ሚያዝያ—መልካም ለማድረግ ቅንዓታችንን የምናሳይበት ወር!
1 ሕዝብ በብዛት ወደሚኖርበት አቅጣጫ በከፍተኛ ፍጥነት የሚከንፍ አውሎ ነፋስ እንዳለ ቢታወቅ አደጋው ባጠላበት አካባቢ ለሚኖሩ ሰዎች ማስጠንቀቂያ መንገር አጣዳፊ ይሆናል። አውሎ ነፋሱ በጣም በቀረበ ቁጥር ማስጠንቀቂያውም የዚያኑ ያህል በጥብቅ መነገር አለበት። ለምን? ምክንያቱም የሰዎች ሕይወት አደጋ ላይ ወድቋል! አንዳንድ ሰዎች ቀደም ብሎ የተሰጠውን ማስጠንቀቂያ አልሰሙ ይሆናል። ሌሎች ደግሞ ማስጠንቀቂያውን ቢሰሙም እርምጃ ለመውሰድ ቸልተኞች ሆነው ይሆናል። የአምላክ የጽድቅ ቁጣ “አውሎ ነፋስ” ይህን ክፉ ሥርዓት ምንም ርዝራዥ ሳያስቀር ጠራርጎ ከማጥፋቱ በፊት መለኮታዊ ማስጠንቀቂያ እንድንናገር የተሰጠን ተልእኮ ከዚህ ጋር እጅግ የሚመሳሰል ነው። (ምሳሌ 10:25) በቢልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ዘላለማዊ ሕይወት አደጋ አንዣቦበታል! ማስጠንቀቂያው ሊነገር ይገባል። ‘መልካም በማድረግ ረገድ ቅንዓታችንን ማሳየት’ አለብን።—ቲቶ 2:11-14
2 ለበርካታ አሥርተ ዓመታት የይሖዋ ሕዝቦች የመታሰቢያው በዓል የሚከበርበትን ወር ልዩ የአገልግሎት ቅንዓት የሚታይበት ጊዜ ለማድረግ ማበረታቻ ሲሰጣቸው ቆይቷል። በአሁኑ ጊዜ የመንግሥት አገልግሎታችን ተብሎ ከሚጠራው በፊት ይታተም የነበረው ኢንፎርማንት በ1939 የጸደይ ወቅት የሚከተለውን ማበረታቻ ይዞ ወጥቶ ነበር:- “ጥሩ የአየር ሁኔታ በሚኖረው በመጪው የጸደይ ወቅት [የጉባኤ] አስፋፊዎች የመስክ አገልግሎት ሰዓታቸውን በእጥፍ ያሳድጋሉ ብለን እንጠብቃለን። ከአቅኚዎችም እንዲሁ። ሚያዝያ አምስት እሁዶች እንዲሁም አምስት ቅዳሜዎች አሉት። በሚያዝያ እያንዳንዱን ቅዳሜና እሁድ . . . ከወትሮው የተለየ ምሥክርነት በመስጠት ተጠቀሙበት።” ከ60 ዓመት በፊት ለወንድሞች የቀረበላቸው ይህ ግብ የሚያጓጓ ነበር! በ1939 እንደነበረው ሁሉ በዚህ ዓመትም ሚያዝያ ወር አምስት ቅዳሜና እሁዶች አሉት። ታዲያ በዚህ ወር ምን ለማድረግ አቅደሃል? በ2000 የቀን መቁጠሪያ ሚያዝያ ወር ላይ ምን አስፈላጊ ማስታወሻዎችን አስፍረሃል? ከፍተኛ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ በሚደረግበት ልዩ ግምት በሚሰጠው በዚህ ወር ከሌሎች የይሖዋ ሕዝቦች ጋር በመሆን በመልካም ሥራዎች ትርጉም ያለው ተሳትፎ ለማድረግ እቅድ አውጣ።
3 ልናከናውን ያቀድነው:- በያዝነው 2000 ዓመት የላቀ ግምት የምንሰጠው ቀን የሚውለው በሚያዝያ ወር ውስጥ ነው። ይህም ሚያዝያ 19 ሲሆን በዚያ ዕለት የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ በዓል እናከብራለን። በመታሰቢያው በዓል ላይ እንዲገኙ በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች ለመጋበዝ ልዩ ጥረት እናድርግ። ባለፈው ወር በቀረበልን ሐሳብ መሠረት በመታሰቢያው በዓል ላይ ሊገኙ ይችላሉ የምትሏቸውን ሰዎች በሙሉ በዝርዝር ጻፉና ማንንም እንዳልረሳችሁ አረጋግጡ። ማስፋፋት ያቆሙትን፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን፣ ተመላልሶ መጠየቅ የሚደረግላቸውን፣ ጥናት ያቋረጡትን፣ የሥራ ባልደረቦችን፣ የትምህርት ቤት ጓደኞችን፣ ጎረቤቶችን፣ ዘመዶችን፣ እንዲሁም የምናውቃቸውን ሌሎች ሰዎች መጋበዝ አትዘንጉ። መገኘት የሚፈልጉ ሰዎች የትራንስፖርት ችግር ይኖርባቸው ይሆን? ከሆነ በደግነት ልትረዷቸው ትችላላችሁ? ሁላችንም በዚያ ምሽት በመታሰቢያው በዓል ላይ የተገኙ ሰዎች ደስ እንዲላቸው ጥረት የማድረግ መብት አለን። ከበዓሉ በኋላ ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች ተጨማሪ መንፈሳዊ እርዳታ ለማድረግ ተከታትለን ልንጠይቃቸው እንችላለን።
4 ከበዓሉ በፊትም ሆነ በኋላ ባሉት ቀናት ‘መልካም የሆነውን ለማድረግ መቅናት’ ይሖዋ ያደረገልንን ሁሉ በእርግጥ እንደምናደንቅ የምናሳይበት ግሩም መንገድ ነው። ብዙዎቻችን በወንጌላዊነቱ እንቅስቃሴ ያለንን ተሳትፎ ከፍ ለማድረግ ጥረት ማድረግ እንችላለን። ረዳት አቅኚ ከሆናችሁ በተቻለ መጠን 50 ወይም ከዚያ የበለጠ ሰዓት በአገልግሎት ለማሳለፍ ተጣጣሩ። (ማቴ. 5:37) በወሩ መጀመሪያ ላይ ያወጣችሁትን ፕሮግራም በጥብቅ ተከተሉ። (መክ. 3:1፤ 1 ቆሮ. 14:40) የተቀረነው አስፋፊዎች ደግሞ ለአቅኚዎች ማበረታቻ በመስጠትም ሆነ በመስክ አገልግሎት አብሮ በመሥራት ከጎናቸው እንደቆምን ለማሳየት የምንችለውን ሁሉ እናድርግ። (ከ2 ነገሥት 10:15, 16 ጋር አወዳድር።) በሚያዝያ በቅንዓት የምንዘራ ከሆነ ታላቅ ደስታና የይሖዋን በረከት ልናገኝ እንችላለን። (ሚል. 3:10) እንዲህ የምናደርግ ከሆነ በረዳት አቅኚነት ለመቀጠል ወይም ወደ ዘወትር አቅኚነት ለመሸጋገር ድልድይ ሊሆንልን ይችላል። በሚያዝያ የምናደርገው የተጠናከረ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ በተከታዮቹ ወራት አዘውታሪ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ሆነን ለመቀጠል ጥሩ ማነቃቂያ እንዲሆንልን እንመኛለን።
5 በዚህ ወር በሺዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ሕዝቦች ተጨማሪ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እንደሚያስጀምሩ ምንም ጥርጥር የለውም። አንተስ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር ትፈልጋለህ? ጥናት ማግኘት እንደምትፈልግ ጠቅሰህ ጸሎት አቅርብ፤ ከዚያም ከጸሎትህ ጋር የሚስማማ ጥረት አድርግ። ልበ ቅን ሰው አግኝተህ ለማስጠናት በማሰብ በትህትና ያቀረብከው ጸሎት በይሖዋ ዘንድ አድናቆት እንደሚቸረው እርግጠኛ ልትሆን ትችላለህ።—1 ዮሐ. 3:22
6 ከዚህ በመቀጠል ውይይት በማስጀመር ረገድ በመስክ ላይ ተሠርቶበት ጥሩ ውጤት ያስገኘ አንድ አቀራረብ እንመልከት። የሚከተለውን ጥያቄ በመጠየቅ ጀምር:- “በትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚታዩት የዓመፅ ድርጊቶች በሙሉ ምንጫቸው የአጋንንት ግፊት ነው ብለው ያስባሉ ወይስ ልጆችን ቀጥቶ በማሳደግ ረገድ የወላጆች ቸልተኝነትም አስተዋጽዖ አበርክቷል?” መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት። ሰውዬው “የአጋንንት ገፋፊነት” ብሎ መልስ ከሰጠ ራእይ 12:9, 12ን አንብብና በዓለም ላይ ለሚታየው ሁከትና ብጥብጥ ዲያብሎስ ያበረከተውን ሚና ጎላ አድርገህ ተናገር። ከዚያም አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ከተባለው ብሮሹር ላይ ትምህርት 4ን አውጣና ዲያብሎስ ከየት መጣ? የሚል ጥያቄ መጥቶበት ያውቅ እንደሆነ ጠይቀው። ቀጥለህ የመጀመሪያዎቹን ሁለት አንቀጾች አንብብና አወያየው። ሰውዬው በትምህርት ቤቶች ለሚታየው ዓመፅ ምክንያቱ “ልጆችን ቀጥቶ በማሳደግ ረገድ ወላጆች ቸልተኛ መሆናቸው ነው” የሚለውን ከመረጠ ደግሞ 2 ጢሞቴዎስ 3:1-3ን አንብብለትና በትምህርት ቤት ለሚታየው ዓመፅ መባባስ አስተዋጽዖ ያበረከቱትን ባሕርያት በግልጽ አስረዳው። ከዚያም አምላክ ከእኛ የሚፈልገው የተባለውን ብሮሹር ትምህርት 8 ላይ አውጣና አንቀጽ 5ን አንብበህ ውይይቱን ቀጥል። ተመልሰህ ለመምጣት ቀጠሮ ከወሰድክ ሰውዬውን ቋሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር መንገድ ይከፍትልሃል። በሚቀጥለው ጊዜ ተመላልሶ መጠየቅ ስታደርግለት እሱ በመማር ላይ ያለውን ትምህርት ለማወቅ የሚፈልግ ሌላ ሰው ይኖር እንደሆነ ጠይቀው።
7 በሚያዝያ ወር ‘መልካሙን በማድረግ ቅንዓታችንን’ የምናሳይበት ሌላው መንገድ በተለያዩ የስብከቱ ዘርፎች መካፈል ነው። በመናፈሻ ቦታዎች ወይም በመኪና ማቆሚያ አካባቢ ምሥክርነት ስለመስጠት አስበሃል? በአውቶቡስ ማቆሚያ ወይም በባቡር ጣቢያ መሥክረህስ? ወይም ደግሞ በስልክ፣ በመንገድ ላይ ወይም በንግድ አካባቢዎች መመሥከርን መሞከር ትፈልጋለህ? ይህን ሐሳብህን በዚህ ወር ለምን በተግባር አትሞክረውም? አስፈላጊ የሆነውን ድፍረት እንድታገኝ ይሖዋ ይረዳሃል። (ሥራ 4:31፤ 1 ተሰ. 2:2ለ) ምናልባትም በእነዚህ የአገልግሎት ዘርፎች በመመሥከር ረገድ ልምድ ካለው አንድ አቅኚ ወይም አስፋፊ ጋር አብረህ ለመሥራት ቀጠሮ ልትይዝ ትችላለህ።
8 በመመሥከሩ ሥራ ያለውን ተሳትፎ ከፍ ለማድረግ ፍላጎት ያለው ማንኛውም አስፋፊ መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት በመስጠት እንደሚሳተፍ የታወቀ ነው። አብዛኛውን ጊዜ መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት ለመስጠት ቀላሉ ዘዴ ሰውዬውን ወዳጃዊ ወደሆነ ውይይት ማስገባት ነው። በጋራ የሚያሳስባችሁን አንድ ርዕሰ ጉዳይ አንሳ። ምናልባት በአንቀጽ 6 ላይ በተጠቀሰው አቀራረብ ልትጠቀም ትችላለህ። አብራችሁ የምትቆዩት ለአጭር ደቂቃ ቢሆንም እንኳን በዚያች ጊዜ በአግባብ ለመጠቀም ጥረት አድርግ። ገና ለገና ድፍን ብር አልሞሉም ብለን ዝርዝር አምስት ሳንቲሞችን እንደማንጥላቸው የታወቀ ነው። ታዲያ አምስት፣ አሥር ወይም አሥራ አምስት ደቂቃ ቢሆን እንኳን መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት በመስጠት ለምን በአግባቡ አንጠቀምበትም?
9 ልናሰላስልባቸው የሚገቡ ነገሮች:- “የአምላክ ትንቢታዊ ቃል” በሚል ርዕስ ባለፈው ዓመት በወሰድነው የአውራጃ ስብሰባ ላይ የቀረበው ድራማ ያጎላቸውን ነጥቦች ቆም ብለህ ለማሰብ ጊዜ ይኑርህ። መንፈሳዊ ውርሻችንን ማድነቅ በሚል ርዕስ የቀረበው ድራማ በያዕቆብና በኤሳው መካከል የነበረውን ልዩነት በጥንቃቄ እንድናነጻጽር አድርጎናል። ኤሳው እንደ ያዕቆብ ሁሉ እርሱም ለመንፈሳዊ ነገሮች ፍላጎት እንዳለው ተናግሯል። ይሁን እንጂ በተግባር ያሳየው ይህን አይደለም። (ዘፍ. 25:29-34) ይህ ለእኛስ እንዴት ያለ ከባድ ማስጠንቀቂያ ነው! ልክ እንደ ያዕቆብ የይሖዋን በረከት ለማግኘት መጣጣር አልፎ ተርፎም እስከመጨረሻው መታገል ይገባናል። (ዘፍ. 32:24-29) ያገኘነውን አስደናቂ መንፈሳዊ ውርሻ አቅልለን እንደማንመለከት ለማሳየት ሚያዝያንና ከዚያም በኋላ ያሉትን ወራት ተጠቅመን ያለንን ቅንዓት ለምን አናድስም?
10 “ታላቁ የእግዚአብሔር ቀን ቀርቦአል፤ የእግዚአብሔር ቀን ድምፅ ቀርቦአል እጅግም ፈጥኖአል።” (ሶፎ. 1:14) የመንግሥቱ ምሥራች ሊነገር ይገባል። የሰዎች ሕይወት አደጋ አንዣቦበታል! ይህ ወር ሁሉም የይሖዋ ሕዝቦች በአንድነት ሆነው ‘መልካም ለማድረግ በሚያሳዩት ቅንዓት’ ብዙ በረከት የሚገኙበት እንዲሆን ምኞታችን ነው።
[ገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የመታሰቢያውን በዓል የሚመለከቱ ማሳሰቢያዎች
◼ ስብሰባው የሚደረግበትን ሰዓት ስትወስኑ ቂጣውና ወይኑ ፀሐይ ከመጥለቋ በፊት መዞር እንደሌለባቸው አስታውሱ።
◼ ተናጋሪውን ጨምሮ ለሁሉም ተሰብሳቢዎች በዓሉ የሚከበርበት ትክክለኛ ሰዓትና ቦታ ሊነገራቸው ይገባል።
◼ ተገቢው ዓይነት ቂጣና ወይን ተዘጋጅቶ መቀመጥ አለበት።—መጠበቂያ ግንብ 2-106 ገጽ 17ን ተመልከቱ።
◼ ሳህኖች፣ ብርጭቆዎች እንዲሁም ተስማሚ የሆነ ጠረጴዛና የጠረጴዛ ጨርቅ ቀደም ብሎ ወደ መንግሥት አዳራሹ መጥተው በየቦታቸው መቀመጥ ይኖርባቸዋል።
◼ የመንግሥት አዳራሹም ሆነ ሌላ የመሰብሰቢያ ቦታ ቀደም ብሎ በሚገባ መጽዳት አለበት።
◼ አስተናጋጆች እንዲሁም ቂጣውንና ወይኑን የሚያዞሩ ወንድሞች በቅድሚያ ሊመረጡና ተገቢ ስለሆነው አሠራርና ስለሥራ ድርሻቸው መመሪያ ሊሰጣቸው ይገባል።
◼ የአካል ጉዳተኞች በመሆናቸው ምክንያት በቦታው መገኘት ከአቅማቸው በላይ የሚሆንባቸው ቅቡዓንን ለማስተናገድ ዝግጅት መደረግ ይኖርበታል።
◼ የሚቻል ከሆነ እያንዳንዱ ጉባኤ ራሱን ችሎ የመታሰቢያውን በዓል ቢያከብር ይመረጣል። የበዓሉ ሥነ ሥርዓት በአንድ የመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ከአንድ ጊዜ በላይ እንዲደረግ ፕሮግራም ተይዞ ከሆነ በመተላለፊያዎች ላይና በመኪና ማቆሚያው አካባቢ ጭንቅንቅ እንዳይፈጠር ለማድረግ በጉባኤዎቹ መካከል ጥሩ ቅንጅት ሊኖር ይገባል።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በዚህ ዓመት የመታሰቢያው በዓል የሚከበረው ረቡዕ ሚያዝያ 19 ነው። ሽማግሌዎች ለሚከተሉት ጉዳዮች ትኩረት ሊሰጡ ይገባቸዋል:-