ምስጋና መንፈስ ያድሳል
1 ትንሿ ልጅ አልጋዋ ውስጥ ገብታ እያለቀሰች “ዛሬ ጨዋ ልጅ ሆኜ አልዋልኩም?” በማለት እናቷን ትጠይቃታለች። የልጅቷ ጥያቄ እናትየዋን ሳያስገርማት አልቀረም። የዚያን ዕለት ትንሿ ልጅ ጨዋ ሆና መዋሏን ብታስተውልም አንድም ጊዜ አላመሰገነቻትም። የዚህች ትንሽ ልጅ እንባ ሕፃን አዋቂ ሳይባል ሁላችንም ምስጋና እንደሚያስፈልገን ያስገነዝበናል። እኛስ ሰዎች ላደረጉት መልካም ነገር አድናቆታችንን በመግለጽ ሌሎችን እናበረታታለን?—ምሳሌ 25:11
2 ክርስቲያን ባልንጀሮቻችን እንድናመሰግናቸው የሚያደርጉ ብዙ ጥሩ ነገሮች አሏቸው። ሽማግሌዎች፣ የጉባኤ አገልጋዮችና አቅኚዎች ኃላፊነቶቻቸውን ለመወጣት ጠንክረው ይሠራሉ። (1 ጢሞ. 4:10፤ 5:17) ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ወላጆች ልጆቻቸውን በይሖዋ መንገድ ለማሳደግ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ያደርጋሉ። (ኤፌ. 6:4) ክርስቲያን ወጣቶች ‘የዓለም መንፈስ” እንዳያሸንፋቸው ብርቱ ትግል ያደርጋሉ። (1 ቆሮ. 2:12፤ ኤፌ. 2:1-3) ሌሎች ደግሞ የዕድሜ መግፋት፣ የጤና ችግር ወይም ሌሎች ፈተናዎች እያሉባቸውም ይሖዋን በታማኝነት ያገለግላሉ። (2 ቆሮ. 12:7) እነዚህ ሁሉ ምስጋና ይገባቸዋል። ታዲያ መልካም ጥረታቸውን ጠቅሰን እናመሰግናቸዋለን?
3 ለይታችሁ በመጥቀስ በግለሰብ ደረጃ አመስግኑ:- ሁላችንም መላው ጉባኤ ከመድረክ ሲመሰገን ስንሰማ በእጅጉ እንደሰታለን። ይሁን እንጂ ምስጋና ይበልጥ መንፈስን የሚያድሰው በግለሰብ ደረጃ ሲሰጥ ነው። ለምሳሌ ያህል ጳውሎስ በሮም ለሚኖሩ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ምዕራፍ 16 ላይ ፌቤን፣ ጵርስቅላና አቂላ፣ ፕሮፊሞና እና ጢሮፊሞሳ፣ ጠርሲዳ እንዲሁም ሌሎች ያደረጉትን በቀጥታ በመጥቀስ አመስግኗቸዋል። (ሮሜ 16:1-4, 12) እነዚህ ታማኝ ክርስቲያኖች በጳውሎስ ቃላት ምን ያህል ተበረታተው ይሆን! እንዲህ ያለው ምስጋና ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንደሚፈለጉ እንዲሰማቸው የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ እርስ በርስ ይበልጥ ያቀራርበናል። አንተስ የሚያስመሰግኑ ነገሮችን በቀጥታ በመጥቀስ በቅርቡ በግል ያመሰገንከው ሰው አለ?—ኤፌ. 4:29
4 ከልብ የመነጨ ይሁን:- ምስጋና መንፈስን የሚያድስ እንዲሆን ከተፈለገ ከልብ የመነጨ መሆን ይኖርበታል። ሰዎች የምንናገረው ነገር ከልብ ይሁን ወይም እንዲያው ‘ሽንገላ’ መለየት አያቅታቸውም። (ምሳሌ 28:23 አ.መ.ት) የሰዎችን መልካም ጎን ለመመልከት ጥረት ባደረግን መጠን ልባችን እነርሱን ለማመስገን ይገፋፋል። እንግዲያው ‘በጊዜው የተነገረ ቃል መልካም’ መሆኑን ተገንዝበን ከልባችን በማመስገን ረገድ ለጋሶች እንሁን።—ምሳሌ 15:23