የትምህርት ቤት ሕይወታችሁን በተሻለ መንገድ ተጠቀሙበት
1 ይህ ወቅት ብዙ ወጣቶች “ትምህርት የሚጀመርበት ጊዜ ደረሰ ማለት ነው?” ብለው የሚጠይቁበት ጊዜ ነው። ትምህርት ከመጀመሩ ጋር የተያያዙ አንዳንድ ፈታኝና የሚያስጨንቁ ነገሮች ቢኖሩም የሚያገኙትን ትምህርት በተሻለ መንገድ ለመጠቀም የሚፈልጉ ወጣቶች ብዙ ጥቅሞችን ሊያገኙ ይችላሉ።
2 ጥሩ መሠረታዊ የሆነ ትምህርት ለአንድ ሰው መንፈሳዊ እድገት አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይችላል። አንድ ሰው በወጣትነት ዘመኑ የሚያደርገው ነገር አዋቂ በሚሆንበት ጊዜ ሊያከናውን በሚችለው ነገር ረገድ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል። “ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና” የሚለው ጥቅስ በትምህርት መስክም ይሠራል። (ገላ. 6:7) ወጣቶች በትምህርት ቤት የሚሰጧቸውን ትምህርቶች በትጋት የሚያጠኑ ከሆነ በይሖዋ አገልግሎት ይበልጥ ጠቃሚ እንዲሆኑ የሚረዳቸውን ችሎታ ሊያዳብሩ ይችላሉ።
3 የምንከታተላቸውን ትምህርቶች በትክክል ለመምረጥ ጥንቃቄ የተሞላበት እቅድ ያስፈልጋል። ወላጆች ልጆቻቸው ከሁሉ የተሻለ ተግባራዊ ስልጠና የሚያገኙበትንና በሕይወታቸው ውስጥ መንፈሳዊ ግቦችን እንዲጨብጡ የሚያስችሏቸውን ትምህርቶች እንዲመርጡ ሊረዷቸው ይገባል። ወጣቶች ችሎታቸውን ማዳበራቸው አቅኚ ሆነው በሚያገለግሉበት ጊዜ ራሳቸውን በገንዘብ ለመርዳት ያስችላቸዋል። ያገኙት መሠረታዊ ትምህርት በማንኛውም ቦታ ቢያገለግሉ ይሖዋን ለማወደስ ሊረዳቸው ይገባል።
4 ወጣቶች ሆይ በትምህርት ቤት የምታሳልፏቸውን ዓመታት በተሻለ መንገድ ለመጠቀም ሞክሩ። ይህንንም ስታደርጉ ትኩረታችሁ በቅዱስ አገልግሎት ለመጠመድ እንጂ ዓለማዊ ሥራ ለማሳደድ አይሁን። ሕይወታችሁን የይሖዋን ፈቃድ በማድረግ ለመጠቀም ተጣጣሩ። እንዲህ ካደረጋችሁ ሥራችሁ ለይሖዋ ክብር በሚያመጣ መንገድ ይከናወንላችኋል።—መዝ. 1:3