ዓለም አቀፍ የመንግሥት አዳራሽ ግንባታ በአንዳንድ የአውሮፓ አገሮች
1 ባለፉት አሥርተ ዓመታት ምሥራቅ አውሮፓን ጨምሮ በበርካታ የአውሮፓ አገራት የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ ታግዶ ነበር። በአብዛኞቹ አገሮች በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የተጣለው እገዳ በጣም ጥብቅ ነበር። በይፋ መሰብሰብ የማይቻል ከመሆኑም በላይ የመንግሥት አዳራሽ መሥራት ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነበር። ይሁን እንጂ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ “እግዚአብሔር ታላቅ ነገርን አደረገልን፣ ደስም አለን” የሚለው ጥቅስ ፍጻሜውን እያገኘ ነው።—መዝ. 126:3
2 ከ1983 ጀምሮ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የተጣለው እገዳ እየላላ መጣ። በ1989 የፖላንድና የሃንጋሪ መንግሥታት ለይሖዋ ምሥክሮች ሕጋዊ እውቅና ሰጡ። በ1991 ደግሞ በሩሲያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ሕጋዊ እውቅና አገኙ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በሩሲያና በቀድሞዋ ሶቭዬት ሕብረት ሥር በነበሩ አገሮች ውስጥ የስብከቱ ሥራ ከፍተኛ ዕድገት አድርጓል። ከመጋቢት 1996 እስከ ጥቅምት 1998 ባለው ጊዜ ውስጥ የአስተዳደር አካሉ 11 የአውሮፓ አገሮችን በበላይነት የሚቆጣጠሩት ቅርንጫፍ ቢሮዎች ላቀረቧቸው 359 የመንግሥት አዳራሽ ግንባታ የብድር ጥያቄዎች ፈቃድ ሰጥቷል።
3 በዚህ አባሪ ጽሑፍ ላይ ያሉትን ፎቶግራፎች ስትመለከት ይሖዋ ለሕዝቦቹ ምን ያህል ታላቅ ሥራ እየሠራ እንዳለ ልታስብ ትችላለህ። (መዝ. 136:4) ኢየሱስ በዮሐንስ 13:35 ላይ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” ሲል የተናገረውን ተግባራዊ በማድረግ በዓለም ዙሪያ ያሉ ወንድሞች የሚሰጡት የገንዘብ መዋጮ በአግባቡ ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑን ስታውቅ ደስ እንደሚልህ ግልጽ ነው።
4 የገንዘብ አቅማቸው ውስን የሆኑ አገሮች የመንግሥት አዳራሽ መገንባት እንዲችሉ ለመርዳት ከተደረገው ዝግጅት ተጠቃሚ ከሆኑ የአውሮፓ አገሮች አንዷ ሩማኒያ ስትሆን በዚህች አገር ከሐምሌ 2000 ጀምሮ ባለው ጊዜ ውስጥ 36 የመንግሥት አዳራሾች ተገንብተዋል። በዩክሬን ለአብዛኞቹ የመንግሥት አዳራሾች ተመሳሳይ የግንባታ ፕላን በመጠቀም በ2001 61 የመንግሥት አዳራሾች የተገነቡ ሲሆን በ2002 ደግሞ ተጨማሪ 76 አዳራሾች ተሠርተዋል። ለመንግሥት አዳራሽ ግንባታ በሚደረገው መዋጮ በመጠቀም በመቄዶንያ፣ በሞልዶቫ፣ በሞንቴኔግሮ፣ በሩሲያ፣ በሰርቢያ፣ በቡልጋሪያ እና በክሮኤሺያ በመቶዎች የሚቆጠሩ የመንግሥት አዳራሾች ተገንብተዋል።
5 በአንዳንድ አገሮች የመንግሥት አዳራሽ መገንባት ብዙ ውጣ ውረድ ይጠይቃል። አብዛኛውን ጊዜ ይህ ሂደት ጊዜ የሚወስድ ከመሆኑም በላይ በእነዚህ የአውሮፓ አገሮች የመንግሥት አዳራሽ መገንባት በአብዛኞቹ የአፍሪካ ወይም የደቡብ አሜሪካ አገሮች ውስጥ አዳራሽ መገንባት ከሚጠይቀው የበለጠ ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃል። ይሁን እንጂ ይሖዋን የሚያመልኩ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ መጠን እየጨመረ በመሆኑ የገንዘብ አቅማቸው ውስን በሆኑ የአውሮፓ አገሮች ውስጥ አሁንም በመቶዎች የሚቆጠሩ የመንግሥት አዳራሾች ያስፈልጋሉ።
6 በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ የመንግሥት አዳራሾች እየተገነቡ እንዳሉ መመልከቱ ምንኛ የሚያስደስት ነው! የተለያዩ ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት የአዳራሾቹ ግንባታ በአካባቢው ለሚኖሩ ሰዎች ግሩም ምሥክርነት ሰጥቷል። ወንድሞች የአካባቢውን የግንባታ ፈቃድ ተከትለው አዳራሾቹን በመገንባት ረገድ ባሳዩት ትብብር በአንዳንድ ቦታዎች ያሉ ባለሥልጣናት በጣም ተደንቀዋል።
7 ኢሳይያስ በዚህ ዘመን እውነተኛው አምልኮ እንደሚስፋፋ በትክክል ተንብዮአል። አምላክ በነቢዩ አማካኝነት “እኔ እግዚአብሔር በዘመኑ ይህን አፋጥነዋለሁ” ሲል ተናግሯል። (ኢሳ. 60:22) በእርግጥም ባለፉት አሥር ዓመታት ይሖዋ በምሥራቅ አውሮፓ ከፍተኛ ጭማሪ እንዲገኝ አድርጓል። ለመንግሥት አዳራሽ ግንባታ መዋጮ በማድረግ በብዙ አገሮች የሚካሄደውን የግንባታ ሥራ ለማፋጠን የምናደርገውን ጥረት ይሖዋ አብዝቶ መባረኩን እንዲቀጥል ምኞታችን ነው! ይህም የገንዘብ አቅማቸው ውስን በሆኑ አገሮች ውስጥ ብዙ ተጨማሪ የመንግሥት አዳራሾች እንዲገነቡ አስተዋጽኦ ያደርጋል። እንዲሁም በበርካታ የአውሮፓ አገሮች ንጹህ አምልኮ እንዲስፋፋና ምሥክርነቱ “እስከ ምድር ዳርቻ” እንዲዳረስ ያስችላል።—ሥራ 13:47
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በሞስኮ፣ ሩሲያ የተገነባው የመንግሥት አዳራሽ
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በምሥራቅ አውሮፓ የተገነቡ
አዳዲስ የመንግሥት አዳራሾች
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ስትሩሚሳ፣ መቄዶንያ
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዳሩቫር፣ ክሮኤሺያ
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሶካል፣ ለቪቭ አውራጃ፣ ዩክሬን
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቢቶልያ፣ መቄዶንያ
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሶፊያ፣ ቡልጋሪያ
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ፕሎቭዲፍ፣ ቡልጋሪያ
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክራስኖኪትያብሪስኪ፣ ማይኮፕ፣ ሩሲያ
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ባትቻካ ፒትሮቫትዝ፣ ሰርቢያ እና ሞንቴኔግሮ
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ትሉማክ፣ ኢቫኖ-ፍራንኪቭስክ አውራጃ፣ ዩክሬን
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ራቫ-ሩስካ፣ ለቪቭ አውራጃ፣ ዩክሬን
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ስታራ ፓዞቫ፣ ሰርቢያ እና ሞንቴኔግሮ
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዜኔትሳ፣ ቦስኒያ እና ሄርዞጎቪና
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሶካል፣ ለቪቭ አውራጃ፣ ዩክሬን
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዜዳቺቭ፣ ለቪቭ አውራጃ፣ ዩክሬን