የይሖዋን ፍትሕ ኮርጁ
1 “እግዚአብሔር ፍትሕን ይወዳል።” (መዝ. 37:28) በመሆኑም ይሖዋ በዚህ ዓመጸኛ ዓለም ላይ ጥፋት ቢበይንም አስቀድሞ ማስጠንቀቂያ እንዲነገር ዝግጅት አድርጓል። (ማር. 13:10) ይህም ሰዎች ንስሐ እንዲገቡና ከጥፋት እንዲድኑ አጋጣሚ ይሰጣቸዋል። (2 ጴጥ. 3:9) እኛስ እንደ ይሖዋ ፍትሐዊ ለመሆን ጥረት እያደረግን ነው? በሰው ልጆች ላይ የሚደርሰው ሥቃይና መከራ የመንግሥቱን ተስፋ እንድናካፍላቸው ይገፋፋናል? (ምሳሌ 3:27) ፍትሕን የምንወድ ከሆነ በስብከቱ ሥራ በንቃት ለመካፈል እንገፋፋለን።
2 ያለ አድልዎ ስበኩ፦ የአምላክን ዓላማ ሳናዳላ ለሁሉም ሰው በመስበክ ‘ፍትሕን እናደርጋለን።’ (ሚክ. 6:8) ፍጹማን ባለመሆናችን ምክንያት የሰዎችን ውጪያዊ ገፅታ በማየት መፍረድ ይቀናናል፤ ሆኖም ይህን ዝንባሌ ለማስወገድ ጥረት ማድረግ ይገባናል። (ያዕ. 2:1-4, 9) ይሖዋ “ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነትን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ ይፈልጋል።” (1 ጢሞ. 2:4) በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው እውነት ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ አስደናቂ ለውጦችን እንዲያደርጉ ይረዳቸዋል። (ዕብ. 4:12) ይህን እውነታ መገንዘባችን ከዚህ በፊት አነጋግረናቸው ለመስማት ፈቃደኛ ያልነበሩትን ጨምሮ ሁሉንም ሰዎች ለማነጋገር ድፍረት እንዲኖረን ያደርጋል።
3 ሱቅ ውስጥ የምትሰራ አንዲት እህት አለባበሱንና የጸጉር አያያዙን በመመልከት የምትፈራው አንድ ደንበኛ ነበራት። ሆኖም ምቹ አጋጣሚ ስታገኝ አምላክ ስለ ገነት የሰጠውን ተስፋ ነገረችው። እርሱም ተጨባጭነት በሌለው ተረት እንደማያምንና ሂፒ እንደሆነ እንዲሁም የዕፅ ሱሰኛ መሆኑን በግልፅ ነገራት። እህት ግን ተስፋ አልቆረጠችም። አንድ ቀን ስለ ጸጉሩ መርዘም አስተያየት እንድትሰጠው ሲጠይቃት መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ምን እንደሚል በዘዴ ነገረችው። (1 ቆሮ. 11:14) በሚቀጥለው ቀን ጺሙን ተላጭቶና ጸጉሩን በአጭሩ ተስተካክሎ ስታየው በጣም ተደሰተች! መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት እንደሚፈልግ ሲነግራት ለማስጠናት ፈቃደኛ ከሆነ አንድ ወንድም ጋር አገናኘችው። ከዚያም እድገት በማድረግ ራሱን ወስኖ ተጠመቀ። ልክ እንደዚህ ሰው ሁሉ ዛሬ ያሉ በርካታ የይሖዋ አገልጋዮች ሌሎች ክርስቲያኖች ያለ አድልዎ የመንግሥቱን መልእክት ለእነርሱ ለመንገር ጥረት በማድረጋቸው አመስጋኞች ናቸው።
4 ይሖዋ በቅርቡ ዓመጸኞችን ከምድረ ገፅ ጠራርጎ ያጠፋቸዋል። (2 ጴጥ. 3:10, 13) በቀረን ጥቂት ጊዜ ሁሉንም ሰዎች በዓመጸኛው የሰይጣን ዓለም ላይ ሊመጣ ካለው ጥፋት እንዲተርፉ በመርዳት የይሖዋን ፍትሕ እንኮርጅ።—1 ዮሐ. 2:17