ሥርዓታማነት—ለአምላክ ያደሩ ሰዎች መለያ
1 ዛሬ ሥርዓታማነት ጠፍቷል ለማለት ይቻላል። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ሰዎች ከመጣደፋቸው የተነሳ “እባክህ፣” “አመሰግናለሁ፣” ወይም “ይቅርታ” የመሳሰሉትን መሠረታዊ የአክብሮት ቃላት መጠቀም ብዙም ትዝ አይላቸውም። የአምላክ ቃል በመጨረሻው ዘመን ሰዎች ‘ራሳቸውን የሚወዱ፣ ትምክህተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ የማያመሰግኑ፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ መልካም የሆነውን የማይወዱና ችኩሎች’ እንደሚሆኑ በመናገር የሥነ ምግባር ደረጃቸው እንደሚያሽቆለቁል አስቀድሞ ተንብዮአል። (2 ጢሞ. 3:1-4) እነዚህ ሁሉ የመጥፎ ምግባር መለያ ናቸው። ክርስቲያኖች ለአምላክ ያደሩ ሰዎች እንደመሆናቸው መጠን ይህ ዓለም ለሌሎች ያለው አክብሮት የጎደለው አመለካከት እንዳይጋባባቸው መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል።
2 ሥርዓታማነት ምንድን ነው? ሥርዓታማነት ለሌሎች ስሜት ከልብ መጠንቀቅ፣ ከሌሎች ጋር በሰላም የመኖር ችሎታ ተብሎ ሊገለጽ ይችላል። አሳቢነት፣ የታረመ ጠባይ፣ ደግነት፣ አክብሮት፣ ብልህነትና አስተዋይነት ሥርዓታማነት የሚገለጽባቸው ባሕርያት ናቸው። እነዚህ ባሕርያት አንድ ሰው ለአምላክና ለጎረቤቱ ከሚኖረው ፍቅር የሚመነጩ ናቸው። (ሉቃስ 10:27) ምንም ወጪ አይጠይቁም፤ ሆኖም ከሌሎች ጋር ያለንን ግንኙነት በማሻሻል ረገድ በጣም ጠቃሚ ናቸው።
3 ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ምሳሌ ትቶልናል። “ሰዎችም ሊያደርጉላችሁ እንደምትወዱ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው” የሚለውን ወርቃማ ሕግ ሁልጊዜ ተግባራዊ ያደርግ ነበር። (ሉቃስ 6:31) ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በነበረው ግንኙነት ያሳየው አሳቢነትና ፍቅር አያስገርመንም? (ማቴ. 11:28-30) ያሳየው ሥርዓታማ ባሕርይ በግብረ ገብ መጻሕፍት ላይ ከሰፈሩት ደንቦች የተወሰደ አይደለም። ከቀናና ገር ልብ የመነጨ ነው። እኛም እሱ የተወውን ግሩም ምሳሌ ለመኮረጅ ጥረት ማድረግ ይገባናል።
4 ክርስቲያኖች ሥርዓታማ ጠባይ ማሳየት ያለባቸው መቼ ነው? በሌሎች ዘንድ ጥሩ ስም ማትረፍ በምንፈልግባቸው ልዩ አጋጣሚዎች ብቻ ነውን? ሥርዓታማ ጠባይ ማሳየት የሚገባን በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ብቻ ነውን? እንዲህ መሆን የለበትም! በማንኛውም ጊዜ ሥርዓታማ ጠባይ ማሳየት ይኖርብናል። በተለይ ደግሞ በጉባኤ ውስጥ እርስ በርስ ባለን ግንኙነት ይህ ጉዳይ ሊያሳስበን የሚገባው በየትኞቹ መንገዶች ነው?
5 በመንግሥት አዳራሽ:- የመንግሥት አዳራሹ የአምልኮ ቦታችን ነው። እዚያ የምንገኘው ይሖዋ አምላክ ጋብዞን ነው። በሌላ አባባል እንግዶች ነን ማለት ነው። (መዝ. 15:1) ታዲያ በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ በምናሳየው ጠባይ ምሳሌ የምንሆን እንግዶች ነን? በአለባበሳችንና በአጋጌጣችን ረገድ ተገቢውን ጥንቃቄ እናደርጋለን? በአዘቦት ቀን የሚለበስ ዓይነት ወይም ልከኛ ያልሆነ ልብስ ከመልበስ መቆጠብ እንደምንፈልግ የታወቀ ነው። የይሖዋ ሕዝቦች በአውራጃ ስብሰባ ላይም ሆነ በሳምንታዊ የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ሲገኙ አምላክን እንፈራለን ለሚሉ ሰዎች በሚገባ የጨዋ አለባበስ ተለይተው ይታወቃሉ። (1 ጢሞ. 2:9, 10) በዚህ መንገድ በሰማይ ለሚገኘው ጋባዣችንም ሆነ እንደ እኛው ተጋብዘው ለመጡ ሌሎች እንግዶች ተገቢውን አሳቢነትና አክብሮት እናሳያለን።
6 ከስብሰባዎች ጋር በተያያዘ ሥርዓታማ ጠባይ የምናሳይበት ሌላው መንገድ በሰዓቱ መገኘት ነው። እንዲህ ማድረግ ሁልጊዜ ቀላል እንደማይሆን የታወቀ ነው። አንዳንዶች ራቅ ባለ አካባቢ ይኖሩ ይሆናል ወይም ደግሞ ወደ ጉባኤ ለመምጣት የሚያዘጋጁት ትልቅ ቤተሰብ ይኖራቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ በአንዳንድ ጉባኤዎች ግማሽ በግማሽ የሚሆኑት አስፋፊዎች ከመክፈቻው መዝሙርና ጸሎት በኋላ የመድረስ ልማድ እንዳላቸው ተስተውሏል። ይህ የሚያሳስብ ጉዳይ ነው። ሥርዓታማ ጠባይ ለሌሎች ስሜት አሳቢ ከመሆን ጋር የተያያዘ መሆኑን ማስታወስ ጥሩ ነው። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ አክብሮ የጠራን አምላክ ይሖዋ ይህን መንፈሳዊ ድግስ ያዘጋጀው ለእኛ ጥቅም ሲል ነው። ሰዓት አክባሪ በመሆን ስለ እሱ ስሜት እንደምናስብና ዝግጅቱን እንደምናደንቅ እናሳያለን። ከዚህም በተጨማሪ በስብሰባዎች ላይ አርፍዶ መድረስ አሳብ የሚከፋፍል ከመሆኑም ሌላ ቀደም ብለው ለተገኙ ተሰብሳቢዎች አክብሮት ማጣትን የሚያሳይ ነው።
7 በስብሰባዎች ላይ ስንገኝ በስብሰባው ላይ አዳዲሶች መገኘታቸውን እናስተውላለን? ቀረብ ብሎ እንኳን ደህና መጣችሁ ማለት አንዱ የሥርዓታማ ጠባይ ማረጋገጫ ነው። (ማቴ. 5:47፤ ሮሜ 15:7) የአክብሮት ሰላምታ ማቅረብ፣ ሞቅ ባለ ሁኔታ መጨበጥ፣ ደግነት የሚነበብበት ፈገግታ ማሳየት፣ መጽሐፍ ቅዱሳችንን፣ የመዝሙር መጽሐፋችንን ወይም የሚጠናውን ጽሑፍ አብረውን እንዲያዩ ማድረጉ ቀላል ነገሮች ቢሆኑም እውነተኛ ክርስቲያኖች መሆናችንን የሚያረጋግጡ ተጨማሪ ማስረጃ ተደርገው ሊቆጠሩ ይችላሉ። (ዮሐ. 13:35) አንድ ሰው በመንግሥት አዳራሽ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተገኘ በኋላ እንዲህ ብሏል:- “እዚያ በሄድኩበት የመጀመሪያ ዕለት ከዚያ በፊት የማላውቃቸውን ከልባቸው አፍቃሪ የሆኑ ሰዎች አይቻለሁ። ከልጅነት እስከ እውቀት በኖርኩበት ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ያለ ነገር አላየሁም። እውነትን እንዳገኘሁ ገብቶኝ ነበር።” በዚህም ምክንያት በአኗኗሩ ላይ ለውጥ ያደረገ ሲሆን ከሰባት ወራት በኋላ ተጠመቀ። አዎን፣ በጎ ምግባር ከፍተኛ ውጤት ሊያስገኝ ይችላል!
8 ተጋብዘው ለመጡ ሰዎች ሥርዓታማ ጠባይ የምናሳይ ከሆነ “ይልቁንም ለሃይማኖት ቤተ ሰዎች” እንዲህ ማድረግ አይገባንምን? (ገላ. 6:10) “ሽማግሌውንም [ወይም አሮጊቷን] አክብር” የሚለው መሠረታዊ ሥርዓት ይሠራል። (ዘሌ. 19:32) በስብሰባዎቻችን ላይ እንደነዚህ ያሉት ችላ ሊባሉ አይገባም።
9 በትኩረት ማዳመጥ:- ክርስቲያን አገልጋዮች በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ንግግር ሲያቀርቡ ዓላማቸው እኛን ለማነጽ የሚጠቅም መንፈሳዊ ስጦታ ማካፈል ነው። (ሮሜ 1:11) የምናንቀላፋ፣ ማስቲካ የምናኝክ፣ አጠገባችን ከተቀመጠ ሰው ጋር በተደጋጋሚ የምናንሾካሹክ፣ ሳያስፈልግ ወደ መጸዳጃ ቤት የምንመላለስ፣ ከሚቀርበው ትምህርት ጋር ግንኙነት የሌለው ጽሑፍ የምናነብ ወይም ስብሰባው እየተካሄደ እያለ ሌላ ነገር የምናደርግ ከሆነ ሥርዓታማነት አይሆንም። ሽማግሌዎች በዚህ ረገድ ምሳሌ መሆን ይገባቸዋል። ሥርዓታማ ክርስቲያናዊ ባሕርያት ለተናጋሪውና ለሚያቀርበው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መልእክት ያልተከፋፈለ ትኩረታችንን በመስጠት አክብሮት እንድናሳይ ይገፋፋናል።
10 በተጨማሪም ለተናጋሪውም ሆነ ለአድማጮች ካለን አሳቢነት በመነሳት ፔጀር እና ሞባይል ቴሌፎን ስብሰባዎችን እንዳያውኩ መጠንቀቅ ይገባናል።
11 ሥርዓታማነትና ልጆች:- ወላጆች የልጆቻቸውን ባሕርይ ምንጊዜም መከታተል አለባቸው። አንድ ትንሽ ልጅ ማልቀስ ቢጀምር ወይም ስብሰባው እየተደረገ እያለ ቢቁነጠነጥና ሌሎችን ቢያውክ ልጁን ዝም ለማሰኘት በተቻለ መጠን ቶሎ ከአዳራሹ ይዞ መውጣት ጥሩ ነው። አንዳንዴ እንዲህ ማድረጉ ቀላል ላይሆን ይችላል። ሆኖም ይህን ማድረጋችሁ ለሌሎች ሰዎች ስሜት እንደምትጠነቀቁ የሚያሳይ ይሆናል። አርፈው የማይቀመጡ ትንንሽ ልጆች ያሏቸው ወላጆች በስብሰባው ወቅት ወደ ውጪ መውጣት ቢያስፈልጋቸው በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች እንዳይረብሹ ሲሉ ብዙውን ጊዜ ወደኋላ አካባቢ መቀመጥ ይመርጣሉ። የተቀሩት ተሰብሳቢዎች አስፈላጊ ከሆነ ቤተሰብ ያላቸው እንዲጠቀሙበት የመጨረሻዎቹን መደዳዎች በመተው ተገቢውን አሳቢነት ማሳየት ይችላሉ።
12 እንዲሁም ወላጆች ልጆቻቸው ከስብሰባ በፊትና በኋላ የሚያሳዩትን ጠባይ በትኩረት መከታተል አለባቸው። አደጋ ሊያስከትል ስለሚችል ልጆች በአዳራሹ ውስጥ ወዲያ ወዲህ መሯሯጥ አይኖርባቸውም። በተለይ ለዓይን ያዝ ማድረግ ሲጀምር ከመንግሥት አዳራሹ ውጪ ከወዲያ ወዲህ መሯሯጥ አደገኛ ሊሆን ይችላል። ከግቢው ውጪ ጮክ ብሎ ማውራት ጎረቤቶችን ሊረብሽና አምልኳችንን ሊያስነቅፍ ይችላል። በመንግሥት አዳራሹ ውስጥም ሆነ ውጪ ልጆቻቸውን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥረት የሚያደርጉ ወላጆች አንድ ላይ መሰብሰባችን አስደሳች እንዲሆን አስተዋጽኦ ስለሚያደርጉ ሊመሰገኑ ይገባል።—መዝ. 133:1
13 በመጽሐፍ ጥናት:- የጉባኤ ስብሰባ እንዲደረግበት ቤታቸውን የፈቀዱ ወንድሞችና እህቶች የሚያሳዩትን የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ እናደንቃለን። በስብሰባው ላይ ስንገኝ ለንብረታቸው አክብሮትና አሳቢነት ማሳየት ያስፈልገናል። ወለሉን ወይም ምንጣፉን እንዳናቆሽሽ ወደ ውስጥ ከመግባታችን በፊት ጫማችንን በር ላይ በደንብ መጥረግ ይገባናል። ወላጆች ልጆቻቸው ለመጽሐፍ ጥናት ከተመደበው የቤቱ ክፍል ርቀው እንዳይሄዱ መከታተል ይገባቸዋል። ቡድኑ አነስተኛ ተሰብሳቢዎች ሊኖሩትና የአንድ ቤተሰብ መልክ ሊኖረው ስለሚችል በሌሎች ሰዎች ቤት የፈለግነውን ለማድረግ ነጻነት ሊሰማን አይገባም። አንድ ትንሽ ልጅ መጸዳጃ ቤት መሄድ ቢያስፈልገው ወላጅ አብሮ መሄድ ይኖርበታል። ከዚህ በተጨማሪ መጽሐፍ ጥናትም የጉባኤ ስብሰባ ስለሆነ ወደ መንግሥት አዳራሽ ስንሄድ የምንለብሰው ዓይነት ልብስ መልበስ ይኖርብናል።
14 ሥርዓታማ ጠባይ ማሳየት የግድ አስፈላጊ ነው:- ክርስቲያናዊ ባሕርያትን መልበስ አገልግሎታችን እንዳይነቀፍ ማድረጉ ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ጋርም መልካም ግንኙነት እንዲኖረን ያደርጋል። (2 ቆሮ. 6:3, 4, 6) ደስተኛ የሆነው አምላክ አምላኪዎች እንደመሆናችን መጠን ፈገግታ ለማሳየት፣ ከሌሎች ጋር ስምም ለመሆን አልፎ ተርፎም ሌሎች ደስ የሚሰኙበትን ጥቂት የደግነት ተግባር ለማድረግ ሊከብደን አይገባም። እነዚህ ሥርዓታማነት የሚገለጽባቸው ባሕርያት ለአምላክ ያደርን በመሆን ለምንመራው ሕይወት ውበት ይጨምሩለታል።