ራእይ መደምደሚያው ለተባለው መጽሐፍ ጥናታችን ከፍተኛ ግምት ስጡት
1 ራእይ ታላቁ መደምደሚያው የተባለው መጽሐፍ ርዕስ ያለበት ገጽ ራእይ 1:3ን ጠቅሶ “ዘመኑ ቀርቧልና የሚያነበው የትንቢቱን ቃል የሚሰሙትና በውስጡ የተጻፈውን የሚጠብቁት ብፁዓን [ደስተኞች አዓት ] ናቸው” ይላል። በእርግጥም በዛሬው ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የራእይ መጽሐፍ ባቀፋቸው ትንቢቶች ዘመናዊ ፍጻሜ ሳቢያ የይሖዋ ሕዝቦች ደስታ በከፍተኛ መጠን ጨምሯል። በዚህ “በጌታ ቀን” እየተፈጸሙ ስላሉ ክስተቶች በአሁኑ ጊዜ ያለን መረዳት ራእይ መደምደሚያው ደርሷል! በተባለው መጽሐፍ ላይ ሰፍሯል። (ራእይ 1:10) ይህን መጽሐፍ በማጥናታችን ከፍተኛ ትርጉም ስላላቸው የዓለም ሁኔታዎች በተለይም የዓለምን የሐሰት ሃይማኖት ግዛትና ይሖዋ ከሕዝቦቹ ጋር ያደረገውን ግንኙነት ጨምሮ ብሔራት ወደ አርማጌዶን ስለሚያደርጉት ግስጋሴ ጥልቅ ማስተዋል አግኝተናል።
2 ይህን መጽሐፍ ማጥናታችን ለብዙዎቻችን ከዚህ በፊት የምናውቃቸውን ነገሮች እንድናስታውስ አእምሯችንን ከማነቃቃቱም በተጨማሪ ይሖዋ በጠላቶቹ ሁሉ ላይ ድል ወደሚያደርግበት የይሖዋ ቀን ለሚያመሩ ወቅታዊ ክስተቶች ያለንን መንፈሳዊ አመለካከት ጥልቅ ያደርግልናል። ሁላችንም ራእይ መደምደሚያው የተባለው መጽሐፍ በጉባኤ መጽሐፍ ጥናት ላይ ሲጠና እንደምንጠቀም የተረጋገጠ ነው።
3 በየሳምንቱ በደንብ ለመዘጋጀትህ፣ በጥናቱ ላይ ለመገኘትህና ትርጉም ባለው መንገድ ለመሳተፍህ እርግጠኛ ሁን። መጽሐፍህ ላይ አስምርበት፤ ልጆችህ እንዲዘጋጁ እርዳቸው። በራእይ መጽሐፍ ውስጥ በተመዘገቡት ትንቢቶች ብርሃን የዓለም ሁኔታዎችን ትርጉም ይበልጥ በግልጽ ስታስተውል ብዙ ጥቅሞችን በማግኘት ትባረካለህ። በእርግጥም ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ወቅታዊ ስለሆነ እንዲህ ዓይነቱን ትምህርት ክብደት ሰጥተነው ልንምረምረው ይገባል። ይህን ስለ ዘመናችን የተነገረውን አስደሳች ትንቢት ስናነብ፣ ስናዳምጥና ስናሰላስልበት በትንቢቱ ላይ ቃል የተገባልንን ደስታ የምናገኝ ያድርገን!