የተማሪዎቻችሁን ልብ ለመንካት ጣሩ
1 ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት እሱ ያዘዛቸውን ሁሉ “እንዲጠብቁ” ሌሎችን ያስተምሩ ዘንድ ለደቀ መዛሙርቱ ነግሯቸው ነበር። (ማቴ. 28:19, 20) አንድ ሰው የክርስቶስን ትእዛዛት ‘እንዲጠብቅ’ ካስፈለገ መልእክቱ ልቡን ሊነካው ይገባል። (መዝ. 119:112) መጽሐፍ ቅዱስ የምታስጠኑትን ሰው ልብ መንካት የምትችሉት እንዴት ነው?
2 የይሖዋን መመሪያ ለማግኘት ጸልዩ፦ ደቀ መዛሙርት ማድረግ አምላክ የሰጠን ሥራ ስለሆነ ስኬታማ ለመሆን የሚያስችለን የእኛ ችሎታ ሳይሆን የእሱን በረከት ማግኘታችን ነው። (ሥራ 16:14፤ 1 ቆሮ. 3:7) ስለሆነም ለሌሎች እውነትን ስናስተምር የይሖዋን እርዳታ ለማግኘት መጸለይ የግድ አስፈላጊ ነው።—ነህ. 2:4፤ ኢሳ. 50:4
3 ተማሪው ምን ብሎ እንደሚያምን አስተውሉ:- ሰዎች ምን እንደሚያምኑና ለምን በዚያ እንደሚያምኑ ማወቁ ልባቸውን ለመንካት ምን ማለት እንዳለብን እንድናስተውል ሊረዳን ይችላል። አንድ ተማሪ አንድን ትምህርት ማራኪ ሆኖ ያገኘው ለምንድን ነው? እንዲያምንበት ያደረገው ምክንያት ምንድን ነው? ይህን ማወቃችን በማስተዋል እንድንናገር ሊረዳን ይችላል።—ሥራ 17:22, 23
4 ምክንያታዊና ቅዱስ ጽሑፋዊ የመከራከሪያ ነጥቦችን አቅርቡ፦ ተማሪው የተማረው እውነት ትርጉሙ ሊታየው ይገባል። (ሥራ 17:24-31) ስለ ተስፋችን ተጨባጭ ማስረጃ ማቅረብ ይኖርብናል። (1 ጴጥ. 3:15) ይሁን እንጂ ይህን ስናደርግ ሁልጊዜ ደግነትና ትዕግሥት ሊለየን አይገባም።
5 በምሳሌ አጠናክሩት፦ ምሳሌዎች ተማሪው የሚማረውን ነገር በቀላሉ እንዲረዳው ማድረግ ብቻ ሳይሆን ስሜቱ እንዲቀሰቀስም ያደርጋሉ። ምሳሌ አእምሮንም ሆነ ልብን ይነካል። ኢየሱስ ብዙውን ጊዜ በምሳሌ ተጠቅሟል። (ማር. 4:33, 34) እርግጥ ነው፣ ውጤታማ ለመሆን ከተፈለገ ምሳሌው ውይይት ከሚደረግበት ነጥብ ጋር የሚዛመድና ከተማሪው ሕይወት ጋር የሚያያዝ መሆን ይገባዋል።
6 እውነትን መቀበል ያለውን ጥቅም ንገሯቸው፦ ሰዎች የተማሩትን ነገር ተግባራዊ ማድረግ ያለውን ጥቅም ማወቅ ይፈልጋሉ። ተማሪያችሁ በ2 ጢሞቴዎስ 3:14-17 ላይ የሚገኙት የጳውሎስ ቃላት ያዘሉትን ጥበብ እንዲገነዘብ እርዱት።
7 አንዳንድ ሰዎች ላስተማራችኋቸው እውነቶች በጎ ምላሽ ባይሰጡ ተስፋ አትቁረጡ። ሰዎች ሁሉ ተቀባይ ልብ አላቸው ማለት አይደለም። (ማቴ. 13:15፤ ዮሐ. 12:39, 40) ይሁን እንጂ አንዳንድ ግለሰቦች ያምናሉ። (ሥራ 17:32-34) በምሥራቹ መልእክት የሰዎችን ልብ ለመንካት የምታደርጉት ጥረት ብዙዎች ኢየሱስ ያዘዘውን እንዲቀበሉና “እንዲጠብቁ” የሚረዳቸው እንዲሆን እንመኛለን።