“ሰዎች ሁሉ እርስ በእርሳቸው የሚዋደዱበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?”
1 በቅርቡ ማራኪ፣ ቀስቃሽና አስደሳች የሆነ መልእክት በዓለም አቀፍ ደረጃ በ169 ቋንቋዎች ይታወጃል። መልእክቱ ምንድን ነው? እንዴትስ ይሰራጫል?
2 መልእክቱ ስለ ጎረቤት ፍቅር የሚገልጽ ነው። “ሰዎች ሁሉ እርስ በእርሳቸው የሚዋደዱበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?” የሚል ርዕስ ባለው የመንግሥት ዜና ቁ. 35 ላይ የሚገኝ ይሆናል። ይህ የመንግሥት ዜና በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ ያለው ሁኔታ ምን እንደሚመስል በመመርመር በአሁኑ ጊዜ በሰፊው ተንሰራፍቶ ለሚገኘው ሐዘንና ሥቃይ ዋነኛ መንስኤ በሰዎች ዘንድ ፍቅር መጥፋቱ እንደሆነ ይገልጻል። ትራክቱ በተለይ በዚህ እኛ ባለንበት ዘመን ባሉ ሰዎች መካከል የጎረቤት ፍቅር የቀዘቀዘበት ምክንያት ምን እንደሆነና ይህም ለወደፊቱ ጊዜ ምን ትርጉም እንደያዘ ያብራራል።
3 በሌላ በኩል ደግሞ ይሄው የመንግሥት ዜና ቁ. 35 በአሁኑ ጊዜ ባለው ዓለም ውስጥ የሚኖሩ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እውነተኛ የጎረቤት ፍቅር እንዳላቸው ይገልጻል። ኢየሱስ ክርስቶስ ባስተማረው መሠረት ለጎረቤት ፍቅር በማሳየት ተለይቶ የሚታወቀው የመጀመሪያው መቶ ዘመን አምልኮ ማለትም የጥንቱ ክርስትና መልሶ እንዲያንሰራራ ጥረት በማድረግ ላይ ያሉ ሰዎች ተለይተው የሚታወቁት በዚህ ፍቅር ነው።—ሉቃስ 10:25-37
4 የመንግሥት ዜና ቁ. 35 በክርስቶስ በሚተዳደረው የአምላክ መንግሥት ሥር መላው የሰው ዘር ዓለም በቅርቡ የጎረቤት ፍቅርን በሥራ ላይ የሚያውልበትን መንገድ በማብራራት ይደመድማል። ይህንን መልእክት የሚያነቡ ሁሉ አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የተባለውን ብሮሹር እንዲያገኙና በአምላክ ቃል ውስጥ በዝርዝር እንደተገለጸው የዚህ ምድር አቀፍ ፍቅራዊ ዝግጅት ክፍል መሆን እንዴት እንደሚችሉ እንዲማሩ ይበረታታሉ።
5 ይህን መልእክት ለሰዎች የሚያደርሰው ማን ነው? በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ስለ ጎረቤት ፍቅር የሚናገረውን ይህን መልእክት በጥቅምትና በኅዳር ወራት ለሚያውቋቸው ሰዎች፣ ለጎረቤቶቻቸውና ለዘመዶቻቸው ያካፍላሉ። በዚህ ዘመቻ መሳተፍ የሚችሉ ሁሉ የመንግሥት ዜና ቁ. 35ን እንዲያሰራጩ እናበረታታቸዋለን።
6 የዚህ ዘመቻ ዋና ዓላማ አምላክ ከእኛ የሚፈልገው በተባለው ብሮሹር ወይም እውቀት በተባለው መጽሐፍ አማካኝነት መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠኑ የሰዎችን ፍላጎት መቀስቀስ ነው። ከዚህም በተጨማሪ እያንዳንዱ የይሖዋ አገልጋይ በሙሉ ልብ የሚያደርገው ጥረት የፍቅር አምላክ ለሆነው ለይሖዋና ለልጁ ለኢየሱስ ክርስቶስ ታላቅ ምሥክርነት ያሰጣል።