ከጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት የበላይ ተመልካቻችሁ ጋር ተባበሩ
1 ሁላችንም ከጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት በርካታ ጥቅሞች እናገኛለን። ባለፈው ወር የጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት የበላይ ተመልካች ኃላፊነቱን እንዴት እንደሚወጣ ተወያይተን ነበር። ይሁን እንጂ እኛስ ከእርሱ ጋር በመተባበር ራሳችንንም ሆነ ሌሎችን መጥቀም የምንችለው እንዴት ነው?
2 በየሳምንቱ ተገኙ:- በመጽሐፍ ጥናት ቡድን ውስጥ የሚታቀፉት አስፋፊዎች ቁጥር አነስተኛ ስለሆነ የአንድ ሰው መምጣት ወይም መቅረት የጎላ ልዩነት ያመጣል። ስለዚህ ሁልጊዜ ለመገኘት ግብ አውጡ። የመጽሐፍ ጥናት የበላይ ተመልካቹ ስብሰባውን ያለ ችግር መምራት እንዲችል ስለሚረዳው ሰዓት አክባሪ በመሆንም እገዛ ልናበረክት እንችላለን።—1 ቆሮ. 14:40
3 የሚያንጹ መልሶችን በማካፈል:- ሌላው ተባባሪ መሆናችንን ማሳየት የምንችልበት መንገድ በሚገባ በመዘጋጀትና በስብሰባው ላይ የሚያንጹ ሐሳቦችን በማካፈል ነው። በአንድ ነጥብ ላይ ብቻ የሚያተኩሩ መልሶችን መመለስ አብዛኛውን ጊዜ የተሻለ ከመሆኑም በላይ ሌሎችም እንዲሳተፉ ያበረታታል። በአንቀጹ ውስጥ ያለውን ሐሳብ በሙሉ ለመሸፈን አትሞክሩ። በትምህርቱ ውስጥ የነካችሁ አንድ ነጥብ ካለ ያንን በማካፈል ውይይቱን ሕያው አድርጉ።—1 ጴጥ. 4:10
4 የመጽሐፍ ጥናት ቡድኑን በንባብ የምትረዳ ከሆነ ይህን ኃላፊነትህን በትጋት ለመወጣት ጥረት አድርግ። ጥርት ያለ ንባብ ጥናቱን ይበልጥ አስደሳች ለማድረግ ይረዳል።—1 ጢሞ. 4:13
5 የቡድን ምሥክርነት:- የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባዎች በአብዛኞቹ የመጽሐፍ ጥናት መሰብሰቢያ ቦታዎች ይደረጋሉ። እነዚህን ዝግጅቶች መደገፋችን የበላይ ተመልካቹ በወንጌላዊነቱ ሥራ በግንባር ቀደምትነት ለመሥራት ለሚያደርገው ጥረት እገዛ ያበረክትለታል። እነዚህን ዝግጅቶች ከወንድሞች ጋር ለመቀራረብና እነርሱን ለማበረታታት እንደሚያስችሉ አጋጣሚዎች አድርገን እንመልከታቸው።
6 የመስክ አገልግሎት ሪፖርት:- ከበላይ ተመልካቹ ጋር ልንተባበር የምንችልበት ሌላው መንገድ በወሩ መጨረሻ ላይ የመስክ አገልግሎት ሪፖርታችንን ሳንዘገይ በመስጠት ነው። የአገልግሎት ሪፖርታችሁን በቀጥታ ለእርሱ ልትሰጡት ወይም በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ ለዚህ ዓላማ ተብሎ በተዘጋጀው ሳጥን ውስጥ ልትከቱት ትችላላችሁ። የጉባኤው ጸሐፊ የመጽሐፍ ጥናት የበላይ ተመልካቾች የሰበሰቡትን የመስክ አገልግሎት ሪፖርት ለመቀበል ይህን ሣጥን ሊጠቀምበት ይችላል።
7 ለጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት የበላይ ተመልካቻችሁ የምታደርጉትን እገዛ በእጅጉ እናደንቃለን። ከሁሉም በላይ ይሖዋ ‘ከመንፈሳችሁ ጋር እንደሚሆን’ እርግጠኛ ልትሆኑ ትችላላችሁ።—ፊልጵ. 4:23