አንተም የተሰለፍክበት የፈረሰኛ ሰራዊት
1, 2. በዛሬው ጊዜ የአምላክ አገልጋዮች ራእይ 9:13-19 ላይ ተመዝግቦ በሚገኘው ትንቢታዊ ራእይ አፈጻጸም ረገድ ምን ድርሻ አላቸው?
1 “ስድስተኛው መልአክ መለከቱን ነፋ።” ከዚያም ብዛታቸው “ሁለት መቶ ሚሊዮን” የሚያክል ‘የፈረሰኛ ሰራዊት’ ሲያፈተልኩ እንደ ነጎድጓድ የሚያስገመግም ድምፅ ተሰማ። ይህ ሰራዊት የምናውቀው ዓይነት ወታደራዊ ኃይል አይደለም። “የፈረሶቹ ራስ የአንበሶችን ራስ ይመስል ነበር።” ከአፋቸው እሳት፣ ጢስና ዲን የሚወጣ ከመሆኑም ሌላ “ጅራታቸውም እባብ ይመስል ነበር።” ይህ ምሳሌያዊ የፈረሰኛ ሰራዊት ባለፈበት ቦታ ሁሉ አካባቢውን ያወድማል። (ራእይ 9:13-19) በዚህ አስደናቂ ትንቢታዊ ራእይ አፈጻጸም ረገድ ምን ድርሻ እንዳለህ ታውቃለህ?
2 ቅቡዓን ቀሪዎችና ባልንጀሮቻቸው የሆኑት ሌሎች በጎች የአምላክን የፍርድ መልእክቶች በማወጁ ሥራ በጋራ ይሳተፋሉ። በዚህ እንቅስቃሴ አማካኝነት ሕዝበ ክርስትና በመንፈሳዊ ሁኔታ ሙት መሆኗ ሙሉ በሙሉ ሊጋለጥ ችሏል። የአምላክ ሕዝቦች የሚያከናውኑት አገልግሎት እጅግ ውጤታማ ሊሆን የቻለው ለምን እንደሆነ የሚያጎሉትን የትንቢታዊውን ራእይ ሁለት ገጽታዎች እስቲ እንመልከት።
3. የአምላክን ቃል ውጤታማ በሆነ መንገድ ማቅረብ እንድትችሉ ምን ዓይነት ሥልጠና አግኝታችኋል?
3 የአምላክን ቃል እንድናደርስ ሥልጠናና ትጥቅ አግኝተናል:- በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤትና በሌሎች የጉባኤ ስብሰባዎች አማካኝነት የአምላክ አገልጋዮች የአምላክን ቃል በልበ ሙሉነት እንዲናገሩ ሥልጠና ተሰጥቷቸዋል። የኢየሱስንና የደቀ መዛሙርቱን አርዓያ በመከተል ሰዎች በሚገኙበት ቦታ ሁሉ በመስበክ የሚገባቸውን ሰዎች ለማግኘት ጥረት ያደርጋሉ። (ማቴ. 10:11፤ ማር. 1:16፤ ሉቃስ 4:15፤ ሥራ 20:18-20) የመጽሐፍ ቅዱስ ድጋፍ ያለው ይህ የስብከት ዘዴ እጅግ ውጤታማ መሆኑ ታይቷል!
4. አስፋፊዎች የስብከት ሥራቸውን ማከናወን እንዲችሉ የትኞቹ መሣሪያዎች ተዘጋጅተውላቸዋል?
4 የምሥራቹ አገልጋይ የሆኑ ክርስቲያኖች መለኮታዊውን የስብከት ተልዕኮ ለመወጣት ባደረጉት ጥረት በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ መጽሐፍ ቅዱሶች፣ መጽሐፎች፣ ብሮሹሮችና መጽሔቶች አሰራጭተዋል። እነዚህ ጽሑፎች ወደ 400 በሚጠጉ ቋንቋዎች የተዘጋጁ ከመሆኑም ሌላ የተለያዩ ሰዎችን ለመማረክ በሚያስችሉ መንገዶች በርካታ ርዕሰ ጉዳዮችን ይዘው ይወጣሉ። በእነዚህ መሣሪያዎች በሚገባ እየተጠቀማችሁባቸው ነው?
5, 6. የይሖዋ ሕዝቦች መለኮታዊ ድጋፍ እንዳላቸው እንዴት ማወቅ እንችላለን?
5 መለኮታዊ መመሪያና ድጋፍ:- ከዚህ በተጨማሪ ትንቢታዊው ራእይ በምሳሌያዊው የፈረሰኛ ሰራዊት የተመሰለው የስብከት እንቅስቃሴ መለኮታዊ ድጋፍ እንዳለው በግልጽ ያሳያል። (ራእይ 9:13-15) ዓለም አቀፋዊው የስብከት ሥራ ሊከናወን የቻለው በሰው ጥበብ ወይም ኃይል ሳይሆን በአምላክ መንፈስ አማካኝነት ነው። (ዘካ. 4:6) ይሖዋ ለሥራው አመራር እንዲሰጡ በመላእክት ይጠቀማል። (ራእይ 14:6) በመሆኑም በምድር ላይ ያሉ ምሥክሮቹ ከሚያደርጉት ጥረት በተጓዳኝ ይሖዋ ትሑት የሆኑ ሰዎች ወደ እርሱ እንዲመጡ መለኮታዊ ድጋፍ ይሰጣል።—ዮሐ. 6:45, 65
6 የይሖዋ ሕዝቦች የአምላክን ቃል ለማድረስ በሚገባ የሠለጠኑና የታጠቁ እንዲሁም በመላእክት የሚታገዙ በመሆናቸው ማንም ሊያስቆማቸው አይችልም። ከዚህ አስደናቂ ትንቢታዊ ራእይ ፍጻሜ ጋር በተያያዘ የበኩላችንን ድርሻ ማበርከታችንን እንቀጥል።