መጽሔቶችን ለማበርከት ምን ማለት ይቻላል?
ንቁ!መስከ.2001
“እንደሚያውቁት ብዙዎቹ ወጣቶቻችን የወደፊት ሕይወታቸው ያሳስባቸዋል። አንዳንዶች በጣም ይጨነቃሉ። እርዳታ ማግኘት የሚችሉ ይመስልዎታል? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] ይህ መጽሔት ወጣቶችን ምን እንደሚያስጨንቃቸውና እንዴት መርዳት እንደሚቻል ይናገራል።”
መጠበቂያ ግንብ ነሐሴ 15, 2001
ብዙዎች ወጣትነት በሕይወት ውስጥ ልዩ ወቅት ነው ቢባል ይስማማሉ። ሆኖም ወጣትነት የመደሰቻ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ስለ ወደፊቱ ሕይወት በቁም ነገር የሚታሰብበት ጊዜ ጭምር ነው። ምክንያቱም በወጣትነታችን የምናከናውናቸው ነገሮች በጎልማሳነት እድሜያችን ላይ ትልቅ ተጽዕኖ አላቸው። ስለሆነም ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን ለወጣቶች በመክብብ 11:9, 10 ላይ የሚገኘውን ምክር ለግሷል። [አንብበው።] ይህ መጽሔት ወጣቶች ሕይወታቸውን ስኬታማ እንዲያደርጉ መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት ሊረዳቸው እንደሚችል ያሳያል።
መጠበቂያ ግንብ መስከ. 1, 2001
በዓለም ላይ የክፋት ድርጊቶች እንዲፈጸሙ የሚያደርግ ዲያብሎስ የሚባል አካል በእርግጥ አለ ወይስ ይህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ያልተማሩ ሰዎች አጉል እምነት ነው? የሚለው ጥያቄ በብዙዎች አእምሮ ውስጥ ይጉላላል። አንዳንዶች ዲያብሎስ በእርግጥ እንዳለ ለማስረዳት ከመጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው ያሉ ጥቅሶችን በማስረጃነት ይጠቅሳሉ። [1 ዮሐንስ 5:19ን አንብብ።] ስለዚህ ጉዳይ የሚያብራራው ይህ መጽሔት ኢየሱስ ራሱ በዲያብሎስ መኖር ያምን እንደነበረና እኛም ራሳችንን ከዲያብሎስ ለመጠበቅ ምን ማድረግ እንደምንችል እንድናውቅ ይረዳናል።
መጠበቂያ ግንብ መስከ. 15, 2001
“በሁሉም ሃይማኖቶች ውስጥ ለማለት ይቻላል እውነትን የሚያፈቅሩ ሰዎች አሉ። ሆኖም በጥቅሉ ሃይማኖት ሰዎችን የመከፋፈል አዝማሚያ ይታይበታል። ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች አንድ ለማድረግ ምን መደረግ ይኖርበታል? [መልስ ከሰጠ በኋላ ሶፎንያስ 3:9ን አንብብ።] ይህ መጽሔት ከእውነተኛው አምላክ የሚገኘው እውቀት በየትኛውም ሥፍራ የሚኖሩ ሰዎችን እንዴት አንድ እያደረገ እንዳለ ይገልጻል።”