር ያላቸውን ሰዎች ብቻ ነው።—ገላ. 5:22፤ 2 ተሰ. 2:10, 11

ዳዊት ጠንካራ እምነት ያዳበረው እንዴት ነው?

አስደናቂ እምነት ከነበራቸው ሰዎች አንዱ ንጉሥ ዳዊት ነው። (ዕብ. 11:32, 33) እንዲህ ያለ እምነት የነበራቸው ግን ሁሉም የቤተሰቡ አባላት አይደሉም። ለምሳሌ ያህል፣ ዳዊት እስራኤላውያንን እየተገዳደረ ስለነበረው ስለ ጎልያድ ለማወቅ በሞከረበት ወቅት ታላቅ ወንድሙ የሆነው ኤልያብ ተቆጥቶት ነበር፤ ይህ አጋጣሚ ኤልያብ በይሖዋ የማዳን ኃይል ላይ ያለው እምነት ጠንካራ እንዳልሆነ የሚያሳይ ነው። (1 ሳሙ. 17:26-28) እምነት ስንወለድ ጀምሮ የሚኖረን ወይም ከወላጆቻችን የምንወርሰው ነገር አይደለም፤ በመሆኑም ዳዊት እንዲህ ያለ እምነት ሊያዳብር የቻለው ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና ስለነበረው መሆን አለበት።

መዝሙር 27 ዳዊት እንዲህ ያለ ጠንካራ እምነት እንዲያዳብር የረዳው ምን እንደሆነ ይጠቁመናል። (ቁ. 1) ዳዊት ቀደም ሲል ስላጋጠሙት ነገሮች እንዲሁም ይሖዋ ከጠላቶቹ እንዴት እንደታደገው ያሰላስል ነበር። (ቁ. 2, 3) ይሖዋ ለንጹሕ አምልኮ ያደረገውን ዝግጅት ከፍ አድርጎ ይመለከት ነበር። (ቁ. 4) ዳዊት ከእምነት ባልንጀሮቹ ጋር በመሆን በማደሪያው ድንኳን ይሖዋን ያመልክ ነበር። (ቁ. 6) ወደ ይሖዋ አጥብቆ ይጸልይ ነበር። (ቁ. 7, 8) ከዚህም ሌላ ዳዊት የአምላክን መንገድ የመማር ፍላጎት ነበረው። (ቁ. 11) ዳዊት ለእምነት ትልቅ ቦታ ይሰጥ ስለነበር “እምነት ባይኖረኝ ኖሮ ምን ይውጠኝ ነበር!” ብሏል።—ቁ. 13

እምነትህን ማጠናከር የምትችለው እንዴት ነው?

አንተም በመዝሙር 27 ላይ የተገለጸው ዓይነት አመለካከትና ልማድ ካዳበርክ እንደ ዳዊት ጠንካራ እምነት ሊኖርህ ይችላል። እምነት በትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ ነው፤ በመሆኑም የአምላክን ቃልና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ባጠናህ መጠን፣ የአምላክ መንፈስ ፍሬ ገጽታ የሆነውን ይህን ባሕርይ ማዳበር ቀላል እየሆነልህ ይሄዳል። (መዝ. 1:2, 3) በምታጠናበት ወቅት ለማሰላሰል ጊዜ መድብ። ለተክል እድገት፣ አፈር አስፈላጊ እንደሆነ ሁሉ አድናቆታችን እየጨመረ እንዲሄድም ማሰላሰል ያስፈልገናል። ለይሖዋ ያለህ አድናቆት እየጨመረ ሲሄድ ደግሞ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ እሱን በማምለክና ተስፋህን ለሌሎች በማወጅ እምነትህን በተግባር ለማሳየት ያለህ ፍላጎትም እየጨመረ ይሄዳል። (ዕብ. 10:23-25) ከዚህም ሌላ ‘ተስፋ ሳትቆርጥ መጸለይህን’ በመቀጠል እምነት እንዳለህ ማሳየት ትችላለህ። (ሉቃስ 18:1-8) ስለዚህ ይሖዋ ‘ስለ አንተ እንደሚያስብ’ በመተማመን ‘ዘወትር ጸልይ።’ (1 ተሰ. 5:17፤ 1 ጴጥ. 5:7) እምነት ለተግባር ያነሳሳናል፤ እምነታችንን በተግባር መግለጻችን ደግሞ እምነታችን ይበልጥ እንዲጠናከር ያደርጋል።—ያዕ. 2:22

በኢየሱስ ላይ እምነት ይኑርህ

ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ላይ ደቀ መዛሙርቱን “በአምላክ እመኑ፤ በእኔም ደግሞ እመኑ” ብሏቸዋል። (ዮሐ. 14:1) ስለዚህ በይሖዋ ብቻ ሳይሆን በኢየሱስም ማመን አለብን። ለመሆኑ በኢየሱስ ማመን ሲባል ምን ማለት ነው? ይህን ማድረግ የምንችልባቸውን ሦስት መንገዶች እስቲ እንመልከት።

ኢየሱስ ከ11 ታማኝ ሐዋርያቱ ጋር

በኢየሱስ ማመን ሲባል ምን ማለት ነው?

አንደኛ፣ ቤዛውን አምላክ በግለሰብ ደረጃ እንደሰጠህ ስጦታ አድርገህ ተመልከተው። ሐዋርያው ጳውሎስ “የምኖረው በወደደኝና ለእኔ ሲል ራሱን አሳልፎ በሰጠው በአምላክ ልጅ ላይ ባለኝ እምነት ነው” ብሏል። (ገላ. 2:20) በኢየሱስ ላይ እምነት ካለህ ቤዛው በግለሰብ ደረጃ ለአንተ የተሰጠ ስጦታ እንደሆነ፣ የኃጢአት ይቅርታና የዘላለም ሕይወት ተስፋ ማግኘት የቻልከው በዚህ ዝግጅት አማካኝነት እንደሆነ እንዲሁም አምላክ ለአንተ ያለውን ፍቅር የሚያረጋግጥ የላቀ ማስረጃ እንደሆነ ትተማመናለህ። (ሮም 8:32, 38, 39፤ ኤፌ. 1:7) እንዲህ ያለው እምነት ስለ ራስህ የሚሰማህን አሉታዊ ስሜት ለማሸነፍ ይረዳሃል።—2 ተሰ. 2:16, 17

ሁለተኛ፣ የኢየሱስ መሥዋዕት በከፈተው አጋጣሚ በመጠቀም ወደ ይሖዋ ጸልይ። ቤዛ ስለተከፈለልን “እርዳታ በሚያስፈልገን ጊዜ ምሕረትና ጸጋ እናገኝ ዘንድ ያለምንም ፍርሃት” ወደ ይሖዋ መጸለይ እንችላለን። (ዕብ. 4:15, 16፤ 10:19-22) ጸሎት በኃጢአት ላለመሸነፍ ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ያጠናክርልናል።—ሉቃስ 22:40

ሦስተኛ፣ ኢየሱስን ታዘዝ። ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በወልድ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ ወልድን የማይታዘዝ ግን የአምላክ ቁጣ በላዩ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም።” (ዮሐ. 3:36) ዮሐንስ በኢየሱስ የሚያምኑ ሰዎችን እሱን ከማይታዘዙ ጋር እያነጻጸረ እንደተናገረ ልብ በል። ከዚህ አንጻር፣ በኢየሱስ የምታምን ከሆነ እሱን መታዘዝ ይኖርብሃል ማለት ነው። ኢየሱስን የምትታዘዘው “የክርስቶስን ሕግ” ማለትም እሱ ያስተማራቸውንና ያዘዛቸውን ነገሮች በሙሉ በመፈጸም ነው። (ገላ. 6:2) በተጨማሪም ኢየሱስ ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ በኩል የሚሰጠውን መመሪያ በመከተል እሱን መታዘዝ ትችላለህ። (ማቴ. 24:45) ኢየሱስን የምትታዘዝ ከሆነ እንደ ኃይለኛ አውሎ ነፋስ ያሉ ችግሮችን ለመቋቋም የሚያስችል ጥንካሬ ይኖርሃል።—ማቴ. 7:24, 25

“እጅግ ቅዱስ በሆነው እምነታችሁ ላይ ራሳችሁን ገንቡ”

በአንድ ወቅት አንድ ሰው ኢየሱስን “እምነት አለኝ! እምነቴ እንዲጠነክር ደግሞ አንተ እርዳኝ!” ብሎት ነበር። (ማር. 9:24) ይህ ሰው በተወሰነ መጠን እምነት ነበረው፤ ሆኖም ተጨማሪ እምነት እንደሚያስፈልገው መገንዘቡን በትሕትና ገልጿል። ልክ እንደዚህ ሰው ሁላችንም ተጨማሪ እምነት የሚጠይቁ ሁኔታዎች ያጋጥሙናል። ደግሞም ሁላችንም ከአሁኑ እምነታችንን ለማጠናከር ማድረግ የምንችለው ነገር አለ። ቀደም ብለን እንደተመለከትነው የአምላክን ቃል በማጥናትና በዚያ ላይ በማሰላሰል ለይሖዋ ያለን አድናቆት እየጨመረ እንዲሄድ ካደረግን እምነታችን ይጠናከራል። ከዚህም ሌላ ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ይሖዋን ማምለካችን፣ ስለ ተስፋችን ለሌሎች መናገራችንና በጸሎት መጽናታችን እምነታችን እንዲጠናከር ያደርጋል። እምነታችን ሲጠናከር ደግሞ ከሁሉ የላቀውን ሽልማት እናገኛለን። የአምላክ ቃል እንዲህ በማለት ያሳስበናል፦ “የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ እናንተ ግን እጅግ ቅዱስ በሆነው እምነታችሁ ላይ ራሳችሁን ገንቡ፤ . . . ይህን የምታደርጉት . . . ከአምላክ ፍቅር ሳትወጡ እንድትኖሩ ነው።”—ይሁዳ 20, 21

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ