መለኮታዊውን ስም ማስታወቅ
1. የአምላክን ስም ማወቅ በሰዎች ላይ ምን ስሜት ሊያሳድር ይችላል?
1 ለመጀመሪያ ጊዜ ስለ አምላክ ስም ስታውቅ ምን ተሰማህ? የአብዛኞቹ ሰዎች ስሜት እንደሚከተለው ብላ ከተናገረችው ሴት ጋር ይመሳሰላል:- “የአምላክን ስም ለመጀመሪያ ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስመለከት አለቀስኩ። የአምላክን ስም አውቄ በዚህ ስም ልጠራው እንደምችል ሳውቅ በጣም ተደሰትኩ።” ይህቺ ሴት ይሖዋን በቅርብ ለማወቅና ከእርሱ ጋር የጠበቀ ዝምድና ለመመሥረት ስሙን ማወቅ አስፈላጊ እንደሆነ ተሰምቷታል።
2. ሰዎችን ስለ ይሖዋ ማስተማራችን አጣዳፊ የሆነው ለምንድን ነው?
2 ስሙን ማስታወቅ የሚኖርብን ለምንድን ነው? የአምላክ ስም ከባሕርያቱ፣ ከዓላማዎቹና ከሥራዎቹ ጋር የተዛመደ ነው። ከሰዎች መዳን ጋርም የተያያዘ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “የጌታን [“የይሖዋን፣” NW ] ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል” ሲል ጽፏል። ሆኖም ጳውሎስ ሰዎች በቅድሚያ ስለ ይሖዋ ካልተማሩና በእርሱ ላይ እምነት ካላሳደሩ “እንዴት አድርገው ይጠሩታል?” በማለት ጠይቋል። በመሆኑም ክርስቲያኖች የአምላክን ስምና ከስሙ ጋር የተያያዙትን ነገሮች ለሰዎች ማሳወቃቸው አጣዳፊ ነው። (ሮሜ 10:13, 14) ይሁን እንጂ የአምላክን ስም ማስታወቅ አስፈላጊ የሆነበት ዋነኛው ምክንያት ይህ አይደለም።
3. የምንሰብክበት ዋነኛ ዓላማ ምንድን ነው?
3 በ1920ዎቹ ዓመታት የአምላክ ሕዝቦች ከአምላክ ሉዓላዊነት መረጋገጥና ከስሙ መቀደስ ጋር በተያያዘ በአጽናፈ ዓለሙ ውስጥ የተነሳውን አከራካሪ ጉዳይ ከቅዱሳን ጽሑፎች መረዳት ቻሉ። ይሖዋ ስሙን ከነቀፋ ነፃ ለማድረግ ክፉዎችን ከማጥፋቱ በፊት ስለ እርሱ የሚናገረው እውነት ‘በምድር ሁሉ ላይ መታወቅ’ አለበት። (ኢሳ. 12:4, 5፤ ሕዝ. 38:23) በዚህ የተነሳ በስብከቱ ሥራ የምንካፈልበት ዋነኛ ምክንያት ይሖዋን በሕዝብ ፊት ለማወደስና ስሙን በሰው ዘር ሁሉ ዘንድ ለመቀደስ ነው። (ዕብ. 13:15) ለአምላክና ለሰዎች ያለን ፍቅር አምላክ የሰጠንን ይህንን ሥራ በሙሉ ነፍስ እንድናከናውን ያነሳሳናል።
4. የይሖዋ ምሥክሮች በአምላክ ስም ተለይተው ሊታወቁ የቻሉት ለምንድን ነው?
4 ‘ለስሙ የሚሆን ወገን’፦ በ1931 የይሖዋ ምሥክሮች ተብለን መጠራት ጀመርን። (ኢሳ. 43:10) ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የአምላክ ሕዝቦች መለኮታዊውን ስም በስፋት እያስታወቁ በመሆኑ አዋጅ ነጋሪዎች የተባለው መጽሐፍ በገጽ 124 ላይ እንዲህ ብሏል:- “በየትኛውም የምድር ክፍል አንድ ሰው በአምላክ ስም በተደጋጋሚ የሚጠቀም ከሆነ ሰዎች በቀጥታ የይሖዋ ምሥክር እንደሆነ ያስባሉ።” አንተስ በዚህ ትታወቃለህን? ይሖዋ ላሳየን ጥሩነት ያለን የአመስጋኝነት መንፈስ አመቺ ሆኖ ባገኘነው በማንኛውም አጋጣሚ ስለ እርሱ በመናገር ‘ስሙን እንድንባርክ’ ሊያነሳሳን ይገባል።—መዝ. 20:7፤ 145:1, 2, 7
5. ምግባራችን በአምላክ ስም ከመጠራታችን ጋር የተያያዘ የሆነው እንዴት ነው?
5 ‘ለስሙ የተለየን ወገን’ እንደመሆናችን መጠን የሥነ ምግባር መሥፈርቶቹን መጠበቅ አለብን። (ሥራ 15:14፤ 2 ጢሞ. 2:19) ብዙውን ጊዜ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮችን በተመለከተ በቅድሚያ የሚያስተውሉት መልካም ምግባራቸውን ነው። (1 ጴጥ. 2:12) አምላካዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ቸል በማለት ወይም ለእርሱ የሚገባውን አምልኮ በሕይወታችን ውስጥ ሁለተኛ ቦታ በመስጠት የአምላክን ስም ማጉደፍ ፈጽሞ አንፈልግም። (ዘሌ. 22:31, 32፤ ሚል. 1:6-8, 12-14) ከዚህ ይልቅ አኗኗራችን በመለኮታዊው ስም የመጠራት መብታችንን ከፍ አድርገን እንደምንመለከተው የሚያሳይ ይሁን።
6. አሁንም ሆነ ለዘላለም ምን የማድረግ መብት አለን?
6 በአሁኑ ወቅት “ከፀሐይ መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያዋ ድረስ ስሜ በአሕዛብ ዘንድ ታላቅ ይሆናልና” በማለት ይሖዋ የተናገረው ትንቢት ፍጻሜውን ሲያገኝ እየተመለከትን ነው። (ሚል. 1:11) ስለ ይሖዋ የሚናገረውን እውነት ማስታወቃችንንና ‘የተቀደሰውን ስሙን ለዘላለም ዓለም መባረካችንን’ እንቀጥል።—መዝ. 145:21