ዘወትር በስብሰባ ለመገኘት ቅድሚያ መስጠት አለብን
1 ክርስቲያን ቤተሰቦች ዘወትር በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ቅድሚያ ይሰጣሉ። ሆኖም በዛሬው ጊዜ ልናከናውናቸው የሚገቡ የተለያዩ ሥራዎች ፈታኝ ሁኔታ ሊያስከትሉብን ይችላሉ። የቤት ውስጥ ሥራዎች፣ ተቀጥረን የምንሠራው ሥራ ወይም ትምህርት ለይሖዋ አምልኮ የመደብነውን ጊዜ እየተሻሙብን ነው? በሕይወታችን የሚያጋጥሙንን ነገሮች በይሖዋ ዓይን መመልከት መቻላችን ማስቀደም ያለብንን ጉዳዮች እንድናስቀድም ይረዳናል።—ምሳሌ 3:5, 6
2 አንድ እስራኤላዊ የይሖዋን አመለካከት ሆነ ብሎ ቸል በማለት በሰንበት እንጨት ሲለቅም ተገኘ። ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ነገር እያሟላ እንደሆነ ተሰምቶት ወይም ጉዳዩን አቅልሎ ተመልክቶት ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ለአምልኮ በተወሰነ ጊዜ ሥጋዊ ነገሮችን ማሳደድ ከባድ መዘዝ እንደሚያስከትል ይሖዋ በሰጠው ፍርድ አማካኝነት አሳይቷል።—ዘኍ. 15:32-36
3 እንቅፋቱን መወጣት:- ብዙዎች ተቀጥረው የሚሠሩት ሥራ ከስብሰባ እንዳያስቀራቸው ከፍተኛ ትግል ማድረግ ጠይቆባቸዋል። አንዳንዶች አለቃቸውን በማነጋገር፣ የሥራ ፈረቃቸውን ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር በመቀያየር፣ አንዳንድ ኮርሶችን ወይም የሥራ እድገት ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆን፣ ይበልጥ ተስማሚ የሆነ ሥራ በመፈለግ ወይም ሕይወታቸውን ቀላል በማድረግ እንቅፋት የሆነባቸውን ነገር መወጣት ችለዋል። ለእውነተኛው አምልኮ ስንል የምንከፍላቸው እነዚህን የመሳሰሉ መሥዋዕቶች የአምላክን ልብ ያስደስታሉ።—ዕብ. 13:16
4 ተማሪዎችም የሚሰጣቸው የቤት ሥራ እንቅፋት ሊሆንባቸው ይችላል። አንዲት ወጣት “የተወሰነውን የቤት ሥራዬን ከስብሰባ በፊት፣ የቀረውን ደግሞ ወደ ቤት ከተመለስኩ በኋላ እሠራለሁ” ብላለች። ልጆች ስብሰባ በሚሄዱበት ምሽት የተሰጣቸውን የቤት ሥራ ማጠናቀቅ ካልቻሉ አንዳንድ ወላጆች ወደ አስተማሪዎቹ ሄደው ቤተሰቡ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ቅድሚያ እንደሚሰጥ ይገልጻሉ።
5 የቤት ውስጥ ሥራዎችን አጠናቅቆ ሁሉም የቤተሰቡ አባል በስብሰባዎች ላይ በሰዓቱ መገኘት እንዲችል የትብብር መንፈስ ማሳየትና ጥሩ እቅድ ማውጣት ቁልፍ ነገሮች ናቸው። (ምሳሌ 20:18) በተወሰነ ሰዓት ላይ ከቤት ለመውጣት ትንንሽ ልጆችም ጭምር ለባብሰውና ተዘገጃጅተው እንዲቆዩ ሥልጠና ሊሰጣቸው ይችላል። ወላጆች ምሳሌ ሆነው በመገኘት የስብሰባን አስፈላጊነት ልጆቻቸው እንዲገነዘቡ ማድረግ ይችላሉ።—ምሳሌ 20:7
6 ይህ ሥርዓት የሚያስከትለው ውጥረት እያየለ በሄደ መጠን ዘወትር በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘታችን በጣም አስፈላጊ ነው። በሕይወታችን የሚያጋጥሙንን ነገሮች በይሖዋ ዓይን መመልከታችንንና ዘወትር በስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ቅድሚያ መስጠታችንን እንቀጥል።—ዕብ. 10:24, 25