ትሕትናን ልበሱ
1 አንድ ልጅ እግር እረኛ በይሖዋ በመተማመን ኃያል የሆነን ጦረኛ አሸነፈ። (1 ሳሙ. 17:45-47) አንድ ባለጸጋ ሰው የደረሰበትን መከራ በጽናት ተቋቋመ። (ኢዮብ 1:20-22፤ 2:9, 10) የአምላክ ልጅ ትምህርቱን ያገኘው ከአባቱ መሆኑን ተናገረ። (ዮሐ. 7:15-18፤ 8:28) በሦስቱም ሁኔታዎች ላይ ጎልቶ የሚታየው ባሕርይ ትሕትና ነው። ዛሬም በተመሳሳይ የሚያጋጥሙንን የተለያዩ ሁኔታዎች ለመወጣት ትሕትና በጣም ይረዳናል።—ቆላ. 3:12
2 በምንሰብክበት ጊዜ:- ክርስቲያን አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን በዘራቸው፣ በባህላቸው ወይም በአስተዳደጋቸው ምክንያት አድልዎ ሳናደርግ ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ምሥራቹን በትሕትና እንሰብካለን። (1 ቆሮ. 9:22, 23) አንዳንዶች ቢያመናጭቁን ወይም ለመንግሥቱ መልእክት ንቀት የተሞላበት ምላሽ ቢሰጡን አጸፋውን ከመመለስ ይልቅ የሚገባቸውን ሰዎች በትዕግሥት መፈለጋችንን እንቀጥላለን። (ማቴ. 10:11, 14) እኛ ከምናቀርበው ከማንኛውም ሐሳብ ይልቅ የአምላክ ቃል ይበልጥ አሳማኝ እንደሆነ በመገንዘብ የሰዎችን ትኩረት ወደ ቃሉ ለማዞር እንጥራለን እንጂ በእውቀታችን ወይም በትምህርታችን ልናስደምማቸው አንሞክርም። (1 ቆሮ. 2:1-5፤ ዕብ. 4:12) የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ይሖዋ እንዲመሰገን እናደርጋለን።—ማር. 10:17, 18
3 በጉባኤ ውስጥ:- ክርስቲያኖች ‘እርስ በርሳቸው እየተዋረዱ ትሕትናን እንደ ልብስ መታጠቅ’ አለባቸው። (1 ጴጥ. 5:5) ሌሎች ከእኛ እንደሚበልጡ አድርገን የምናስብ ከሆነ ወንድሞቻችን እንዲያገለግሉን ከመጠበቅ ይልቅ እነርሱን ማገልገል የምንችልባቸውን መንገዶች እንፈልጋለን። (ዮሐ. 13:12-17፤ ፊልጵ. 2:3, 4) የመሰብሰቢያ አዳራሹን ማጽዳትን የመሳሰሉ ሥራዎች ክብራችንን እንደሚነኩ አድርገን ማሰብ አይገባንም።
4 ትሕትና ‘እርስ በእርሳችን በፍቅር እንድንታገሥ’ ስለሚያስችለን በጉባኤ ውስጥ ሰላምና አንድነት ለማስፈን ይረዳል። (ኤፌ. 4:1-3) ለጉባኤው አመራር እንዲሰጡ ለተሾሙት ወንድሞች እንድንገዛ ይረዳናል። (ዕብ. 13:17) የሚሰጠንን ማንኛውንም ምክር ወይም ተግሣጽ እንድንቀበል ያነሳሳናል። (መዝ. 141:5) ከዚህም በላይ ትሕትና በጉባኤ ውስጥ የሚሰጠንን ማንኛውንም ኃላፊነት በመወጣት ረገድ በይሖዋ እንድንታመን ያደርገናል። (1 ጴጥ. 4:11) እንደ ዳዊት እኛም ሊሳካልን የሚችለው በሰብዓዊ ችሎታ ሳይሆን በአምላክ እርዳታ መሆኑን እንገነዘባለን።—1 ሳሙ. 17:37
5 በአምላካችን ፊት:- ከሁሉ በላይ ደግሞ ‘ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችንን ማዋረድ’ ይገባናል። (1 ጴጥ. 5:6) አስቸጋሪ ከሆኑ ሁኔታዎች ጋር እየታገልን ከሆነ የአምላክ መንግሥት መጥቶ እንዲገላግለን እንናፍቅ ይሆናል። ሆኖም ይሖዋ የገባውን ቃል በወሰነው ጊዜ እስኪፈጽም ድረስ በትሕትና እንጠብቃለን። (ያዕ. 5:7-11) በአቋሙ እንደጸናው እንደ ኢዮብ ሁሉ እኛም በዋነኛነት የሚያሳስበን “የእግዚአብሔር ስም የተባረከ” መሆኑ ነው።—ኢዮብ 1:21
6 ነቢዩ ዳንኤል ‘ሰውነቱን በአምላኩ ፊት በማዋረዱ’ የይሖዋን ሞገስና ሌሎች ብዙ አስደሳች መብቶች በማግኘት ተባርኳል። (ዳን. 10:11, 12) በተመሳሳይ እኛም “ትሕትናና እግዚአብሔርን መፍራት ባለጠግነት ክብር ሕይወትም” እንደሆነ በመገንዘብ ትሕትናን እንልበስ።—ምሳሌ 22:4
[በገጽ 1 ላይ የሚገኝ የሥዕል መግለጫ]
(በገጽ 3 የመጀመሪያው አምድ ላይ ይቀጥላል )
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል መግለጫ]
ትህትናን ልበሱ
(ከገጽ 1 የዞረ )