ለስብሰባዎች ‘ከበፊቱ የበለጠ’ ትኩረት ስጡ
1 ስብሰባዎች ለይሖዋ ሕዝቦች ትልቅ አስተዋጽኦ ሲያበረክቱ ቆይተዋል። እስራኤላውያን ቤተ መቅደሱንና ምኩራቦቻቸውን ለእውነተኛ አምልኮ፣ ለመለኮታዊ ትምህርትና አስደሳች ለሆነ ኅብረት ማዕከል አድርገው ይጠቀሙባቸው ነበር። በተመሳሳይም የጥንት ክርስቲያኖች አንድ ላይ ይሰበሰቡ ነበር። በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ተጽእኖዎችና አስቸጋሪ ሁኔታዎች እየጨመሩ በሄዱ መጠን እኛም ብንሆን በጉባኤ ስብሰባዎቻችን አማካኝነት የሚቀርቡልን መንፈሳዊ ማበረታቻዎች ‘በይበልጥ’ ያስፈልጉናል። (ዕብ. 10:25) በስብሰባዎች ላይ የምንገኝባቸውን ሦስት ምክንታቶች ተመልከቱ።
2 ከወንድሞችና እህቶች ጋር ለመቀራረብ፦ ቅዱስ ጽሑፉ “እርስ በርሳችሁ ተመካከሩ አንዱም አንዱም ሌላውን ያንጸው” በማለት ያሳስበናል። (1 ተሰ. 5:11) ለአምላክ ካደሩ ሰዎች ጋር መቀራረባችን አእምሮአችን ጥሩ ጥሩ በሆኑ ሐሳቦች እንዲሞላና መልካም ተግባር ለመፈጸም እንድንነሳሳ ያደርገናል። ይሁን እንጂ ራሳችንን ካገለልን የቂልነት፣ የራስ ወዳድነትና አልፎ ተርፎም የብልግና ሐሳቦች ማውጠንጠናችን የማይቀር ነው።—ምሳሌ 18:1
3 ትምህርት ለማግኘት፦ ለአምላክ ያለን ፍቅር ሕያው ሆኖ በልባችን ውስጥ እንዲቀጥል ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች የማያቋርጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ፕሮግራም ያቀርቡልናል። ስብሰባዎች “የእግዚአብሔርን ምክር ሁሉ” በሥራ ላይ በማዋል ረገድ ተግባራዊ የሆነ መመሪያ ይሰጣሉ። (ሥራ 20:27) ስብሰባዎች ምሥራቹን የመስበክና የማስተማር ችሎታችንን እንድናዳብር ይረዱናል። ይህ ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የሚቀበሉ ሰዎችን ፈልጎ በመርዳቱ ሥራ ወደር የሌለው ደስታ እንድናገኝ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ ነው።
4 ጥበቃ ለማግኘት፦ በዚህ ክፉ ዓለም ውስጥ ጉባኤዎች ሰላምና ፍቅር የሰፈነባቸው እውነተኛ መንፈሳዊ መሸሸጊያ ናቸው። በጉባኤ ስብሰባዎች ስንገኝ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ በእኛ ላይ ኃይለኛ ተጽእኖ ስለሚያሳድርብን የመንፈስ ፍሬ የሆኑትን “ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ እምነት፣ የውሃት፣ ራስን መግዛት” እንድናፈራ ያደርገናል። (ገላ. 5:22, 23) ስብሰባዎች አቋማችንን እንድንጠብቅና እምነታችን ጽኑ እንዲሆን ያበረቱናል። ወደፊት ለሚገጥሙን አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንድንዘጋጅ ያደርጉናል።
5 አዘውትረን በስብሰባዎች በመገኘት በመዝሙር 133:1, 3 ላይ “ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ፣ እነሆ፣ መልካም ነው፣ እነሆም፣ ያማረ ነው” በማለት መዝሙራዊው የገለጸውን ዓይነት ስሜት ልንቀምስ እንችላለን። በአሁኑ ጊዜ የአምላክ ሕዝቦች የትም ቦታ ቢያገለግሉና ቢሰበሰቡ ‘በዚያ ይሖዋ በረከቱን ሕይወትንም እስከ ዘላለም አዝዞላቸዋል።’