የአውራጃ ስብሰባው ለአምላክ ክብር እንድንሰጥ አነሳስቶናል!
“ለአምላክ ክብር ስጡት” በሚል ጭብጥ እስከ አሁን ድረስ በተካሄዱት የአውራጃና ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች አማካኝነት ከፍተኛ ምሥክርነት ተሰጥቷል። እነዚህ የላቀ ትርጉም ያላቸው ቲኦክራሲያዊ ስብሰባዎች የይሖዋን ስም ለማወደስና ‘ለስሙ የሚገባ ክብር የማምጣት’ ችሎታችንን ለማሳደግ አስችለውናል። (መዝ. 96:8) በእርግጥም ግሩም ባሕርያቱ በተንጸባረቁባቸው አስገራሚ የፍጥረት ሥራዎቹ የተነሳ ይሖዋ ክብር ሊሰጠው ይገባል።—ኢዮብ 37:14፤ ራእይ 4:10, 11
ቀጥሎ የቀረቡትን ጥያቄዎችና የያዝከውን ማስታወሻ ተጠቅመህ ታኅሣሥ 1 በሚጀምረው ሳምንት ለሚቀርበው የአውራጃ ስብሰባ ፕሮግራም ክለሣ ተዘጋጅተህ ለመምጣትና በክለሣው ላይ ለመሳተፍ ጥረት አድርግ።
1. ግዑዝ የሆኑት የፍጥረት ሥራዎች የአምላክን ክብር የሚያውጁት እንዴት ነው? ይህስ ሰዎች እርሱን ከሚያወድሱበት መንገድ የሚለየው እንዴት ነው? (መዝ. 19:1-3፤ “ፍጥረት የአምላክን ክብር ያውጃል”)
2. ኢየሱስ በተዓምራዊ ሁኔታ መለወጡ ዛሬ እውን ለሆነው ለየትኛው ክንውን ትንቢታዊ ጥላ ነው? ይህ ክንውን በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖችን ለተግባር ያነሳሳቸውስ እንዴት ነው? (የስብሰባውን ጭብጥ የሚያብራራ ንግግር፣ “ክብር የተላበሱት ትንቢታዊ ራእዮች ለተግባር ያንቀሳቅሱናል!”)
3. ነቢዩ ዳንኤል ያሳየው ዓይነት ትሕትና እንዴት ማዳበር እንችላለን? እንዲህ በማድረጋችንስ ምን ጥቅም እናገኛለን? (ዳን. 9:2, 5፤ 10:11, 12፤ “ይሖዋ ክብሩን ለትሑታን ሰዎች ይገልጣል”)
4. (ሀ) መለኮታዊ ፍርድን በተመለከተ ከአሞጽ ትንቢት የምንማራቸው ሦስት ነገሮች ምንድን ናቸው? (አሞጽ 1:3, 11, 13፤ 9:2-4, 8, 14) (ለ) በዛሬው ጊዜ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች አሞጽ 2:12 ላይ ከሚገኘው የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ምን ተግባራዊ ትምህርት ማግኘት ይችላሉ? (“የአሞጽ ትንቢት—ለዘመናችን የሚያስተላልፈው መልእክት”)
5. (ሀ) አንድ ሰው ባይሰክርም እንኳ የአልኮል መጠጦችን ከልክ በላይ የሚወስድ ከሆነ ለየትኞቹ አደጋዎች ሊጋለጥ ይችላል? (ለ) ከልክ በላይ የመጠጣት ልማድን ማሸነፍ የሚቻለው እንዴት ነው? (ማር. 9:43፤ ኤፌ. 5:18፤ “የአልኮል መጠጥ ወጥመድ እንዳይሆንባችሁ ተጠንቀቁ”)
6. ከአዲሱ ብሮሹር ምን ጥቅም አግኝታችኋል? (“ለመጪዋ ገነት አምሳያ የምትሆነው ‘መልካሚቱ ምድር’”)
7. ‘የይሖዋን ክብር እንደ መስተዋት የምናንጸባርቅባቸው’ ሦስት መንገዶች የትኞቹ ናቸው? (2 ቆሮ. 3:18፤ “የይሖዋን ክብር እንደ መስተዋት እናንጸባርቃለን”)
8. ያለ ምክንያት የምንጠላው ለምንድን ነው? እንዲህ ዓይነት ጥላቻ ቢደርስብንም በአቋማችን እንድንጸና ሊረዳን የሚችለው ምንድን ነው? (መዝ. 109:1-3፤ “ያለ ምክንያት መጠላት”)
9. በሌሎች ዘንድ ክብር ስለማግኘት የክርስቶስ ዓይነት አመለካከት ማዳበር ሲባል ምን ማለት ነው? አንድ ሰው እንዲህ ዓይነቱን አመለካከት በተሟላ መልኩ ማዳበር እንዳለበት ማወቅ የሚችለው እንዴት ነው? (ማቴ. 20:20-26፤ “በሌሎች ዘንድ ክብር ስለማግኘት የክርስቶስ ዓይነት አመለካከት ማዳበር”)
10. ሰውነታችን ቢዝልም በመንፈሳዊ ብርቱ ሆነን ለመኖር ምን ሊረዳን ይችላል? (“ሰውነታችን ቢዝልም መንፈሳችን አይደክምም”)
11. ሰይጣን የሐሰት ትምህርት የሚያስፋፋባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው? እምነታችንን ለማዳከም ለሚሰነዘሩ ሙከራዎች የምንሰጠው ቅዱስ ጽሑፋዊ ምላሽ ምን መሆን አለበት? (ዮሐ. 10:5፤ “‘እንግዳ ለሆኑ ድምፆች’ ጆሯችሁን እንዳትሰጡ ተጠንቀቁ”)
12. (ሀ) ወላጆች ማርቆስ 10:14, 16 ላይ ተመዝግቦ በሚገኘው መሠረት የኢየሱስን ምሳሌ መኮረጅ የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) ከአዲሱ መጽሐፍ የወደድኸው ነገር ምንድን ነው? (“ልጆቻችን— ውድ ስጦታ ናቸው”)
13. ወጣቶች ይሖዋን እያወደሱ ያሉት እንዴት ነው? (1 ጢሞ. 4:11, 12፤ “ወጣቶች ይሖዋን ማወደስ የሚችሉት እንዴት ነው?”)
14. “ተቃውሞ ቢኖርም በድፍረት መመስከር” ከተባለው ድራማ በደንብ ትዝ የሚሉህ ነጥቦች የትኞቹ ናቸው?
15. (ሀ) ጴጥሮስና ዮሐንስ (ሥራ 4:10)፣ (ለ) እስጢፋኖስ (ሥራ 7:2, 52, 53) እንዲሁም (ሐ) የመጀመሪያው መቶ ዘመን የክርስቲያን ጉባኤ የተዉትን ምሳሌ መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው? (ሥራ 9:31፤ ድራማውና “ምሥራቹን ‘ያለማሰለስ’ ስበኩ” የተባለው ንግግር)
16. (ሀ) በየትኞቹ መንገዶች ለአምላክ ክብር ለመስጠት ወስነናል? (ለ) “ለአምላክ ክብር ስጡት” በተባለው የአውራጃ ስብሰባ ላይ የተማርናቸውን ነገሮች በሥራ ካዋልን ምን እንደምናገኝ እርግጠኞች መሆን እንችላለን? (ዮሐ. 15:9, 10, 16፤ “‘ብዙ ፍሬ በማፍራት’ ለይሖዋ ክብር ስጡ”)
በስብሰባው ላይ በቀረቡት ግሩም መንፈሳዊ ትምህርቶች ላይ የምናሰላስል ከሆነ የተማርናቸውን ነገሮች በሥራ ለማዋል እንነሳሳለን። (ፊልጵ. 4:8, 9) ይህም ‘የምናደርገውን ሁሉ ለአምላክ ክብር ለማድረግ’ የገባነውን ቃል ያጠናክርልናል።—1 ቆሮ. 10:31