ወደ ይሖዋ ቅረብ የተባለውን መጽሐፍ በማጥናት ተጠቀሙ
1 “ቀናተኛ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች” በተባለው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ወደ ይሖዋ ቅረብ የተሰኘውን መጽሐፍ በማግኘታችን ተደስተን ነበር። ብዙዎች ይህንን መጽሐፍ ወዲያውኑ አንብበውታል። ሌሎች ደግሞ “ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል” በሚለው የ2003 የዓመት ጥቅስ ተበረታተው መጽሐፉን እንዳነበቡት አያጠራጥርም።—ያዕ. 4:8
2 በነሐሴ ወር ወደ ይሖዋ ቅረብ የተሰኘውን መጽሐፍ በጉባኤ መጽሐፍ ጥናት ማጥናት እንጀምራለን። ከጥናቱ ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? ዝግጅት አስፈላጊ ነው። እያንዳንዱ ምዕራፍ የሚሸፈነው በሁለት ሳምንት በመሆኑ በአንድ ሳምንት እንዲጠኑ የተመደቡት ቁጥሮች አነስተኛ ናቸው። ይህም ትምህርቱን አጥንታችሁና አሰላስላችሁበት ጥልቀት ያለው ሐሳብ ለመስጠት ያስችላችኋል። ከዚህም በላይ ለየት ባለው የመጽሐፉ ገጽታ ላይ ማተኮር እንዲቻል የእያንዳንዱ ምዕራፍ የመጨረሻ አንቀጾች በሚጠኑበት ሳምንት ውይይት የሚደረግባቸው ቁጥሮች አነስ ያሉ ናቸው።
3 ከምዕራፍ 2 ጀምሮ በየምዕራፉ መጨረሻ ላይ “ለማሰላሰል የሚረዱ ጥያቄዎች” የሚል ሣጥን ይገኛል። የመጽሐፍ ጥናቱ የበላይ ተመልካች የምዕራፉ የመጨረሻ ቁጥር ከተጠና በኋላ በዚህ ሣጥን ውስጥ በቀረቡት ሐሳቦች ላይ እንዲወያዩ ያደርጋል። የቡድኑ አባላት በጥቅሶቹ ላይ በማሰላሰል ያገኟቸውን ጠቃሚ ሐሳቦች እንዲናገሩ ያበረታታቸዋል። (ምሳሌ 20:5) በሣጥኑ ውስጥ ከቀረቡት ጥያቄዎች በተጨማሪ አንዳንድ ጊዜ እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎችን ሊያነሳ ይችላል:- “ይህ ሐሳብ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረናል? ሕይወታችንን የሚነካው እንዴት ነው? ሌሎችን ለመርዳት ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው?” ይህንን የሚያደርግበት ዓላማ ከልብ የመነጨ ሐሳብ እንዲሰጡ ለማበረታታት እንጂ በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ እምብዛም ጠቃሚ ባልሆኑ ዝርዝር ጉዳዮች ላይ የአድማጮቹን እውቀት ለመፈተን አይደለም።
4 ወደ ይሖዋ ቅረብ የተባለው መጽሐፍ ከሌሎች ጽሑፎች ለየት ያለ መጽሐፍ ነው። “ታማኝና ልባም ባሪያ” የሚያዘጋጃቸው ሁሉም ጽሑፎች ይሖዋን የሚያወድሱ ቢሆኑም ይህ መጽሐፍ በይሖዋ ባሕርያት ላይ ብቻ ያተኮረ ነው። (ማቴ. 24:45-47 የ1954 ትርጉም ) በእርግጥም አስደሳች ዝግጅት ተደርጎልናል! የይሖዋን ባሕርያት በጥልቀት በማጥናት በጣም እንጠቀማለን። የምናደርገው ጥናት በሰማይ ወደሚኖረው አባታችን ይበልጥ ለመቅረብና ሌሎችም እንዲሁ እንዲያደርጉ ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመርዳት የሚያስችለን ይሁን።