ጽናት ይክሳል
1 “ጸንታችሁም በመቆም ነፍሳችሁን ታተርፋላችሁ።” (ሉቃስ 21:19) ኢየሱስ ስለ ‘ሥርዓቱ መጨረሻ’ የተናገረው ትንቢት ክፍል የሆኑት እነዚህ ቃላት ታማኝነታችንን ከመጠበቅ ጋር በተያያዘ በርካታ ፈተናዎች ሊደርሱብን እንደሚችሉ መጠበቅ እንዳለብን በግልጽ ያሳያሉ። ይሁን እንጂ ከይሖዋ በምናገኘው ብርታት ሁላችንም ‘እስከ መጨረሻው መጽናትና መዳን’ እንችላለን።—ማቴ. 24:3, 13፤ ፊልጵ. 4:13
2 ስደት፣ የጤና እክል፣ የኢኮኖሚ ችግርና የመንፈስ ጭንቀት እያንዳንዱን ቀን ፈታኝ ሊያደርግብን ይችላል። ይሁን እንጂ ሰይጣን ለይሖዋ ያለንን ታማኝነት እንድናጓድል ለማድረግ እየጣረ መሆኑን መዘንጋት አይኖርብንም። በሰማይ ለሚኖረው አባታችን ያለንን ታማኝነት ጠብቀን በምናሳልፈው በእያንዳንዱ ቀን ይሖዋን ለሚሰድበው ለሰይጣን መልስ እየሰጠን ነው። መከራ ሲያጋጥመን የምናፈሰው ‘እንባ’ ተረስቶ እንደማይቀር ማወቃችን ምንኛ ያስደስታል! ያፈሰስነው እንባ በይሖዋ ፊት ውድ ከመሆኑም በላይ በታማኝነት መጽናታችን ልቡን ደስ ያሰኘዋል።—መዝ. 56:8፤ ምሳሌ 27:11
3 በመከራ የተፈተኑ ባሕርያት፦ መከራ እምነታችን ደካማ መሆኑን እንዲሁም እንደ ኩራት ወይም ትዕግሥት ማጣት ያለ ድክመት እንዳለብን ሊጠቁም ይችላል። ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ መንገዶችን ተጠቅሞ ፈተናን ለማስቀረት ወይም ለማምለጥ ከመሞከር ይልቅ “ትዕግሥት ሥራውን ይፈጽም” ዘንድ አጋጣሚ እንድንሰጠው የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር መከተል አለብን። ለምን? ምክንያቱም ፈተናዎችን በጽናት ማለፋችን “ፍጹማንና ምሉአን” እንድንሆን ይረዳናል። (ያዕ. 1:2-4) ጽናት እንደ ምክንያታዊነት፣ ርኅሩኅነትና መሐሪነት ያሉ በዋጋ ሊተመኑ የማይችሉ ባሕርያትን እንድናዳብር ሊረዳን ይችላል።—ሮሜ 12:15
4 በፈተና የጠራ እምነት፦ ፈተናዎችን በጽናት ስንወጣ በአምላክ ዘንድ ትልቅ ዋጋ ያለውን በመከራ ተፈትኖ የጠራ እምነት እናዳብራለን። (1 ጴጥ. 1:6, 7) እንዲህ ያለው እምነት ወደፊት የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች በታማኝነት ለማለፍ ያስችለናል። ከዚህም በላይ የአምላክን ሞገስ እንዳገኘን የሚሰማን ሲሆን ይህም ይበልጥ ሕያውና ጠንካራ የሆነ ተስፋ እንዲኖረን ያደርጋል።—ሮሜ 5:3-5
5 ጽናት የሚያስገኝልን ከሁሉ የላቀ ሽልማት በያዕቆብ 1:12 ላይ እንዲህ ተብሎ ተገልጿል:- “በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው፤ ምክንያቱም ፈተናን ሲቋቋም . . .የሕይወትን አክሊል ያገኛል።” እንግዲያው ይሖዋ “ለሚወዱት” የተትረፈረፈ በረከት እንደሚሰጥ ሙሉ በሙሉ በመተማመን ታማኞች ሆነን እንቀጥል።