ራሳችንን ስንወስን ከገባነው ቃል ጋር ተስማምቶ መኖር
1 የተጠመቅኸው በቅርቡም ይሁን ከረጅም ጊዜ በፊት በሕይወትህ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የጀመርክበትን ይህን ዕለት እንደምታስታውሰው የታወቀ ነው። ጥምቀት በሕይወት ዘመናችን ሁሉ በሙሉ ልብ ለምናቀርበው አገልግሎት የመጀመሪያ እርምጃ እንጂ የመጨረሻው አይደለም። (1 ዮሐ. 2:17) ራሳችንን ስንወስን ከገባነው ቃል ጋር ተስማምቶ መኖር ምን ምን ነገሮችን ይጨምራል?
2 የኢየሱስን ምሳሌ መከተል:- ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ ‘የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል’ ‘ማስተማር ጀመረ።’ (ሉቃስ 3:23፤ 4:43) እኛም ራሳችንን ለይሖዋ መወሰናችንን በውኃ ጥምቀት ባሳየንበት ወቅት የተሾምን የምሥራቹ አገልጋዮች ሆነናል። ለሕይወት የሚያስፈልጉንን ቁሳዊ ነገሮች ለማሟላት ብዙ ጊዜና ጥረት የሚጠይቅብን ቢሆንም ዋነኛው ሥራችን ግን ክርስቲያናዊ አገልግሎታችን ነው። (ማቴ. 6:33) ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ሰዎች ሀብት ወይም ዝና ለማግኘት ከመጣጣር ይልቅ ልክ እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ‘አገልግሎታቸውን ለማክበር’ ይፈልጋሉ። (ሮሜ 11:13) ያገኘኸውን ይሖዋን የማገልገል ልዩ መብት ታደንቃለህን? እርሱን ለማገልገልስ የሚቻልህን ሁሉ ታደርጋለህ?
3 እኛም እንደ ኢየሱስ ‘ዲያብሎስን መቃወም’ አለብን። (ያዕ. 4:7) ሰይጣን ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው እንደፈተነው ሁሉ በአሁኑ ጊዜም ራሳቸውን የወሰኑ የይሖዋ አገልጋዮችን የጥቃቱ ዒላማ ያደርጋቸዋል። (ሉቃስ 4:1-13) የምንኖረው ሰይጣን በሚቆጣጠረው ዓለም ውስጥ ስለሆነ ራሳችንን በመገሠጽ አእምሯችንንና ልባችንን ሊበክል ከሚችል ከማንኛውም ነገር መራቅ አለብን። (ምሳሌ 4:23፤ ማቴ. 5:29, 30) ክርስቲያኖች “ከጌታ ማዕድና ከአጋንንት ማዕድ” መካፈል እንደማይችሉ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል። (1 ቆሮ. 10:21) ይህ ደግሞ ከመጥፎ የመዝናኛ ዓይነቶች፣ ከክፉ ባልንጀርነትና በኢንተርኔት ከሚተላለፉ ጎጂ ነገሮች ራስን መጠበቅን ይጠይቃል። እንዲሁም በከሃዲዎች ከሚዘጋጁ ጽሑፎች መራቅን ይጨምራል። እነዚህንና እነዚህን የመሳሰሉ ሌሎች የሰይጣን ዘዴዎችን አውቀን መጠንቀቃችን ራሳችንን ስንወስን ከገባነው ቃል ጋር ተስማምተን ለመኖር ይረዳናል።
4 አምላክ ባደረገልን ዝግጅቶች መጠቀም:- ይሖዋ ራሳችንን ስንወስን ከገባነው ቃል ጋር ተስማምተን እንድንኖር በቃሉና በክርስቲያን ጉባኤ አማካኝነት ይረዳናል። መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብና ወደ ይሖዋ መጸለይን የዕለት ተዕለት ልማድህ አድርግ። (ኢያሱ 1:8፤ 1 ተሰ. 5:17) በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት የሚያስደስትህ ይሁን። (መዝ. 122:1) ይሖዋን ከሚፈሩና ትእዛዛቱን ከሚጠብቁ ጋር ተቀራረብ።—መዝ. 119:63
5 ይሖዋ በሚያደርግልህ እርዳታ ራስህን ለእርሱ ስትወስን ከገባኸው ቃል ጋር ተስማምተህ መኖርና እርሱን ለዘላለም በማገልገል የሚገኘውን ደስታ ማጨድ ትችላለህ።—መዝ. 22:26, 27፤ ፊልጵ. 4:13