የይሖዋ ማሳሰቢያዎች በመንፈሳዊ እያነቃቁን ነውን?
1 መዝሙራዊው “ማሳሰቢያዎችህ ትዝታዎቼ ናቸው” በማለት ይሖዋን አወድሶታል። (መዝ. 119:99 አዓት) “ማሳሰቢያዎችህ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ይሖዋ በሕግጋቱ፣ በሥርዓቱ፣ በትእዛዙና ባወጣው ደንቦች ውስጥ የተገለጸውን ነገር እንደሚያስታውሰን ያሳያል። ለእነዚህ ማሳሰቢያዎች ቀና ምላሽ የምንሰጥ ከሆነ በመንፈሳዊ ከመነቃቃታችንም በተጨማሪ ደስተኛ እንሆናለን።— መዝ. 119:2 አዓት
2 የይሖዋ ሕዝቦች እንደመሆናችን መጠን ሁልጊዜ ተግሣጽና ምክር ይሰጠናል። አብዛኞቹ ከዚህ በፊት የሰማናቸው ናቸው። ምንም እንኳ ይህንን ማበረታቻ ብናደንቀውም ብዙውን ጊዜ እንረሳዋለን። (ያዕ. 1:25) ይሖዋ በትዕግሥት ፍቅራዊ ማሳሰቢያዎችን ይሰጠናል። ‘የጌታን ትእዛዝ ማስታወስ ስላለብን ቅን ልቦናችንን ለማነቃቃት’ ሐዋርያው ጴጥሮስ ከእነዚህ ማሳሰቢያዎች መካከል አንዳንዶቹን መዝግቧል።— 2 ጴጥ. 3:1, 2
3 የግል ጥናትንና በስብሰባ ላይ የመገኘትን አስፈላጊነት በተመለከተ በተደጋጋሚ ማሳሰቢያ ተሰጥቶናል። ይህ የሆነው እነዚህ እንቅስቃሴዎች ለመንፈሳዊ ደህንነታችን የግድ አስፈላጊ ስለሆኑ ነው።— 1 ጢሞ. 4:15፤ ዕብ. 10:24, 25
4 ለአንዳንዶች ከሁሉ ይበልጥ ፈታኝ የሆነባቸው ክርስቲያናዊ ተልዕኮ የሆነውን የስብከት ሥራ ማከናወን ነው። ይህ ሥራ ጥረት፣ ቆራጥነትና መንፈሰ ጠንካራነት ይጠይቃል። የስብከቱ ሥራ ብዙ ጥረት ቢጠይቅብንም እንኳ ‘እግሮቻችን የምሥራቹን ትጥቅ በመጫማት ጸንተው እንዲቆሙ’ የሚያስችል እርዳታ ተደርጎልናል።— ኤፌ 6:14, 15 አዓት
5 አገልግሎታችንን የምናከናውነው ይሖዋ ያወጣቸውን ብቃቶች በማወቃችን ብቻ መሆን የለበትም። ልባችን ‘በአፋችን መሥክረን ለመዳን’ እንድንችል የሚያስፈልገንን ግፊት እንደሚያሳድርብን ሐዋርያው ጳውሎስ አሳስቦናል። (ሮሜ 10:10) ጠንካራ እምነት ካለንና ልባችንን ለይሖዋ ማሳሰቢያዎች ክፍት ካደረግን ስሙን ለማወደስ እንገደዳለን።— መዝ. 119:36፤ ማቴ. 12:34
6 መልካም ሥራዎች ለማከናወን ጠንክረን ስንሠራ ደስታ እናገኛለን ብለን መጠበቃችን ተገቢ ነው። (መክ. 2:10) ደስታ የይሖዋ መንፈስ ፍሬ እንደሆነ ጳውሎስ ገልጿል፤ ደስታን ለማሳየት ‘ብርቱ ጥረት ማድረግ’ አለብን። (ገላ. 5:22) “ትጋት” ማሳየት ደስታ የሚሰጥ ፍሬያማ አገልግሎት እንደሚያስገኝ ጴጥሮስ ጨምሮ ገልጿል።— 2 ጴጥ. 1:5–8
7 ፈታኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ሐዋርያት “ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ዝም ማለት አንችልም” በማለት ያሳዩትን ጽኑ አቋም ማስታወስ አለብን። (ሥራ 4:20) ‘ይህንን በማድረግ ራሳችንንና የሚሰሙንን እንደምናድን’ ስናስታውስ በያዝነው ሥራ ወደፊት ለመግፋት የሚያስችለን ብርታት እናገኛለን።— 1 ጢሞ. 4:16
8 ባለማቋረጥ ማሳሰቢያዎች ሲሰጡን ብቃት የለንም ብለን አንበሳጭም ወይም ቅር አንሰኝም። ከዚህ ይልቅ እነዚህ ማሳሰቢያዎች ያላቸውን ውድ ዋጋ ከፍ አድርገን እንመለከታለን። (መዝ. 119:129) ይሖዋ በእነዚህ አስጨናቂ ጊዜያት በመንፈሳዊ እንድንነቃቃና መልካም ሥራ በመሥራት ረገድ ቀናተኞች እንድንሆን ማሳሰቢያዎች መስጠቱን በመቀጠሉ አመስጋኞች ነን!— 2 ጴጥ. 1:12, 13