ወላጆች—ልጆቻችሁ ጠቃሚ ልማዶችን ማዳበር በሚችሉበት መንገድ ቅረጿቸው
1 ጠቃሚ ልማዶች በተፈጥሮ ወይም እንዲያው በአጋጣሚ የሚገኙ ነገሮች አይደሉም። ከሁሉም በላይ ደግሞ ልጆች መልካም ልማዶችን ማዳበር በሚችሉበት መንገድ መቅረጽ ጊዜ ይጠይቃል። “መቅረጽ” ተብሎ የተተረጎመው ኢንስቲል የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል “ደረጃ በደረጃ ማስተላለፍ” ወይም “ቀስ በቀስ ማስረግ” ማለት ነው። ወላጆች ‘ልጆቻቸውን በይሖዋ ምክርና በተግሣጽ ለማሳደግ’ ጽኑ አቋም መያዝ ይኖርባቸዋል።—ኤፌ. 6:4
2 ከሕፃንነታቸው ጀምሩ:- ሕፃናት አዳዲስ ነገሮችን ለመማርና ለማድረግ ያላቸው ችሎታ የሚያስደንቅ ነው። ብዙውን ጊዜ ትልልቅ ሰዎች አዲስ ቋንቋ መማር ሲቸገሩ ዕድሜያቸው ለትምህርት ያልደረሱ ትንንሽ ልጆች ግን በአንድ ጊዜ ሁለት ወይም ሦስት ቋንቋዎች መማር ይችላሉ። ልጃችሁ ጥሩ ልማድ ማዳበር በሚችልበት ዕድሜ ላይ አልደረሰም ብላችሁ አታስቡ። ልጁ ገና ትንሽ እያለ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ማስተማር ከተጀመረና ሳይቋረጥ የሚቀጥል ከሆነ አእምሮው “መዳን የሚገኝበትን ጥበብ” ሊሰጠው በሚችል እውቀት ይሞላል።—2 ጢሞ. 3:15
3 የመስክ አገልግሎትን ልማድ አድርጉ:- አንድ ልጅ ገና ከልጅነቱ ሊቀረጽበት የሚገባው ጠቃሚ ልማድ የአምላክን መንግሥት ምሥራች ዘወትር የመስበክ ልማድ ነው። ብዙ ወላጆች ልጆቻቸው ገና ሕፃናት ሳሉ ከቤት ወደ ቤት ይዘዋቸው በመሄድ ይህን ጠቃሚ ልማድ መቅረጽ ጀምረዋል። ወላጆች ምሥክርነት በመስጠቱ ሥራ አዘውትረው መካፈላቸው ልጆቹ ለአገልግሎቱ አድናቆትና ቅንዓት እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል። ወላጆች ልጆቻቸው በእያንዳንዱ የመስክ አገልግሎት ዘርፍ ምሥክርነት መስጠት የሚችሉበትን ዘዴ ሊያሳዩአቸው ይችላሉ።
4 በተጨማሪም ልጆች በቲኦክራሲያዊ አገልግሎት ትምህርት ቤት መመዝገባቸው ይረዳቸዋል። በማስተዋል ማንበብንና ማጥናትን የመሰሉ ጥሩ ጥሩ ልማዶችን ያስተምራቸዋል። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይትና ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግን እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራትን ይማራሉ። ይህ ዓይነቱ ስልጠና ለአቅኚነት እንዲነሳሱና ለልዩ የአገልግሎት መብቶች እንዲጣጣሩ ይገፋፋቸዋል። ብዙ ቤቴላውያንና ሚስዮናውያን ገና ልጆች እያሉ በትምህርት ቤቱ የተካፈሉበትን ጊዜ በደንብ የሚያስታውሱ ሲሆን ትምህርት ቤቱ ጠቃሚ ልማዶችን እንዲያዳብሩ የረዳቸው ዝግጅት እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል።
5 ሁላችንም ብንሆን በታላቁ ሸክላ ሠሪ በይሖዋ እጅ ውስጥ እንዳለ ጭቃ ነን። (ኢሳ. 64:8) ጭቃው ወዲያው እንደተቦካ ሳይደርቅ ቅርጽ መስጠት በጣም ቀላል ነው። ተቦክቶ በቆየ መጠን ግን ቅርጽ መስጠቱ አስቸጋሪ እየሆነ ይመጣል። ሰዎችም እንደዚሁ ናቸው። ልጆችን በቀላሉ የተፈለገውን ቅርጽ ማስያዝ የሚቻለው በልጅነታቸው ስለሆነ ገና ከሕፃንነታቸው መቅረጽ መጀመር የተሻለ ይሆናል። ለበጎም ሆነ ለመጥፎ የሚቀረጹት በለጋ ዕድሜያቸው ነው። ማንኛውም አፍቃሪ ወላጅ እንደሚያደርገው ልጆቻችሁ በክርስቲያናዊ አገልግሎት ጠቃሚ የሆኑ ልማዶችን እንዲያዳብሩ ሕፃናት እያሉ መቅረጽ ጀምሩ።