ከሁሉ ለላቀው ሥራ የሚያስታጥቀን ትምህርት ቤት
1 ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ ያለሙት ግብ ላይ ለመድረስ ትምህርት ቤት ገብተው ይማራሉ። ይሁን እንጂ ሕይወት ሰጪ የሆነውን አምላክ ከማወደስና ሰዎች ዓላማዎቹንና መንገዶቹን እንዲማሩ ከመርዳት የተሻለ ምን ግብ ሊኖር ይችላል? ምንም ግብ ሊኖር አይችልም። የቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ዓላማ ሌሎችን ስለ እምነታችን ለማስተማር እኛን ማሰልጠን ነው። ስለሆነም በየሳምንቱ በትምህርት ቤቱ ላይ ስንገኝ በሕይወታችን ውስጥ የላቀ ቦታ ለምንሰጠው ሥራ የሚያስታጥቀንን ጥበብ እንቀስማለን።
2 “የ2003 ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ፕሮግራም” ባለፈው ወር የመንግሥት አገልግሎታችን እትም ውስጥ ይገኛል። ፕሮግራሙ ትምህርት ቤቱ እንዴት እንደሚካሄድ የሚገልጽ ዝርዝር መመሪያም ይዟል። በየሳምንቱ በሚካሄደው በዚህ ትምህርት ቤት ላይ ስትገኝ ፕሮግራሙ እንዳይለይህ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም በተባለው መጽሐፍህ ውስጥ ብታስቀምጠው ጥሩ ሊሆን ይችላል። የ2003 ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት አንዳንድ ገጽታዎችን እስኪ እንመልከት።
3 የንግግር ባሕርይ:- ከጥር ጀምሮ በየሳምንቱ አንድን የንግግር ባሕርይ ወይም የንባብ፣ የጥናት አሊያም የማስተማር ችሎታን ማሻሻል የሚቻልበትን መንገድ የሚዳስስ የአምስት ደቂቃ ንግግር በትምህርት ቤቱ ይቀርባል። ይህን የመክፈቻ ንግግር የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች ያቀርበዋል ወይም ጥሩ ችሎታ ያለው ሌላ ሽማግሌ እንዲያቀርበው ሊያደርግ ይችላል። ክፍሉን የሚያቀርበው ወንድም የንግግር ባሕርይውን ትርጉምና ይህን ባሕርይ ማዳበር አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት ይገልጻል። ከዚያም ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌዎችን በመጥቀስ፣ እንዴት ሊሠራበት እንደሚችል በማስረዳትና ይህን ማድረጉ በአገልግሎት የሚኖረንን ውጤታማነት በማሻሻል ረገድ ያለውን ድርሻ በማብራራት ትምህርቱን ማስፋት ይችላል።
4 ክፍል ቁ. 1:- ከዚህ ቀደም እንደተጠቆመው ማስተማሪያ ንግግሩን የሚያቀርቡ ወንድሞች “በትምህርቱ ተግባራዊ ጠቀሜታ ላይ ማተኮር” ይኖርባቸዋል። እንዲህ ሲባል ጉባኤው ትምህርቱን እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚችል መግለጽ ይኖርባቸዋል ማለት ነው። ይህ ክፍል ከተሰጠህ እንዴት መዘጋጀት እንደምትችል ለማወቅ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መማሪያ መጽሐፍ ከገጽ 48-49ን አንብብ፤ እንዲሁም በመጽሐፉ ማውጫ ውስጥ “የትምህርቱ ጥቅም” በሚለው ርዕስ ሥር የተጠቀሱትን ገጾች አውጥተህ አጥናቸው።
5 የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራም:- ከዚህ ቀደም የሳምንቱን የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ዘወትር በማንበብ ረገድ አልተሳካልህ ከሆነ ለዚህ ዓመት የወጣው ፕሮግራም አንድም ሳያመልጥህ ለማንበብ ለምን ቁርጥ ውሳኔ አታደርግም? እንዲህ የሚያደርጉ በዓመቱ መጨረሻ ላይ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችን አንብበው ይጨርሳሉ። መጽሐፍ ቅዱስን አንብቦ ለመጨረስ ንባቡን ከክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች መጀመር ምን ጥቅሞች እንዳሉት በአገልግሎት ትምህርት ቤት መማሪያ መጽሐፍ ገጽ 10 አንቀጽ 4 ላይ ተገልጿል።
6 የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ጎላ ያሉ ነጥቦች:- አድማጮች ለሳምንቱ በተመደበው የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ላይ ሐሳብ መስጠት እንዲችሉ ሲባል ይህ ክፍል ወደ አሥር ደቂቃ እንዲራዘም ተደርጓል። ይህን ክፍል እንዲያቀርቡ የተመደቡ ወንድሞች ሰዓት ማሳለፍ አይኖርባቸውም። ክፍሉ የቃል ክለሳ የሚደረግበትን ሳምንት ጨምሮ በእያንዳንዱ ሳምንት ይቀርባል። ለሳምንቱ የተመደቡትን ምዕራፎች በምታነቡበት ጊዜ ለቤተሰብ ጥናታችሁ፣ ለአገልግሎታችሁ ወይም ለግል ሕይወታችሁ የሚጠቅሟችሁን ነጥቦች ለማግኘት ሞክሩ። ይሖዋ ከሰዎች ወይም ከብሔራት ጋር ባደረገው ግንኙነት ያንጸባረቃቸው ባሕርያት የትኞቹ ናቸው? እምነታችሁን የሚያጠናክርና ለይሖዋ ያላችሁን አድናቆት ከፍ የሚያደርግ ምን ትምህርት አግኝታችሁበታል? ክፍል ቁጥር 2ን የሚያቀርበው ወንድም በሚያነባቸው ቁጥሮች ላይ ማብራሪያ ስለማይሰጥ እነርሱን ጨምሮ ለሳምንቱ በተመደቡት ምዕራፎች ላይ ሐሳብ መስጠት ትችላለህ።
7 ክፍል ቁ. 2:- በየሳምንቱ በሚቀርበው የመጀመሪያው የተማሪ ክፍል አማካኝነት ለሌሎች የማንበብ ልምምድ ይደረጋል። በእያንዳንዱ ወር በመጨረሻው ሳምንት ላይ ከሚቀርበው ንባብ በስተቀር ሁሉም የሚቀርበው ከሳምንቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ላይ ነው። በወሩ የመጨረሻ ሳምንት ላይ ንባብ የሚቀርበው ከመጠበቂያ ግንብ ይሆናል። ተማሪው ክፍሉን ያለ መግቢያ ወይም ያለ መደምደሚያ በንባብ ብቻ ማቅረብ ይኖርበታል። ተማሪው በዚህ መንገድ በዋነኛነት የሚያተኩረው የንባብ ችሎታውን በማሻሻል ላይ ይሆናል።—1 ጢሞ. 4:13
8 ክፍል ቁጥር 3 እና 4:- ከእነዚህ ክፍሎች መካከል አንዳንዶቹ ከማመራመር መጽሐፍ ላይ የተወሰዱ በርከት ያሉ አንቀጾችን ያካተቱ ናቸው። ሌሎቹ ደግሞ ጭብጡን ብቻ የያዙ ናቸው። ክፍሉ በጣም አጭር በሚሆንበት ወይም ጭብጡ ብቻ በሚመደብበት ጊዜ ተማሪዎቹ በክርስቲያናዊ ጽሑፎቻችን ላይ ምርምር በማድረግ ንግግራቸውን ለማዳበር የሚያስችላቸውን ተጨማሪ ሐሳብ ማግኘት ይችላሉ። እንዲህ ያለው አጋጣሚ እህቶች ክፍሉን ከረዳቶቻቸው ሁኔታ ጋር አስማምተው እንዲያዘጋጁ ያስችላቸዋል።
9 መቼቶች:- በአገልግሎት ትምህርት ቤት መማሪያ መጽሐፍ ገጽ 45 ላይ እንደተገለጸው የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች ክፍሉ የሚቀርብበትን መቼት ይሰጥ ይሆናል። ይህ ካልሆነ ግን እህቶች በገጽ 82 ላይ ከተዘረዘሩት መቼቶች መካከል አንዱን መምረጥ ይችላሉ። አንዲት እህት በሁለት ወር አንድ ጊዜ ክፍል የማቅረብ ተራ የሚደርሳት ከሆነ 30ዎቹን መቼቶች ሳትደጋግም ለአምስት ዓመት ልትጠቀምባቸው ትችላለች። በተራ ቁጥር 30 ላይ የሚገኘውን “ለጉባኤው ክልል ተስማሚ የሆነ ሌላ መቼት” የሚለውን ለመጠቀም የመረጡ እህቶች መቼታቸውን በክፍል መስጫው ቅጽ (S-89) ግርጌ ላይ ወይም በጀርባው በኩል መጻፍ ይኖርባቸዋል። የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች ተማሪዋ ክፍልዋን ያቀረበችበትን ዕለት በራስዋ መጽሐፍ ገጽ 82 ላይ ክፍልዋን ለማቅረብ ከተጠቀመችበት መቼት ጎን ባለው ቦታ ላይ ይጽፋል። በተማሪዋ ምክር መስጫ ቅጽ ላይ ምልክት ሲያደርግ ይህንንም በዚያው ማድረግ ይችላል።
10 ምክር መስጫ ነጥቦችን የያዘ ቅጽ:- ምክር መስጫ ነጥቦችን የያዘው ቅጽ በመጽሐፍህ ውስጥ ከገጽ 79-81 ላይ ይገኛል። ስለሆነም ክፍል ባቀረብክ ቁጥር መጽሐፍህን ለትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች መስጠት ይኖርብሃል። የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች ተማሪዎቹ በየትኞቹ የምክር መስጫ ነጥቦች ላይ እየሠሩበት እንዳሉ የሚገልጽ መረጃ ሊኖረው ይገባል።
11 የቃል ክለሳ:- የቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ክለሳ የሚቀርበው በቃል ይሆናል። ክለሳው የሚደረገው በሁለት ወር አንድ ጊዜ ሲሆን ለ30 ደቂቃ ይካሄዳል። የክለሳው ጥያቄዎች ከዚህ ቀደም ይደረግ እንደነበረው በመንግሥት አገልግሎታችን ላይ ይወጣሉ። ክለሳው የወረዳ ስብሰባ በሚደረግበት ወይም የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ጉባኤውን በሚጎበኝበት ሳምንት ላይ በሚውልበት ጊዜ የቀጣዩን ሳምንት ክፍሎች ከክለሳው ጋር አቀያይሮ መውሰድ ይቻላል።
12 በተጨማሪ አዳራሾች የሚቀርቡ ክፍሎች:- በትምህርት ቤቱ ከ50 በላይ ተማሪዎች ባሉባቸው ጉባኤዎች ውስጥ ሽማግሌዎች የተማሪ ክፍሎች የሚያቀርቡባቸው ተጨማሪ አዳራሾች ሊያዘጋጁ ይችላሉ። “በእነዚህ አዳራሾች ውስጥ ሁሉም የተማሪ ክፍሎች ወይም የመጨረሻዎቹ ሁለቱ ብቻ ሊቀርቡ ይችላሉ።” (የአገልግሎት ትምህርት ቤት፣ ገጽ 285) የመጨረሻዎቹ ሁለቱ ብቻ የሚቀርቡበት ዝግጅት የሚደረገው በጉባኤው ውስጥ ያሉት ክፍል የሚያቀርቡት እህቶች ብዙ ሆነው ሳለ ሁለተኛውን የተማሪ ክፍል የሚያቀርቡ ወንድሞች አነስተኛ በሚሆኑበት ጊዜ ነው። ሽማግሌዎች በተጨማሪ አዳራሽ ለሚቀርቡ ክፍሎች ምክር የሚሰጡ ጥሩ ችሎታ ያላቸው ወንድሞች መምረጥ ይኖርባቸዋል።
13 ረዳት ምክር ሰጪ:- በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ፕሮግራም ላይ እንደተገለጸው ረዳት ምክር ሰጪ ሆኖ የሚያገለግለው ወንድም የሚመረጠው በሽማግሌዎች አካል ሲሆን ኃላፊነቱም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ጎላ ያሉ ነጥቦችንና ማስተማሪያ ንግግሩን ለሚያቀርቡ ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች በግል ምክር መስጠት ነው። ይህ ኃላፊነት ልምድ ላለውና ምክሩ ተቀባይነት ሊያገኝ ለሚችል ወንድም መሰጠት ይኖርበታል። ረዳት ምክር ሰጪው ገንቢ ምክር መስጠት እንዲሁም የንግግሩን ጥሩ ጎንና የማስተማሪያ ዘዴዎችን ተከታትሎ ማመስገን ይኖርበታል። በተጨማሪም መሻሻል የሚያስፈልጋቸውን አንድ ወይም ሁለት ነጥቦችን መጠቆም ያስፈልገዋል። አዘውትሮ ክፍል ለሚያቀርብ ወንድም ንግግር ባቀረበ ቁጥር ምክር መስጠት አያስፈልግም። ይሁን እንጂ ምክር ሰጪው፣ የሕዝብ ንግግር የሚያቀርቡ ወንድሞች እንኳን ምክር ቢሰጣቸው ተጨማሪ እድገት ሊያደርጉ እንደሚችሉ መዘንጋት አይኖርበትም።—1 ጢሞ. 4:15
14 ምክር ሰጪዎች መከታተል የሚኖርባቸው ነገር:- አንድ ምክር ሰጪ ንግግሩ ጥሩ መሆን አለመሆኑን ለመወሰን ምን ሊረዳው ይችላል? የአገልግሎት ትምህርት ቤት መማሪያ መጽሐፍ ካሉት 53 ምዕራፎች መካከል አብዛኞቹ በሦስተኛው ሣጥናቸው ውስጥ ምን ነገር መከታተል እንዳለበት የሚጠቁም ጠቅለል ያለ ሐሳብ ይዘዋል። ከዚህም በተጨማሪ የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች ንግግሩ በጥሩ ሁኔታ የዳበረና አቀራረቡም ውጤታማ መሆኑን ቶሎ ለማወቅ የሚረዱትን መጽሐፉ የያዛቸውን ሌሎች ማሳሰቢያዎች ወይም ሐሳቦች ትኩረት ሰጥቶ ሊያጠናቸው ይገባል። ለምሳሌ ያህል ገጽ 55 ላይ የሚገኙትን ተከታታይ ጥያቄዎችና ገጽ 163 ሦስተኛው አንቀጽ ላይ የሚገኙትን ሐሳቦች ተመልከት።
15 ክፍት ቦታዎችን ተጠቀምባቸው:- የአገልግሎት ትምህርት ቤት መማሪያ መጽሐፍ ሰፋፊ ከሆኑ ኅዳጎች በተጨማሪ ከግል ጥናትና ከቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የምታገኛቸውን ጠቃሚ ነጥቦች ማስታወሻ ለመያዝ የሚያስችሉ ክፍት ቦታዎች አሉት። (ገጽ 77፣ 92፣ 165፣ 243፣ 246ን እና 250ን ተመልከት) በየሳምንቱ በትምህርት ቤቱ ላይ በምትገኝበት ጊዜ ይህ መጽሐፍ ሊለይህ አይገባም። የመክፈቻው ንግግር በሚቀርብበት ጊዜ አውጥተህ ተከታተል። ቀሪው የትምህርት ቤቱ ፕሮግራም በሚቀርብበት ጊዜም መጽሐፍህን እንደገለጥህ መከታተል ይኖርብሃል። የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች ምክር በሚሰጥበት ጊዜ ማስታወሻ ያዝ። ተናጋሪዎች የሚጠቀሙባቸውን የማስተማሪያ ዘዴዎች፣ ጥያቄዎች፣ ምሳሌዎች፣ ዘይቤዎች፣ ንጽጽሮችንና ሌሎች መንገዶችን በትኩረት ተከታተል። ጥሩ ማስታወሻ የምትይዝ ከሆነ ከትምህርት ቤቱ የምትቀስማቸውን ግሩም የሆኑ ነጥቦች ማስታወስና በሥራ ላይ ማዋል ትችላለህ።
16 ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ሰው የአምላክን መንግሥት ምሥራች ከመስበክ የበለጠ ምንም መብት ሊሰጠው እንደማይችል ጠንቅቆ ያውቅ ነበር። የእርሱም ዋነኛ ተልእኮ ይህ ነበር። (ማር. 1:38) “ስለዚህ ተልኬአለሁና ለሌሎቹ ከተማዎች ደግሞ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል እሰብክ ዘንድ ይገባኛል” በማለት ተናግሯል። (ሉቃስ 4:43) እርሱ ያቀረበላቸውን ግብዣ ተቀብለው እንደተከተሉት ሌሎች ሰዎች ሁሉ እኛም ምሥራቹን በመስበኩ ሥራ መጠመድ እንፈልጋለን። እንዲሁም የምናቀርበው ‘የምሥጋና መሥዋዕት’ ጥራቱ እየተሻሻለ እንዲሄድ ጥረት ከማድረግ ወደኋላ አንልም። (ዕብ. 13:15) እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ በሕይወታችን ውስጥ የላቀ ቦታ ለምንሰጠው ሥራ እኛን ለማሰልጠን በተዘጋጀው በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት አዘውትረን ለመገኘትና ተሳትፎ ለማድረግ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።