የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • km 6/03 ገጽ 3-4
  • ‘የምሥክርነቱን ሥራ’ በትጋት አከናውኑ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ‘የምሥክርነቱን ሥራ’ በትጋት አከናውኑ
  • የመንግሥት አገልግሎታችን—2003
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት ለመስጠት ዝግጁ ናችሁ?
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2009
  • መደበኛ ባልሆነ መንገድ መመሥከር ትችላላችሁ!
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2010
  • ‘የተሟላ ምሥክርነት ስጡ’
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2013
  • ምሥራቹን በሚገባ ለመመሥከር ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2008
ለተጨማሪ መረጃ
የመንግሥት አገልግሎታችን—2003
km 6/03 ገጽ 3-4

‘የምሥክርነቱን ሥራ’ በትጋት አከናውኑ

1, 2. ጳውሎስ በስብከቱ ሥራ ረገድ ከነበረው አመለካከት ምን ትምህርት አግኝተሃል? ምሳሌውን መኮረጅ የምንችለውስ እንዴት ነው?

1 ኢየሱስና በጥንት ዘመን የነበሩ በርካታ ታማኝ አገልጋዮች እንዳደረጉት ሁሉ ሐዋርያው ጳውሎስም በማንኛውም ሁኔታ ሥር ‘ምሥክርነት በመስጠት’ ረገድ ቀናተኛ የምሥራቹ ሰባኪ ነበር። ጳውሎስ የቁም እስረኛ እያለም እንኳ “ወደ እርሱም የሚመጡትን ሁሉ ይቀበል ነበር፤ . . . የእግዚአብሔርን መንግሥት እየሰበከ ስለ ጌታ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እጅግ ገልጦ ያስተምር ነበር።”​—⁠ሥራ 28:16-31

2 እኛም በማንኛውም ጊዜ ‘የምሥክርነቱን ሥራ’ በትጋት ማከናወን እንችላለን። ይህም በምንሄድበት ቦታ ሁሉ መስበክን ይጨምራል።​—⁠ሥራ 28:23፤ መዝ. 145:​10-13

3. መደበኛ ባልሆነ መንገድ የምንሰጠው ምሥክርነት የአጋጣሚ ምሥክርነት ሊባል የማይችለው ለምንድን ነው?

3 የአጋጣሚ ምሥክርነት ወይስ መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት? ልዩነት አላቸው? አዎ፣ አላቸው። በአጋጣሚ የሚሆን ነገር አስቀድሞ ያልታሰበበት ወይም እምብዛም ቦታ ያልተሰጠው ነው። አገልግሎታችንን በተመለከተ እንዲህ ማለት አይቻልም። እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ሁሉ ምሥራቹን በመስበክ አምላክን ማክበር ትልቅ ቦታ የምንሰጠው ሥራ በመሆኑ አመቺ በሆነ በማንኛውም አጋጣሚ ለመመሥከር ዝግጁዎች መሆን ይገባናል። ሆኖም ከሰዎች ጋር ውይይት የምንጀምረው በጭውውት መልክ፣ ዘና ባለ ሁኔታና ወዳጃዊ በሆነ መንገድ ስለሆነ እንደዚህ ዓይነቱ ምሥክርነት መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት ሊባል ይችላል። በዚህ መንገድ ሰዎችን ማነጋገራችን ጥሩ ውጤት ያስገኛል።

4. ጳውሎስ በመኖሪያ ቤቱ ሆኖ መመሥከር የቻለው እንዴት ነው?

4 ለመመሥከር ዝግጁ ሁኑ:- ጳውሎስ በሮም የቁም እስረኛ በነበረበት ወቅት ለመመሥከር የሚያስችሉትን አጋጣሚዎች ይፈልግ ነበር። የአይሁድ መሪዎችን ወደ ቤቱ እንዲመጡ ጋብዟቸዋል። (ሥራ 28:17) ምንም እንኳን ሮም ውስጥ የክርስቲያን ጉባኤ የነበረ ቢሆንም ጳውሎስ በዚያ የነበረው የአይሁድ ኅብረተሰብ ስለ ክርስትና እምነት እምብዛም እንደማያውቅ ተገንዝቦ ነበር። (ሥራ 28:22፤ ሮሜ 1:7) በመሆኑም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስና ስለ አምላክ መንግሥት ‘መሥክሮላቸዋል።’

5, 6. መደበኛ ባልሆነ መንገድ የምንመሠክርባቸው ምን አጋጣሚዎች ሊኖሩ ይችላሉ? በዚህ ረገድ ውጤታማ ለመሆን ምን ዝግጅት ማድረግ እንችላለን?

5 በተለያየ አጋጣሚ የምታገኛቸውን ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ብዙም የማያውቁ በርካታ ሰዎች እስቲ አስብ። ሌላው ቀርቶ መጽሐፍ ቅዱስን በነፃ እንደምናስጠና እንኳ ላያውቁ ይችላሉ። ስትጓዝ፣ ስትገበይ፣ በሆቴል ስታርፍ፣ በምግብ ቤት ውስጥ ስትመገብ፣ በሕዝብ መጓጓዣዎች ስትጠቀምና በመሳሰሉት ቦታዎች ለምታገኛቸው ሰዎች ለመመሥከር የሚያስችሉህን አጋጣሚዎች ተጠቀምባቸው። ምን ብለህ ውይይት እንደምትጀምርና እንዴት አድርገህ አጠር ያለ ምሥክርነት መስጠት እንደምትችል አስቀድመህ አስብበት። ለጐረቤቶችህ፣ ለዘመዶችህ፣ ለሥራ ባልደረቦችህና ለምታውቃቸው ሌሎች ሰዎች መደበኛ ባልሆነ መንገድ በመመሥከር መለማመድ ትችል ይሆናል።

6 መደበኛ ባልሆነ መንገድ ስትመሠክር የምታበርክታቸው ጽሑፎች መያዝ ያስፈልግሃል። የትኞቹን ጽሑፎች ልትይዝ ትችላለህ? ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ ማወቅ ትፈልጋለህ? በተባለው ትራክት ልትጠቀም ትችላለህ። መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ አስፈላጊ የሆነባቸውን የተለያዩ ምክንያቶች በሚዘረዝሩት በመጀመሪያዎቹ አምስት አንቀጾች ላይ አተኩር። ነፃ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲመራላቸው ከፈለጉ ከጀርባ ያለውን ቅጽ መሙላት እንደሚችሉ ንገራቸው። ፍላጎት ያለው ሰው ካገኘህ አምላክ ከእኛ የሚፈልገው የተባለውን ብሮሹር አበርክትለት። በትራንስፖርት የምትጓዝ ከሆነ ለመንግሥቱ መልእክት ልባዊ ፍላጎት ለሚያሳዩ ሰዎች የምታበረክታቸው ሌሎች ጽሑፎችም መያዝ ትችል ይሆናል።

7, 8. በጉዞ ላይ በምንሆንበትም ሆነ በምንዝናናባቸው ጊዜያት አለባበሳችንንና ምግባራችንን በተመለከተ ምን ጥንቃቄ ማድረግ አለብን?

7 አለባበስህና ምግባርህ:- አለባበሳችንም ሆነ ምግባራችን ሰዎች ስለ ይሖዋ ድርጅት የተሳሳተ አመለካከት እንዲያድርባቸው ወይም ‘ክፉ እንዲናገሩ’ የሚያደርግ እንዳይሆን መጠንቀቅ ይኖርብናል። (ሥራ 28:22 አ.መ.ት ) ይህ ደግሞ በስብሰባ ላይ ስንገኝ ወይም አገልግሎት ስንወጣ ብቻ ሳይሆን በጉዞ ላይ በምንሆንበትና በምንዝናናበት ጊዜም ሊታሰብበት ይገባል። የነሐሴ 1, 2002 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 18፣ አንቀጽ 14 እንዲህ የሚል ማሳሰቢያ ይሰጣል:- “አለባበሳችን ለታይታ የሚደረግ፣ ቅጥ ያጣ፣ ለወሲብ የሚጋብዝ፣ ዕርቃንን የሚያሳይ ወይም ዘመን አመጣሽ መሆን የለበትም። በተጨማሪም አለባበሳችን ‘አምላክን ለሚያመልኩ’ ሰዎች የሚገባ መሆን አለበት። ይህ ልናስብበት የሚገባ ጉዳይ ነው፤ አይደለም እንዴ? በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ስንገኝ በሥርዓት እንለብሳለን በሌሎች ጊዜያት ግን እንዳሻን እንሆናለን ማለት አይደለም። በቀን ውስጥ የ24 ሰዓት ክርስቲያን አገልጋዮች በመሆናችን አለባበሳችን ምንጊዜም የሚያስከብር መሆን አለበት።”​—⁠1 ጢ⁠ሞ. 2:9, 10

8 አለባበሳችን ጨዋነት የሚንጸባረቅበትና የሚያስከብር መሆን አለበት። አለባበሳችንና ምግባራችን ምንጊዜም ከክርስቲያናዊ እምነታችን ጋር የሚስማማ ከሆነ በማንኛውም ጊዜ መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት ለመስጠት አናፍርም።​—⁠1 ጴ⁠ጥ. 3:15

9. ጳውሎስ በሮም የሰጠው ምስክርነት ምን ውጤት አስገኝቷል?

9 መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት ፍሬ ያስገኛል:- ጳውሎስ የቁም እስረኛ ሆኖ በሮም ባሳለፋቸው ሁለት ዓመታት ለመመሥከር ያደረገው ጥረት ጥሩ ፍሬ እንዳስገኘ ለመመልከት ችሏል። ሉቃስ “እኵሌቶቹም የተናገረውን አመኑ” ሲል ዘግቧል። (ሥራ 28:24) ጳውሎስ ራሱም እንደሚከተለው ሲል በጻፈ ጊዜ ‘ምስክርነት መስጠቱ’ ውጤት እንዳስገኘ ገልጿል:- “ይህ የደረሰብኝ በእውነት ወንጌልን ለማስፋት እንደ ሆነ ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ። ስለዚህም እስራቴ ስለ ክርስቶስ እንዲሆን በንጉሥ ዘበኞች ሁሉና በሌሎች ሁሉ ዘንድ ተገልጦአል፣ በጌታም ካሉት ወንድሞች የሚበዙት ስለ እስራቴ ታምነው የእግዚአብሔርን ቃል እንዲነግሩ ያለ ፍርሃት ከፊት ይልቅ ይደፍራሉ።”​—⁠ፊልጵ. 1:12-14

10. አንድ ባልና ሚስት መደበኛ ባልሆነ መንገድ በመመሥከራቸው ምን ውጤት አገኙ?

10 ባለፈው ዓመት አንድ ባልና ሚስት ከአውራጃ ስብሰባ ሲመለሱ ደረታቸው ላይ ስላደረጉት ካርድ ለጠየቀቻቸው አንዲት የሆቴል ቤት አስተናጋጅ መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት መስጠታቸው ጥሩ ውጤት አስገኝቷል። ስለ አውራጃ ስብሰባውና መጽሐፍ ቅዱስ የወደፊቱን ጊዜ አስመልክቶ ስለሚሰጠው ተስፋ ነገሯት። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ ማወቅ ትፈልጋለህ? የሚለውን ትራክት ከሰጧት በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን በነፃ ማጥናት የምትችልበት ዝግጅት እንዳለ ገለጹላት። ሴትዮዋ አንድ ሰው ተመልሶ እንዲጠይቃት እንደምትፈልግ ከነገረቻቸው በኋላ በትራክቱ ጀርባ ላይ ስሟንና አድራሻዋን ጽፋ ባልና ሚስቱ የሚያስጠናት ሰው እንዲያገናኟት ጠየቀቻቸው። አንተስ ‘የምሥክርነቱን ሥራ’ በትጋት በማከናወን ምን አስደሳች ውጤት ታገኝ ይሆን?

11. ‘የምሥክርነቱን ሥራ’ በትጋት በማከናወን ምሥራቹን ለማስፋፋት ምን ዝንባሌ ማዳበር አለብን?

11 ምሥራቹን በትጋት ስበኩ:- ጳውሎስ ክርስቲያን ባልንጀሮቹ የእርሱን ምሳሌ በመኮረጅ በቅንዓት እያገለገሉ እንዳሉ ሲሰማ ምን ያህል ተደስቶ እንደሚሆን ገምት! እኛም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለ ተመሠረተው እምነታችን መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለመመሥከር የቻልነውን ሁሉ እናድርግ።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መደበኛ ባልሆነ መንገድ በምንመሠክርበት ጊዜ የሚያስፈልጉን ጽሑፎች

■ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ ማወቅ ትፈልጋለህ? (ትራክት)

■ አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? (ብሮሹር)

■ ጉድ ኒውስ ፎር ኦል ኔሽንስ (ቡክሌት)

■ ሌሎች ጽሑፎች

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አትርሷቸው!

እነማንን? በክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ ወይም በልዩ የሕዝብ ንግግሩ ላይ የተገኙትን ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች አስታውሰን ልንጠይቃቸው ይገባል። በልዩ ስብሰባ፣ በዚህ ዓመት በሚደረገው የአውራጃ ስብሰባና በሌሎች ስብሰባዎች ላይ እንዲገኙ ጋብዘናቸዋል? አብዛኞቹ በደግነት ካበረታታናቸው በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ሊገኙ ይችላሉ። በስብሰባዎቹ ላይ ተገኝተው ከወንድሞች ጋር ሲቀራረቡና የሚያበረታታውን መንፈሳዊ ፕሮግራም ሲያዳምጡ ወደ ይሖዋና ወደ ድርጅቱ ይበልጥ ለመቅረብ ይገፋፋሉ። ጋብዘሃቸው የሚሰጡትን ምላሽ ለምን አትመለከትም? የጉባኤ ስብሰባ፣ የልዩ፣ የወረዳ ወይም የአውራጃ ስብሰባ የሚደረግበትን ሰዓትና ቦታ እንዲሁም ስብሰባው እንዴት እንደሚካሄድ አስቀድመህ ንገራቸው።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ