በላይ ያለውን አስቡ
1 በታኅሣሥ 31, 1994 ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ እትም ላይ የወጣ አንድ ርዕስ በአሁኑ ጊዜ ስላለው ትውልድና ይህ ትውልድ ስለወደፊቱ ጊዜ ስላለው አመለካከት ሲናገር እንዲህ ብሎ ነበር:- “ሰዎች ወደፊት ምን ይመጣ ይሆን ብለው ይፈራሉ። ሥራን በተመለከተ፣ በሽታን በተመለከተ፣ የኢኮኖሚ ሁኔታን በተመለከተ የዓለምን ሁኔታ በተመለከተ የወደፊቱ ጊዜ ያስፈራቸዋል።” በየትኛውም አቅጣጫ ስንመለከት ሰዎች ሕይወት ዋስትና እንደሌለው ይሰማቸዋል። የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን አገልግሎታችን እንደዚህ ዓይነት ስሜት ከሚሰማቸው ሰዎች ጋር በየዕለቱ ያገናኘናል። እነርሱን የሚያጋጥሟቸው ችግሮች በእኛም ላይ የሚደርሱ ቢሆንም የአምላክ ቃል በሚሰጣቸው አስተማማኝ ተስፋዎች ላይ ያለን እምነትና ትምክህት ሕይወትንና የሰዎችን የወደፊት ዕጣ ፋንታ በተመለከተ ከእነርሱ በጣም የተለየ አመለካከት እንዲኖረን አስችሎናል።— ኢሳ. 65:13, 14, 17
2 ብዙ ልበ ቅን ሰዎች ስለ ወደፊቱ ጊዜ ብሩኅ አመለካከት መያዛችንና ባለን ተስፋ ላይ እምነት ያለን መሆናችን የምንነግራቸውን መልእክት እንዲቀበሉ ያደርጋቸዋል። የመንፈስ ጭንቀት የሚሰማቸውና ጭቆና የደረሰባቸው ብዙ ሰዎች ከእኛ ጋር መነጋገሩ ያጽናናቸዋል። አንዳንዶቹ የሚሰሙት ነገር ስለሚያስደስታቸው አብረውን መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ይስማማሉ። አንዳንድ ጊዜ ግን በመጀመሪያ የግል ችግሮቻቸውን አውጥተው መናገር ይፈልጋሉ። ጥቂት ጊዜ ወስደን ያስጨነቋቸውን ነገሮች ማዳመጥ ብንችልም ዋናው ዓላማችን በአምላክ ቃል ውስጥ ያለውን አስተማማኝ እውነት ለሰዎች ማስተማር መሆኑን መዘንጋት የለብንም።
3 ሸክማቸው የከበደባቸው ሰዎች ያለባቸው ችግር የሚገባን መሆን አለብን። ኢየሱስ በማቴዎስ 11:28 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደ እኔ ኑ” ብሎ በተናገረ ጊዜ ምሳሌ ትቶልናል። እኛም በዚህ ዓይነት ሁኔታ ሰዎችን ማበረታታት አለብን። ነገር ግን ኢየሱስ በቁጥር 28 መደምደሚያ ላይ “እኔም አሳርፋችኋለሁ” በማለት የተናገረውን ልብ በል። ግባችን ይህ መሆን አለበት። በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን መንፈስን የሚያድስ ተስፋ ለሰዎች በማካፈል ይህንን እናከናውናለን። ጥሩ አድማጭ መሆናችን አሳቢና ለሰዎች የምንጨነቅ እንደሆንን ከማሳየቱም በላይ የመንግሥቱን ምሥራች የመስበክና የአምላክ መንግሥት የሰው ልጆች ላሉባቸው ችግሮች ሁሉ እውነተኛ መፍትሄ እንደሆነ ሰዎች እንዲገነዘቡ የመርዳት ተልእኳችንን ለመፈጸም አስፈላጊ ነው።— ማቴ. 24:14
4 ሥራችን ከጤና ባለሙያዎች ሥራ የተለየ ነው። የእኛ ሥራ ሐዋርያው ጳውሎስ በ1 ጢሞቴዎስ 4:6 ላይ በገለጸው “መልካም ትምህርት” ይኸውም በአምላክ ቃል ውስጥ በሚገኘው ትምህርት ላይ ያተኮረ አገልግሎት ነው። የግል ወይም ስሜታዊ ችግሮች ያሉባቸው ሰዎች በይሖዋ ላይ እንዲደገፉ ልናበረታታቸው ያስፈልጋል። “በላይ ያለውን” ማለትም ከመንግሥቱ ተስፋ ጋር የተያያዙ ነገሮችን ‘እንዲያስቡ’ አስተምራቸው። (ቆላ. 3:2) ሰዎች በአምላክ ቃል ላይ ሲያተኩሩ የአምላክ ቃል በሕይወታቸው ውስጥ በሚያሳድረው ኃይለኛ ተጽዕኖ የተነሳ መንፈሳቸው ሊያንሰራራ ይችላል።— ዕብ. 4:12
5 ስለዚህ ግባችን ሰዎች ‘ጽድቅ፣ ንጽሕና፣ ፍቅርና ምስጋና’ ያለበትን ነገር እንዲያስቡ መርዳት ነው። (ፊልጵ. 4:8) በመንግሥቱ ተስፋ ላይ የሚያተኩሩ ከሆነ እኛ እንደተባረክነው እነርሱም ይባረካሉ። ይሖዋ በመንግሥቱ አማካኝነት ያሉባቸውን ችግሮች በጠቅላላ እንደሚፈታላቸው በማወቅ የሚገኘውን ደስታ ይቀምሳሉ።— መዝ. 145:16