የኮምፒዩተር ቴክኖሎጂን በተመለከተ ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ
1 ሐዋርያው ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩትን ክርስቲያኖች ‘የቀረው ዘመን አጭር ስለሆነ’ ሐሳባቸው እንዳይከፋፈል አሳስቧቸዋል። (1 ቆሮ. 7:29) የዚህ አሮጌ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ ስለቀረበ ‘መንግሥቱንና ጽድቁን አስቀድመን መፈለጋችንና’ ‘ጊዜ መዋጀታችን’ ምንኛ አጣዳፊ ነው! ጊዜ ውድ ነው።— ማቴ. 6:33፤ ኤፌ. 5:15, 16
2 ቴክኖሎጂ ጊዜን በእጅጉ ይቆጥባል እየተባለ ይወደሳል። ለምሳሌ አንድ የኮምፒዩተር ቁልፍ በመጫን ተጠቃሚው ሰው ከመቅጽበት በጣም ብዙ መረጃ ማግኘት ይችላል። በሌላ መንገድ ብንሠራው ብዙ ሰዓት ወይም ሳምንታት የሚወስድብንን ነገር ኮምፒዩተሮች በሴኮንዶች በሚቆጠር ጊዜ ሊሠሩት ይችላሉ። ኮምፒዩተሮች በአግባቡ ስንጠቀምባቸው ጠቃሚ መሣሪያዎች ናቸው።
3 በእርግጥ ጊዜ ይቆጥባልን?፦ በሌላ በኩል እንዲህ ያለው የቴክኖሎጂ ውጤት ተጠቃሚው ገንዘቡንና ጊዜውን በማጥፋት መሥዋዕትነት እንዲከፍል መጠየቁ አይቀርም። ኮምፒዩተሩ አንዳንድ ሥራዎችን የሚሠራው እንዴት እንደሆነ ለማወቅ ብዙ ሰዓታት ማጥፋት ሊያስፈልገን ይችላል። በተጨማሪም ለቴክኖሎጂው ፍቅር ያደረበት አንድ ሰው ለተሻለ ነገር ሊያውለው የሚችለውን ጊዜ ሊያባክን ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ ‘እንደ ጥበበኞች ዘመኑን በመዋጀት’ እንድንመላለስ በሰጠን ምክር ውስጥ ያለውን መሠረታዊ ሥርዓት በማስታወስ ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ አለብን።— 1 ቆሮንቶስ 7:31ን ተመልከት።
4 በርከት ያሉ ሰዎች በቅን ልቦና ተነሳስተው የኮምፒዩተር ፕሮግራሞችን የጉባኤ ፋይሎች ለማስቀመጥ እንደሚያመቹ አድርገው ያዘጋጅዋቸዋል። ይጠቀሙባቸዋል። እርግጥ ነው፣ አንድ ሰው በኮምፒዩተሩ የሚጠቀምበትን መንገድ የሚወስነው ራሱ ነው። ቢሆንም ልጆች ወይም ያልተፈቀደላቸው ሰዎች ፋይሎቹን መክፈት ስለሚችሉ ቅጾች የተዘጋጁላቸው የጉባኤ መዝገቦች ኮምፒዩተር ውስጥ መቀመጥ የለባቸውም። የሒሳብ መዝገብ፣ የጉባኤ የአስፋፊዎች ካርድ መዝገብና ሌሎቹም የጉባኤ መዛግብት ማኅበሩ ባዘጋጃቸው ቅጾች ላይ መሥፈር አለባቸው፤ እንዲሁም በእነዚህ የጉባኤ ቅጾች ላይ የሚገኙ መረጃዎች ኮምፒዩተር ውስጥ መግባት የለባቸውም። በዚህ መንገድ የጉባኤው መዛግብት የያዙት ምሥጢር አይባክንም።
5 ከዚህም በተጨማሪ በአንዳንድ ቦታዎች የጉባኤ ክፍሎችን ለመመደብ በኮምፒዩተር ፕሮግራሞች ይጠቀማሉ። ኃላፊነት ያለባቸው የበላይ ተመልካቾች የቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤትና የአገልግሎት ስብሰባ ፕሮግራም ክፍል ሲሰጡ አስተዋይ መሆን አለባቸው። በክፍሉ ውስጥ የሚሸፈኑትን ትምህርቶች በአእምሯቸው መያዝ ያስፈልጋቸዋል። ለምሳሌ በትምህርት ቤቱ ውስጥ አንዳንድ ክፍሎች አንዳንድ ተማሪዎችን ላይመጥኗቸው ይችላሉ። የአቀራረቡን ዓላማ እንዲሁም የግለሰቡን ብቃትና የትምህርቱን ይዘት ግምት ውስጥ ማስገባት ይገባል። ይህንን ኮምፒዩተሩ እንዲወስነው ማድረግ አይገባም።
6 በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ክፍል ያለው አንድ ወንድም የሚያቀርበው ክፍል በአንድ የኮምፒዩተር ኔትዎርክ ውስጥ ስለሚገኝና በዚህ መጠቀሙ ሥራውን ስለሚያቃልለት ብቻ በሌላ ሰው በተለይም በማያውቀው በሌላ ግለሰብ የተዘጋጀ ጽሑፍ መጠቀም የለበትም። ኃላፊነት የሚሰማቸው ክርስቲያኖች የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግሮችን ወይም በስብሰባ ላይ የሚቀርቡትን ክፍሎች ከተዘጋጁ በኋላ ሌሎች እንዲጠቀሙበት በኮምፒዩተር ኔትዎርክ ውስጥ ትተውት አይሄዱም። ነገር ግን ኮምፒዩተርና ማኅበሩ በሲዲ–ሮም ላይ ያዘጋጀው የመጠበቂያ ግንብ ቤተ መጻሕፍት በግል ያላቸው ወንድሞች በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ ምርምር ለማድረግ የሚችሉባቸው ዋጋማ መሣሪያዎች ይሆኑላቸዋል።
7 የኮምፒዩተር ፕሮግራሞችን፣ ዝርዝር መግለጫዎችንና የመሳሰሉትን መረጃዎች እንደገና ከማዘጋጀትና ለወንድሞች ከማሰራጨት እንዲሁም የአገልግሎት ስብሰባና የቲኦክራሲያዊ አገልግሎት ትምህርት ቤት ክፍሎችን በኤሌክትሮኒክ ወይም በሌላ መንገድ አዘጋጅቶ ከማሰራጨት ይልቅ ወንድሞች ክፍላቸውን ለጉባኤያቸው እንደሚጠቅም አድርገው ራሳቸው ቢዘጋጁ የተሻለ ነው። (1 ጢሞ. 4:13, 15) ከጉባኤ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በማንኛውም መንገድ የገንዘብ ማግኛ መሆን የለባቸውም።
8 በመጠበቂያ ግንብ ጥናት ወይም በጉባኤ መጽሐፍ ጥናት ላይ የተጠቀሱ ጥቅሶችን ከኮምፒዩተር በማውጣት ወረቀት ላይ አትሞ ስለማሰራጨት ምን ሊባል ይቻላል? አስፋፊዎች በመጽሐፍ ቅዱሳቸውና እየተጠና ባለው ጽሑፍ ላይ የራሳቸውን ማስታወሻዎችና ምልክቶች ቢያደርጉ ይመረጣል። በስብሰባ ወቅት በጽሑፉ ላይ ምዕራፋቸውና ቁጥራቸው ብቻ የተጻፉትን ጥቅሶች ከኮምፒዩተር ወጥተው ወረቀት ላይ በታተሙ ጥቅሶች የምንከታተል ከሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጥቅሶች እያወጣን እንዳንመለከት ሊያሰንፈን ይችላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ወቅት ወይም በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ጥቅሶችን እያወጡ መመልከት ከምናገኛቸው ሥልጠናዎች መካከል አንዱ ነው። እንዲህ ማድረጋችን በመስክ አገልግሎት ላይ መጽሐፍ ቅዱስን ጥሩ አድርገን ለመጠቀም ያስችለናል። ብዙውን ጊዜ በተለይ ጥቅሶቹ ረጃጅም ሲሆኑና አዳማጮች መጽሐፍ ቅዱስ አውጥተው እንዲከታተሉ ሐሳብ ሲቀርብላቸው ቀጥታ ከመጽሐፍ ቅዱስ ማንበቡ ይበልጥ ጠቃሚ ነው።
9 ሌሎች አሳሳቢ ወጥመዶች፦ በነሐሴ 1, 1993 መጠበቂያ ግንብ እትም ገጽ 17 ላይ እንደተገለጸው ኮምፒዩተርን ከኤሌክትሮኒክ የመጽሔት ዓምድ ጋር ማያያዝ ከባድ መንፈሳዊ አደጋዎችን ያስከትላል። አንድ ተንኮለኛ ሰው በመጽሔት ዓምድ ላይ ቫይረስ ማለትም የኮምፒዩተር ፋይሎችን ለማበላሸትና ለማጥፋት የተዘጋጀ ፕሮግራም ማስገባት እንደሚችል ሁሉ ከሃዲዎች፣ ቀሳውስትና ሌሎችን በሥነ ምግባር ወይም በሌላ መንገድ ለማበላሸት የሚፈልጉ ሰዎች መርዘኛ ሐሳቦቻቸውን ያለምንም ችግር በኤሌክትሮኒኩ መጽሔት ዓምዶቹ ውስጥ ማስገባት ይችላሉ። ሌላው ቀርቶ “ለይሖዋ ምሥክሮች ብቻ” የሚል ኤሌክትሮኒክ የመጽሔት ዓምድ እንኳ የጎለመሱ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ብቻ እንዲጠቀሙበት በማድረግ ተገቢው ቁጥጥር ካልተደረገ በስተቀር በዚህ የሚጠቀሙ ክርስቲያኖችን ‘ለመጥፎ ባልንጀርነት’ ሊያጋልጣቸው ይችላል። (1 ቆሮ. 15:33) እንደዚህ ያሉ የግል ኔትዎርክ ግንኙነቶች መንፈሳዊ ጉዳዮች ላይ ከማተኮር አልፈው መጥፎ ምክር ለመስጠት ሐሜትንና የሐሰት መረጃዎችን ለማሰራጨት፣ አፍራሽ አስተሳሰቦችን ለመንዛት፣ የአንዳንዶችን እምነት የሚያዳክሙ ጥያቄዎችንና ጥርጣሬዎችን ለማነሳሳት እንዲሁም አንዳንድ ጥቅሶችን በራሳቸው አባባል በመተርጎም ለማሰራጨት ጥቅም ላይ እንደዋሉ ማኅበሩ ሪፖርት ደርሶታል። አንዳንዶቹ መረጃዎች ከውጪ ሲታዩ የሚያስደስቱና እውቀት የሚጨምሩ መስለው ቢታዩም በመርዝ የተቀመሙ ሊሆኑ ይችላል። ክርስቲያኖች በሰዓቱ የሚቀርብ መንፈሳዊ ምግብና ማብራሪያ የሚጠባበቁት ‘ከታማኝና ልባም ባሪያ’ ነው። (የሐምሌ 1, 1994 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 9–11 ተመልከት።) አንድ ክርስቲያን መጥፎ ተጽእኖ በማሳደር እምነቱን ከሚያበላሹ ነገሮች ራሱን የመጠበቅ ከባድ ኃላፊነት አለበት። ይህን ለማድረግ ደግሞ ጊዜውን የሚያሳልፈው ከእነማን ጋር እንደሆነ ማወቁ ወሳኝ ነው።— ማቴ. 24:45–47፤ 2 ዮሐ. 10, 11
10 ይኸው የመጠበቂያ ግንብ ርዕስ የቅጂን መብት አስመልክቶ የወጡትን ሕጎች የማክበርን አስፈላጊነት ጠበቅ አድርጎ ይገልጻል። የኮምፒዩተር ፕሮግራሞችን የሚያዘጋጁና የሚሸጡ አብዛኞቹ ኩባንያዎች ሕጋዊ የሆነ የቅጂ መብት ያላቸው ሲሆን በፕሮግራሙ ሕጋዊ በሆነ መንገድ መጠቀም የሚቻለው እንዴት እንደሆነ የሚገልጽ የምሥክር ወረቀት ያዘጋጃሉ። ብዙውን ጊዜ የምሥክር ወረቀቱ ባለንብረቱ የፕሮግራሙን ቅጂ ለሌላ ሰው መስጠት እንደማይችል ይገልጻል፤ እንዲያውም ዓለም አቀፍ የቅጂ መብት ሕግ እንዲህ ማድረጉ ሕጋዊ እንዳልሆነ ይገልጻል። ብዙዎቹ ስግብግብ ሰዎች ይህን ሕግ መጣስ ከባድ ነገር ሆኖ አይታያቸውም። ክርስቲያኖች ግን የቄሣርን ለቄሣር በመስጠት በሕጋዊ ጉዳዮች ጠንቃቆች መሆን አለባቸው።— ማቴ. 22:21፤ ሮሜ 13:1
11 አንዳንድ ትልልቅ ኩባንያዎች የምሥክር ወረቀት ያላቸው ፕሮግራሞች በውስጣቸው የያዙ ኮምፒዩተሮች ይሸጣሉ። ነገር ግን አንዳንድ የኮምፒዩተር ሱቆች ኮምፒዩተሩ ውስጥ ያስገቡት ፕሮግራም ሕጋዊ ስላልሆነ የምሥክር ወረቀት አያዘጋጁም። የገዛው ሰው በፕሮግራሞቹ ሲጠቀም ሕግን እየተላለፈ ነው ማለት ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ መልኩ ክርስቲያኖች የቅጂ መብታቸው የተጠበቀና (እንደ ማኅበሩ ጽሑፎች) ያለባለቤቶቹ ሕጋዊ ፈቃድ የሚባዙ ኤሌክትሮኒክ የመጽሔት ዓምዶች ላይ የሚወጡ ጽሑፎችን ወደ ኮምፒዩተራቸው ማስገባት ወይም ማዘዋወር የለባቸውም።— ዕብ. 13:18
12 ማንኛውም የቴክኖሎጂ ውጤት የሚሰጠው ጥቅም አገልግሎት ላይ ሲውል ከሚያስከትላቸው ጉዳቶች አንጻር ሊመዘን ይገባል። ቴሌቪዥን ጥሩ አገልግሎት ሊሰጥ ቢችልም በሰው ዘር ላይ ያስከተለው መጥፎ ውጤት ዓለማውያን እንኳ በጣም እንዳሳሰባቸው እንዲገልጹ አድርጓቸዋል። የኮምፒዩተር ኔትዎርክ በዓለም ዙሪያ ስለተስፋፋ ቁጥር ስፍር የሌላቸውን ጠቃሚ መረጃዎች ወደ መኖሪያ ቤት ወይም ወደ መሥሪያ ቤት ሊያመጣ ይችላል። የግል ጉዳዮቻቸውንና ንግዳቸውን ካለንበት በሥራ የሚዋከብ ዓለም ጋር እኩል ማራመድ ለሚፈልጉ ኩባንያዎችና ድርጅቶች እንዲሁም ግለሰቦች ኮምፒዩተሮች ብዙ አስፈላጊ የሆኑ አገልግሎቶችን ይሰጣሉ። በሌላ በኩል የኮምፒዩተር ኔትዎርክ አገልግሎቶች የብልግና ሥዕሎችን፣ መከፋፈልን የሚያመጣ የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ እንዲሁም ብልግናና መጥፎ ተግባራትን እንዴት መፈጸም እንደሚቻል የሚያሳዩ ዝርዝር መረጃዎች የመሳሰሉ ነገሮችን በገፍ በማቅረብ ችግር ይፈጥሩብናል።
13 ስለዚህ አንድ ክርስቲያን በኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ ረገድ ሚዛናዊ የሆነ አመለካከት ለመያዝ የሚገደድባቸው ብዙ አንገብጋቢ ምክንያቶች አሉ። ብዙ ሰዎች ማኅበሩ በኮምፒዩተር ዲስኬቶች ባዘጋጃቸው በአዲሲቱ ዓለም ትርጉም፣ ጠለቅ ብሎ ማስተዋል በተባለው መጽሐፍ ጥራዞችና በጥቅስ ማውጫ ፕሮግራም ይጠቀማሉ። ሌሎች ደግሞ ማኅበሩ በሲዲ–ሮም ባዘጋጀው ተጨማሪ ምርምር ለማድረግ ከሚያስችለው የመጠበቂያ ግንብ ቤተ መጻሕፍት ጥቅም አግኝተዋል። እንደነዚህ ያሉትን ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለጥሩ ዓላማ የሚገለገልባቸው ሰው አንድ ዓይነት የቴክኖሎጂ ውጤት ጠቃሚ መሆኑን ቢገነዘብም ካሉት መጥፎ ገጽታዎች ራሱንና ሌሎችን በንቃት መጠበቅ አለበት። የኮምፒዩተር ቴክኖሎጂውን ጉዳት በሌለው መንገድ የምንጠቀምበት ቢሆንም እንኳ ውድ ጊዜያችንን እንዳይወስድብን ወይም ከዋነኛው ሥራችንና ግባችን ወደ ኋላ እንዳያደርገን ሚዛናዊ መሆን ያስፈልገናል።— ማቴ. 6:22፤ 28:19, 20