አገልግሎታችን የእውነተኛ ፍቅር መግለጫ ነው
1 ከሁሉም የሚበልጡትን ሁለቱን ትእዛዞች እየፈጸምን መሆናችንን የምናሳየው በአገልግሎታችን ነው። (ማቴ. 22:37-39) ለይሖዋ ያለን ፍቅር ስለ እሱ ጥሩነት እንድንናገር ይገፋፋናል። ለሰዎች ያለን ፍቅር ስለ አምላክ ፈቃድና ዓላማ ለማወቅ ፍላጎት እንዲያድርባቸው ሰዎችን ለማነሳሳት ያንቀሳቅሰናል። ይህ ደግሞ እነሱም እንደ እኛ ይሖዋን የሚወዱና ለዘላለም ሕይወት ሽልማት የሚበቁ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል። ስለዚህ በአገልገሎታችን የይሖዋን ስም እናስከብራለን እንዲሁም እጅግ ውድ የሆነውን የመንግሥቱን ተስፋ ለሰዎች እናበስራለን። አዎን፣ አገልግሎታችን ለአምላክና ለሰዎች ያለንን እውነተኛ ፍቅር የምንገልጽበት መንገድ ነው።
2 ይህ ፍቅር ሁሉንም ሰዎች በማንኛውም ቦታና አጋጣሚ እንድናነጋግር ግድ ይለናል። (1 ቆሮ. 9:21-23) ለምሳሌ ያህል:- አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ በአውሮፕላን ሲጓዝ ከአንድ የካቶሊክ ቄስ አጠገብ ተቀምጦ ነበር። ይህ ሽማግሌ በጥበብ አንዳንድ ጥያቄዎች በመጠየቅ ከቄሱ ጋር ውይይት ከጀመረ በኋላ የውይይቱን ርዕስ ወደ መንግሥቱ መልእክት ቀየረው። ቄሱ ከአውሮፕላኑ የመውረጃው ጊዜ ሲደርስ ሁለት መጻሕፍት ተቀበለ። ይህ ሽማግሌ ለሰዎች ላሳየው እውነተኛ ፍቅር እንዴት ያለ መልካም ውጤት አግኝቷል!
3 እውነተኛ ፍቅር እንድንሰብክ ይገፋፋናል፦ ረዳት አቅኚና የሙሉ ጊዜ አቅኚ በመሆን የሚያገለግሉ ወንድሞችና እህቶች በእርግጥም ለአምላክና ለሰዎች ያላቸውን እውነተኛ ፍቅር እየገለጹ ነው። አቅኚዎች ሌሎች ሰዎችን በመንፈሳዊ ለመርዳት ሲሉ ያለማቋረጥ ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን መሥዋዕት ያደርጋሉ። እንዲህ እንዲያደርጉ የገፋፋቸው ምንድን ነው? አንዲት አቅኚ እንዲህ ስትል ተናግራለች:- “ፍቅር የአምላክ መንፈስ ፍሬ እንደሆነ አውቃለሁ። ስለዚህ ፍቅር ባይኖረኝ እንኳን አቅኚ ልሆን ይቅርና በእውነት ውስጥ አልገኝም ነበር። ፍቅር ለሰዎች እንዳስብና ስለሚያስፈልጋቸው ነገር ንቁ እንድሆን ያደርገኛል፤ ሰዎች ደግሞ ፍቅር ሲያሳዩአቸው አዎንታዊ ምላሽ እንደሚሰጡ አውቃለሁ።” ኢየሱስ እንዲህ ዓይነቱን ፍቅር ለሰዎች አሳይቷል። በአንድ ወቅት እሱና ደክሟቸው የነበሩት ደቀ መዛሙርቱ ወደ አንድ ቦታ ‘ጥቂት ለማረፍ’ ሲሄዱ፣ በቦታው ብዙ ሕዝብ ቀድሟቸው ተገኘ። ኢየሱስ ምን አደረገ? ‘ስለ አዘነላቸው እነሱን ለማስተማር ሲል’ ለራሱ ያስፈልገው የነበረውን ነገር መተው መርጧል።—ማር. 6:30-34
4 ሰዎች ለምሥራቹ ጥሩ ምላሽ ባይሰጡም እንኳ መዳን እንዲያገኙ በፍቅር ተነሳስተን የተቻለንን ሁሉ እንዳደረግን ስለምናውቅ ውስጣዊ እርካታ እናገኛለን። ሁላችንም በክርስቶስ ፊት በምንቀርብበት ጊዜ ‘አገልግሎታችንን በተሟላ ሁኔታ በመፈጸም’ እውነተኛ ፍቅር በማሳየታችን እጅግ እንደሰታለን።—2 ጢሞ. 4:5