ዘወትር በስብሰባዎች መገኘት ምንኛ መልካም ነው!
1 በምሥራቅ አውሮፓ የሚገኙ ብዙ ውድ ወንድሞቻችን ለበርካታ አሥርተ ዓመታት በይፋ እንዳይሰበሰቡ ታግደው ነበር። በእኛም አገር የሚገኙ ብዙ ወንድሞች ተመሳሳይ ሁኔታ ገጥሟቸዋል። እገዳዎቹ ተነስተው በነፃነት መሰብሰብ በቻሉበት ወቅት የተሰማቸውን ደስታ እስቲ ገምቱ!
2 አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች ይህን የመሰለ የደስተኝነት መንፈስ ባለው አንድ ጉባኤ ያደረገውን ጉብኝት በማስመልከት እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ማክሰኞ ምሽት ላይ ጉብኝቴን እንደጀመርኩ አዳራሹን የሚያሞቀው መሣሪያ ተበላሸ። ውጪ ያለው ቅዝቃዜ ዜሮ ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ የደረሰ ሲሆን አዳራሹ ውስጥ ያለው የሙቀት መጠን ደግሞ ከ5 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ አይበልጥም ነበር። ወንድሞች የተቀመጡት ካፖርታቸውን፣ ያንገት ፎጣቸውን፣ ጓንታቸውን፣ ኮፍያቸውን እና ቦት ጫማቸውን እንዳደረጉ ነው። ገጾቹን መግለጥ የማይቻል በመሆኑ አንድም ሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ እያወጣ መከታተል አልቻለም። መድረኩ ላይ ሆኜ ንግግር ስሰጥ ቅዝቃዜው አጥንቴ ውስጥ ገብቶ ስለነበር በምናገርበት ጊዜ ከአፌ የሚወጣው ትንፋሽ ይታየኝ ነበር። ሆኖም በጣም ያስደነቀኝ ነገር አንድም ሰው አለማጉረምረሙ ነው። ሁሉም ወንድሞች በስብሰባው ላይ መገኘት አስደሳችና ጠቃሚ እንደነበረ ተናግረዋል!” እነዚህ ወንድሞች ከስብሰባው የመቅረት ሐሳብ እንኳ ወደ አእምሯቸው አልመጣም!
3 እኛስ እንደዚህ ይሰማናልን? በሳምንታዊ ስብሰባዎቻችን ላይ በነፃነት የመሰብሰብ አጋጣሚያችንን አሁንም ከፍ አድርገን እንመለከተዋለንን? ወይስ ሁኔታዎቹ አመቺ ሆነው እያሉም ለስብሰባዎች አድናቆት እንደሌለን እናሳያለን? አዘውትሮ በስብሰባዎች መገኘት ቀላል ላይሆን ይችላል፤ አንዳንድ ጊዜም ከስብሰባዎች እንድንቀር የሚያደርገን አጥጋቢ ምክንያት ሊኖር ይችል ይሆናል። ይሁን እንጂ በመካከላችን የሚገኙ አንዳንዶች በዕድሜ የገፉ፣ ስር የሰደደ የጤና እክል ያለባቸው፣ የአካል ጉዳተኞች የሆኑ፣ አድካሚ ሥራ ያለባቸው እንዲሁም ሌሎች ከባድ ኃላፊነቶች ያሉባቸው ቢሆኑም እንኳ የስብሰባዎችን አስፈላጊነት በመገንዘብ ዘወትር በስብሰባዎች ላይ እንደሚገኙ ፈጽሞ መዘንጋት የለብንም። ልንከተላቸው የሚገቡ እንዴት ያሉ ግሩም ምሳሌዎች ናቸው!—ከሉቃስ 2:37 ጋር አወዳድር።
4 ከትንሹ የመጽሐፍ ጥናት ቡድን አንስቶ እስከ ትልቁ የአውራጃ ስብሰባ ድረስ በሁሉም ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት እውነተኛውን አምልኮ የመደገፍ ልማድ እናዳብር። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ የመገኘትን አስፈላጊነት አክብደን መመልከት የሚገባን ለምንድን ነው? አንዱ ምክንያት አብሮ መሰብሰብ መለኮታዊ ትእዛዝ ስለሆነ ነው። ሆኖም ሌሎች ጠቃሚ ምክንያቶችም አሉ። ሁላችንም መለኮታዊ መመሪያና የመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ያስፈልገናል። ይህን ደግሞ የምናገኘው በስብሰባዎች ላይ ስንገኝ ነው። (ማቴ. 18:20) ከወንድሞቻችን ጋር ስንገናኝ አንዳችን ሌላውን በማበረታታት እርስ በርሳችን እንተናነጻለን።—ዕብ. 10:24, 25
5 ኢየሱስ በተአምር በተለወጠበት ወቅት ጴጥሮስ “መምህር ሆይ! እዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው” ሲል ተናግሯል። (ሉቃስ 9:33 የ1980 ትርጉም) እኛም ለሁሉም ክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን ተመሳሳይ የሆነ ዝንባሌ ማሳየት ይኖርብናል። በእርግጥም ዘወትር በስብሰባዎች መገኘት ምንኛ መልካም ነው!