ታላቁ ሰው በተባለው መጽሐፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ማስጀመር
1 የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማግኘት ለአንተና ለቤቱ ባለቤት ለሁለታችሁም እጅግ የሚያስደስትና የድካም ዋጋ የሚገኝበት ነው። የመጽሐፍ ቅዱስን እውቀት ለሌሎች በማካፈል ከሚገኘው ደስታ ጋር ሊወዳደር የሚችል ምንም ነገር የለም። — ምሳ. 11:25
2 የመጨረሻዎቹ ቀናት ምልክት፦ ከላይ ባለው ርዕሰ ትምህርት ላይ በቀረበው ሐሳብ ተጠቅመህና ‘ይህ ዓለም ከመጥፋት ይተርፍ ይሆንን?’ በተባለው ትራክት ውይይትህን ጀምረህ ከሆነ ታላቁ ሰው በተባለው መጽሐፍ ላይ ያለውን ምዕራፍ 111ን ተጠቅመህ ጥናት ማስጀመር የምትችለው እንዴት ነው? መጽሐፉን ገልጠህ ምዕራፍ 111ን አውጣና የመጀመሪያዎቹን ሦስት አንቀጾች አንብብ። ከዚያም በምዕራፉ መጨረሻ ላይ ያለውን ጥያቄ ልትጠይቅ ትችላል:- “ሐዋርያት ጥያቄ እንዲጠይቁ ያነሳሳቸው ምንድን ነው? ይሁን እንጂ በአእምሮአቸው የያዙት ሌላ ነገር እንደነበረ ከሁኔታዎቹ መረዳት ይቻላል?” የቤቱ ባለቤት በጉዳዩ ላይ እንዲመራመር እርዳው። ሥዕሎቹንም ለማስተማር ተጠቀምባቸው። ከአራት እስከ ስድስት ያሉትን አንቀጾች ካነበብክ በኋላ ሁለተኛውን ጥያቄ ጠይቀው:- “በ70 እዘአ የኢየሱስ ትንቢት የትኛው ክፍል ተፈጸመ? ሆኖም በዚያን ጊዜ ያልተፈጸመ ምን ትንቢት አለ?” የቤቱ ባለቤት ፍላጎት ካሳየና ጊዜ ካለው ውይይትህን ቀጥል።
3 የቤቱ ባለቤት በሌላ ጊዜ መወያየቱን ይበልጥ ተስማሚ ሆኖ ካገኘው እንዲህ ብለህ ልትጠይቅ ትችላለህ:- “የዚህ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ መቼ እንደሚሆን የበለጠ ማወቅ ይፈልጋሉን?” ከዚያም ይህን ጥያቄ ለመመለስ ተመልሰህ የምትሄድበትን ሁኔታ ልታመቻች ትችላለህ።
4 ሰላም የሰፈነበት ዓለም ሊገኝ ይችላልን? ታላቁ ሰው ወደ ተባለው መጽሐፍ ለመምራት ሰላም በሰፈነበት ዓለም ውስጥ የሚገኝ ሕይወት የተባለውን ትራክት ተጠቅመህ ከነበረ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር ምዕራፍ 133ን ጠቃሚ ሆኖ ልታገኘው የምትችለው እንዴት ነው?
2 ጴጥሮስ 3:13ን ካነበብክ በኋላ ትራክቱ ላይ ገጽ 3 ላይ የሚገኘውን ሁለተኛውን አንቀጽ ልታነብ ወይም ፍሬ ነገሩን በአጭሩ ልታቀርብ ከዚያም እንዲህ ልትል ትችላለህ፦
◼ “የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ የይሖዋ መንግሥት ንጉሥ ይሆናል። እስከ ዛሬ ድረስ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው የተባለው መጽሐፍ ኢየሱስን እንዴት አድርጎ እንደሚገልጸውና ወደፊት ስለሚያከናውነው ነገር ምን ማብራሪያ እንደሚሰጠን ልብ ብለው ይመልከቱ።” ከዚያ በኋላ ምዕራፉን በሙሉ አንብብ። የቤቱን ባለቤት በምዕራፉ መጨረሻ ላይ ያለውን የመጀመሪያ ጥያቄ ጠይቀው:- “ከአርማጌዶን የሚተርፉ ሰዎችና ልጆቻቸው የሚያገኟቸው አስደሳች ጥቅሞች ምንድን ናቸው? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት። ሌሎቹ ጥያቄዎች በተመሳሳይ መንገድ ውይይት ሊደረግባቸው ይችላል።] ኢየሱስ የሚገዛት አዲሲቷ ምድር አባል ለመሆን ይፈልጋሉን? ይህን ሁኔታ እርስዎም ሊያገኙት የሚችሉት መሆኑን ከመጽሐፍ ቅዱስ መመልከት እንዲችሉ ለመርዳት የሚያስችል አጋጣሚ በየሳምንቱ ባገኝ ደስ ይለኛል።”
5 አንዳንድ ግለሰቦች በዚህ ጉብኝት ወቅት ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ተጨማሪ ውይይት ለማድረግ ፍላጎት ያሳዩ ይሆናል።
እንዲህ ልትል ትችላለህ፦
◼ “በአራቱ ወንጌሎች ላይ ሰፍሮ እንደሚገኘው በዚህ መጽሐፍም ላይ ስለ ኢየሱስ ምድራዊ ሕይወት ለመግለጽ ጥረት ተደርጓል። ኢየሱስ በምድር ላይ ስላሳለፈው ሕይወት የበለጠ ለመማር ይፈልጋሉን?” የቤቱ ባለቤት ከተስማማ በምዕራፍ 15 ላይ ያሉትን የኢየሱስን የመጀመሪያ ተአምራት ልታወያየው ትፈልግ ይሆናል።
6 ጽድቅን የሚያፈቅሩና ለገጠሟቸው ችግሮች መፍትሔ የሚሹ ቅን ልብ ያላቸው ብዙ ሰዎች አሁንም አሉ። በእውነትም በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አማካኝነት የኢየሱስን ትምህርቶች ለማካፈል ራስን በፈቃደኝነት ማቅረቡ ከፍተኛ ዋጋ የሚከፍል ሥራ ነው።