ዕለት ዕለት እእለታችንን መፈጸም
1 መዝሙራዊው ዳዊት “ለስምህ ለዘላለም እዘምራለሁ ስእለቴን ሁልጊዜ እፈጽም ዘንድ” በማለት ለይሖዋ ለመናገር ተገፋፍቷል። (መዝ. 61:8) ዳዊት ስእለት በፈቃደኝነት የሚከናወን ነገር እንደሆነ ያውቅ ነበር። አንድ ጊዜ ከተሳለ በኋላ ግን ስእለቱን የመፈጸም ግዴታ እንዳለበት ተገንዝቧል። (መክ. 5:4-6) ቢሆንም ስእለቱን ዕለት ዕለት ለመፈጸም የሚያስችል አጋጣሚ በማግኘቱ ይሖዋን አመስግኗል።
2 ራሳችንን ለይሖዋ ስንወስን ፈቃዱን ለማድረግ በፈቃደኝነት ተስለናል። ራሳችንን ከካድን በኋላ በሕይወታችን ውስጥ በአንደኛ ደረጃ የምንከታተለው ጉዳይ ይሖዋን ማገልገል ሆኗል። (ሉቃስ 9:23) ስለዚህ እኛም ስእለታችንን ዕለት ዕለት መፈጸም አለብን። (ማቴ. 5:37) በውኃ ስንጠመቅ በሕዝብ ፊት ያሳየነው ውሳኔ በጠቅላላው አኗኗራችን መንጸባረቅ ይኖርበታል፤ ምክንያቱም ‘ሰው ለመዳን ሕዝባዊ ምሥክርነት መስጠት እንዳለበት እናውቃለን።’ (ሮሜ 10:10) ይህም ምሥራቹን መስበክን ይጨምራል። (ዕብ. 13:15) የግል ሁኔታዎች በጣም የተለያዩ ሊሆኑ ቢችሉም ሁላችንም ምሥራቹን ለሌሎች ሰዎች የማካፈሉን አስፈላጊነት ዕለት ዕለት ትኩረት ልንሰጠው እንችላለን።
3 በየቀኑ ለመስበክ የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ፍጠሩ፦ ምሥራቹን ለሌላ ሰው ማካፈል ያስደስታል። ይህንንም በየቀኑ ለማከናወን እንድንችል ሁኔታዎቻችን በፈቀዱልን በማንኛውም ጊዜ ለመስበክ የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን መፍጠር አለብን። በትምህርት ቤት፣ በጎረቤት ወይም በየቀኑ በአጋጣሚ ለሚያገኟቸው ሰዎች መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለመመሥከር ራሳቸው ቀዳሚ ሆነው ውይይት በመጀመራቸው ብዙ አስደሳች ተሞክሮዎችን አግኝተዋል። ደብዳቤ መጻፍ ወይም ስልክ መደወል እንኳ ለሌሎች ለመመሥከር የሚያስችሉ መንገዶች ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህ መንገዶችና ዘወትር ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው ምሥክርነት ለመካፈልና ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ ጊዜ መመደብ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በመምራት ወደሚገኘው ልዩ ደስታ ሊመሩ ይችላሉ። አዎን፣ በየቀኑ ለመስበክ የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ልንፈጥር እንችላለን።
4 አንዲት እህት በሥራ ቦታዋ ባላት የእረፍት ሰዓት ቅዱሳን ጽሑፎችን በየዕለቱ መመርመር የተሰኘውን ቡክሌት ማንበብ ጀመረች። የዕለቱን ጥቅስ አብራት እንድታነብ አንዲት የሥራ ባልደረባዋን ጋበዘቻት። ይህም ብዙም ሳይቆይ ከሴትዮዋ ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመር የሚያስችል መንገድ ከፈተ። በሳምንት ባሉት አምስት ቀናት በየቀኑ ለግማሽ ሰዓታት አጠኑ። ሌላ የሥራ ባልደረባቸው በየቀኑ ሲያጠኑ ተመለከተ። እርሱም አገልግሎት ያቆመ ወንድም መሆኑን ገለጸላት። እህት ባሳየችው ቅንዓት ተነሳስቶ እንደገና አገልግሎት ለመጀመር ከአንድ ሽማግሌ ጋር ተነጋገረ። ይህች እህት ስእለቷን ዕለት ዕለት ለመፈጸም ባደረገችው ጥረት በሌሎች ሁለት ሰዎች ሕይወት ላይ በጎ የሆነ ተጽዕኖ አሳድራለች።
5 ልባችን ይሖዋ ላደረገልን መልካም ነገሮች ባለን አድናቆት ሲሞላ ራሳችንን ስንወስን የገባነውን ስእለት ለመፈጸም በየቀኑ የምናደርገው ጥረት ደስታና እርካታ ያስገኝልናል። እንደ መዝሙራዊው “አቤቱ አምላኬ ሆይ፣ በልቤ ሁሉ አመሰግንሃለሁ፣ ለዘላለምም ስምህን አከብራለሁ” ልንል እንችላለን።— መዝ. 86:12