የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን ለአገልግሎት አዘጋጃቸው
1 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ስንመራ ዋናው ግባችን ሌሎችን በማስተማሩ ሥራ አብረውን የሚሠሩ አዳዲስ ደቀ መዛሙርትን ማፍራት ነው። (ማቴ. 28:19, 20) ስለዚህ የጥናቱ ዓላማ እንዲሁ እውቀት እንዲያገኙ ብቻ አይደለም። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ በተማሪዎቻችን ውስጥ ልብን የሚነካ እምነት ለመትከልና ተስፋቸውን ለሌሎች ማካፈል እንዲችሉ ማዘጋጀት ነው። (2 ቆሮ. 4:13) ሌሎችን ለማስተማር ብቃት እንዲኖራቸው ተግባራዊ በሆኑ በምን መንገዶች ልንረዳቸው እንችላለን? — 2 ጢሞ. 2:2
2 አገልግሎትን ግብ አድርገህ ከፊታቸው አስቀምጥ፦ ገና ከመጀመሪያው እውነተኛ አምልኮ ‘ሕዝባዊ ምሥክርነት መስጠትን’ የሚጨምር መሆኑን ግልጽ አድርግለት። (ሮሜ 10:10) የይሖዋ ምሥክሮቸ የሚለው ስማችን ለሌሎች መናገር ያለብን መሆኑን ያሳያል። እየተማሩ ያሉት ለራሳቸው መዳን ብቻ አለመሆኑን እንዲገነዘቡ እርዳቸው። እነሱ ራሳቸው አስተማሪዎች ሲሆኑ የሚሰሟቸው ሰዎችም የመዳንን አጋጣሚ ያገኛሉ። — 1 ጢሞ. 4:16
3 የተማረውን ከልስለት፦ ከዚህ በፊት የተማራቸውን የተወሰነ ጊዜ ካለፈ በኋላ መከለሱ ጠቃሚ የማስተማሪያ መንገድ ነው። በየጊዜው ክለሳ ማድረጉ ተማሪው በመንፈሳዊ እንዲያድግና አዲስ የተማራቸው እውነቶች በአእምሮውና በልቡ ውስጥ ጠልቀው እንዲገቡ ይረዳል። እኛ ራሳችን በመጠበቂያ ግንብ ጥናት ላይ ያሉትን የክለሳ ጥያቄዎች ስንመልስ ይህ እውነት መሆኑን አይተናል። ተማሪህ በራሱ አነጋገር የሚመልሳቸው ቀላልና ቀጥተኛ ጥያቄዎችን አዘጋጅ።
4 የምታቀርብለት የክለሳ ጥያቄ የመስክ አገልግሎት አቀራረብ ያለው ሊሆን ይችላል። ለሌሎች ስንመሠክር ብዙውን ጊዜ የሚያጋጥመንን ጥያቄ ወይም ሁኔታ አቅርብለት። አንተ እንደቤቱ ባለቤት ሁንና ተማሪህ ምን ብሎ እንደሚመልስ ያሳይ። በደንብ አድርጎ ስላቀረበ አመስግነውና ለሚቀጥለው ጊዜ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን የሚረዱትን ተግባራዊ ሐሳቦች አካፍለው። ይህ ዓይነቱ ስልጠና የተማረውን እንዴት በሥራ ላይ እንደሚያውል ያስተምረዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ የመጠቀም ችሎታውንም ያዳብርለታል።
5 ምክንያቱን ማስረዳት፦ ተማሪህ እንግሊዝኛ ማንበብ የሚችል ከሆነ ምክንያቱን ማስረዳት የተባለው መጽሐፍ አንድ ቅጂ እንዲኖረው አለዚያም ቢያንስ በአማርኛ የተተረጎመው ክፍል እንዲኖረው አድርግ። በመጽሐፉ እንዴት መጠቀም እንደሚቻል ማለትም ውይይት ለመጀመር፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችን ለመመለስና ተቃውሞ ሲያጋጥም እንዴት አድርገን መቋቋም እንዳለብን መጽሐፉ የሚያቀርባቸውን ሐሳቦች አሳየው። በጥናቱ ወቅት በሚያሳምን መንገድ ከሌሎች ጋር እንዴት መነጋገር እንደሚቻል ለማሳየት በመጽሐፉ ተጠቀም። ይህ መጽሐፍ እምነቱን ሊገነባለትና የመንግሥቱን መልእክት ለማወጅ ያለውን ፍላጎት ከፍ ሊያደርግለት ይችላል።
6 የስብሰባዎችን አስፈላጊነት አጉልተህ ግለጽ፦ የጉባኤ ስብሰባዎች በተለይም የአገልግሎት ስብሰባና ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት እኛን ለመስክ አገልግሎት ብቁ ለማድረግ በጥንቃቄ ታስቦባቸው የሚዘጋጁ ናቸው። ውጤታማ የሆነ ምሥክርነት ለመስጠት የሚያስፈልጉን መሠረታዊ ነገሮች ሁሉ ልምድና ችሎታ ባላቸው ወንድሞች በንግግርና በትዕይንት ይቀርባሉ። የስብሰባዎቹን አስፈላጊነት አጥብቀህ ግለጽለት፤ እንዲሁም በስብሰባዎቹ እንዲገኝ በምትችለው ሁሉ እርዳው። ተማሪህ አዘውትሮ በስብሰባ መገኘቱ እውነተኛ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ለመሆን የሚያስፈልገውን የልብ ግፊት ያስገኝለታል።
7 አንተ በግልህ የምታሳየው ምሳሌም ሊታሰብበት ይገባል። በስብከቱ ሥራ በፈቃደኝነት አዘውትረህ መካፈልህ ለእውነት ያለህን ጥልቅ አድናቆት ያሳያል። እንዲህ ያለው አካሄድ ተማሪህ ስለ እምነቱ በሕዝብ ፊት ለመመሥከር ይበልጥ ጥረት እንዲያደርግ ያበረታታዋል። (ሉቃስ 6:40) ይህ ሁሉ አንድ አዲስ ሰው፣ አገልግሎት መብት መሆኑን እንዲገነዘብና በዚህ ረገድ የበኩሉን ድርሻ ለማበርከት በመቻሉ አመስጋኝ እንዲሆን ያደርገዋል። — 1 ጢሞ. 1:12