“አባት ለሌላቸው ልጆች” ፍቅራዊ አሳቢነት አሳዩአቸው
1 ይሖዋ “አባት ለሌላቸው ልጆች አባት” ነው። (መዝ. 68:5 የ1980 ትርጉም ) ለጥንቱ የእስራኤል ብሔር የሰጠው የሚከተለው ትእዛዝ ለደህንነታቸው የሚያስብ መሆኑን ያሳያል:- “መበለቲቱንና ድሀ አደጎቹን [‘አባትና እናት የሌለውን ልጅ፣’ አ.መ.ት ] አታስጨንቁአቸው። ብታስጨንቁአቸውና ወደ እኔ ቢጮኹ እኔ ጩኸታቸውን ፈጽሞ እሰማለሁ።” (ዘጸ. 22:22, 23) የአምላክ ሕግ የእነዚህን ልጆች ሰብዓዊ ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችል ደንብም የያዘ ነበር። (ዘዳ. 24:19-21) በክርስትና ሥርዓት ውስጥ እውነተኛ አምላኪዎች ‘ወላጆች የሌላቸውን ልጆች ባልቴቶችንም [“ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች፣” አ.መ.ት ] በመከራቸው እንዲጠይቁ’ ተመክረዋል። (ያዕ. 1:27) በአንድ ወላጅ በሚተዳደር ወይም በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ ለሚኖሩ ልጆች ፍቅራዊ አሳቢነት በማሳየት የይሖዋን ምሳሌ መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው?
2 መንፈሳዊ ሥልጠና:- ልጆቻችሁን ያለ እናት ወይም ያለ አባት የምታሳድጉ ወይም የማያምን የትዳር ጓደኛ ያላችሁ ወላጆች ከልጆቻችሁ ጋር አዘውትሮ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት አስቸጋሪ ሊሆንባችሁ ይችላል። ሆኖም ልጆቹ ሲያድጉ ሚዛናዊና የጎለመሱ ሰዎች እንዲሆኑ ከተፈለገ ቋሚ የሆነና የቤተሰቡን ፍላጎት ግምት ውስጥ ያስገባ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሊኖራችሁ ይገባል። (ምሳሌ 22:6) በየዕለቱ ከእነርሱ ጋር መንፈሳዊ ውይይት ማድረግም በጣም አስፈላጊ ነው። (ዘዳ. 6:6-9) አንዳንድ ጊዜ ይህን ኃላፊነት ልትወጡት እንደማትችሉ ይሰማችሁ ይሆናል፤ ሆኖም ተስፋ አትቁረጡ። “ልጆቻችሁን በጌታ ምክርና በተግሣጽ” ለማሳደግ በምታደርጉት ጥረት መመሪያና ድጋፍ እንዲሰጣችሁ ይሖዋን ጠይቁት።—ኤፌ. 6:4
3 ቅዱስ ጽሑፋዊ ኃላፊነቶቻችሁን ለመወጣት እርዳታ የሚያስፈልጋችሁ ከሆነ ሽማግሌዎችን አነጋግሩ። ተግባራዊ የሆኑ ሐሳቦች ሊያቀርቡላችሁ ወይም ለቤተሰባችሁ የሚሆን ጥሩ መንፈሳዊ ፕሮግራም እንድታወጡ ሊረዷችሁ ይችላሉ።
4 ሌሎች እርዳታ ሊያበረከቱ የሚችሉበት መንገድ:- በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖር የነበረው ጢሞቴዎስ በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤት ውስጥ ቢያድግም ቀናተኛ የይሖዋ አገልጋይ መሆን ችሏል። እናቱና አያቱ በልጅነቱ ቅዱሳን ጽሑፎችን ለማስተማር ያደረጉት ትጋት የተሞላበት ጥረት ለዚህ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳደረገ ምንም ጥርጥር የለውም። (ሥራ 16:1, 2፤ 2 ጢሞ. 1:5፤ 3:15) ይሁን እንጂ ጢሞቴዎስን ‘የምወደውና የታመነው በጌታ ልጄ የሆነው’ በማለት የጠራውን ሐዋርያው ጳውሎስን ጨምሮ ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር የነበረው ባልንጀርነትም ጠቅሞታል።—1 ቆሮ. 4:17
5 በተመሳሳይ ዛሬም በመንፈሳዊ የጎለመሱ ወንድሞችና እህቶች በጉባኤ ውስጥ ላሉት ወላጅ የሌላቸው ልጆች ፍቅራዊ አሳቢነት ማሳየታቸው ምንኛ ጠቃሚ ነው! እያንዳንዳቸውን በስማቸው ታውቋቸዋላችሁን? በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይና በሌሎች አጋጣሚዎችም ቀርባችሁ ታጫውቷቸዋላችሁን? በመስክ አገልግሎት አብረዋችሁ እንዲያገለግሉ ጋብዟቸው። አልፎ አልፎ ልጆቻቸውን ያለ አባት ወይም ያለ እናት የሚያሳድጉ አሊያም የማያምን የትዳር ጓደኛ ያላቸውን ወላጆችና ልጆቻቸውን በቤተሰብ ጥናታችሁ ወይም ጤናማ በሆኑ የመዝናኛ ፕሮግራሞች ላይ እንዲገኙ ልትጋብዟቸው ትችሉ ይሆናል። እነዚህ ልጆች እንደ ጓደኛቸው አድርገው የሚመለከቷችሁ ከሆነ ምሳሌነታችሁን መኮረጅና የምትሰጧቸውን ማበረታቻ መቀበል ይበልጥ ቀላል ይሆንላቸዋል።—ፊል. 2:4
6 ይሖዋ አባት ለሌላቸው ልጆች በጥልቅ ያስብላቸዋል፤ እኛም በፍቅር ተገፋፍተን እውነትን የራሳቸው እንዲያደርጉ ለመርዳት የምናደርገውን ጥረት እየባረከው ነው። በአንድ ወላጅ በሚተዳደሩ ወይም በሃይማኖት በተከፋፈሉ ቤተሰቦች ውስጥ ያደጉ ብዙ ወጣቶች እንደዚህ ዓይነት ማበረታቻ ስላገኙ አሁን አቅኚዎች፣ የጉባኤ አገልጋዮች፣ ሽማግሌዎች፣ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች፣ ሚስዮናውያን ወይም የቤቴል ቤተሰብ አባላት ሆነው በታማኝነት እያገለገሉ ነው። ሁላችንም ሰማያዊ አባታችንን በመምሰል አባት ለሌላቸው ልጆች ፍቅራችንን ‘የምናሰፋበት’ አጋጣሚ እንፈልግ።—2 ቆሮ. 6:11-13