ክፍል 1—የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን እድገት እንዲያደርጉ መርዳት
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ምንድን ነው?
1 በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የአምላክ ሕዝቦች በየወሩ ወደ ስድስት ሚሊዮን የሚጠጉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ይመራሉ። ውጤታማ የሆኑ የማስተማሪያ ዘዴዎችን በመጠቀም እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ራሳቸውን ወደ መወሰንና ወደ መጠመቅ እንዲደርሱ ብሎም “ሌሎችን ለማስተማር ብቃት” እንዲኖራቸው መርዳት እንችላለን። (2 ጢሞ. 2:2) የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህ እንዲህ ዓይነት እድገት እንዲያደርግ ትፈልጋለህ? የመንግሥት አገልግሎታችን ከዚህ እትም ጀምሮ በተከታታይ በሚወጡ ርዕሰ ትምህርቶች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን እድገት እንዲያደርጉ ለመርዳት የሚያስችሉ መሠረታዊ ነጥቦችን ያብራራል።
2 ጥናቶችን ሪፖርት የምናደርገው ከመቼ ጀምሮ ነው? በመጽሐፍ ቅዱስና መጽሐፍ ቅዱስን ለማስጠናት ከምንጠቀምባቸው ጽሑፎች በአንዱ በመጠቀም ቅደም ተከተሉን በጠበቀ መንገድ ለጥቂት ደቂቃዎችም ቢሆን ከአንድ ሰው ጋር ቋሚ የሆነ ውይይት ካደረግን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እየመራን ነው። ከሰውየው ጋር ውይይት የምናደርገው ወደ ቤት ሳንገባ በር ላይ ቆመን ወይም ደግሞ በስልክ ቢሆንም እንኳ እንደ ጥናት ይቆጠራል። ጥናቱ እንዴት እንደሚካሄድ ካሳየናቸው በኋላ ሁለት ጊዜ ካስጠናናቸው እንዲሁም ጥናቱ እንደሚቀጥል ከተሰማን ጥናት ብለን ሪፖርት ማድረግ እንችላለን።
3 እውቀት መጽሐፍና አምላክ ከእኛ የሚፈልገው የተባለው ብሮሹር መጽሐፍ ቅዱስን ለማስጠናት እንዲረዱ ታስበው የተዘጋጁ ጽሑፎች ናቸው። አንድ ሰው እነዚህን ሁለት ጽሑፎች አጥንቶ ከጨረሰ በኋላ ቀስ በቀስም ቢሆን እድገት በማድረግ ላይ መሆኑ ከታየና ለሚማረው ነገር አድናቆት እያዳበረ ከሆነ የአምልኮ አንድነት በተባለው መጽሐፍ ጥናቱን መቀጠል እንችላለን። በትምህርታቸው ብዙም ላልገፉና ማንበብ ለሚያስቸግራቸው ሰዎች የአምላክ ወዳጅ መሆን ትችላለህ! የሚለውን ብሮሹር ማስጠናት እንችላለን።
4 መጽሐፍ ቅዱስን የማስጠናቱ ሥራ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እውነተኛ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ ለመርዳት አስችሏል። (ማቴ. 28:19, 20) ከዚህ ቀጥሎ በሚወጡት የመንግሥት አገልግሎታችን እትሞች ላይ የሚቀርቡትን የዚህን ርዕስ ተከታታይ ትምህርቶች ተግባራዊ በማድረግ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን እድገት እንዲያደርጉ መርዳት እንችላለን።